Site icon Dinknesh Ethiopia

መንግሥት የችግሩ ወይስ የመፍትሄው አካል?

Democracia Header

ቅጽ 50፣ ቁ 2                                                                                                    ሐምሌ፣ 2014 ዓ. ም

መንግሥት የችግሩ ወይስ የመፍትሄው አካል?

ከለውጡ ወዲህ ያለውን የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሁኔታ “ተስፋና ስጋትን ያዘለ” በሚል መግለፅ እየተለመደ መጥቷል፡፡ ሆኖም ከዓመት ወደ ዓመት የለውጡ ተስፋ እየተሟጠጠ፣ ስጋቱ እየጨመረ መምጣቱን የመንግሥት ደጋፊዎችም ሆኑ ተቃዋሚዎች ባመዛኙ የሚስማሙበት ነው፡፡

ኢሕአፓ ከዚህ ቀደም ባወጣቸው ሁለት የዴሞክራሲያ እትሞች፣ በአንደኛው “ለውጡ የት ገባ?” (ቅጽ 47 ቁ. 2፣ ጳጉሜን 2011 ዓ. ም) በሚል ርዕስ፤ በሁለተኛው “ከቀውስ ወደ ባሰ ቀውስ” (ቅጽ 48 ቁ. 2፣ መጋቢት 2012 ዓ. ም) በሚል ለውጡ የገጠሙትን ችግሮችና እምቅ ተስፋውን ለማሳየት ሞክሯል፡፡

የአገራችን ችግሮች በተለያየ አውድ ይገለፃሉ፡፡ በፍትኅ ሥርዓቱ ብልሹነት፣ በተረኝነት፣ በኑሮ ውድነት፣ በሙስና፣ በማኅበራዊ ትስስርና መተሳሰብ መዝቀጥና በአስፈሪ ሁኔታ በመላ አገሪቱ ሊባል በሚቻል ደረጃ ሥርዓት አልበኝነትና ጦርነት በሰፈነበት ሁኔታ ሲገለፁ፣ ይህን ለመቅረፍ የሚችሉና አማራጭ ራዕይ የሚያቀርቡ ተደማጭ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች አለመኖርም የችግሩ አካል ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ሳናጣራ አናስርም” ብለው ባደረጉት ንግግር የኢትዮጵያን ሕዝብ ካማለሉ በኋላ፣ “ፅድቁ ቀርቶ በወጉ በኮነነኝ” እንዲሉ፣ ሳያጣሩ ማሰር ቀርቶ እንዲያውም ጋዜጠኞችንና ተቃዋሚዎችን በጠራራ ፀሐይ እንደ ወንበዴ ማፈንና መዳረሻቸውን ለሳምንታት አለማሳወቅ፣ ለፍርድ አለማቅረብ፣ ፍርድ ቤት በዋስ የለቀቃቸውን ፖሊስ በሥልጣኑ መልሶ ማሰር ወይም አለመልቀቅ እየተለመዱ መጥተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሚመሩት መንግሥት ያሉትን የፍትኅ ተቋማት በጉቦኝነትና በዘረኝነት በአደባባይ እየከሰሱ፣ የተቀናበረ እርምት መጀመር ቢሳናቸው እንኳን ይህን ማስቀጠልና አጥፊዎችን ለሕግ አለማቅረብ የተለመደው አሠራራቸው ሆኖ እየቀጠለ ነው፡፡

