Site icon Dinknesh Ethiopia

የወልቃይት ጠገዴ አማራ ግልፅ አቋም

ወልቃይት ጠገዴ

“የተከበራችሁ ጎረቤት የትግራይ ሕዝብ ሆይ!…የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ የናንተን ትግሬነት እንደምናከብረው ሁሉ እናንተም የኛን አማራነት ልታከብሩ ይገባል፡፡”

(አንብበው ለሌሎች ያጋሩ)

ግንቦት 27/2015 በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን በሁሉም ህዝቡ ሰልፍ ባደረገባቸው ቦታዎች የተላለፈ የዞኑ አስዳደር መልዕክት
******
የተከበርከው ጀግናው፣ አይበገሬው የወልቃይት-ጠገዴ ሕዝብ ክቡራት እና ክቡራን የአማራ ሕዝብ የኢትዮጵያን ሃገረ-መንግሥት ከመሠረቱና ካፀኑ አንጋፋ የአገሪቱ ሕዝቦች ውስጥ አንድ ነው፡፡

በኢትዮጵያ ሦስት ሺሕ ዘመናት በዘለቀ ሃገረ መንግሥትነትና የሀገር ግንባታ ሂደት ውስጥ ከሳባዊት አክሱም ሥሌጣኔ እስከ ዘመናዊት ኢትዮጵያ አመሠራረት ሂደት ውስጥ አማራ የራሱ የሆኑ አንጸባራቂና በጎ ሚናዎችን ተጫውቷሌ፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ የአማራ ሕዝብ ምንጩ ከወዴት ነው ተብሎ የታሪክ መዝገቦች ሲፈተሹ የአማራ መነሻው ከወሌቃይት-ጠገዴ ነው፡፡

የጥንታዊት ኢትዮጵያ ነገዶች ታሪክ ፀሃፊያን እንደሚያስረዱት፣ እኛም ከአያት ቅድመ አያቶቻችን እንደተማርነው፣ ወልቃይት-ጠገዴ የከለው ሌጅ፤ የአማራ የዘር ግንድ መነሻ ነው፡፡ ወልቃይት-ጠገዴ፤ የአማራ ህዝብ ዕትብት የተቀበረበት እና የአማራ የትላንት ብቻ ሳይሆን የዛሬና የነገ ታሪኩ፣ ጀብዱ እና ኩራቱ መነሻ አስኳል ከሆኑት ታሪኮቹ መካከሌ የዋናው ሰበዝ መነሻ ነው፡፡

አማራ ከኢትዮጵያ ብሔር ብሄረሰቦች ጋር በጋራ ሀገር ገንብቷል ስንል መነሻውን ከዚህ ምድር አድርጎ ነው፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን ወልቃይት-ጠገዴ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ደህንነት ማስጠበቂያ ቁልፍ በርም ነው፡፡

የተከበርከው ጀግናው፣ አይበገሬው የወልቃይት-ጠገዴ ሕዝብ የተከበራችሁ የዚህ ታሪካዊ ሰልፍ ተሳታፊዎች::

ክብራትና ክቡራን ወልቃይት-ጠገዴ በኢትዮጵያ የሺ አመታት ታሪክ ይሁን የዓመተ ዓለም ታሪክ ውስጥ በትግራይ ውስጥ መጠቃለል ቀርቶ ከትግራይ የመጣ ሰው ገዝቶታል የሚል ታሪክ የለም።

ከቅድመ አክሱም እስከ 1983 ዓ.ም. ድረስ በየትኛውም የኢትዮጵያ አስተዳደራዊ ታሪክ ውስጥ ወልቃይት-ጠገዴ የበጌምዴር እንጅ የትግሬ ግዛት አልነበረም፡፡ ለሁለቱ ሕዝቦች ተከዜ ተፈጥሯዊ ድንበር ነው፡፡ ነገር ግን የግዛት ተስፋፊው የትግራይ ወራሪ ተከዜን ተሻግሮ እግሩን ከተከለበት ግዜ ጀምሮ በወልቃይት-ጠገዴ ያልተፈጸመ የግፍ አይነት አልነበረም፡፡

