የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መንግሥት ባለፉት አራት ዓመታት ከኢትዮጵያ ዋና ዋና የእምነት ተቋማት ጋር የገነባው ግንኙነት በአዎንታዊና በአሉታዊ ገጾች የሚነሳ መሆኑን ብዙዎች ይናገራሉ፡፡ በኢትዮጵያ ሙስሊሞች መጅሊስ ውስጥ ተፈጥሮ የነበረውን ልዩነት ለማስታረቅ ዓብይ (ዶ/ር) ያደረጉት ጥረት አድናቆት የተቸረው ነበር፡፡ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የቆየውን መከፋፈል ወደ አንድ የማምጣቱ ጥረታቸውም፣ እንዲሁ ከቤተ ክርስቲያኗ የወርቅ ካባ ያስሸለመ ተመሥጋኝ ሥራቸው መሆኑ ተደጋግሞ ይጠቀሳል፡፡
ይሁን እንጂ በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) ሥልጣን ዘመን እነዚህ ጠንካራ የእምነት ተቋማት ከባድ ፈተናዎች እንደገጠሟቸው ብዙዎች ይናገራሉ፡፡ በኢትዮጵያ የዘለቀው አለመረጋጋትና ግጭት የእምነት ተቋማቱን በተደጋጋሚ የጉዳት ሰለባ እንዳደረጋቸው ብዙ የተባለበት ነው፡፡
ከዚህ በመነሳትም መንግሥት የኢትዮጵያን መሠረት የጣሉ ታላላቅ የእምነት ተቋማትን ከጥቃትና ጉዳት መታደግ አልቻለም እየተባለ በተደጋጋሚ ሲወቀስ ይሰማል፡፡
ከሰሞኑ ደግሞ በጠቅላይ ሚኒስትሩ አስተዳደርና በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መካከል ከባድ ውዝግብ ተነስቷል፡፡ ጥር 14 ቀን 2015 ዓ.ም. በሶዶ ደሙ ወረዳ ሀሮ በአለወልድ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በተደረገ ስብሰባ የጳጳሳት ሹመት መካሄዱ የውዝግቡ መነሻ ነው፡፡ የወሊሶና የምሥራቅ አፍሪካ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ሳዊሮስ፣ የመቱና የሚኒሶታ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ኤዎስጣቴዎስ እንዲሁም የቦረና ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ዜና ማርቆስ የጠሩት ነው በተባለው በዚህ ስብሰባ የ25 ጳጳሳት ሹመት መደረጉ፣ ከባድ ቁጣና ተቃውሞ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ዕምነት ተከታዮች ዘንድ ቀስቅሷል፡፡
ጉዳዩን መፈንቅለ ሲኖዶስ ነው በሚል በርካቶች የተቃወሙት ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሲኖዶስ በአራት ቀናት ልዩነት ፈጣን ውሳኔ ማስተላለፉ ይታወሳል፡፡
ቅዱስ ሲዶኖስ ጥር 18 ቀን 2015 ዓ.ም. ባስተላለፈው ውሳኔ፣ ‹‹ጳጳሳት ሾመናል ባሉ አካላትና ተሹመናል በሚሉት አካላት ላይ ውግዘትና ከድቁና ጀምሮ የነበራቸውን ሥልጣን የመሻር፤›› ዕርምጃ እንደወሰደ በይፋ አስታውቋል፡፡
ይሁን እንጂ ቅዱስ ሲኖዶስ ይህን ዕርምጃ ባስተላለፈ በጥቂት ቀናት ልዩነት ማለትም ጥር 23 ቀን 2015 ዓ.ም. ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰጡት ማብራሪያ፣ ጉዳዩ የበለጠ እየተካረረ እንዲሄድ አድርጎታል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሚኒስትሮችና ለካቢኔዎቻቸው በሰጡት ማብራሪያ፣ በቤተ ክርስቲያኗ ጉዳይ ያነሷቸው ነጥቦች ከሲኖዶሱ በኩል ጠንከር ያለ የቅሬታ መግለጫ ያስከተለ ነበር፡፡
