Site icon Dinknesh Ethiopia

ኢትዮጵያን ከጥፋት አደጋ ለመታደግ የቀረበ ጥሪ

በኢትዮጵያ የረዥም ዘመን ታሪክ ውስጥ ተከስቶ በማይታወቅ መልኩ በውጭ ጠላቶች በሚቆሰቆስና በሀገር ውስጥም ባሉ ውስብስብ ችግሮች ምክንያት፣ ጊዜው ሀገራችን ከፍተኛ ውጥረት ውስጥ የምትገኝበት ወቅት ነው።

ህወሓት መሩ የኢህአዴግ አገዛዝ ለ27 ዓመታት ተግባራዊ ያደረጋቸው ፖሊሲዎች፣ ሕዝባችን በጠላትነት እንዲተያይ፣ የአንዱ ክልል መጠቀም የሌላው መጎዳት ሆኖ እንዲታይ፣ እኛና እነሱ (መጤዎች) የሚል አስተሳሰብ እንዲሰርፅ፣ ኢትዮጵያውያን እንደ አንድ ሀገር ዜጎች ለጋራ እሴትና ለጋራ ህልውና ትኩረት ከመስጠት ይልቅ በክልል፣ በዞን፣ በጎጥ፣ በመንደር በመከፋፈል በስጋት እንዲኖሩ የረጅም ጊዜ ሥራ ሲሠራ እንደነበረ ይታወቃል። ህወሓት ይህንን አደገኛ የጥፋት ተግባሩን በቀጣይነት ተፈጻሚ እንዲሆን በሕገ-መንግሥትና በመዋቅር ተደግፎ ህጋዊነትንም አግኝቶ እንዲንቀሳቀስ እድርጓል።

የህወሓት የአገዛዝ ሥርዓት አንዱን በወዳጅነት ሌላውን በጠላትነት እየመደበ፣ ሕዝቡ በጥርጣሬ እንዲተያይ፣ እንዲፈናቀል፣ እርስበርሱ እንዲጠፋፋ…ወዘተ በመቀስቀስ የብዙዎች ሕይወትና ንብረት አንዲወድም አድርጓል።  ህወሓት የጥፋት ተግባሩን የሚያሰፋፋበትና የሚያስፈጽምበትን ተቋማት በራሱ ታማኝ ካድሪዎች እንዲዘወሩ በማደርግ፣ ተቋማቱ ለሕዝብና ለሀገር ጥቅም ሳይሆን ህወሓትን በሥልጣን ላይ ለማቆየት፣ ዘረፋና ሙስና በቀጣይነት እንዲስፋፉ አድርጓል።

ህወሓት በዘረጋቸው የተንኮል መረቦች አማካኝነት ሕዝቡን ረግጦና አፍኖ ለ27 ዓመታት በሥልጣን ላይ ቆይቷል። ይሁን እንጂ ሕዝቡ በህወሓት መጠነ-ሰፊ ግፍ በመማረሩ፣ ሙስናና ዘረፋ ዓይን ያወጡ በመሆናቸው፣ አድልዖና ሽብርተኝነት በስፋት በመስፈኑ፣ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ተረግጠው የሕግ የበላይነት ጉድ በሚያስብል ደረጃ በመጣሱ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ የሕይወት ዋጋ ከፍሎ አልገዛም በማለት ህወሓትን ከማዕከላዊ መንግሥት ሥልጣኑ አስወግዷል።

