Dinknesh Ethiopia

ክፋትን ተላብሶ የተዘራው ዘር መርዛማ ፍሬውን አፍርቷል – ሰለ መተከል የ ኢ ህ አ ፓ መግለጫ

eprpHeader2020

ታህሳስ ፳፪ ቀን ፪ ሺህ ፲፫ ዓ.ም

ከሕግ መንግሥቱ ከመነጨው የፌዴራል ስርዓት የተነሳ የተጀመረው የዜጎች መፈናቀል እየከረረና እየመረረ መጥቶ ለዜጎች ሕይወትና ንብረት ውድመት ምክንያት ከሆነ ዓመታትን አስቆጠረ። ዛሬም እንደትናንቱ ዘርን መሠረት ያደረገው ጭፍጫፋ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና በአንዳንድ የኦሮሚያ አካባቢዎች ተጠናክሮ መቀጠሉን ስንሰማ የተሰማንን ሃዘን ለመግለጽ ቃላት ያጥረናል፡፡ በየትኛውም አገር ውስጥ በሥልጣን ላይ ያለ መንግሥት በዝቅተኛ ደረጃ ከሚጠበቅበት ሃላፊነቶች ውስጥ ደህንነትን ማስከበርና የዜጎችን በሰላም የመኖር መብት ማረጋገጥ ነው።

በአገራችን ዘርን እየለዩ ማጥቃት፣ ዘግናኝ በሆነ ሁኔታ መጨፍጨፍና ማፈናቀል የተጀመረውና የተዘራው ዘረን መሠረት ያደረገ ክልል ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ ነው፡፡ ቀደም ሲል አልፎ አልፎ ግጭቶች ቢኖሩም በሀገር ሽማግሌዎች የሚፈቱ እንጂ እንደአሁኑ ጠርዝ የረገጡ እንዳልነበሩ እናውቃለን፡፡ በታሪክ አጋጣሚ በሁሉም የሀገራችን አካባቢዎች እንደጨው ተበትኖ የሚገኘው የአማራ ማኅበረሰብ የጥቃቱ ገፈት ቀማሽ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት ዘር የማፅዳት ዘመቻው ሌሎችንም አካቶ በይፋ ቀጥሏል፡፡ ነገሩን የበለጠ አሳሳቢ የሚያደርገው፣ ከእልቂቱና ከማፈናቀሉ ጀርባ በተለያየ ደረጃ የሚገኙ የመንግሥት አካላት ለእልቂቱ ተባባሪና ዋና ዘዋሪ ሆነው መገኘታቸው ነው፡፡

የጥፋት ቡድኖችና ግለሰቦች ዕቅድ እያወጡ፣ በዘር ላይ ያነጣጠረ ተከታታይ ጭፍጨፋ ሲደረግ የክልሉ መንግሥት ምን ይሠራ ነበር? ብሎ መጠየቁ ተገቢ ይሆናል፡፡ ቢያንስ ቢያንስ በየክልሎቹ የተቀመጠው ሕገመንግሥት “ሁሉም ዜጎች በሚኖሩበት ክልል በሰላም ሠርተው መኖር ይችላሉ” ይላል፡፡ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በኦሮሚያ፣ በጉራፈርዳ…ወዘተ ያሉ የመንግሥት አካላት ይህን ለምን አያስከብሩም ብሎ ከበላይ ያለው የመንግሥት አካል መጠየቅ በተገባው ነበር፡፡ ነገር ግን ጥፋቱ መፈጸሙን ከማመን የዘለለ የየክልል አመራሮች ተጠያቂ ሲደረጉ አይታይም፡፡

ሰሞኑን በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ዜጎቻችን ላይ አሰቃቂና ዘግናኝ ግድያ ስፈጸም በከፍተኛ ሃዘንና ቁጭት እየተመለከትን ነው። የክልሉ አመራር ሁኔታው ከአቅማችን በላይ አይደለም ሲልም ተደምጧል፡፡ ታዲያ ዜጎች በማንነታቸው ተለይተው አማራ፣ ኦሮሞ፣ ሺናሻና አገው እየተባሉ በእርሻ ቦታቸው ሲገደሉ፣ ለገበያ በወጡበት ሲታረዱ፣ በቀስት ግንባራቸው እየተበሳ ሲሞቱ፣ ሆድ ዕቃቸው በቀስት ሲወጋ፣ ህፃናት ሲታረዱ፣ ነፍሰ ጡር ሴቶች በሣንጃ ሆዳቸው ሲቀደድ ፣ ከሆድ የወጣዉም ህጻን ሲታረድ፣ ሰዎች መገደላቸው አንሶ ከተገደሉ በኋላ አስከሬናቸው በእሳት ሲቃጠል፣ በቤታቸው ውስጥ ህፃናትና አረጋውያን በተኙበት እሳት ሲለኮስባቸው፣ ከእሳቱ ለማምለጥ ሲሞክሩ ከውጭ ጠብቀው በጥይት ሲለቅሟቸው ለምን ጥፋቱን ማስቆምና ዜጎችን ለመከላከል አልተቻለም? በሀገሩ ዜጎች ላይ አሰቃቂ ግድያ ሲፈጸምባቸው፣ ተሰምቶም ታይቶም በማይታወቅ አስደንጋጭ ሁኔታ በግሬደር ቆፍሮ የሰዉን ልጅ እንደቆሻሻ አመሠቃቅሎ መቅበርን “ለምን?” ብሎ ጥያቄ የማያነሳ መንግሥት በሕግ የተሰጠውን ሃላፊነት በአግባቡ አልተወጣም ማለት ተገቢ ይሆናል፡፡

