Site icon Dinknesh Ethiopia

በኢትዮጵያ ላይ ስለተፈጸሙ ወንጀሎች ስለሚያስከትሉት ቅጣት የወንጀል ሕግ ምን ይላል?

FDRE AG

“የሀገር መከላከያ ኃይልን መጉዳት ከአምስት እስከ 25 ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት፣ እንዲሁም ነገሩ እጅግ ከባድ በሆነ ጊዜ በእድሜ ልክ ጽኑ እስራት ወይም በሞት ያስቀጣል።”    

መንግሥት የሕዝቦቹን ሰላም እና ደህንነት የመጠበቅ እንዲሁም ሕግን የማስከበር ኃላፊነት የሚወጣ ቢሆኑም በተለያዩ ሁኔታዎች በሀገር ላይ ወንጀሎች ሊፈጸሙ ይችላሉ። የእነዚህ ወንጀሎች መፈፀም በአጠቃላይ በማኅበረሰቡ ሰላም፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ህይወት ላይ ጉዳት ማስከተሉ አይቀሬ በመሆኑም መንግሥት የሀገርን ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥሉ ወንጀሎች እንዳይፈጸሙ አስቀድሞ የመከላከል፤ ተፈጽመው ሲገኙም ሕግን የማስከበር ኃላፊነት አለበት። በሀገር ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች በኢ.ፌ.ዲ.ሪ የወንጀል ሕግ ሦስተኛ መፅሐፍ በመንግሥት፣ በሀገርና በዓለም አቀፍ ጥቅሞች ላይ የሚደረጉ ወንጀሎች በሚል ስር ተካቶ ይገኛል።

በዚህ አጭር የንቃተ ሕግ ፅሁፍ በሀገር ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች እና የሚያስከትሉትን የወንጀል ቅጣት እንዳስሳለን። በሕገ-መንግሥትና በሕገ-መንግሥት ሥርዓት ላይ የሚደረጉ ወንጀሎች በ1996 ዓ.ም በወጣው የወንጀል ሕግ አንቀፅ 238 ስር እንደተደነገገው ማንም ሰው በኃይል፣ በዛቻ፣ በአድማ ወይም ሕገ-ወጥ በሆነ ማናቸውም መንገድ የፌደራሉን ወይም የክልልን ሕገ-መንግሥት ያፈረሰ፣ የለወጠ ወይም ያገደ እንደሆነ ወይም በፌደራሉ ወይም በክልል ሕገ-መንግሥት የተቋቋመውን ሥርዓት ያፈረሰ ወይም የለወጠ እንደሆነ ከሦስት ዓመት እስከ 25 ዓመት ለመድረስ በሚችል ጽኑ እስርት ይቀጣል። ወንጀሉ ሲፈፀም በሕዝብ ደህንነት ወይም ኑሮ ላይ ከፍተኛ ቀውስ ደርሶ እንደሆነ አድራጊው በዕድሜ ልክ እስራት ወይም በሞት ይቀጣል።

የሕገ-መንግሥታዊ ሥልጣንን ተግባራዊነት ማሰናከል ሌላው በወንጀል ሕጉ የወንጀል ድርጊት ተብሎ የተፈረጀ ተግባር ሲሆን ማንም ሰው በኃይል ሥራ፣ በዛቻ፣ ወይም ሕገ-ወጥ በሆነ ሌላ ማናቸውም መንገድ በፌደራል ወይም በክልል ሕገ-መንግሥት ስልጣን የተሰጠውን አካል ወይም ባለስልጣን ተግባሩን እንዳያከናውን ያደናቀፈ፣ የከለከለ ወይም አስገድዶ ውሳኔ እንዲሰጥ ያደረገ እንደሆነ ከ15 ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እስራት ይቀጣል።

የጦር መሣሪያ ይዞ በማመፅ፣  ወይም የእርስ በርስ ጦርነት በማስነሳት በመንግሥት ላይ የሚደረግ ወንጀል (የወንጀል ሕግ አንቀፅ 240) — ማንም ሰው አስቦ በሕገ-መንግሥት በተቋቋሙት አካላት  ወይም ባለስልጣናት ላይ ሕዝብ፣ ወታደሮች ወይም ሽፍቶች የትጥቅ አመፅ እንዲያነሱ ያደራጀ ወይም የመራ እንደሆነ ወይም ዜጎችን ወይም በሀገር ነዋሪ የሆኑትን በማስታጠቅ ወይም አንዱ ወገን በሌላው ላይ የጦር መሣሪያ እንዲያነሳ በማነሳሳት የእርስ በእርስ ጦርነት እንዲነሳ ያደረገ እንደሆነ ከ10 ዓመት እስከ 25 ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት ይቀጣል።እንዲሁም ድርጊቱ በሕዝብ ደህንነት ወይም ኑሮ ላይ ከፍተኛ ቀውስ ይስከተለ እንደሆነ በእድሜ ልክ ጽኑ እስራት ወይም በሞት ይቀጣል።

የሀገሪቱን የፖለቲካ የግዛት አንድነት በመንካት የሚደረግ ወንጀል (የወንጀል ሕግ አንቀጽ 241) — ማንም ሰው በኃይል ወይም በሌላ ማናቸውም ሕገ-መንግሥትን የሚፃረር መንገድ፣ በቀጥታ ወይም በእጅ አዙር፣ የሀገሪቱን ሕዝቦች አንድነት እንዲፈርስ ወይም ፌዴሬሽኑ እንዲከፋፈል ወይም ከፌዴሬሽኑ ግዛት ከፊሉ እንዲገነጠል የሚያደርግ ተግባር የፈፀመ እንደሆነ ከ10 ዓመት እስከ 20 ዓመት ለመድረስ በሚችል ጽኑ እስራት ወይም ነገሩ ከባድ በሆነ ጊዜ በእድሜ ልክ እስራት ወይ በሞት ይቀጣል።