ከሥልጣን መወገዱ አልዋጥለህ ያለው ህወሓት፣ ቀደም ሲል ባዋቀራቸው የጥፋት መሣሪያዎቹ አማካኝነት፣ ሀገር እንድትተራመስ ተከታታይ ጥፋቶችንና በደሎችን ሲያካሄድ እንደነበረ ፀሐይ የሞቀው እውነታ ነው።  ህወሓት በራሱና ባዋቀራቸው የጥቅም ቡድኖቹ አማካኝነት ያፈሰሰው ደምና ያወደመው ንብረት ሳይበቃው፣ የመንግሥት ሥልጣንን እንደገና ለመያዝ አቅዶ ተነሳ። ከ20 ዓመታት በላይ በትግራይ ውስጥ የሕዝቡን ኑሮ እየኖሩ፣ ገበሬውን በጉልበት እያገዙ፣ ሀገርን ሲጠብቁ በነበሩ የሰሜን ዕዝ የመከላከያ ሠራዊት አባላት ላይ ኢ-ሰብዓዊ በሆነ መልክ እጅግ ዘግናኝ ጭፍጨፋ ፈጸመ።  የኢትዮጵያን ሕዝብ እጅግ ያስቆጣው ድርጊት በመክላከያ ኃይል፣ በአፋርና በአማራ ክልል ልዩ ኃይሎች እንዲሁም ከሁሉም የሀገራችን ክፍሎች በተገኘው ሰፊ ድጋፍና ትብብር፣ ህወሓትና የፖለቲካ አመራሩ እንዲፈራርስ ሆነ።  ሀገር አጥፊው ቡድን ከፈረሰ በኋላም ሀገርንና ሕዝብን ለማበጣበጥ ሙከራም እያደረገ ነው።  ከዚህ ውስጥ ጎልቶ የሚተየውም በማይካድራ በማንነት ላይ ባተኮረ ጭፍጨፋ ከአንድ ሺህ በላይ የአማራ ማኅበረሰብ ተወላጆች ኢ-ሰብዓዊና አስቃቂ በሆነ መንገድ የተፈጸመው ጭፍጨፋ ነው።  ህወሓት ለአሥርተ-ዓመታት በዘለቀው የሥልጣን ዘመኑ ወቅት በዘረፈው ሀብት በገዛቸው አፈቀላጤዎቹ አማካኝነት በዘረጋው ዓለምአቀፋዊ የግንኙነት መረብ በመጠቀም በሀገራችን ላይ ጉዳት ለማስከተል የሚያስችል ከፍተኛ ጫና ለማድረግ እየሞከረ ይገኛል።

ከዚህ በተጨማሪ በሀገራችን ውስጥ በህወሓት ተግባር በተከተለው አለመረጋጋትና የተፈጠረውን ክፍተት በመጠቀም፣ ሱዳን የሀገራችንን ድንበር ተሻግራ የተወሰኑ ቦታዎችን በኃይል ይዛ ከመገኘቷም በላይ ይበልጥ ለመስፋፋትም እየሞከረች ነው።  የግብፅ መንግሥትም ኢትዮጵያ የአባይን ውሃ ለመብራት ኃይል ማመንጫ የማዋል መብቷን በመዳፈር፣ የዕድገት ጉዟችንን ለማስቆም፣ የህዳሴ ግድቡ ያለነርሱ ፈቃድ መገንባቱና ሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌቱ የሚቀጥል ከሆነ፣ ወታደራዊ እርምጃ ለመውስድ መዘጋጀቷን አልደበቀችም።

ይህ ሁሉ አደጋ በሀገራችን ላይ ባንዣበበት አውድ ውስጥ ደግሞ፣ የአሜሪካና የአውሮፓ መንግሥታት ትግራይ ውስጥ የተፈጠረውን ቀውስ ምክንያት በማደረግ በሀገራችን የውስጥ ጉዳይ በቀጥታ ጣልቃ እየገቡ ነው።  ኢትዮጰያ የውጭ መንግሥታት የሚሉትን ካልፈጸመች የቅጣት እርምጃዎችን ለመውሰድ እንዲቻል በተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤትና በአውሮፓ ኅብረት አንዲሁም በአፍሪካ አንድነት በኩል በሀገራችን ላይ ጫና ለማድረግ የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን እያደረጉ ይገኛሉ።