ህወሓት ጥሎት ካለፈው ጠንቅ (ወደፊት ሥልጣን ሊጋራ እንደሚችል ወይም እንደማይችል እርግጠኞች ባንሆንም) አንዱና ዋነኛው ኤኮኖሚውንም-ፖለቲካውንም-ማኅበራዊ ሥሪቱንም በሙሉ ባመዛኙ በትግርኛ ተናጋሪ ኣባላቱና 2 ደጋፊዎቹ መጠቅለሉ ነበር፡፡ ዛሬም ሥልጣኑን የያዘው የኦህዴድ ብልፅግና ይኸው የህወሓት በሽታ ተጠናውቶት የአዲስ አበባን የሥነ-ሕዝብ ስርጭት በሕገወጥ መንገድ ኦሮምኛ ተናጋሪዎችን በማስገባት ለመለወጥ መሞከር፣ ለነዚሁ ዜጎችና ለኦህዴድ ካድሬዎች ሕገወጥ የኮንዶሚኒየም እደላ ማድረግ፣ የአዲስ አበባን ሕጋዊ ስፋት በመጣስ የተወሰኑ ወረዳዎቿን ወደ ኦሮሚያ ክልል ማስገባትና ለማስገባት መሞከር፣ የጋራ ታሪክን መጠየፍ – ለምሳሌ የምንሊክን የንግሥና ታሪክ ማንቋሸሽና የዓድዋ ጦርነት መሪነትን ማሳነስ፣ በታሪካዊነት የተመዘገቡ ቅርሳ ቅርሶችን ማፍረስ፣ በአንዳንድ የአዲስ አበባ ት/ቤቶች ተማሪዎችን በሁለት መስመር አሰልፎ የኦሮሞ ብሄረሰብና ሌሎች ኢትዮጵያውያን በሚል መድቦ የኦሮሚያ ክልል መዝሙርን በአንድ ወገን፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ መዝሙርን በሌላው ማዘመርና የወላጆችን ተቃውሞ ማስነሳትን የመሳሰሉ አስፀያፊ እርምጃዎችን እንዲተገበሩ ሆኗል፡፡ (ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰኔ መጀመሪያ ሳምንት ፓርላማ ቀርበው ለዚህ ፀያፍ ተግባር ማጠየቂያ ለመስጠት የተጓዙበትን የውሸት ርቀት፤ ደፋርና አዋቂ ጠበቆችና ዜጎች ቢያስቡበት፣ በአገር ማፍረስ ክህደት ሊያስጠይቃቸው የሚችል ንግግር ነበር)፡፡

የአዲስ ኣበባ ተማሪዎች እንዲዘምሩት የሚፈለገው የኦሮሚያ ክልል ለተማሪዎቹ ያዘጋጀው መዝሙር ጥላቻን የሚሰብክና ኢትዮጵያዊነትን የሚያፈርስ ዘርኝነትን የሚያነግሥ ነው፡፡ መዝሙሩ “ከእናታችን በቀር- ከኦሮሚያ በቀር“፣ “የመቶ ዓመት እድፍ በደማችን አጠብንልሽ”፣ “ሥልጣን መልሰን አገኘን”፣ “ነፍጠኛ የሠራውን ማሰብ ያንገበግባል”፣ “እንደ በግ ግልገል በየመንገዱ ታረድን”፣ በሚሉ በጥላቻና በሃሰት ትርክት የታጨቁ ስንኞች ያሉበት መዝሙር ነው፡፡

በአገራችን ውስጥ እየናረ የሄደው የኑሮ ውድነት ሕዝባችንን ሰቅዞ ይዞታል፡፡ የአገራችን ሕዝብ በተዛባና አብዛኛውን ዜጋ ደሃ ያደረገውን የኤኮኖሚ ሥርዓት ለአንዴና ለሁል ጊዜ ለመለወጥ እንዲሁም ፍትኅ የሰፈነባት ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ለመመሥረት ነበር ኢሕአፓ ከምሥረታው ጀምሮ የታገለው፡፡ በ 1966 ዓ. ም የለውጥ እንቅስቃሴ ወቅት “የጤፍ ዋጋ 60፤ የኔ ደሞዝ 30” የሚል ላባአደራዊ የሰላማዊ ሰልፍ መፈክር ነበር፡፡ በኩንታል 60 ብር የነበረው የጤፍ ዋጋ ዛሬ እስከ 6000 ብር ይጠየቅበታል፡፡ በረንዳ አዳሪዎችን፣ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውንና ተፈናቃዮችን (በዓለም አንደኛ ደረጃ የያዝንበትን አሳፋሪ ክስተት) ከስሌት አውጥተን፣ መካከለኛ ገቢ ያላቸውና የመንግሥት ሠራተኞች በቀን ከአንድ ምግብ በላይ ለመመገብ ፈታኝ እንደሆነባቸው የሚያሳየው አምስት ሊትር የዘይት ዋጋ 1000 ብር ሲጠጋ፣ በአማካይ 4000 ብር ገቢ ያላቸው ለቤት ኪራይ፣ ለልጆች ወጭ፣ ለምግብና ለቤተሰብ ጤና እንዴት ማብቃቃት ይችላሉ?

በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ፣ ድርቅ በቦረናና በከፊል የሶማሌ ክልሎች ከብቶችን እየጨረሰ፣ ገበሬዎች እንደ ጥማድ በሬ ሆነው የሚያርሱበትን ክስተት ተመልክተናል፡፡ እንዲሁም ትዕቢተኛው ህወሓት ባደረሰው ጥቃት በዋግ እምራ የተፈናቀሉ ዜጎች በበሽታና በረሃብ እየተሰቃዩ ይገኛሉ፡፡

ሙስናን በተመለከተ በመንግሥት ተቋማት ከፍተኛ ዝርፊያዎች እንደሚፈፀሙ ቀጥተኛ ያልሆኑ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ጠቅላይ ምኒስትሩም በአደባባይ ሙስና በብልጽግና ውስጥ መረን የለቀቀ መሆኑን በተደጋጋሚ ነግረውናል፡፡ አገልግሎት ተጠቃሚዎች በአብዛኛው እንደሚናገሩት ጉቦና ምልጃ የሚጠበቁ የሥራ ማሳለጫዎች ናቸው፡፡ በመንግሥት በኩል ፍትኅ አጉዳዮች ጠያቂ እንደሌለባቸው ሙሰኞችንም እንደዚሁ የሚነካቸው የለም፡፡ ለምሳሌ የአንድ ሚኒስትር መሥሪያ 3 ቤት ለፓርላማ ያቀረበው የሥራ ዕቅድ ከቀደመው ዓመት ዕቅድ ምንም ሳይለውጥ፣ ሳይጨምርና ሳይቀንስ አቅርቦ ተተችቷል፡፡ ተጠያቂነት በሌለበት አገዛዝ ይኽው መሥሪያ ቤት ፈጣሪን ካልፈራ ያንኑ የቀድሞ ዕቅድ ለፓርላማ በየዓመቱ እንደማያቀርብ ዋስትና የለም፡፡

ማኅበራዊ ትስስራችን በእጅጉ ተጎድቷል፣ ሳስቷል፡፡ ወንጀል መፈጸም፣ ይሉኝታ ማጣት፣ የተደራጁና የወታደር ልብስ የለበሱ ዘራፊዎች ሕዝባችንን መዝረፍ ተበራክቷል፡፡ በአገራችን ውስጥ እየተበራከቱ ያሉትን ችግሮች ለማሳየት በመንግሥት ላይ ተስፋ መቁረጥ፣ የሃይማኖት ተቋሞች የፍትኅና የተስፋ ቤቶች ከመሆን ይልቅ የሙስናና አንዳንዴም በመንግሥት ጣልቃ ገብነት የሽኩቻ መድረክ መሆን፣ የውጭ የባህል ተጽዕኖ በአገሪቱ ውስጥ መንሰራፋት፣ የትምህርት ቤት የክፍል መልቀቂያ ፈተና በባለሥልጣናት መስረቅና ጥላቻን ማስተማር ከብዙዎች ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ “የኔ ብሄር ወንጀለኛ የለውም፣ ወንጀለኞች ሁሉ የምጠላው ብሄር አባሎች ናቸው” የሚል ከዕውነት የራቀ ፍልስፍና በሰፊው ሕዝብ ዘንድ እንዲሰርጽም እየተደረገ ነው፡፡

ሞትንና ጅምላ ጭፍጨፋን ባለፉት ዓመታት በመለማመዳችን የሟቾች ቁጥርና አሰቃቂ የአገዳደሉ ሁኔታ ስሜትን አልኮረኩር ካለ ሰንብቷል፡፡ ወንጀሉም በጊዜና በቦታ በፍጥነት እየተለዋወጠ በመምጣቱ “ትኩሱ ሬሳ የበፊቱን አስረሳ” እንደሚባለው ሆነና ከሁለት ዓመት በፊት ከደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ታፍነው መዳረሻቸው ያልታወቁት ሴት ተማሪዎች ተረስተውና ታሪክ ሆነው ካለፉ ሰነበተ፡፡