በተለይም ሥልጣን ላይ ከወጣበት ድኀረ-1983 ጀምሮ አማራዊ ማንነታችን ወንጀል ሆኖ፤ ኢትዮጵያን መዉደዳችን እንደሃጢያት ተቆጥሮብን ሕወሓት ለሰላሳ ዓመታት የበቀሌ ማወራረጃ አድርጎን ኑሯል፡፡የምንግዜም ቅዠቱ ለሆነችው ለ ‹‹ታላቋ ትግራይ ሪፐብሊክ›› ምስረታ የውጭ በር እንዲሆነው በወረራ በያዘው መሬት ላይ የወልቃይት-ጠገዴ ባላባቶች፣ አባት አርበኞች፣ ታሪክ አዋቂዎች፣ የአገር ሽማግሌዎችና በማኀበረሰቡ ዘንድ ተሰሚነት ያላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች አንድ በአንድ እየተለዩ ደብዚቸው እንዲጠፋ ተደርጓል፡፡

በሕወሓት የወረራ ዘመን በምድሩ ላይ ተናገረው የሚሰሙ፣ መክረውና ዘክረው የሚደመጡ ታላላቆች እንዳይኖሩ ግልጽና ስውር የዘር ማጥፋት ወንጀል ተሰርቷል፡፡
አማራነት ወንጀል፤ ኢትዮጵያን መወደድ ሃጢያት ሆኖብን፤ በትግሬ ፋሽስቶች በጠላትነት እንድንታይ ከመደረጉም በላይ የሞታችን፣ የእስራታችን፣ የመሰደዳችን፣ ሀብት ንብረታችንን የማጣታችን፣ የቤተሰባችን መበተን፣ የሁለንተናዊ ስቅይታችን ምክንያት አማራነታችን ነበር፡፡ በርስታችን ማንነታችን ወንጀል ሆኖብን ከሞት የከፋ በደል ተፈጽሞብናል፡፡

የግዛት ተስፋፊው ሕወሓት ከሞት የከፋ በደል ፈጽሞብናል ስንል ጥቃቱ ዘርፈ ብዙ በመሆኑ ነው፡፡ በአካል ላይ የደረሰ የዘር ማጥፋት ወንጀል እና የባህል ማንነታችን ላይ ያነጣጠረ የባህል ማጥፋት ወንጀል ተፈጽሞብናል።
ከነውራቸው ብዛት፡- “ካብ ወሌቃይት ጠገዴ ንህና ንደልዮ ደቂ አንስትዮምን መሬቶምን ጥራህ እዩ
(“እኛ ከወልቃይት ጠገዴ የምንፈልገው ሴቶቹን እና መሬቱን ነው”)። በሚል የጥላቻቸውን ጥግ ከሞት የከፋ በደል በመፈጸም አሳይተውናል፡፡

ይህን በትግረኛ ቋንቋ የሚነገር የዘር ማጥፋት የሀሳብ ክፍልን የሚያስረዳ የጥላቻ አባባል ማንኛውም የወልቃይት-ጠገዴ ሕዝብ ላለፉት ሦስት አስርት ዓመታት ሲነገረው ብቻ ሳይሆን ይህን የጥላቻ አባባል፣ ከአባባልነት አልፎ በተግባር ተተግብሮበታል፡፡
በመሆኑም፣ ከቅኝ ግዛት ከከፋው የሕወሓት አገዛዝ ነጻ ለመውጣት ከከፋኝ አርበኞች ተጋድሎ እስከ የአማራ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ ድረስ በአመጽም፣ በሠላማዊ መንገድም ሕዝባችን የማያቋርጥ ትግል አድርጓል፡፡ ጥያቄችን ከ2008 ጀምሮ በአዲስ ምዕራፍ የአማራ ሕዝብ የትግል ማዕከል ሆኖ በበርካታ የአማራ ክልል ከተሞች ‹ወልቃይት ሆይ ብረሳሽ ቀኜ ትርሳኝ› በሚል ወጣቶች የማይተካ ሕይወታቸውን ገብረዋል፡፡
የወልቃይት ጠገዴ የነጻነት ትግል የእውነት የፍትሕ እና የርትዕ ሕዝባዊ ጥያቄ ሆኖ ሳለ ህወሓት ለሰላሳ ዓመታት ያለማቋረጥ መዋቅራዊ በሆነ መንገድ ነባሩን ሕዝብ በማጥፋት በርካታ ዓለም አቀፍ ወንጀሎችን ፈጽሟል፡፡

