መስከረም 11 ቀን፣ 2019 ዓ.ም.
ትብብር ለሕልውና ምስረታ መታወጁን አስመልክቶ ከኢትዮጵያውያን ትብብር ንቅናቄ የተሰጠ መግለጫ
መስከረም 10 ቀን 2019 አ.ም. የኢትዮጵያ ሕዝባዊ ኃይሎች ትብብር ለሕልውና (ትብብር ለሕልውና) መመስረቱን የትብብሩ ሰብሳቢ አርበኛ ዘመነ ካሴ አዉጇል። ትብብሩን የመሰረቱት 7 ድርጅቶች ናቸዉ። ትብብር ለሕልውና ሌሎች የታጠቁና ያልታጠቁ ኢትዩጵያዊ ድርጅቶች በዚሁ ትብብር ተሳታፊ እንዲሆኑ ጥሪ አድርጓል።
የኢትዮጵያዉያን ትብብር ንቅናቄ (በእንግሊዝኛዉ Ethiopian Solidarity Movement)
የታወጀዉ ድርጅት “ትብብር ለሕልውና” በይፋ በመነገሩ የተሰማዉን ልባዊ ደስታ ለመግለጽ ይወዳል።
የኢትዮጵያ ሕዝብ የረጅም ጊዜ ጥያቄ የሆነዉ የትብብር አጄንዳ ዛሬ በይፋ መልስ ማግኘቱ ለሕዝባችን ሰላምና መረጋጋት፤ እንዲሁም ለማያዳግም ድል ለሚያበቃ ትግል እመርታን ይፈጥራል ብለን እናምናለን። የኛ እንቅስቃሴ በኢትዮጵያ ምድር እንደዚህ ያለ አደረጃጅት እንዲፈጥር የበኩሉን ያላሰለሰ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል። የዛሬ 8 አመት በታላቅ ተስፋ ወደ ስልጣን የመጣው የአብይ አገዛዝ ባለፉት 8 አመታት
አደራውን በልቶ፤ በዘር ፍጅትና በማፈናቀል ተሰማርቶ አገራችንን የምድር ሲኦል እንዳደረጋትና መወገድ ያለበት አገዛዝ መሆኑን አብዛኛው ይስማማበታል። ሥርዓቱን ለማስወገድና አገራችን ወደ ሰላማዊ ሽግግር እንድትገባ ለማድረግ የትብብር ለሕልውና መመስረትና መታወጅ ትልቅ እርምጃ ነዉ።
ትብብር ለሕልውና በድህረ አብይ አገዛዝ ማግስት አገር ከማረጋጋት ባሻገር የአገራችንን አንድነትና ልኡአላዊነት የሚያስከብር አካታች የሽግግር መንግስት መመስረት እንዳለበት በትክክል ባስቀመጠዉ መሰረት ትብብራችን የሲቪልና የፖለቲካ ድርጅቶች ለቀረበዉ ጥሪ ገንቢ መልስ እንዲሰጡ እናሳስባለን።በተጨማሪም ትብብር ለሕልውና የአብይን አገዛዝ በአጭር ጊዜና በጥቂት መስዋእትነት የሚያስወግድ የተቀናጀ ወታደራዊ ስትራተጂ እንደሚተገብር ተስፋ እናደርጋለን። እንዲሁም ትብብር ለሕልውና በአንድ ድምፅና በአንድ ቃል ብቻ በተማከለ መንገድ መግለጫ የሚሰጡበትን አሰራር እናያለን
ብለን ተስፋ እናደርጋለን። በመጨረሻም ትብብር ለሕልውና በሚያዘጋጃቸዉ የሽግግር ቻርተርና ሌሎች ሰነዶች ሕዝባዊ ተሳትፎ እንዲኖርና የዴሞክራሲ አሰራር መሰረት እንዲጣል አበክረን እንመክራለን። ደግሞም ሁላችንም ኢትዮጵያዉያን ይህንን ትብብር ለሕልውና በምንችለዉ መንገድ ሁሉ ለማገዝ እንዘጋጅ።
እንኳን ደስ አለን!
በትግላችን የዴሞክራሲዊትና የሉአላዊት ኢትዮጵያን ትንሳዔ እናበስራለን።
የኢትዮጵያውያን ትብብር ንቅናቄ!!!

