*በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ከኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ – ኢሕአፓ የተሰጠ መግለጫ*
የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ – ኢሕአፓ በቅርቡ በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ተከታዮች እና በቤተክርስቲያኒቱ ላይ አነጣጥረው እየተሰራጩ ያሉ የጥላቻ፣ የመከፋፈል፣ ማነትን የማጥቃትና ታሪክን የማዛባት መልዕክቶች ከተራ የአመለካከት ልዩነት ያለፉ ከባድ ስጋቶች ናቸው ብሎ ያምናል።
በተለይም የኢትዮጵያን ክርስትናዊ ታሪካዊ ማንነት አፍርሰናል፣ ወደፊትም ይህንኑ ተግባር እንቀጥላለን የሚሉ ዛቻዎች የአንድን ሐይማኖት ተከታዮች ከመዝለፍ ያለፈ፣ የሀገሪቱን ታሪክና የጋራ ማንነት ለመናድ ያለሙ አደገኛ አቋሞች ናቸው።
በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ተከታዮች የግድያ፣ የማስፈራራትና የጥቃት ሰለባ የመሆናቸው ሓቅ ደግሞ መሰል ንግግሮች ተራ ዛቻዎች ሳይሆኑ ወደመሬት እየወረዱ ላሉ እቅዶች የፕሮፖጋንዳ ግብዓቶች ለመሆናቸው ያስረግጣል።
በሐይማኖት ማንነት ምክንያት የሚፈጸሙ ግድያዎችንና ጥቃቶችን እንደ ተራ የጸጥታ ችግር መቁጠር ሀገራዊ ውድቀት ነው።
ይህንን አቋም ስናንጸባርቅ ግን ከሁሉም በላይ ልናሳስብ የምንፈልገው የሐይማኖት ጽንፈኝነትንና በሐይማኖት ማንነት ላይ የሚፈጸምን ጥቃት መቃወም በምንም መልኩ ቤተ እምነት ላይ ያነጣጠረ ተቃውሞ ስላለመሆኑ ነው።
የምንቃወመው እና የምንታገለው በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ተከታዮች እና በቤተክርስቲያኒቱ ላይ ያነጣጠሩ ዛቻዎችን፣ ዘለፋዎችን፣ ማሳደዶችን እና ግድያዎችን የሚፈጽሙ ማናቸውንም አካላት ነው። ይህ አቋም የሚያስቆጣቸው አካላት ካሉ እነርሱ ገዳዮቹና ተባባሪዎቻቸው ስለመሆናቸው ግልጽ ነው።
ይበልጥ አሳሳቢው ጉዳይ ደግሞ እነዚህ የጥላቻ መልዕክቶችና የጥቃት ዛቻዎች በግልጽ እየተሰራጩ እና በሐይማኖት ማንነት ምክንያት የሚፈጸሙ ጥቃቶችም እየተደጋገሙ ሳሉ ስልጣን ላይ ያለው አካል ዝምታ በተራ የአስተዳደር ድክመት ስም ሊሸፈን የሚችል ሳይሆን ከሚፈጸሙት ድርጊቶች ጋር ያለው ግንኙነትና የሚያደርገው ድብቅ ድጋፍ ምንድነው ብለን እንድንጠይቅ የሚያስገድድ ነው። ስልጣን ይዣለሁ የሚል አካል በአንድ እምነት ተከታዮች ላይ የሚፈጸምን ጥቃት በዝምታ የሚመለከት ከሆነ ገለልተኛነቱ በራሱ አጠያያቂ ይሆናል፤ ጥቃቱም መዋቅራዊ ስለመሆኑ አመላካች ተደርጎ የሚወሰድ ነው።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ-ክርስቲያን ከሀገራችን ታሪክ፣ ባህል፣ ቋንቋ፣ ሥነ ጽሑፍ፣ የፊደል ባህልና ሥልጣኔ ጋር ጥልቅና የማይነጣጠል ታሪካዊ ትስስር ያላት ተቋም ናት።
ይህንን ታሪካዊ አስተዋጽኦ መካድ፣ ማሳነስ ወይም ለማጥፋት መሞከር የታሪክን እውነት ለመካድ መሞከር ነው።
የአንዱን ታሪክ ለማክበር ከሰሞኑ እየተደረገ እንዳለው የሌላውን ታሪክ መካድ፤ የአንዱን ማንነት ለማሳደግ የሌላውን ማንነት ማጥፋትን አይጠይቅም።
ኢሕአፓ በተደጋጋሚ እንደገለጸው በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ተከታዮች እና በቤተ-ክርስቲያኒቱ ላይ እየደረሰ ያለውን የታቀደ እና የተደራጀ ጥቃት አጥብቆ ያወግዛል። በአንድ ቡድን፣ ሐይማኖት ወይም ብሄር ላይ አነጣጥሮ በተደራጀ ሁኔታ የሚፈጸም ጥቃት የዘር ፍጅት ሊባል እንደሚችል የሚታወቅ ሲሆን በኢትዮጵያ ውስጥም እየተፈጸሙ ያሉ መሰል ጥቃቶችን በተመለከተ ገለልተኛ የሆነ አለም አቀፍ ተቋም በአስቸኳይ ጣልቃ ገብቶ እንዲመረምር ጥሪያችንን እናቀርባለን።
ማንም የሌላውን ሐይማኖት ወይም ታሪካዊ ማንነት በማፍረስ የሀገሪቱን ታሪክ ባለቤት ለመሆን ሊሞክር አይችልም። ሀገር የሁሉም ነው፤ ታሪኳም የሁሉም ነው።
ኢሕአፓ የሐይማኖቶች መከባበር፣ የሕዝብ አብሮነት፣ የታሪክ እውነትና የዜጎች እኩልነት መሠረታዊ የሀገራዊ አንድነት መርሆዎች እንዲጠበቁ ያሳስባል። የሀገርን ታሪካዊ ማንነት ለማጥፋት የሚደረግ ማንኛውም ጥረት፣ በሃይማኖት ማንነት ላይ የሚፈጸም ጥቃትና እነዚህን ድርጊቶች የሚያበረታታ ወይም በዝምታ የሚያልፍ የፖለቲካ አካሄድ ለሀገራችን ሰላም፣ ለሕዝቧ አብሮነትና ለወደፊት ህልውናዋ ከባድ አደጋ ነው።
የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ – ኢሕአፓ
ሕዳር 9 ቀን 2019 ዓ.ም
አዲስ አበባ፤ ኢትዮጵያ