በዚህም ባለፉት ሠላሳ ዓመታት በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ አማራዎች በማንነታቸው ተገድለው በጅምላ ተቀብረዋል፡፡ ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ወገኖቻችን ወደ ትግራይ ታፍነው ተወስደው በእስር ሲማቅቁ ኑረዋል፤ ብዘዎችም በእስር ቤት ድብደባ ሕይወታቸው አልፏል፡፡

በሠላሳ ዓመቱ የሕወሓት አፓርታይዲዊ ዘመን ከቆላ እስከ ደጋ አያሌ የወልቃይት ጠገዴ አማራ ከእርስቱ ተፈናቅሎ፣ ወደእናት ግዛቱ ጎንደር እና ወደ መሀል ሀገር አልፎም ወደ ጎረቤት ሀገራት እንደሰደድ ተደርጓል፡፡

ከ30 ዓመት ያልተቋረጠ ትግል በኋላ ለዘመናት በከፈለው መስዋትነት እና ለውጡን ተከትሎ እኩልነትን ያለመቀበል ደዌ ያለበት ሕወሓት፣ የሀገረ-መንግሥቱ የመጨረሻው ምሽግ በሆነው የአገር መከላከያ ሠራዊት የሰሜን ዕዝ አባላትን ከጀርባ መውጋቱን ተከትሎ በተጀመረው የህልውናና ሕግ የማስከበር ዘመቻ ምክንያት የሕወሓትና ተላላኪዎቹ እንዲሁም ባለፉት ሠላሳ ዓመታት በተፈጸሙ የዘር ማጥፋት ወንጀሎች የሀሳብና የተግባር ተሳታፊ የነበሩና ጦርነቱን ተከትሎ ንጹሃንን በማይካድራና በሁመራ በመጨፍጨፍ ተሳትፎ ያላቸው የቡድኑ አባላትና የሀሳቡ ደጋፊዎች የሕወሓት ታጣቂዎችን ተከትለው ከወልቃይት ጠገዴ ጠቅልለው ወደ ትግራይ የወጡ መሆኑና በዚህ አጋጣሚ የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ የዘመናት የማንነትና የወሰን ጥያቄ በልጆቹ እና በመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ መስዋዕትነት እንዱሁም በለውጡ አመራር ሰጭነት ከድቅድቅ ጨለማ በመውጣት ነጻነቱን ከተጎናጸፈ ይሄው 3 ዓመታት አስቆጥሯል፡፡
ሕወሓት፣ የሀገር ክህደት ወንጀል ከፈጸመባት ምሽት ጀምሮ በተጀመረው የህልውናና ህግ የማስከበር ዘመቻ ከፌደራልና ከአማራ የጸጥታ ኃይል ጋር ተሰልፎ የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ ራሱን ከወራሪ ሀገሩን ደግሞ ከከዳተኛና ባንዳ ነጻ በማውጣት ተፋፋሟል፡፡ ትርጉም የሚሰጥ መስዋዕትነት ከፍሎ ነፃነቱን አግንቷል፡፡ በዚህም የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ ከብዛ መስዕዋትነት በኋሊ የፈለገውን ነፃነት በማወጅ የታሪኩና የማንነቱ አካል ከሆነው የአማራ ሕዝብ ጋር መመራትና መተዳደር ጀምሯል፡፡

ይሁን እንጂ አሁንም ጠላቶቹ ከትናንት ጥፋታቸው ሳይታረሙ የተረገመውን ዘመን ለመድገም የጥፋት ድግስ ላይ ናቸው፡፡ በሃሰት ሪፖርት፣ በበሬ ወለደ ውንጀላ፣ በባዕዳን ሴራ፣ እየተመሩ ወደ ጨለማው ዘመን ሊመልሱን ጥረት ላይ ናቸው፡፡

