Site icon Dinknesh Ethiopia

የሚጠቅመው ይውሰደው! – በጌታቸው ሺፈራው

ህዝብ ላይ የሚደርሰው በደል ብዙ አቅም ያላቸው ሰዎች ወደ ፖለቲካው እንዲመጡ ሲያደርግ፣ ፖለቲካው አካባቢ ያሉ አካላት የመጡትንም የሚያርቁበት አጋጣሚ ብዙ ነው። ይህ እንዳይሆን ጥረት ማድረግ ጥሩ ነው።

1) የመጣበትን ህዝብ በሚያስፈርጅ መልኩ ሌላ ህዝብ ወዘተን በቲክቶክ ይሁን በሌላ የሚሰድብን ማበረታታት፣ ስድቡን ወዘተ እንደ መዝናኛ መመልከት ሄዶ ሄዶ ለራስ ይተርፋል። ዛሬ ሌላ ሲሰድብ ተው ያልተባለ ነገ የራስክን ህዝብ በጎጥና በአደረጃጀት እየከፈለ ያዋርዳል። ሌላው ላይ የለመደውን ወደ ራስህ ህዝብ ያመጣዋል። እንደ ህዝብ ስድብ ነውር መሆኑን አውቆ አለማበረታታት ያዋጣል።

2) አንዳንድ የማያዋጡ አካሄዶችን አያለሁ። አንድ ድርጅት ሰሞኑን “ቄሶችና ሽማግሌዎች አርፋችሁ ተቀመጡ” የሚል መግለጫ አውጥቶ ተመልክቻለሁ። አክሳሪ ነው። አዎ! ገዥዎቹ በሽምግልና ሰበብ ትግል ማኮላሸት ይፈልጋሉ። ነገር ግን ትግል ላይ ያለ አካል “አትምጡብኝ” አይደለም የሚለው። ለገዥዎቹ ስልት አዋጭ አማራጭ ይፈልጋል። መጀመርያ በሽምግልና መልክ የሚመጡ አካላት ምን ሊያደርጉ እንደሚችሉ፣ ቢመጡ ምን መደረግ፣ ከማን ጋር መነጋገር፣ ምን መልስ መሰጠት እንዳለበት መወሰንን ይጠይቃል። ከሚመጣው ሽማግሌ የአገዛዙን መረጃ ታገኛለህ፣ ፍላጎቱን ታጠናለህ፣ አሳስቶ ከሆነ የላከው አንተ የሚፈፀመውን በደል በመረጃ ትግተዋለህ፣ ብልጥ ከሆንክ በስልታዊ መንገድ የአንተው የትግል አካል ታደርገዋለህ እንጅ አትገፋውም። ከገፋኸው “መንግስት ነው ትክክል፣ እነዚህ ናቁኝ፣ ችግራቸውን እንኳን ማስረዳት የማይችሉ” ይልሃል። የማትፈልግ ከሆነም ጊዜ ትገዛበታለህ። እንገናኛለን እያልክ ታራዝማለህ እንጅ ቃል በቃል “እንዳትመጣብኝ” አዋጭ አይደለም። ሽምግልና ላትቀመጥ ትችላለህ “እንዳላይህ” ግን አትለውም።

ፖለቲካን ግንባሩን ብቻ ካየኸው ይህ ሀሳብም ላይመችህ ይችላል። የሚጠቅመው እንዲወስደው ብቻ ነው። ሽምግልና እያስጠቃህ ከሆነም ምን ይሻላል? ብሎ ሌላ መፍትሄ መፈለግ ነው። ከገዥዎቹ የተሻለ የምታስረዳው ሀሳብ ካለህ ሽምግልና ተብሎ የሚመጣውን ስልት ገልብጠህ ትጠቀምበታለህ እንጅ “አልይህ” ካልከው ጉዳቱ የባሰ ነው። ከገፋኸውም በአደባባይ መግለጫ አይደለም።