ከህወሓት ጋር የተደረው ጦርነት በምን መልክ በድርድር ሊቋጭ እንደተፈለገ ወይም እንደታሰበ ሕዝቡ ምንም ፍንጭ የለውም፡፡ መንግሥት ለታሰበው ድርድር ኮሚቴ እንዳዋቀረ ገልጿል፡፡ ለትግራይ ሕዝብ ኢትዮጵያዊ ወገናችን ነውና ሕዝቡን ለመታደግ እህል፣ መድኃኒትና ነዳጅ የጫኑ የዕርዳታ የጭነት መኪናዎች በስፋት ወደ መቀሌ መግባታቸው ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡ በተመሳሳይም ህወሓት “ከበባ” የሚለውን የመብራት፣ የባንክና የቴሌፎን/ኢንተርኔት አገልግሎት እጦት ከጦርነቱ በፊት ወደ ነበረበት ይዞታ መመለሱ ተገቢነት አለው፡፡

ይህንን ስንል ህወሓት የጦርነት ዝግጅት በማድረግ ላይ እንዳለና ድርጅቱ በታሪኩ ድርድርን ለጊዜ መግዣ እንደሚጠቀም አጥተነው አይደለም፡፡ ኢሕአፓ የዚህ መሰሪ ድርጅት ሰለባ ስለሆነ ተንኮሉን ሊስተው አይችልም፡፡ ሆኖም የመንግሥት ስትራቴጂ ህወሓትን ከትግራይ ሕዝብ የመነጠልና ድርጅቱ ለትግራይ ሕዝብ ችግር እንጂ መፍትሄ የማያመጣ መሆኑን በተከታታይ መግለጫና ለትግራይ ሕዝብ ተጨባጭ ተግባራዊ ድጋፍ በማድረግ ለማሳመን መጣር አለበት እንላለን፡፡ ድርድሩን በተመለከተ በጦርነቱ በግምባር ተጠቂ የሆኑት የአፋርና የአማራ ክልሎችን የደህነነት ስጋቶች ዕይታ ውስጥ በማስገባትና የመደራደሪያ ነጥቦቹ ለሕዝብ ይፋ እየተደረጉ መካሄድ አለበት እንላለን፡፡ የውጭ ተጽዕኖን በመፍራት የክልሎቹ ስጋቶችን ለምሳሌ ወልቃይትን፣ ጠገዴን፣ ጠለምትና ራያን ለህወሓት አሳልፎ ለመስጠት ውል ውስጥ መግባት አገሪቱን የበለጠ ቀውስ ውስጥ የሚያስገባ ክህደት እንደሚሆን ከወዲሁ ለመግለጽ እንወዳለን፡፡

ኢሕአፓ ከህወሓት ጋር ሊደረግ ስለታሰበው ድርድር፣ ምንም እንኳን በሺህ የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ከረገፉ፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ከተፈናቀሉና በቢሊዮን የሚገመት ንብረት ከወደመ በኋላ መሆኑ ቢያሳዝነንም፣ በሰላማዊ መንገድ መፍትሄ ለማምጣት የሚደረገውን ጥረት ይደግፋል፡፡ ይሁን እንጂ መታለፈ የሌለበት ቀይ መስመር እንዳለ አጠንክረን ልንገልጽም እንወዳለን፡፡ ይኽውም የአገር አንድነት ጉዳይ ነው፡፡ ስለሆነም፦

1ኛ) ከድርድሩ በፊት የህወሓት ጦር ትጥቁን ማውረድ አለበት፡፡
2ኛ) የወልቃይት ጠገዴ፣ ሁመራ፣ ጠለምት፣ ራያና ከአፋር አንዳንድ ቦታዎች ህወሓት በጉልበት ነጥቆ የወሰዳቸው በመሆኑ በድርድሩ ውስጥ እንደ ቅድመ ሁኔት መቅረብ የለባቸውም፡፡
3ኛ) በወንጀል የሚፈለጉ የህወሓት አመራሮች ለሕግ መቅረብ አለባቸው፡፡
4ኛ) ውሳኔ-ሕዝብ (ሬፈራንደም) የሚባል ጥያቄ ለመደራደሪያ የሚቀርብ ጥያቄ አለመሆኑ መረጋገጥ አለበት፡፡
5ኛ) ድርድር የሚደረግ ከሆነ ከህወሓት ጋር በተናጠል እንጂ ከሌሎች ጋር ተዳብሎ ሊሆን አይገባም፡፡
6ኛ) ድርድሩ በአፍሪቃ ኅብረት በኩል እንጂ በሌላ አካል በተለይም በምዕራባውያን አማካኝነት የሚደረግ መሆን የለበትም፡፡
7ኛ) ህውሓት በጫረው ጦርነት ሳቢያ ለደረሰው ውድመት ሃላፊነት መውሰድ አለበት፡፡