በወልቃይት-ጠገዴ ሕዝብ መሪዎችና በአጠቃላይ ሕዝባችን ላይ የተደራጀ የስም ማጥፋት ዘመቻ በመክፈት የተለመደ የማዎናበጃ ዘድያቸውን በመጠቀም ዓለም አቀፉን ማኀበረሰብ ለማደናገር በቅጠረኛ ተቋማቶቻቸው በኩል እየጣሩ ይገኛል፡፡
ጥንተ-ጠላት ሕወሓትና የጥፋት ሀሳቡ ተከታዩች ባለፉት ሠላሳ ዓመታት በእኛ ላይ ወረራ ፈጸሙ፣ ርስታችንና ማንነታችን ነጠቁ፣ የጅምላ ግድያ ፈጸሙ፣ በመጨረሻም ጩኽታችንን ነጠቁ፡፡ ከሰማይ በታች በእኛ ላይ ያልተደረገ ምንም ነገር የለም፡፡ ሁሉም በደል በኛ ላይ ተፈጽሟል፡፡ ነገር ግን ጩኽታችንን ቀምተው በዳዮቹ እንደተበዳይ፣ ጨፍጫፊዎቹ እንደተጨፍጫፊ፣ ወራሪዎቹ እንደተወራሪ፣ አፈናቃዮቹ እንደተፈናቃይ ሆነው ቀርበዋል፡፡

የሀገራችን ሰው የበደልን ብዛት በተረት ሲገልጽ፡-
‹‹ሁለተኛ ግፌ
ጫንቃየን ተገርፌ
ልብሴን ተገፍፌ››ይላል፡፡

እኛን የገጠመን እንደዚህ ዓይነት አይን ያወጣ ግፍና በደል ነው፡፡ ያለፈው ዘመን ግፍና መከራችን ቁስለ ሳይሽር ዛሬም እንደገና በቁስላችን ላይ ጨው ይነሰንሳሉ፡፡ ትላንት ማንነታችንን ለመግፈፍ እንደሞከሩት ሁሉ ዛሬ ደግሞ ማይካድራ ላይ ጨፍጭፈውን፤ ሁመራ ላይ ረሽነውን የአስከሬን ብሔር ቀይረው፣ ጩኽታችንን ቀምተው የአዞ እንባ በማንባት ላይ ናቸው፡፡

የተከበርከው ጀግናው፣ አይበገሬው የወልቃይት-ጠገዳ ሕዝብ
የተከበራችሁ የዚህ ታሪካዊ ሰልፍ ተሳታፊዎች ክብራትና ክቡራን
ባለፉት ሁለት የግጭት ዓመታት ወልቃይት ጠገዴን በኃይል እንደገና ለመውረርና ከአካባቢው ጂኦ-ፖለቲካዊ ፋይዳ አኳያ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ከታሪካዊ ጠላቶቻችን በሚያገኘው እገዛ ደጋግሞ ቢሞክርም ከመላው የኢትዮጵያ ሕዝብና ከጥምር ጦሩ ጋር በመተባበር ህልሙን አምክነንበታል፡፡

በጦር ወረራው ወቅት በሌሎች የአማራና የአፋር አከባቢዎች ያገኛቸውን ጊዜያዊ ድሎች ለመድገም በተደጋጋሚ ቢሞክርም በወልቃይት ጠገዴ አንድ ኢንች መሬት መቆጣጠር ሳይችል ህልሙ ቅዠት ሆኖ በህዝባችን ጥንካሬ የእብሪተኛው ህወሓት ጉልበት ሲደክም ጦርነቱ በፕሪቶሪያው ስምምነት በድል መቋጨቱ ለሁሉም አካል ግልጽ ነው፡፡