ሲዶኖሱ ብቻ ሳይሆን መንግሥት በቤተ ክርስቲያኗ ጉዳይ ፍትሐዊና ሚዛኑን የጠበቀ ዳኝነት አልተከተለም ያሉ ወገኖች በርካታ ቅሬታ እያሰሙ ናቸው፡፡ በግሪክና በተለያዩ አገሮች በኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት ጥናት ያደረጉት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሥነ መለኮት እስከ ሦስተኛ ዲግሪ የተማሩት መጋቤ ብሉይ አብረሃም ሃይማኖት፣ የሰሞኑን ክስተት ሕግ ያልተከተለ ሲሉ ይገልጹታል፡፡
‹‹በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ሕግ መሠረት ሲኖዶስ የማቋቋምም ሆነ ጳጳሳትን የመሰየም ሥልጣን የቅዱስ ሲኖዶሱና የፓትሪያርኩ ብቻ ነው፤›› ይላሉ፡፡
ቤተ ክርስቲያኗ የምትተዳደርበት ራሱን የቻለ መንፈሳዊ ሥርዓት መኖሩንም ይጠቅሳሉ፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ጨምሮ ‹የኦሬንታል አብያተ ክርስቲያናት› በመባል የሚታወቁት የአርመን፣ የግብፅ ኮፕቲክ፣ የህንድ ማላንካራ፣ የሶርያ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት የቤተ ክርስቲያን ሥልጣን ሹመት ጥብቅ ሕግጋትን የተከተለ መሆኑን ያወሳሉ፡፡
እነዚህ አምስት ጥንታዊ አብያተ ክርስቲያናት የኤፌሶን፣ የኒቂያና የቁስጥንጥኒያ ጉባዔዎችን የተቀበሉ ሲሆን፣ የሚመሩበትም ራሱን የቻለ ሥርዓት እንዳላቸው መጋቤ ብሉይ አብረሃም ይናገራሉ፡፡
‹‹የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በምትመራበት ፍትሐ ነገሥት ጳጳሳት የሚሾሙበት መንገድ ራሱን የቻለ መሥፈርት አለው፡፡ በዕውቀትና በመንፈሳዊ ሕይወት መብቃት ተመዝኖ የእምነት አባት እንደሚመረጥ፣ በቅዱስ ሲኖዶሱ ምልዓተ ጉባዔ ሲመተ ጵጵስናው እንደሚፀድቅና የአገልግሎት ምደባ እንደሚካሄድ በሕጉ በግልጽ ተቀምጧል፤›› ሲሉም ያብራራሉ፡፡
‹‹ከዚህ ውጪ የብሔርም ሆነ የቋንቋ ተዋጽኦ የጵጵስና መሥፈርት ሆኖ አያውቅም፤›› የሚሉት መጋቤ ብሉይ፣ አሁን እየተነሳ ያለው የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ተቋም አወቃቀርና አመራርነት የብሔር ተዋጽኦን ያማከለ አይደለም የሚል ጥያቄ ተገቢ አለመሆኑን ያሰምሩበታል፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የብሔርና የቋንቋ ተዋጽኦን ያማከለ አገልግሎት ለመስጠት ብዙ ርቀት መሄዷንም ያወሳሉ፡፡ ‹‹ለአብነት ያህል በሥነ መለኮት ትምህርት የሚማሩ ተማሪዎችን ለየክልሉ በፍትሐዊነት ዕድል በመስጠት ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም ለትምህርት ታስገባለች፤›› በማለትም ይናገራሉ፡፡ ይህ ደግሞ የቋንቋም ሆነ የብሔር ብዝኃነት ያለው አገልግሎት ለመስጠት ያስችላል ያሉት መጋቤ ብሉይ፣ አሁን የተነሳው ጥያቄ ፖለቲካዊ እንጂ ሃይማኖትን ያማከለ አለመሆኑን አስረድተዋል፡፡