ከላይ እንደተጠቀሰው “የዓሣ ግማቱ ከጭንቅላቱ” እንዲሉ፣ ለዚህ ሁሉ የዘር ፍጅት ምክንያት የሆነው ሕገ መንግሥቱና ዘርን መሠረት አድርጎ የተዋቀረው የፌደራል ሥርዓት መሆኑን ሁሉም የሚያውቀው እና ፀሐይ የሞቀው ሃቅ ነው፡፡ ስለሆነም የኢትዮጵያውያንን ይሁንታ ያገኘ ሕገ መንግሥትና ሁሉንም ዜጎች በመፈቃቀድ፣ በእኩልነትና በፍትኅዊነት መብታቸውን ሊያስክብር የሚችል ፌደራላዊ አወቃቀር እስካልተመሠረተ ድረስ፣ በአገራችን ውስጥ ሰላምና መረጋጋት ይኖራል ብሎ ኢሕአፓ አያምንም፡፡ ስለዚህም በዜጎች እኩልነት፣ በአገራችን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት የሚያምኑ ዜጎች ሁሉ በጋራ በመምከር መፍትሄ የመፈለግ ግዴታ አለባቸው። የችግሩ ጥልቀት ይሰማናል፣ ይመለከተናል፣ ኢትዮጵያ እንደ ሀገር መቀጠሏን እንፈልጋለን የምንል ኢትዮጵያውያን ሁሉ ሳንውል ሳናድረ ተሰባስበን በመመካከር ለአገራችንና ለዜጎቻችን ህልውና እንድረስላቸው በማለት ኢሕአፓ ዛሬም ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡ ኢሕአፓም የበኩሉን አስተዋፅኦ ለማበርከት ዝግጁነቱን ያረጋግጣል።

በአሁኑ ሰዓት በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል እና በጉራ ፈርዳ ውስጥ ዘር እየለዩ የሚካሄደውን ጭፍጨፋ ኢሕአፓ በጥብቅ ያወግዛል። በተጠቀሱት አካባቢዎች ለተፈፀመው ዘግናኝና አሰቃቂ የብዙዎች ሕይወት መጥፋት መንግሥትም ያለበትን ኃላፊነት ተገንዝቦ፤ ከፌደራል እስከ ክልል የተዘረጋውን የጥፋት ኃይል መረብ በመበጣጠስ በነዚህ ሀገር አፍራሾችና አረመኒያዊ ባህሪ በተላበሱ ወንጀለኞች ላይ ጠንከር ያለ እርምጃ እንዲወስድና የሰላማዊ ዜጎችን በህይወት የመኖር መብት እንዲያስከብር ኢሕአፓ ይጠይቃል፡፡ ለተፈናቀሉና በጭፍጨፋዉ ለተጎዱ ዜጎች አስቸኳይ ሰብዓዊ እርዳታ እንዲደርሳቸዉ፤ ያዝ ለቀቅ ባልሆነ እና በዘላቂነት የዜጎች ደህንነት በአስተማማኝ ደረጃ የሚጠበቅበትን ሀገራዊ ሰላም በመፍጠር ወደ መጡበት ቀየ የመመለስና መልሶ የማቋቋም ተግባር እንዲፈፀም ኢሕአፓ ለመንግሥት አበክሮ ያሳስባል፡፡

በመጨረሻም፣ ኢሕአፓ እየተከሰተ ባለው ዘግናኝ ፣ አሰቃቂ፣ ጭካኔ የተሞላበትና ኢሰብአዊ ድርጊት የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን እየገለጸ የጭፍጨፋው ሰለባ ለሆኑት ቤተሰቦች የሀዘናቸው ተካፋይ መሆኑን በማሳወቅ መጽናናቱን እንዲሰጣቸው ምኞቱን ያስተላልፋል፡፡

በዚህ እና በመሰል ጉዳዮች ላይ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አስቸኳይ ስብሰባ ጠርቶ በማወያየት እና የጋራ አቋም በመያዝ ትርጉም ያለዉ መልዕክት ለመንግሥት እንዲያስተላልፍ እንጠይቃለን፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝብ በወንድማማችነት፣ በሰላም፣ በፍቅር ለዘለዓለም ይኖራል!

ዘረኝነትን ልንጸየፈው ይገባል!!!

ኢሕአፓ ለተሻለ ነገ!!!

Exit mobile version