የሀገሪቱን መንግሥት እንዲሁም የሀገሪቱን ምልክቶችና በመንግሥት የታወቁ ሌሎች ምልክቶችን መድፈር — ማንም ሰው በንግግር ወይም በአድራጎት ወይም በማናቸውም ሌላ አኳኋን በአደባባይ የሀገሪቱን መንግሥት ያዋረደ፣ የሰደበ፣ ስሙን ያጠፋ ወይም በሀሰት የወነጀለ እንደሆነ ከሦስት ወር በማያንስ ቀላል እስራት ወይም ከ500 ብር በማያንስ መቀጮ ይቀጣል (የወንጀል ሕግ አንቀፅ 244/1)። እንዲሁም በተንኮል፣ በንቀት ወይም ይህንን በመሳሰለ በማናቸውም ሀሳብ በግልጽ የታወቀውን አንድ የሀገር ምልክት፥ ማለትም የፌደራላዊት ኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማን ወይም አርማን እንዲሁም የክልላዊ መንግሥት ሰንደቅ ዓላማን ወይም አርማን በአደባባይ የቀደደ፣ ያቃጠለ፣ ያጠፋ፣ ያበላሸ፣ የሰደበ ወይም በማናቸውም ሌላ አኳኋን ያዋረደ እንደሆነ ከሦስት ወር በማያንስ ቀላል እስራት ወይም በመቀጮ ይቀጣል (የወንጀል ሕግ አንቀፅ 244/2)። በሀገር ነፃነት ላይ የሚደረግ ወንጀል ማንም ሰው፡-

• የሀገሪቱን ነፃነት አደጋ ላይ ለመጣል ወይም ሀገሪቱ ሉአላዊቷን እንድታጣ፣
• የሀገሪቱን ነፃነት አደጋ ላይ ለመጣል የውጪ መንግሥት ጣልቃ እንዲገባ በመገፋፋት፣ ወይም
• የውጪ መንግሥት የጠላትነት ድርጊት በሀገሪቱ ላይ እንዲፈጽም ወይም ከውጪ ሀገር መንግሥት ጋር ጦርነት እንድትዋጋ ወይም የጠላትነት ድርጊት እንድትፈጽም፣ በጠላትነት እንድትከበብ ወይም እንድትያዝ በማሰብ ማናቸውም ድርጊት ያደረገ እንደሆነ ከአምስት ዓመት እስከ 25 ዓመት ለመድረስ በሚችል ጽኑ እስራት፤ ወይም ነገሩ ከባድ ሲሆን በእድሜ ልክ ጽኑ እስራት ወይም በሞት ይቀጣል (የወንጀል ሕግ 246)።

የሀገር መከላከያ ኃይልን መጉዳት (የወንጀል ሕግ አንቀፅ 247/ሀ/ለ/ሐ እና መ) — የሀገር መከላከያ ኃይልን መጉዳት በሀገር ላይ ከሚፈጸሙ ወንጀሎች አንዱ ሲሆን ማንም ሰው አስቦ፡-

ሀ/ ወታደራዊ ፀባይ ያለውን ወይም ለሀገር መከላከያ እንዲሆን የታቀደውን ማናቸውንም የኢኮኖሚ ድርጅት፣ የመከላከያ ሥራ ተቋም ወይም ሥፍራ፣ የመገናኛ ወይም የመጓጓዣ ዘዴ፣ ሥራ፣ ማከማቻ፣ የጦር መሣሪያ ወይም ቁሳቁስ አሳልፎ በመስጠት፣ በማፍረስ፣ የተንኮል ሥራ በመፈፀም ወይም ለአገልግሎት እንዳይውል በማድረግ፣

ለ/ ጠላት ለሆነ ለውጪ ሀገር መንግሥት ወታደሮች በማቅረብ ወይም የኢትዮጵያ ዜጎች ለዚሁ ለጠላት ሀገር በወታደርነት እንዲያገለግሉ በመመልመል ወይም በማግባባት ወይም ራሱ ዜግነቱ ኢትዮጵያዊ ሆኖ ለዚሁ ዓይነት የጠላት ሀገር መንግሥት በመሰለፍ፣

ሐ/ የጦር ወታደሩ የጦር አገልግሎት ከመፈፀም እምቢተኛ እንዲሆን፣ ወታደራዊ አመፅ እንዲያስነሳ ወይም እንዲከዳ በግልፅ በማነሳሳት ወይም የጦር ወታደርነት ግዴታ ያለበት ሰው ከእነዚህ ወንጀሎች አንደኛውን እንዲፈፅም በመገፋፋት ወይም እንዲነሳሳ በማድረግ፣ ወይም

መ/ ለሀገር መከላከያ የሚያገለግሉትን ወታደራዊ የጥንቃቄ እርምጃዎች በማሰናከል፣ በማበላሸት ወይም በማናቸውም ሌላ ዘዴ የተንኮል ድርጊት በመፈፀም በኢትዮጵያ የመከላከያ ኃይል ላይ ጉዳት ያደረሰ እንደሆነ ከአምስት ዓመት እስከ 25 ዓመት ለመድረስ በሚችል ጽኑ እስራት ወይም ነገሩ እጅግ ከባድ በሆነ ጊዜ በተለይም በጦርነት ወይም ጦር አስጊ በሆነበት ጊዜ እንደሆነ በእድሜ ልክ ጽኑ እስራት ወይም በሞት ይቀጣል።

ምንጭ፦ የኢፌዲሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ

ከመንግሥታዊ ተቋማት የሚወጡ ሰሞነኛ ዜናዎችና መግለጫዎች

Source: semonegna.com

Exit mobile version