Site icon Dinknesh Ethiopia

ውጤቱ አስቀድሞ የታወቀ ኢ-ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ውስጥ መሳተፍ ህዝብን መናቅ ነው።

ESCC

ግንቦት ፲ ቀን ፪ሺ፲፰ ዓ.ም / May 18, 2026

 

ውጤቱ አስቀድሞ የታወቀ ኢ-ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ውስጥ መሳተፍ ህዝብን መናቅ ነው።

ተዓማኒነት ከሌለው የምርጫ ስርኣት ዲሞክራሲያዊ የሀገር ግንባታና የስልጣን ሽግግር መጠበቅ የቀን ቅዥት ነው።

ሀገራዊ ምርጫ በአንድ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ውስጥ ተወዳዳሪዎች ሀሳባቸውን ለመራጭ ህዝብ ማቅረብና በእኩል ሜዳና ስርኣት ውስጥ በመወዳደር ለዜጎች መብትን የሚያጎናጽፍ ሂደት ነው። ምንም እንኳ ኢትዮጵያ የስርዓቱ ጥገናዊ ለውጥ መከሰቱን ተከትሎ ውስብስብ በሆነ ማህበራዊ፥ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ  አዘቅትና ችግሮች ውስጥ ብትገኝም ሰባተኛ ሀገራዊ ምርጫ ለማከናወን የተለያዩ ዝግጅቶች ሲከናወኑ መቆየታቸው አይዘነጋም።

የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ በጽኑ በሚያምነውና ባለፉት ሃምሳ ዓመታት ሲታገልለት የቆየውን የዲሞክራሲ ስርኣት ግንባታ መገለጫ ውስጥ አንዱ በሆነው ሀገራዊ ምርጫ ለመሳተፍ፥ ተገቢውን ድጋፍና የህዝብን ድምጽ ለማግኘት መንግስታዊ ስርዓት ውስጥ የቆመለትን የሶሻል ዲሞክራሲ ፖለቲካዊ ርዕዮተ ዓለም ለመተግበር በማቀድ ምንም እንኳ በርካታ አስቻይ ሁኔታዎች ባይኖሩም ቅድመ ሁኔታዎችን በዝርዝር በማስቀመጥ ውሳኔ ማሳለፉ ይታወቃል።

በውጪ የምንገኝ የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ አባላትና ደጋፊዎች በጋራ በመሆን ለዚህ ስኬት የምንችለውን ድጋፋ ስናደርግ መቆየታችን ግልጽ ነው። ጓዶቻችን ጊዜውና እድሉ በፈቀደላቸው የውይይት መድረኮች በመገኘት የተጨቆነውን፥ በደል የደረሰበትን፥ ስቃይ ውስጥ የሚገነውን ህዝብ ብሶት፥ ስሜትና ኡኡታ ለማስደመጥ የሄዳችሁበትን መንገድ ሁሉ የምናደንቅና እውቅና የምንሰጥ መሆኑን በዚህ አጋጣሚ ለመግለጽ እንወዳለን።  ኢሕአፓ በታሪኩ አምባገነን መንግስትን የታገለ፥ ሞት አይፈሬ ጀግኖች የተፈጠሩበት፥ ለመብት ለሕዝብ ነጻነት፤ ለሐገር ሉአላዊነት ፍጹም ህይወታቸውን የሰጡ ጀግኖች የሚታወሱበት፥ የሚዘከሩበትና በህይወት በትግል ላይ አሁንም የቆሙ አባላቶች ያሉት ድርጅት ነው።

የምርጫ ሂደቱንም ከምርጫ አስፈፃሚው አደረጃጀት አሰራር፥ ከፓርቲያችን አወቃቀር፥ ከተወዳዳሪዎቻችን  ምልመላ ብቃትና ከመንግስት ማለትም ከብልጽግና ፓርቲ ነባራዊ ተጽህኖ፥ አሰራርና በምርጫው ውጤት ላይ ሊያደርስ የሚችለውን ጫና በየወቅቱ የመመልከት፥ የመገምገም ሊሆን ይችላል የምንላቸውን ሁኔታዎች (Scenarios)  ካስቀመጥናቸው ቅድመ ሁኔታዎች አንፃር የማመሳከር መሬት ላይ ያለውን እውነታ ስናጠና ቆይተናል።

ይህንንኑ ተከትለን የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ ያቀረባቸው ቅድመ ሁኔታዎች ሙሉ ለሙሉ በመንግስት/ ብልጽግና በኩል ተቀባይነት ካለማግኘታቸው በተጨማሪ ብልጽግና እየወሰዳቸው የመጣውን የጅምላ አፈሳ፥ በግዳጅ የምርጫ ምዝገባ እንዲካሄድ መደረጉ፥ መራጩ ህዝብ በብልጽግና ካድሬዎችና በፀጥታ ሀይሎች የሚደርስበት መዋከብና  የምርጫ አስፈፃሚው የማስፈፀም አቅም ዳካማ መሆን ምርጫውን ተአማኒ፥ ፍትሐዊና ግልፀኝነት የተላበሰ እንደማይሆን ከመገንዘቡም በላይ ብልጽግና በችሮታ ለማዳረስ ለተወዳዳሪ ፓርቲዎች ተወዳዳሪ ባለማቅረብና በመሰል መንገዶች እያካሄዳቸው ያሉ ስራዎችን መታዘብ ችለናል። ይህም በምርጫው መቀጠል የህዝብን አመኔታ ማጣት፥ ለብልጽግና መንግስት በአጃበነትና በአድማቂነት ብቻ እውቅና እንዲያገኝ ማድረግ የመጨረሻ ግብ እንደሚሆን ድምዳሜ ላይ ስለደረስን ከወዲሁ አለው ላለን አለንልህ ላልነው ህዝብ ከምርጫው ራሳችንን ማግለላችንን ማሳወቅ እንደሚገባ  ከውሳኔ ሀሳብ ላይ ደርሰናል።

ይህንን ግምገማችንንና ስጋታችንን ከስራ አስፈፃሚው ጋር በተደጋጋሚ በመወያየየት ግምገማችን ላይ የጋራ መግባባት ላይ ደርሰን የነበረ ቢሆንም   የማዕከላዊ ኮሚቴ ምክር ቤት አባላት ባደረጉት ስብሰባ በግምገማው በተወሰነ ደረጃ  ቢስማሙም በምርጫው እስከመጨረሻው መቀጠልን በአብላጫ ድምጽ መወሰናቸውን ተረድተናል።

ሀገሪቱ ካለችበት ሁለተናዊ ውስብስብ ችግሮች፥ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ውጥረቶች ጦርነትና ዛሬም በፀጥታ ችግርና ምርጫ የማይካሄድባቸው ቦታዎችና ክልል መኖሩን ከዚህም ባለፈ የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ  በምርጫው እንደእውነተኛ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ የህዝቡን ይሁንታ ለማግኘት በሚያደርገው ጥረት  ያቀረባቸው ቅድመ ሁኔታዎች ምንም ዓይነት እርምጃ ያልተወሰደባቸው መሆኑን፥ የምርጫውም ሂደትና ተጠባቂ ውጤት አስቀድሞ የታወቀ በመሆኑ  አሁንም ሂደቱን ከግምት ውስጥ በመክተት ከዚህ የይስሙላ ምርጫ ራሳችሁን ታገሉ ዘንድ በጥብቅ እናሳስባለን።

ድል ሁልጊዜም ከህዝብ ጋር ናት!

የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ

የውጪ ድጋፍ አስተባባሪ ኮሚቴ

 

 

 

 

 

 

 

Exit mobile version