ከኢፖአኮ-በካናዳ የቀረበ መግለጫ
የኢትዮጵያ የፖለቲካ እስረኞች አንድነት ኮሚቴ-በካናዳ (ኢፖአኮ-በካናዳ)፣ ኢትዮጵያ ውስጥ በዜጎቸ ላይ እየደረሰ ያለውን የሰብዓዊ ሆኑ ሌሎችም መሠረታዊ የሰውለጆች መብት ጥሰትን አሁንም እንደበፊቱ በቅርብ እየተከታተለ በደል የሚፈጽሙ ግለሰቦች ይሁኑ መንግሥታዊ አካላትና ተቋማትን ጉዳዩ ለሚመለከታቸው ሁሉ በዓለምአቀፍ ደረጃ በማሳወቅ ተጠያቂ እንዲሆኑ ሲያደርግ የቆየ ህጋዊ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋም ነው።
ኢፖአኮ-በካናዳ አሁን በሥልጣን ላይ ያለው የብልጽግና ፓርቲ በተለያዩ ወቅቶቸ በዜጎቸ ላይ ያደረሰውን ስበዓዊ መብት ጥሰቶች ሲያወግዝ እንደነበር ይታወሳል።
ካለፈው ሳምንት ጀምሮ በበልጽና ፓርቲ የሚመራው መንግሥት በአማራ፣ በአፋር፣ በኦሮሞና በሌሎችም ክልሎች ውስጥ በቀድሞ ወታደራዊ መሪዎች፤ በጋዜጠኞች፣ በፋኖ፣ በፖለቲካ አክቶቪስቶችና ሌሎችም ላይ የጀመረው አፈናና የጅምላ እስራት በእጅጉ አሳስቦናል፡፡ በወንጀል የተጠረጠሩ ዜጎችን በህግ አግባብ ይዞ ለፍርድ ማቅረብ ሲገባ ከአሸባሪነት ባልተናነሰ መልኩ አፍኖ በመውሰድ ያሉበትን አድራሻ በውል ለቅርብ ዘመዶች እንኳ ሳያሳዉቁ አግቶ ማቆየት ፍጹም ተቀባይነት የሌለው ሊወገዝ የሚገባው ኢስበዓዊ ድርጊት ነው።
ኢፖአኮ-በካናዳ የመንግስትን ፖሊሲዎችን አጥብቀው የሚተቹም ሆኑ የሚቃወሙ የብዙሀን መገናኛ ሰራተኞች እና የፖለቲካ ተንታኞች መኖር ለዴሞከራሲ ማበብ፣ ተጠያቂነት ለሰፈነበት ሥርዓት መመሥረት፣ እንዲሁም የሀዝብን ብሶት በይፋ የሚያንጸባርቁ ተቋማትን እውን ላማድረግ እጅግ መሠረታዊ ናቸው ብሎ ብፅኑ ያምናል፡፡ ስለዚህ ስጋታችን እነዚህን የሚያዳክም ማንኛውም መንግሥታዊ ዕርምጃ በተቃራኒው ኢትዮጵያን ወደ ተለመደው የቀውስ አዙሪት እንዳይከታት ነው።
ይህ ሁሉ የሚካሄደው ደግሞ ኢትዮጵያ የሀሳብ ልዩነትን ቅራኔናና ውስብስብ ችግሮቿን በመከከር ለመፍታት እየተዘጋጀች ነው በሚባልበት ጊዜ መሆኑ ይህንን ጅምር መጥፎ ጥላ ያጠላበታል፡፡
ሰለሆነም መንግሥት ህጋዊ ያልሆኑና ሁኔታዎችን እጅግ ከሚያካርር እርምጃ በአስቸኳይ እንዲገታ፣ የታሰሩትን ጋዜጠኞች፣ የፖለቲካ ተንታኞችና አክቲቭስቶችን እንዲፈታና ከፋኖም ጋር ሆነ ሌሎች ጋር የሀሳብ ልዩነቱንም በጠረጴዛ ዙሪያ እንዲፈታ አጥብቀን እናሳስባለን፡፡ በትክክል በወንጀል የሚፈለጉም ቢኖሩ መሠረታዊ መብታቸው ሙሉ በሙሉ እንዲከበር እና ፍትህንም ያገኙ ዘንድ በጥብቅ እናሳስባለን።
ኢፖአኮ-በካናዳ የሀገሪቱ ፓርላማ፣ የሚመለከታቸው የመንግሥት ተቋማት ሆኑ የፖለቲካ ሀይሎችና የሲቪክ ማህበራት፣ ይህ የሰሞኑ ዕርምጃዎች ሃገሪቱ ከአንድ ችግር ሳትወጣ ወደ ሌላ አረንቋ የሚያስገባት መሆኑን ተረድተው ይህ ሁኔታ እንዲቆም አሰፈላጊውን ህጋዊ ግፊት ሁሉ እንዲያድርጉ ከወዲሁ በጥብቅ ያሳስባል
ፍትህ ለፖለቲካ እስረኞች በኢትዮጰያ