ይህም የሆነበት ዋናው ምክንያት የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ የሕወሓት መሰሪነቱን ስለሚገነዘብ፤ በሕወሓት ቀጣፊ ፕሮፖጋንዳ ሊወናበድ ባለመቻሉ፤ ድጋሜ የወያኔ አገዛዝ ፈጽሞ ማየት ስለማይፈልግ እና የከፋ የህልውና አደጋ ውስጥ ስለገጠመው ለጥምር ጦሩ አስተማማኝ ደጀን ከመሆን ባለፈ ግንባር ይዞ እስከመዋጋት በመድረሱ ህልውናውን ማስከበርና ኢትዮጵያን ከመፍረስ በመታደግ ረገድ እጅግ የጎላ ሚና አለው፡፡ ለዚህም በጦር ሜዳ ዋጋ ከከፈለው የሀገር መከላከያ ሰራዊትና የጥምር ጦሩ አባላት በላይ የህዝባችን ሚና ምን እንደነበረ ምስክርነት ሊሰጥ የሚችል አካል አይኖርም፡፡

የሦስተኛው ዙር ጦርነት ፍጻሜና አሁን ላለንበት አንጻራዊ ሠላም መነሻ በሆነው የፕሪቶሪያው ስምምነት ላይ በተወካዮቻችን አማካኝነት ወልቃይት ጠገዴ ጠለምትና ራያ በሕዝቡ ታሪክ፡ ማንነትና ፍላጎት መሰረት ህጋዊ እልባት በፌደራል መንግሥት እስኪሰጣቸው ድረስ በፈለጉት የአማራ ክልል አስተዳደር ስር እንዲቆዩ የሚለው የስምምነቱ አካል መሆኑ በሰማን ጊዜ ድሮም ቢሆን የሕወሓት ጦረኝነት አስገዳጅ ሆኖብን እንጂ ሕዝባችን የታገለለት ዓላማ እስከተከበረለት ድረስ ሠላም ወዳድ የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ ከሰላም እንጂ ከጦርነት እንደማይጠቀም ያውቃል፡፡ በዚህ አቋሙ የፕሪቶሪያው ስምምነት ተግባራዊ እንዲደረግ እየጠየቀ ሰላሙን በማጽናት ተልዕኮ ላይ ተሰማርቶ ይገኛል፡፡

ትዕግስተኛው ሕዝባችን አሁናዊ ሁኔታው ፈተና ያለበት መሆኑ በተለይም እውቅና ያልተሰጠው መሆኑ፤ በጀት እስካሁን ያልተለቀቀለት መሆኑ፤ በአከባቢው የፍትሕ ሥርዓት ያልተዘረጋለት መሆኑ በብዙ ስቃይ ውስጥ የሚገኝ ስለመሆኑ መላ ኢትዮጵያዊያንና ዓለማቀፉ ማኀበረሰብ የሚረዱት እውነታ ነው፡፡

ይህም ሆኖ ኢትዮጵያ ያለችበትን አሁናዊ ሁኔታዎች በመረዳትና በሚደርስበት ጊዜያዊ የመልካም አስተዳደር ችግር ነጻነቱን በምንም ዓይነት መመዘኛ አሳልፎ ሊሰጥ የማይችል ኩሩ ሕዝብ በመሆኑ፡- አማራነቱን በጀት፤ የአከባቢው ሽማግሌዎችን የፍትሕ መሳሪያ አድርጎ የወሰንና ማንት ጥያቄው ሕጋዊ ምላሽ እንዲያገኝ በከፍተኛ ትዕግስትና የትግል ዓላማ ጽናት ውስጥ ሆኖ የፌደራሉን መንግሥት አወንታ ምላሽ እየጠበቀ ይገኛል፡፡
ነገር ግን የሰላም ፀር፤ የአብሮነት አደጋ የሆነው ሕወሓት ጉሌበቱ የደከመ ሲመስለው የፈረመውን የፕሪቶሪያ ስምምነት በመፃረርና በሕዝባችን ላይ ያደረሰው መከራ አልበቃ ብሎት የተደራጀ የሃሰት ፕሮፖጋንዳ በመክፈት የኢትዮጵያን ሕዝብና ዓለማቀፉን ማኀበረሰብ ለማሳሳት በትግራይ ከተሞች ሰልፍ ማካሄዱ ይታወቃል፡፡ ስለሆነም ከእጃችን ያለው እውነት ብቻውን በቂ ባለመሆኑና አለም በሃሰት መረጃ ሲሸወድ የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ በራሱ ደርሶ ያየው ስለሆነ ኢትዮጵያዊያን ወገኖቻችንና ዓለማቀፉ ማኀበረሰብ የሕዝቡን እውነት እንዳይረሱትና እንዲያውቁት ለሕወሓት የቅጥፈት ሰልፍ ምላሽ ከመሥጠት በተጨማሪ መሬት ላይ ያለው ሀቅ ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብና ለዓለማቀፉ ማኀበረሰብ ለማስረዳት የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ በዛሬው ዕለት ሰላማዊ ሰልፍ ወጥቷል፡፡

