Birtukan Midekssa- ብርቱካን ሚደቅሳ
የስራ ሀላፊነትን በፈቃድ ስለመልቀቅ
በ2011 ዓ.ም ታህሳስ ወር የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዋና ሰብሳቢ በመሆን ስራዬን ስጀመር ተቋማችንን ተአማኒ እና ራሱን ችሎ ምርጫን ማከናወን የሚችል ተቋም ለማድረግ በማለም ነበር። ባለፉት አራት አመት ከስድስት ወራት ሶስት ህዝበ ውሳኔዎችን እና አገራዊ ምርጫን በማካሄድ እና ፓለቲካ ፓርቲዎችን በማስተዳደር የተሰጡኝን ሃላፊነቶች ህጋዊነት ፍትሀዊነት እና ቅንነትን በተከተለ ሁኔታ ለማከናወን ስጥር ቆይቻለሁ።
ሆኖም ጤናዬን በሚገባ ለመጠበቅ የረጅም ጊዜ እረፍት የሚያስፈልገኝ ሆኖ በመገኘቱ ከ ነሀሴ 1 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቦርድ ሰብሳቢነቴ በገዛ ፍቃዴ መልቀቄን ለተወካዮች ምክር ቤት አፈጉባኤ ጽህፈት ቤት ሰኔ 5 ቀን 2015 ዓ.ም አሳውቄያለሁ። በሚቀረኝ ጊዜ ያልተጠናቀቁ ስራዎችን የማጠናቀቅ እና አስተዳደራዊ ሽግግር የመፈፀም ሃላፊነቶችን የምወጣበት ይሆናል።
ባለፉት አራት አመት ከ6 ወራት የምርጫ ቦርድን የማስፈጸም አቅምን ለመጨመር፣ ተአማኒነቱን ለማሳደግ ከሌሎች የቦርዱ አመራር አባላትና ከቦርዱ ሰራተኞች ጋር በጋራ ለፍተናል፣ ውጤቱን የሚመለከታቸው አካላትና መራጮች የሚመዝኑት ቢሆንም፣ በእኔ በኩል የቦርዱን ተአማኒነት በማሻሻል ረገድ፣ በተቻለ አቅምም የፓለቲካ ፓርቲዎችን እንቅስቃሴዎች ለማገዝ ባደረግነው ጥረት ስኬታማ ነን ብዬ አምናለሁ። በዚህም ወቅት አብረውኝ የነበሩ የቦርድ አመራር አባላትን፣ የቦርዱን ሰራተኞች በተለይም የየቀኑ ስራዬ በንሸጣ (inspiration) የተሞላ እንዲሆን ያደረጉልኝ ታታሪ የቦርዱ ሴት ሰራተኞችን፣ የቦርዱ የረጅም አመት ሰራተኞች ሆነው ያፈሩትን ልምዳቸውን ለአዲስ ሰራተኞች በማካፈል ስራችንን ቀላል ላደረጉ ሁሉ ከፍተኛ ምስጋና ማቅረብ እፈልጋለሁ።
የፓለቲካ ፓርቲዎች አመራሮችም ቦርዱን እንደ አስተዳዳሪ እና እንደተቆጣጣሪ ከማየት ይልቅ በጋራ እንደሚሰራ ቤተሰብ በመቁጠር የማያስደስታቸውን ውሳኔ በምንወስንበት ወቅትም ጭምር እምነታቸውን አልነሱንም። ለዚህም ለፓርቲዎች እና ለአመራሮቻቸው ከፍ ያለ ምስጋናዬን ላቀርብላቸው እወዳለሁ፡፡
በመጨረሻም ይህን ማህረሰቤን የማገልገል እድል አገኝ ዘንድ ቦርዱን በሰብሳቢነት ለመምራት በእጩነት ላቀረቡኝ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ እንዲሁም እምነቱን ጥሎ ሀላፊነቱን ለሰጠኝ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምስጋናዬን አቀርባለሁ፡፡
ከልብ ከመነጨ በጎ ምኞት ጋር!!
Source: Birtukan Mideksa facebook account