በአሁኑ ጊዜ በአማራ ክልል ሕግን በማስከበር ሽፋን የሚደረገው የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችና የብዙ ሺህ ወጣቶች መታሰር ሥጋታችንን ከፍ አድርጎታል፡፡ መንግሥት እንደሚለው የፋኖዎችን አስተዋጽዖ የሚያከብር ከሆነ፣ በፋኖ ስም ወንጀል የሚሠሩትን፣ ኅብረተሰቡን በማሳተፍ በቁጥጥር ሥር ሊውሉ የሚችሉበትን መንገድ መቀይስ ይችል ነበር፡፡ የአገር ሽማግሌዎችንና በኅብረተሰቡ የተከበሩና የታወቁ ፋኖዎች በማስተባበር ሌቦችንና ሕገወጦችን በቁጥጥር ሥር ማድረግ ይቻላል፡፡ አፈፃፀሙ ግን ከዚህ በተቃራኒው በመሆኑ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ተስተውለዋል፡፡

በሌላ በኩል ዛሬ በመላ አገሪቱ ሊባል በሚችል ደረጃ ከፍተኛ ሥርዓት አልበኝነት፣ ጦርነትና ግድያ በመንግሥትና መንግሥትን በሚቃወሙት በታጠቁ ኃይሎች ይፈጸማል፡፡ አሁንም ድረስ በህወሓት በተያዙ የአማራና የአፋር ክልል ይዞታዎች ውስጥ እዚህና እዚያ ጦርነቶች ይታያሉ፡፡ የዓይነትና የመጠን ልዩነት ካልሆነ በስተቀር በሌሎች ክልሎችም ንፁሃን ይገደላሉ፡፡ ዜጎች ከቤታቸው ወጥተው ለመግባታቸው ዋስትና የላቸውም፡፡ በተለይ በቤኒሻንጉል፣ በኦሮሚያ፣ አንዳንዴም በአዲስ አበባ፣ አሁናዊው ደግሞ በጋምቤላ የጥፋትና የውድመት ዜናዎች የተለመዱ ሆነዋል፡፡ በቅርቡ በጋምቤላ አካባቢ እየተደረገ ያለው ጭፍጨፋ ከምን ጊዜው የከፋ ነው፡፡ ዜጎች በዘራቸው ተለይተው በዘግናኝ ሁኔታ ተጨፍጭፈዋል፡፡ የክልሉ መንግሥትም ሆነ የፌደራል መንግሥቱ ኦነግ ሸኔን ጠራርገን ከኦሮሚያ ክልል ምድረ-ገጽ አጥፍተነዋል ሲሉ የነበረ ቢሆንም እውነታው በተቃራኒው ነው፡፡ በመሆኑም የአገራችንን ችግሮች በአግባቡ ለመፍታት እንዲቻል የሚያደርግ ሃላፊነት የሚሰማው መንግሥት በመታጣቱ ችግሮቻችን ከቀን ወደቀን እየተባባሱ ይገኛሉ፡፡

የማንኛውም መንግሥት ዋነኛ ሃላፊነት የሕግ የበላይነትን በማስከበር ሕዝቡ በሰላም የሚኖርበትን ሁኔታ ማመቻቸት ሲሆን፣ የብልጽግና መንግሥት ግን ይህን ዋነኛ ሃላፊነቱን በአግባቡ እየተወጣ አይደለም፡፡ ስለዚህም ሕዝባችን በመንግሥት ታጣቂዎችና በሌሎች ጠብመንጃ ባነገቡ ኃይሎች፣ በጠራራ ፀሐይ ተወልዶ ባደገበት መንደር እንደ በግ 5 እየታረደ ነው፡፡ ሕዝቡ የመንግሥት ያለህ እያለ ሲጮህ ስሚ ስላጣ መንግሥት መኖሩን መጠራጠር ብቻ ሳይሆን መንግሥትን ራሱን በዳይ አድርጎ ማየት ጀምሯል፡፡ ይህ ደግሞ ከአገሪቱ ኅልውና አንፃር እጅግ አሳሳቢ ዕውነታ ነው፡፡