ስለሆነም ሀገራችን በአሳሳቢ ደረጃ ላይ በምትገኝበት በአሁኑ ወቅት፣ በፖለቲካ ምክንያት የሚታየው መከፋፈል፣ የህወሓት ትንኮሳ ያስከተለውን ወታደራዊ ግጭትና ቀውስ፣ የሱዳንና የግብፅን የወረራና የአደናቃፊነት ሥራና የምዕራቡን ዓለም ተጽዕኖ ጠቅለል አድርገን ስንመለከት፣ በርግጥም ሀገራችን ከፍተኛ አደጋ እንደተደቀናባትና አስቸኳይ መፍትሄ መፈለግ እንደሚገባ ፍንትው አድርጎ የሚያሳዩ እውነታዎች ናቸው።  በሀገራችንና በሕዝባችን ላይ ከተለያዩ አቅጣጫዎች የመጡት የጥፋት አደጋዎች ትውልዱንና የሀገራችንን ሀልውና ከምን ጊዜውም በላይ የሚፈታተንበት ደረጃ ላይ እንዳደረሱት ግልጽ ይመስለናል።  በመሆኑም መፍትሄ በመፈለጉና ተግባራዊ በማድረጉ ላይ ጥረት ካላደረግን ችግሮቹ እኛ ሰላልፈለግናቸው ብቻ በራሳቸው የሚወገዱ አይሆኑም።  ከሁሉም በላይ የሀገር ህልውና እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ የሚገኝበት ወቅት ነው።

ስለዚህ በሀገራችን ላይ ያንዣበበውን አደጋ ለመከላከል ኢትዮጵያውያን ሁሉ በአንድነት መቆም ያለብን ጊዜው አሁን ነው።  የፖለቲካ ድርጅቶችም በሰላማዊ የትግል መድረክ ላይ መፎካከር የምንችለው ሀገር ስትኖር መሆኑን ከልብ በማመን ልዩነታችንን አቻችለንና ለሀገር ቅድሚያ ሰጥተን መፍትሄ ለማግኘት በቅን መንፈስ ልንመካከር ይገባል።   ሀገርን ለማዳን ምን ማደረግ እንደሚገባንም የሰከነ ውይይት በማድረግ መግባባት ላይ መድረስ እንዳለብን የኢትዮጵያ ሕዝብ ፅኑ ፍላጎቱ መሆኑን ለአፍታም መዘንጋት የለብንም።  ወቅቱ አንድነታችንንና የሁላችንንም መተባበር የሚጠይቅበት ወቅት መሆኑንና የተከፋፈለ ሕዝብ ለጥቃት የተጋለጠ መሆኑንም መረዳት ያለብን ጊዜ ነው።

ስለዚህም የፖለቲካ ድርጅቶችና የገዢውን ፓርቲ ብልጽግናን ጨምሮ፣ ሀገራችን በምትገኝበት ሁኔታ ላይ ተመካክሮ መፍትሄ ለማምጣት እንዲቻልና በሀገራችን ላይ ያንዣበበውን አደጋ ለመቀልበስ የምንችልበትን መንገድ በጋራ ልንሻ ስለሚገባ  አስቸኳይ የፖለቲካ ፓርቲዎች ስብሰባ እንዲካሄድ ጥሪ እናቀርባለን።  የሀገራችን ጉዳይ የፖለቲካ ድርጅቶችን ብቻ የሚመለከት እንዳልሆነ ስለምናምን ሌሎች ባለድርሻዎችና ኢትዮጵያውያን ሁሉ በሀገር አድኑ ተገባር ላይ አስተዋጽዖ ለማደረግ እንዲችሉ በጋራ የሚመክሩበትንና በአንድነት የሚነቃነቁበትን መንገድ ለመሻት የመጀመሪያው የምክክር ጉባዔ አንዱ አጀንዳ እንዲሆንም ሃሳብ እናቀርባልን።

ይህ አጣዳፊ ሀገራዊ ተግባር በፍጥነት መከናወን ስላለበት በመንግሥት አስተባባሪነት፣ ካልተቻለ ወይም ፍቃደኝነቱ ከሌለ ደግሞ በፓለቲካ ፓርቲዎች ተነሳሽነት የፖለቲካ ፓርቲዎች ምክር ቤት ሃላፊነቱን ወስዶ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተግባራዊ እንዲያደረግ በከፍተኛ አጽንዖት ጥሪያችንን እናቀርባለን።

ኢትዮጵያ በልጆቿ መስዋዕትነት ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኖራለች!

የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ)

መጋቢት ፮ ቀን ፪ ሺህ ዓ. ም

 

Exit mobile version