በመሆኑም የኢፌድሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አቢይ አሕመድ፣ በአንደበታቸው እንደመሰከሩት የወልቃይት-ጠገዴ ሕዝብ ከፍ ሲል ኢትዮጲዊ ዝቅ ሲል የበጌምድር ሰው (አማራ) ነውና፤ ፍትሃዊና ርትአዊ የሆነውን የሕዝባችንን የወሰንና የማንነት ጥያቄ በተገቢው መልኩ አዎንታዊ ምላሽ እንዲሰጠው እንጠይቃለን፡፡

ከዚህ ቀደም በተደራጀና ሕጋዊ ሥነ-ሥርዓትን በተከተለ መልኩ የወልቃይት-ጠገዴ የአማራ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ ለፌድሬሽን ምክር ቤት በኢፊዴሪ ሕገ-መንግሥት መሰረት ያቀረበው ጥያቄ በሕገ-መንግሥቱ በአንቀጽ ቁጥር 48 የአከላለል ለውጦችን በሚመለከት የፌድሬሽን ምክር ቤት “የሕዝብ አሰፋፈር እና ፍላጎትን መሰረት” በማድረግ እንዲወስን በተሰጠው ሥልጣን መሰረት ምላሸ እንዲሰጠን እንጠይቃለን፡፡
ያለሕገ-መንግሥት አንቀጽ በወረራ የተያዘ መሬት፣ በጉልበት ሊደፈጠጥ የተሞከረው አማራዊ ማንነታችን ዛሬ ሕጋዊ ዕውቅና እንዲሰጠን የሕገ-መንግሥት አንቀጽ ጠቅሰን የምንጠይቀው ሕግና ሥርዓት አክባሪዎች በመሆናችን ስለመሆኑ የፌዳራሉ መንግሥትና መላ ኢትዮጵያዊያን እንዲገነዘቡልን እንሻለን፡፡

የሀገረ-መንግሥት ግንባታ ትውፊታዊ እውቀትና ክህሎት ባለቤቱ የወልቃይት ጠገዴ ጎንደር-አማራ ሕዝብ የፌደራል መንግሥት የነበረበት ጫና በመረዳት ሁሉንም አይነት የመልካም አስተዳደርር ችግር ችሎ ከሕወሓት ነፃ ከወጣ ዕለት ጀመሮ ለ3 ዓመታት የታገሰ ቢሆንም ጥያቄው በዋለ ባደረ ቁጥር ለሕወሓት የሃሰት ፕሮፖጋንዳና ለኢትዮጵያ በጎ ለማይመኙ የታሪካዊ ጠላቶቻችን አጋርና የፖለቲካ መሳሪያ ለሆኑ ዓለማቀፍ ተቋማት አድሎአዊ ፍርድ እየተጋለጠ ስለሆነ እንደ ኢትዮጵያዊነታችን በጀት እንደ አማራነታችን ደግሞ ማንነታዊ እውቅና እንዲሰጠን በዚህ ታሪካዊ ሰልፍ እንጠይቃለን፡፡

ከነጻነታችን ማግስት ጀምሮ ላለፉት ሦስት ዓመታት ሚዛናዊነት የጎደላቸውና የሕዝባችንን የዘመናት መከራና በደል ዛሬም ድረስ የዘለቁ ጠባሳዎችንና የታሪክ ቁስሎቻችን እንዲያመረቅዝ የሚያደርጉ በተለያዩ የውስጥና የውጭ አካላት የሚፈጸሙ የፖለቲካ ሸፍጦች እንዲቆሙ በመላ ሕዝባችን ሥም እናሳስባለን፡፡