ህወሓት በዓለም ተሰምቶ በማይታወቅ ደረጃ የሰሜን ዕዝን በከፍተኛና ዘግናኝ ጭካኔ በማጥቃት አገሪቱ አሁን በምትገኝበት የጦርነት ሁኔታ ውስጥ ካደረሰ በኋላ፣ ሥልጣንን መልሶ ለመያዝ ወደ አዲስ አበባ ሲያመራ፣ የአፋርና የአማራን ክልሎች በመውረር ይህ ነው የማይባል ሕዝቡን፣ የቤት እንስሳትን ያለየሌላ ንብረት አወደመ፡፡ ይህ በሆነበት ጊዜ የብልጽግና መንግሥት የአፋርና የአማራ ሕዝብ በተለይም የአፋር ክልል በተደጋጋሚ የፌደራል መንግሥቱን እርዳታ ቢጠይቅም በበቂ ባለማግኘቱ በአረመኔው ህወሓት እንዲጨፈጨፍ ሆነ፡፡ መንግሥት ያለበትን የሕግ የበላይነትን የማስከበር ኃላፊነቱን ባለመወጣቱ ሕዝባችን እጅግ አሰቃቂ ግፍ እንዲፈጸምበት ሆኗል፡፡ በዚህ ብቻም አላበቃም፣ ኦነግ ሸኔ የተባለው ሽብርተኛ ድርጅት በሰሜን ሸዋ፣ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ አማሮችን በግፍ ሲገድል፣ የጉምዝ ታጣቂ ሌላ እኩይ ኃይል ደግሞ ኦሮሞዎችንና አማሮችን በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ሲጨፈጭፍ ማዕከላዊው መንግሥት ምንም አላደረገም፡፡ በመሆኑም የብልጽግና መንግሥት ተቀዳሚ ሃላፊነቱ የሆነውን የዜጎችን ደህንነት የማስጠበቅ ሃላፊነቱን አልተወጣም፡፡

ስለዚህ፣ በኢትዮጵያ የተንሠራፉትን ችግሮችን ለመቅረፍ ምን መደረግ አለበት?

የብሄራዊ ምክክር ኮሚሽኑ አንድ የመፍትሄ አካል ነው፡፡ ለችግሮቻችን መፍትሄ ለመፈለግ፣ በሌሎች አገሮችም እንደታየው፣ በምክክር ለመፍታት ጥረት ማድረግን ኢሕአፓ በመርኅ ደረጃ ይቀበላል፣ ጥረቱ እንዲሳካም የሚቻለውን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ ነው፡፡ በኮሚሽኑ አመሠራረት ላይ መንግሥት በብቸኝነት በወሰዳቸው የማዋቀር ሂደትና በአካሄዱም ላይ በታዩት ስህተቶች፣ የተወሰኑ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ኮሚሽኑን እንደማይቀበሉ ገልፀዋል፡፡ የኮሚሽኑ ዓላማ ከዜጎች ወኪሎች ጋር በአካታችነትና በኣሳታፊነት መመካከርና መፍትሄ ማፈላለግ ሲሆን፣ ገና ሥራውን ሳይጀምር እንቅፋት ከፊቱ ተጋርጦበታል፡፡ ከ7-10 የሚሆኑ ድርጅቶች የራሳቸውን አማራጭ የምክክር መንገድ እንደሚያዘጋጁ ገልፀዋል፡፡ እነዚህ ክስተቶች ሲታዩ የተመሠረተው የብሄራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ሂደት የተቃና የሚሆን አይመስልም፡፡