ሌላኛው አስተያየት ሰጪ ሊቀ ማዕምራን ፋንታሁን ሙጬ በበኩላቸው፣ ጥቂት ሰዎች ጳጳሳትን መሾማቸው ወይም ሲኖዶስ እንዲመሠረት ማለታቸው ብቻ ሳይሆን ይህ ሁሉ ሲደረግ መንግሥት በዝምታ ማለፉ ትልቁ ጥፋት ነው ይላሉ፡፡
‹‹ሰዎች ሕጋዊ ሰውነት ያላትን ቤተ ክርስቲያን ሕግጋት ጥሰው ቤተ ክርስቲያን እንዲገቡ የመንግሥት ዩኒፎርም የለበሱ ሰዎች እጀባ መስጠታቸው በጣም ያሳዝናል፡፡ ሌላው ግፍ ደግሞ ሕጋዊነት ያላቸው በየአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት የተመደቡ አገልጋዮች ማስፈራሪያና እስራት እየደረሰባቸው መሆኑ የባሰ ጥፋት ነው፤›› በማለት ያክላሉ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) ከሰሞኑ ይህንን ጉዳይ አስመልክቶ የሰጡትን ማብራሪያ በተመለከተ ከጠቅላይ ቤተ ክህነት የተሰጠው ምላሽ ጠንከር ያለ ነበር፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉዳዩን ‹‹በቀላሉ የሚፈታ፣ በሁለቱም ወገን እውነት አለ፣ እንዲሁም ሁለቱም ወገኖች አባቶቻችን ናቸው ተነጋግረው ችግሩን ይፍቱ›› ማለታቸውና ሌሎች ያነሷቸውን ዝርዝር ነጥቦች የፈተሸ መግለጫ ቅዱስ ሲዶኖስ አውጥቷል፡፡ መግለጫው ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፍትሐዊ ዳኝነት ጉዳዩን እንዳልተመለከቱት ነው የሚጠቅሰው፡፡
ሲኖዶሱ በዋናነት ‹‹መንግሥት ሕገወጡን የጳጳሳት ቡድን ሕጋዊ ሰውነት እንዳለው አካል ቆጥሮ ጉዳዩ በሰላምና በንግግር ይፈታ›› ማለቱ አግባብ አለመሆኑን ጠቅሷል፡፡ መንግሥት የሲኖዶሱን ሕግጋት የጣሰውን አካል እንደማስታገስና ሕጋዊ ዕርምጃ እንደመውሰድ ሕጋዊ ዕውቅና አላብሶ ችግሩ በድርድር ዕልባት ያግኝ ብሎ መተው፣ ተገቢ አለመሆኑን ነው ይህ መግለጫ በሰፊው የዘረዘረው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰጡት ማብራሪያ ከሲኖዶሱ ብቻ ሳይሆን ከብዙ አቅጣጫ ‹‹ማስፈራሪያና ቁጣ የተሞላበት ነው›› የሚል ትችት አስከትሏል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለካቢኔ አባላቱና ለሚኒስትሮች፣ ‹አንዳችሁም እጃችሁን ማስገባት አይፈቀድላችሁም› ብለው ማስጠንቀቃቸው ውዝግብ አስነስቷል፡፡ በሌላ በኩል በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በቋንቋ የመገልገልና በአመራር የመወከል ጥያቄ በአግባቡ ሊመለስ የሚገባ ጥያቄ መሆኑን መጥቀሳቸው፣ በሃይማኖት ውስጥ ጣልቃ እንደ መግባት ተደርጎ ነው የተወሰደው፡፡
በኦርቶዶክሳውያን ላይ ያነጣጠረውን ጥቃት በተደራጀና ስልታዊ በሆነ መልኩ የተፈፀመ “ኦርቶዶክሳውያንን የማፅዳት ዘመቻ”ነው ብላ እንደምታምን ቤተክርስቲያን አስታወቀች
ይህን በሚመለከት በአኃዝ የተደገፈ ምላሽ የሰጡት ሊቀ ማዕምራን ፋንታሁን፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለአንድ ወገን ያጋደለ አስተያየት መስጠታቸውን ተችተዋል፡፡
