ከጦርነት የተረፉ ንጹሀን በረሀብ እየተገረፉ መሆኑ ትልቅ የሰብዓዊነት ልሽቀት ነው!
* በሕፃፅ የመጠለያ ካምፕ የተከሰተውን ረሀብ አስመልክቶ ከኢሕአፓ የተሰጠ መግለጫ*
ላለፉት አመታት በከፍተኛ ጦርነት ሲሰቃይ የቆየው የትግራይ ሕዝብ አሁንም ፖለቲካ ወለድ በሆነ ምክንያት በከፍተኛ ስጋት ውስጥ መሆኑን ፓርቲያችን ተመልክቷል። ባልተገባ መንገድ በአገር ውስጥ እና በውጭ ሀይሎች ጦርነት ላይ የቆየው የትግራይ ሕዝብ ለምን ከጥይት አመለጥክ? በሚመስል መልኩ በሰው ሰራሽ ርሀብ ሳይታይ እና ሳይምሰማለት እየተገርፈ ይገኛል።
አሰቃቂውን ጦርነት ተከትሎ ከቤታቸው ተፈናቅለው በየመጠለያ ጣብያው ያሉ ንጹሀን ዜጎች ዘርፈ ብዙ ችግሮች ሲደርስባቸው ቆይቷል። ችግሮቻቸውን የሚፈታላቸው ብቻ ሳይሆን ጉዳዬ የሚላቸውም አካል ባለመኖሩ ለከፋ አደጋ ከተጋለጡ አመታት አልፈዋል።
በሕፃፅ የተፈናቃዮች መጠለያ ካምፕ ላይ የደረሰውም ይሄው ነው። ነገር ግን ረሀብ በፍጹም ጊዜ አይሰጥምና ለእነዚህ ወገኖች በአስቸኳይ የሰብዓዊ እርዳታ እንዲደርሳቸውና ጉዳያቸውም በዘላቂነት እንዲፈታ ኢሕአፓ ይጠይቃል።
ልጆቻቸው በጦርነት ለተማገዱባቸው፤ ጥቂቶች ለስልጣናቸው ሲሉ ከቀያቸው ላፈናቀሏቸው ለእነዚህ ዜጎች የሚደረግ ማንኛውም ድጋፍ እርዳታ ሳይሆን የዜግነት ግዴታ እንደሆነም ሊሰመርበት ይገባል።
የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ – ኢሕአፓ ለመላው የትግራይ ሕዝብ ያለውን ጽኑ አጋርነት እየገለጸ በዚህ ጉዳይም የሚጠበቅበትን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ እንደሆነ ያስታውቃል።
የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ – ኢሕአፓ
ታህሳስ 13 ቀን 2018 ዓ.ም
አዲስ አበባ፤ ኢትዮጵያ