ስለዚህ ለችግሮቻችን መፍትሄ ለማምጣት ምን አማራጭ አለ? ኢሕአፓ፦

1. መንግሥት ተቀዳሚ ሃላፊነቱን በመወጣት የዜጎችን ደህንነት ማስከበር አለበት፡፡ ለዚህም አስፈላጊ እርምጃዎችን በመውሰድ በመላው የአገራችን ክፍሎች ሁሉ ሰላምና መረጋጋትን ማስፈን አለበት፡፡
2. አገራችን አሁን ከምትገኝበት አሳሳቢ የመፈራረስ አደጋ ለመውጣት የምትችልበትን መፍትሄ ፍለጋው ላይ ኢትዮጵያውያን በወኪሎቻቸው አማካኝነት አሳታፊ ማድረግ ይገባዋል፡፡
3. በየክልሎቹ የሚገኙት የታጠቁ ልዩ ኃይሎችን ሁሉ በአገር መከላከያ ሥር በአዲስ መልክ በማዋቀር በማዕከላዊ ዕዝ ሥር እንዲካተቱ ማድረግ አለበት፡፡
4. ታሪካዊ የውጭ ጠላቶቻችን አጋጣሚውን በመጠቀም የአገራችን ድንበር ዘልቀው በመግባት ጉዳት እንዳያደርሱ፣ ወይም የውስጥ ከሃዲዎችን በመጠቀም አገራችን ወደ ከፋ ቀውስ፣ አለመረጋጋትና መፈራረስ ደረጃ እንዳያደርሱ፣
ሕዝቡ በመንግሥት ላይ እምነት እንዲኖረው ለማድረግ ተግቶ መሥራት፣ በሕዝብ ላይ መተማመንና ለአገሩ ዘብ እንዲቆም አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ መስጠት፣ ማደራጀትና ማስታጠቅን ይጨምራል፡፡
5. በተደጋጋሚ እንደተገለጸው፣ ሕገ-መንግሥቱ የችግሮቻችን ሁሉ ምንጭ መሆኑን በማመን ሕገ-መንግሥቱን የማሻሻሉ ሂደት በአፋጣኝ እንዲጀመር ማድረግ ይገባል ይላል፡፡

መንግሥት ከላይ የተጠቀሱትን ለማስተናገድ ከፖለቲካ ድርጅቶች ጋር ምክክር ለማድረግ ፍቃደኛ ሆኖ መገኘት አለበት እንላለን፡፡ መንግሥትም ከቀኖናዊ “መንግሥት ነኝ፣ አዛዥ ናዛዥ ነኝ” ከሚል አስተሳሰብ ወጥቶ በሆደ-ሰፊነት ለአገራችን ሰላም የቀረቡ የአብዛኛውን ሕዝብ ፍላጎቶች ተግባራዊ ለማድረግ ሊተባበር ይገባል፡፡ የመንግሥት ተባባሪነት ከሌለ፣ የብሄራዊ የምክክር ኮሚሽኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሲቪክ ማኅበራት፣ የንግዱ ማኅበረሰብ፣ የሴቶችና የወጣቶች ገለልተኛ ማኅበራትና የሃይማኖት ተቋማት ወኪሎች በጋራና በጥሞና መክረው፣ ከኮሚሽኑ ውጭ ያሉትንም አግባብተው ከሁሉም የሚመጡትን የተጨመቀ የመፍትሄ ሃሳቦችን እንዲያቀርቡ እንዲደረግ እንላለን፡፡

የተፎካካሪ ፓርቲዎችም ቆም ብለው አገሪቱ ያለችበትን ሁኔታ በመመርመር በጋራ ቁጭ ብለው መፍትሄ ማፈላለግ ታሪካዊ ግዴታቸው ነው፡፡ በዚሀ ረገድ የእናት ፓርቲ፣ የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ)ና የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) እየተመካከሩ በጋራ ለመሥራት የሚያደርጉት ጥረትና ጅማሮው እጅግ የሚያበረታታ ነው፡፡ በዚህ አጋጣሚ ሌሎችም የአንድነት ኃይሎች ይህንን ስብሰብ ተቀላቅለው ጠንካራ የአንድነት ኃይል እንዲፈጥሩ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡ በአሁኑ ወቅት እኔ ከዚህ ድርጅት ጋር ልዩነት ስላለኝ አብሬ አልሠራም የሚል አቋም ለአገር የማይበጅና ለችግራችን መፍትሄ የሚያመጣ ሳይሆን የሚያባብስ መሆኑን መረዳይ ይገባል፡፡

ከሁሉም ቅድሚያ ለኢትዮጵያ ሰላም ለዜጎች ደኅንነት!

Exit mobile version