‹‹በ1999 ዓ.ም. በተካሄደው የማዕከላዊ ስታትስቲክስ የሕዝብና የቤት ቆጠራ መሠረት፣ በኦሮሚያ ያሉ ኦርቶዶክሳዊያን ቁጥር ስምንት ሚሊዮን መሆኑ ተቀምጧል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቋንቋ ስለመገልገል ሲያነሱ ኦሮሚያ ውስጥ ኦሮሞ ያልሆኑ ብዙ ኦርቶዶክሳውያን መኖራቸውን ዘንግተውታል፡፡ በዚህ አራት ዓመት ውስጥ በኦሮሚያ ቤተ ክርስቲያን ብዙ መከራ እንደደረሰባት እሳቸውም ሆኑ እኔ አንድ ምስኪን ታዛዣቸው እናውቃለን፡፡ አብያተ ክርስቲያናት መቃጠላቸውን፣ ካህናት መገደላቸውንና ምንም የተወሰደ ሕጋዊ ዕርምጃ አለመኖሩን ያውቃሉ፡፡ የክልሉን ፕሬዚዳንት በተደጋጋሚ ለማነጋገር ተሞክሮ መከልክሉን ያውቃሉ፡፡ በኦሮሚኛ ቋንቋ መሰበክ እንዳለበት ምንም ጥያቄ የለውም፡፡ ነገር ግን የቤተ ክርስቲያን ቀኖና ሕግ ተጥሶ መፈንቅለ ሲዶኖስ ሲፈጸም ሕገወጡን ቡድን ተው ማለት ነበረባቸው፤›› በማለት ነው ሊቀ ማዕምራን ያብራሩት፡፡
መንግሥት በቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ጣልቃ እየገባ የብሔርና የቋንቋ ተዋጽኦ ፖለቲካ ካላራመድኩ ማለቱ የቆየ ጉዳይ መሆኑን፣ መጋቤ ብሉይ አብረሃም ሃይማኖት በበኩላቸው ይናገራሉ፡፡
‹‹አሁን ሲኖዶስ መሠረትን ብለው ጳጳሳትን ከሾሙት መካከል አቡነ ኤዎስጣጢዮስና አቡነ ሳዊሮስ በ1997 ዓ.ም. በሕወሓት/ኢሕአዴግ የፖለቲካ ጫና የተሾሙ ናቸው፡፡ ያለ ዕውቀትና ያለ መንፈሳዊ ብቃታቸው በብሔር ተዋጽኦ ፖለቲካ የመጡ ናቸው፡፡ ሌላኛው አቡነ ዜና ማርቆስ ደግሞ በ2008 ዓ.ም. የጵጵስና ሹመት ያገኙ ናቸው፤›› በማለት ያስረዳሉ፡፡
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ እጅግ ብዙ ሰማዕትነት የከፈሉ ከኦሮሞ ብሔር የወጡ ታላላቅ የእምነት አባቶች እንደነበሩ የሚያስታውሱት መጋቤ ብሉይ፣ ‹‹ቤተ ክርስቲያን ፈጽሞ ኦሮሞን አግልላ አታውቅም፤›› በማለት፣ መንግሥትም ሆነ የተገነጠሉ ሰዎች የሚያራምዱት አቋም የተሳሳተ መሆኑን ይናገራሉ፡፡
‹‹በወራሪው ፋሺስት ጣሊያን የተገደሉትና ለአገራቸው ሰማዕት የሆኑት አቡነ ጴጥሮስ ከኦሮሞ ማኅበረሰብ የወጡ ናቸው፡፡ አቡነ ተክለ ሃይማኖት እኮ በብዙ የኦሮሚያ ምድር ተዟዙረው በማስተማር ነበር የሚታወቁት፡፡ አሁን ባለው ሲኖዶስ ውስጥ ራሱ የባሌው ሊቀ ጳጳስ አቡነ ዮሴፍ፣ የአርሲው ሊቀ ጳጳስ አቡነ ያሬድ፣ የወለጋው አቡነ ናትናኤል፣ የአምቦውና የብዙ አካባቢዎች ሊቃነ ጳጳሳት ኦሮሞ ናቸው፤›› ይላሉ፡፡
‹‹ቤተ ክርስቲያን በዘር ፌዴራሊዝም ሳይሆን በራሷ ሕገ ቀኖና ነው የምትመራው፤›› ሲሉ የጠቀሱት መጋቤ ብሉይ፣ ይህ ደግሞ የሁሉም ኢትዮጵያዊ እናት እንድትሆን ብቻ ሳይሆን ዓለም አቀፋዊ እንዳደረጋትም ይገልጻሉ፡፡
ከሰሞኑ የብሔር ተዋጽኦና የቋንቋ አገልግሎትን ተንተርሶ የተነሳው የቤተ ክርስቲያን ውክልና ጥያቄ ለሲኖዶሱ ጠቅላላ ጉባዔ ቀርቦ መልስ አለማግኘቱን የተገነጠሉት ሰዎች ሲናገሩ ተደምጧል፡፡
ሆኖም ይህን በተመለከተ ምላሽ የሰጡ የእምነት አባቶች በኅዳሩ ጠቅላለ ጉባዔ የጳጳሳት ይሾምልን ጥያቄ መቅረቡን አረጋግጠዋል፡፡ ይህ ጥያቄም ዘግይቶ በመቅረቡ የተነሳ በግንቦቱ ጠቅላላ ጉባዔ ይመለስ ተብሎ በይደር መቆየቱን ነው የእምነት አባቶቹ የጠቀሱት፡፡ አሁን የተገነጠሉት ሰዎች ጥቂት ቢታገሱ ኖሮ ጉዳዩ አደባባይ ሳይወጣና የፖለቲካ ግርግርም ሳይነሳ፣ በቤተ ክርስቲያናዊ ሥርዓት መልስ ለማግኘት ይችል እንደነበር ያስረዳሉ፡፡