3) አንዳንዴ በቅርብ አገኘሁት ብለህ እንደ ጉድ የምትፈርጀው፣ የምትተቸው፣ የምትዘምትበት የአንተው ወገን አደገኛ ጠላትህ ይሆናል። የኢትዮጵያ ፖለቲካ ክፉ የመጠፋፋት ምዕራፍ ውስጥ ነው። ዘመቻ ያስገድላል። ስትዘምትበት ህይወቱን ጭምር ለማዳን ይጥራል። አንተ የገፋኸውን ወልውሎ ጥይት የሚያደርግ ብዙ አካል አለ። ፖለቲካው እልህ አስጨራሽ እንደመሆኑ የምትችለው መአት ነገር ይኖራል። እንኳን አንተ ፌስቡክ ላይ የምትጨቃጨቀው በድሮን የተደባደቡ፣ ከጎኛቸው የነበሩ ጓደኞችና ዘመዶቻቸው ከሰል የሆኑባቸው አካላት ለሌላ ቁማር ሲባል እልሃቸውን ዋጥ አድርገው አብረን እየሰራን ነው እያሉ ነው። የምትፈርጀው አካል ራሱን ለመከላከል ከሌላ ተጠግቶ ወደ አንተ እንዳይተኩስም፣ እንዲተኩስብህም የምታደርገው ራስህ ነህ። በቅርብ በሀሰት የሚዘመትባቸው አካላት በዝተዋል። ሌላን አካል ወዳጅ አደርጋለሁ፣ ጠላት አታብዙ እየተባለ የህዝብን በደል የሚያጋልጡት ላይ መበርታት የሚጠቅመው ለጠላት ነው።

4) የኢትዮጵያ ፖለቲካ የከፋ ሁኔታ ላይ ነው። ነገ ሌላ ቀን ነው። ማታ የነበረውን ጠዋት አታገኘውም። ማታ ተደስተህ ጠዋት የሚያስከፋ፣ ጠዋት ተስፋ አድርገህ ቀን የሚያስጨንቅ ነው። በዚህ ተለዋዋጭ ፖለቲካ ተስፋ አድርገህ የምትዘናጋበት፣ ተስፋ አጥተህ የምትተወው ነገር የለም። ረዠም ላለው መስራት የተሻለ ነው። ግለሰቦች፣ ድርጅቶች፣ ዘመቻዎች፣ ትብብሮች፣ ጦርነቱም፣ ሰላሙም ይቀየራል። በዛ መንገድ ማሰብ ነው።

5) እንደ ኦነግና ህወሓት ብሔሮተኞች ሲናደዱ አገር የሚረግሙትን “ቀስ በል” ብሎ መምከር አዋጭ ነው። ዛሬ መርገም የለመደ፣ ነገ አሁን ያለበትን እየረገመ፣ አውራጃ እየረገመ ወደታች መውረዱን ይቀጥላል። ልጓም ካልተበጀለት እየተንደረደረ ታች ድረስ ወገንህን እየለጋ በተመሳሳይ ስልት ይሄዳል። አገር ሌላ ነው፣ አገርን ያከፉት ሌሎች ናቸው። አገርን የሰሩት የምትኮራባቸው ናቸው፣ አገርን ችግር ውስጥ ያስገቡት በሀሰት ትርክት አገሩ የእኔ ነው የሚሉት ናቸው። ከአባቶቹ እሴትና ታሪክ ተጣልቶ፣ ከጠላቶቹ ቁንፅል ስልት ተውሶ የትግሉን ዳገት መውጣት አይቻልም።

6) እያንዳንዱ የራሱ መረጃ፣ የራሱ ዝንባሌ፣ የራሱ ጥርጣሬ ይኖረዋል። አንተ የለጠፍከውን ሁሉ ወስዶ ላይሰራልህ ይችላል። በሌላ በኩል ያለውን ካገዘ ተወው። በእኔ ጣቶች ፃፍ አትበለው። ከረሳ አስታውሰው፣ መረጃ ከሌለው ስጠው፣ ትኩረት ካላደረገው አሳየው። ካልሆነ የራስክን መስራት ነው።

 

 

 

Source: Facebook account

Exit mobile version