Dinknesh Ethiopia

“ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት” መፈጠር አስመልክቶ የተሰጠ የድጋፍ መግለጫ

Ethiopian Solidarity Movement

September 25, 2025

ከኢትዮጵያውያን ትብብር ንቅናቄ የተሰጠ
የድጋፍ መልዕክት

ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት – ቅንጅት በሚል የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ)፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ)፣ እናት ፓርቲ፣ አንድ ኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ (አኢዴፓ) እና የአማራ ግዮናው ንቅናቄ (አግን) ቅንጅት በመፍጠራችሁ ከልብ የመነጨ ደስታችንን እንገልፃለን።

ይህ ውሳኔያችሁ፣ የሕዝባችንን የጋራ እሴቶች ንቆ፣ በአግላይ አንቀፆች የተሞላ ሕገ መንግሥት ነድፎ፣ ሀገራችንን በቋንቋ መስፈርት ብቻ ከልሎ፣ ታሪካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ የብሔር አስተሳሰብ ትርክቶችን አስፋፍቶ፣ ተቃዋሚ ኃይሎችን አዳክሞ፣ ለማያልቅ እልቂትና መከራ የዳረገውን ፖለቲካ በጋራ ለመለወጥ፣ የሰላም፣ የዲሞክራሲና አንድነት ትግል የሚያበረታታ የመጀመርያ ትልቅ እርምጃ ነው።

የትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት መመስረት፣ ካለፉት ስህተቶች በመማር፣ በትናንሽ የፖለቲካ ቡድኖች ተበታትነው ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ሊያደርጉ የሚችሉ ኃይሎችን የሰው ኃይል፣ የፋይናንስና የስትራቴጂ

አቅምን ያዳብራል። ተሰሚነትን ያፈራል። ተጠያቂነትን ያበረታታል። ይህ ጅምራችሁ እንዲሰፋ፣ በትብብሩ ዓላማዎች የሚያምኑ ሌሎች ኢትዮጵያውያን ድርጅቶች እንዲቀላቀሉ ጥረታችሁ እንደሚቀጥል ሙሉ እምነት አለን።

የኛ የሲቪክ የዜጎች እንቅስቃሴ ነው። በተለይም ከኢትዮጵያ ውጭ የምንኖር ዜጎች፣ የፖለቲካ ሥልጣን ፍላጎት የለንም። ዋናው ዓላማችን በፍትሕ፣ በእኩልነት፣ በዲሞክራሲና በአንድነት ላይ የተመሠረተች ሀገር እንድትገነባ ነው። በነዚህ ጉዳዮች ከሚተባበሩን ወገኖች ጋር አብረን እንሠራለን። በዚህ መንፈስ ነው ለ”ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት” ድጋፋችንን የምንሰጠው። በዚህ የሀገር አድን አንድ አካል በሆነው ጥረት፣ የዲያስፖራው ማህበረሰብ፣ በሰላማዊ ትግል ተልዕኮአችን እንዲተባበረን ጥሪ እናደርጋለን። በተጨማሪም የዓለም አቀፍ አጋሮች፣ የሲቪክ ማህበረሰብ እና የፍትሕ ድርጅቶች፣ ለአዲሱ ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ እንዲያደርጉ እናሳስባለን።

ባደገ ቢሻው (ዶ/ር)፣ሊቀ መንበር
የኢትዮጵያውያን ትብብር ንቅናቄ

Exit mobile version