አሁን ግን ይህን ተገን በማድረግ የራሳቸውን ሲኖዶስ መሥርተናል ያሉትና ጳጳሳት የሾሙት ወገኖች ጉዳዩን ፖለቲካ በማድረግ የቤተ ክርስቲያኒቱን እጅ ለመጠምዘዝ የፈለጉ ናቸው በሚል እየተተቹ ነው፡፡ አንዳንዶች ጉዳዩ የምር የውክልና ከሆነ ከ65 የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት መካከል 16 የሚሆኑት በብሔር ኦሮሞ መሆናቸው ለምን ይዘለላል? ሲሉም ትችት እያቀረቡ ነው፡፡
በሃይማኖት ተቋማት በተለይም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ላይ ለረዥም ዘመናት የፖለቲካ ኃይሎች የተለያዩ ጫናዎችና ጣልቃ ገብነቶች ሲያሳድሩ እንደቆዩ፣ በርካታ ምሁራን በጥናት አስደግፈው ጭምር ያቀርባሉ፡፡
ሠራዊት በቀለ ደበሌ የተባሉ ተመራማሪ እ.ኤ.አ. 2017 በሠሩት ‹‹Religion and Politics in Post 1991 Ethiopia Making Sense of Bryan S.Turner’s Managing Religion›› በተባለ ጥናታቸው፣ በኢሕአዴግ ዘመን የእምነት ተቋማት በፖለቲካው ዘንድ ይታዩ የነበረበትን መንገድ ገምግመዋል፡፡
በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት መሠረት ሃይማኖትና ፖለቲካ የተለያዩ መሆናቸው በግልጽ መደንገጉን አጥኚው ያስረዳሉ፡፡ ይሁን እንጂ መንግሥት አገር የሚመራበት ዕርምጃ ወይም ሥልጣን የማስጠበቅ ፍላጎቱ እንዳይደናቀፍበት ሲል በሒደት የእምነት ተቋማትን በጫና ውስጥ ወደ ማስገባት እንዳመራ ይጠቅሳሉ፡፡ በተለይ የእምነት ተቋማት ለልማትና ለለውጥ እንቅፋት ናቸው ብሎ ማሰብ፣ መንግሥት የሃይማኖት ተቋማት ላይ ግፊት ለማሰደር የበለጠ እየገፋፋው መምጣቱን ዘርዝረዋል፡፡
በርካታ ምሁራን ጥንታዊቷ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለለውጥና ለተራማጅ አስተሳሰቦች ራሷን ዝግ ያደረገች ናት ብሎ የተሳሳተ ብይን መስጠት፣ በፖለቲከኞች ዘንድ ጎልቶ የሚታይ ችግር መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በዚህና በሌሎችም የተዛቡ አመለካከቶች የተነሳ ቤተ ክርስቲያኒቱ ለተለያዩ የፖለቲካ ጫናዎች መዳረጓን ያስታውሳሉ፡፡
የሃይማኖትና የፖለቲካ ተዛምዶሽን በኢትዮጵያ ያጠኑት መሐመድ ግርማ (ዶ/ር)፣ ‹‹Religion, Politics and the Dilemma of Modernizing Ethiopia›› በሚል ርዕስ ባቀረቡት ጥናት፣ ሃይማኖት ለኢትዮጵያውያን ምን ማለት እንደሆነ በጥልቀት ፈትሸዋል፡፡
በብዙ ኢትዮጵያውያን ዘንድ የአገር መሠረት ሃይማኖት ነው የሚል አመለካከት መኖሩን፣ የአገር ህልውና ተጠብቆ የሚቆየውም በሃይማኖት ነው ብሎ የማሰብ ዝንባሌ እንዳለ አጥኚው ያወሳሉ፡፡
የተለያዩ የፖለቲካ ኃይሎች ኢትዮጵያውያንን ባስፈለጋቸው ጊዜ አንድ ለማድረግና ያለ ተቃውሞ ለመምራት ሃይማኖትን ተጠቅመውበት እንዳለፉ ይጠቅሳሉ፡፡ አሁን አሁን ደግሞ የእምነት ተቋማት ለለውጥም ሆነ ለሥልጣን እንቅፋት ናቸው በሚል፣ ሃይማኖትን ሕዝብ ለመከፋፈያ የመጠቀም አካሄድ እንደሚታይ ተመራማሪው አስረድተዋል፡፡
Source: https://www.ethiopianreporter.com/