ወድ ኢትዮጵያዊያን ወገኖቻችን!
የወልቃይት ጠገዴ የአማራ ማንነት ጥያቄ የመላው ፍትህ ወዳድ ኢትዮጵያውንም ጥያቄ መሆኑን የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ በተግባር ያየው ሀቅ ነው፡፡

ከፍትሕ ወዲድ ኢትዮጵያዊያን ላገኘናቸው የትግል አጋርነቶች የላቀ ምስጋና አለን፡፡ ከአሁናዊ የትግል አውድ አኳያም፣የወልቃይት-ጠገዴ ሕዝብ በሰሜኑ ጦርነት የኢትዮጵያ ብሔር ብሄረሰቦች ውህድ ማንነት የሆነውን የሀገር መከላከያ ሰራዊትን የጨፈጨፈው፣ አማራና አፋር ላይ የጦር ወንጀል የፈጸመው ከሃዲው ህወሓት ዛሬም አይኑን በጨው አጥቦ በወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ መሪዎችና በአጠቃላይ በሕዝቡ ላይ የከፈተውን የሃሰት ፕሮፖጋንዳ እንደትላንቱ ሁሉ ዛሬም እንድትገነዘቡልን እንፈልጋለን፡፡
የተከበራችሁ ጎረቤት የትግራይ ሕዝብ ሆይ!

የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ፣ የራሳችንም አሳልፈን አንሰጥም አልን እንጂ የማይገባንን አልፈን አልጠየቅንም፡፡ የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ የናንተን ትግሬነት እንደምናከብረው ሁሉ እናንተም የኛን አማራነት ልታከብሩ ይገባል፡፡

የወልቃይት ጠገዴ አማራ ሕዝብ እንኳንስ ኢትዮጵያዊ ዜግነት ከሚጋራቸው ሕዝቦች ቀርቶ ከጎረቤት ሀገራት ወንድም ሕዝቦች ጋርም በሰላም፣ በፍቅርና በመከባበር መኖር የሁሌጊዜም ምርጫው ነው፡፡ በዚህ አጋጣሚ ወንድም ለሆነው የሱዳን ሕዝብ ያጋጠማቸውን የእርስ በርስ ጦርነት መሪዎቹ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱት፣ ሱዳንም ወደቀደመ ሰላምና መረጋጋቷ እንድትመለስ ልባዊ ምኞታችንን እንገልጻለን፡፡
በመጨረሻም፦

እኛ ወልቃይት-ጠገዴዎች የአማራ የዘር ግንድ መነሻ ነባር አማራ ነነ አልን እንጂ እንደ አዲስ አማራ እንሁን አላልነም፡፡ አማራ ነነ ስንል እንደ ሕወሓት የበሬ ወለደ ማወናበጃ በመጠቀም ሳይሆን እውነተኛ ታሪካችን በማስረጃና በሰነድ አቅርበን በአደባባይ በመሞገት ነው፡፡

ፍላጎታችን፡ ማንነታችንና ሥነ-ልቦናችን ጎንደሬ አማራ ነው፡፡ ስለሆነም ማንም ኃይል ጣልቃ ገብቶ ‹በማንነታችሁ እኔ ልወስን› እንዲለን አንፈቅድም፡፡ እኛ የአማራ ሕዝብ የዘር ግንድ መነሻ የከለው ልጆች ነነ፡፡ አማራነታችን ወንጀል የሚሆንበት ዘመን ላይመለስ ተሸኝቷል፡፡ የወልቃይት-ጠገዴ ሕዝብ የታሪኩና የማንነቱ አካል ከሆነው የአማራ ሕዝብ ጋር በአስተዳደር መጠቃለልና መተዳደር የማይደራደርበት ቀዳሚ ፍላጎቱ ነው፡፡ አማራነት ማንነታችን፤ ኢትዮጵያዊነት የኩራታችን ምንጭ ነው፡፡ ዛሬ ላለንበት ነጻነት ዋጋ ከፍለንበታል፡፡ ወደ ኋላ ላንመለስም ነጻ ወጥተናል፡፡

ሞት አይቀርም ስም አይቀበርም!!
ዘላለማዊ ክብርና ሞገስ ለትግሉ ሰማዕታት!!!

Source: Getachew Shiferaw facebook page
Exit mobile version