በአዲስ አበባ ከተማ ህዳር 30 ቀን 2016 ዓ.ም የተጠራውን ህዝባዊ ሰላማዊ ሰልፍ አስመልክቶ ከአስተባባሪ ኮሚቴው የተሰጠ መግለጫ
ሃገራችን ኢትዮጵያ ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ በኦሮሚያ፣ ትግራይና አማራ እና ሌሎች ክልሎች እንዲሁም የዞን አስተዳድሮች ውስጥ በተደረጉና እየተደረጉ ባሉት ጦርነቶች እና ግጭቶች ህዝባችን ሰላሙን አጥቷል፡፡ በኢትዮጵያ በተለያዩ ማዕዘናት በተደረጉ እና እየተደረጉ ባሉ ጦርነቶች እና ግጭቶች ሞት፣ አካል መጉደል እና ንብረት ውድመት ተከስቷል፡፡
በሃገራችን በአብዛኞች ክልሎች ሊባል በሚችል መልኩ ያልተመጣጠኑና ሃይል የተሞሉ ግጭቶች ጦርነቶች ተበራክተዋል በተለይ በአማራ ፣ በኢሮሚያና በትግራይ ክልሎች የየፈፀሙና የሚፈፀሙ ከፍተኛ ግፍ በደልና ጭፍጨፋዎች እየጨመሩ ይገኛሉ ።
በይክልሎቹ የተፈፀሙና እየተፈፀሙ ያለ የተደራጀ አስገድዶ መድፈር በሴቶች የሚፈፀሙ ውሲባዊ ጥቃቶች እጅግ ዘግናኝና በአሳፈሪ ደረጃ ላይ ደርሷል ።
በኦሮሚያ የመንግስት ፀጥታ ኃይሎች በክልሉ ንፁሃን ላይ እስራትና ቶርቸር መፈፀሙ በሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ጭምር የተረጋገጠ ነው ።በአማራ ክልል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከታወጀ ወዲህ ብቻ በርካታ ግፎች በንፁሃን ዜጎች ላይ እየተፈፀመ ይገኛል ፣ በቅርቡ በሁለቱም ክልሎች የድሮን ጥቃት በፌዴራል መንግስት ተፈፅሟል ።መንግስት በየክልሉ ያሉ ጥቂት አድራሾች በአግባቡ አንዲመረመሩና ተጠያቂ እንዲሆኑ ፍላጎት የለውም በዚህ ምክንያት የተጠቂዎች መከራና ስቃይ ሊቆም አልቻለም።
የዩኒይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ኢትዮጵያን በሚመለከት በሚያወጣቸው የሰብዓዊ መብት ሪፖርቶች በሃገራችን ጦርነት፣ የጦር ወንጀል ፣ የስብዓዊነት ልማት ወንጀል በተደጋጋሚ መፈፀማችን ይፋ እያደረገ ሲሆን የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነርም ለተመድ የስብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ማብራርያ በመስጠት ምክርቤቱ ድጋፍ እንደቸራቸው ይታወቃል።
በታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ሃገርን ለዘርፈ ብዙ ምስቅልቅሎች ከመዳረጋቸው ባሻገር ውል አልባ መፍረስን የማስከተል አቅም ያላቸው መሆኑን ስንገነዘብ ሀዘናችን እና ቁጭታችን እጅግ በጣም ከፍተኛ አድርጎታል፡፡ በመሆኑም እነዚህ አሰከፊ ጦርነትና ግጭቶች እንዲቆሙ፤ሁሉም ተፋላሚ ሃይሎች የፖለቲካ ልዩነታቸውን በፖለቲካዊ ውይይት እንዲፈቱ በማለም የሃገራችን ጉዳይ ይመለከተናል የምንል ዜጎች “ጦርነት ይቁም! ሰላም ይስፈን!” በሚል መሪ ቃል ለህዳር 30/2016 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ መድረሻው መስቀል አደባባይ የሆነ ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ ጥሪ ማድረጋችን ይታወቃል፡፡
ይህን ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ የተቋቋመው አስተባባሪ ኮሚቴ ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ የማያስችል የማሳወቂያ ደብዳቤ በአዋጅ ቁጥር 3/1983 ዓ.ም አንቀጽ 4 መሰረት ለአዲስ አበባ አስተዳድር ከንቲባ ጽ/ቤት ከ12 ቀናት በፊት በ19/03/2016 ዓ.ም አስገብቷል፡፡ የአስተዳደሩ ከንቲባ ጽ/ቤት የእወቁልን ደብዳቤውን ፈርመው ተቀብለዋል፡፡ ሰላማዊ ሰልፉን አስተዳድሩ እንዲያውቅ ከተደረገ በኋላም በሂደት የአዲስ አበባ እና ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነሮች እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሰላም እና ፀጥታ ቢሮ ሀላፊ የሰልፉ አስተባባሪዎችን ውይይት እንድናደርግ በማለት ባደረጉልን ጥሪ ተገኝተን ተወያይተናል፡፡
ሰልፉን የማሳወቅ እና ተከትለው የመጡ የመንግስት አካላትን ህጋዊነት የጎደላቸውን መልሶች እንደየሁኔታው እየገመገመ ቆይቷል፡፡ አስተባባሪ ኮሚቴው ለሰልፉ መካሄድ ግብአት ሊሆኑ የሚችሉ ሌሎች መርሃ ግብሮችን እያከናወነ ይገኛል፤ነገር ግን በነበረበት ጊዜ አስተዳደሩ በአጠቃላይ መንግስት ሰላማዊ ስልፉን ለማኮላሸት እና ለእኩይ አላማ ለማዋል ህገወጥ ድርጊቶችን እየፈጸመ ይገኛል፡፡ ሰላማዊ ሰልፉን የተለያዩ ፀረ-ሰላም ሀይሎች ያዘጋጁት እንደሆነ በማስመሰል፤ አዘጋጆቹ በውጭ ሃገር የሚገኙ ሀገር ለማተራመስ ፍላጎት ያላቸው ኃይሎች እንደሆኑ በመጥቀስ፤ በሰለፉ ቀን መንግስት የጸጥታ አካላትን የማሰማራት ፍላጎት የሌለው መሆኑን በመግለጽ ሰላማዊ ሰልፉን አቅጣጫ በማሳት ሁከትና ብጥብጥ እንዲነሳ በማድረግ በህዝባችን ላይ እልቂት እና ውድመት እንዲፈጸም ፍላጎት ያለው መሆኑን ተገንዝበናል፡፡
መንግስት ከላይ የተጠቀሱትን ሰልፉን የማደናቀፍ ህገወጥ እና እኩይ አካሄዶች በማድረግ ብቻ አልተወሰነም፡፡የሰልፉ ቀን አስተባባሪ ኮሚቴዎችን የአስተዳደሩ እና የመንግስት አፍራሽ አካሄዶች እና ሀሰተኛ ፕሮፐጋንዳዎች ሲነዛ ቆይቷል፡፡ሆኖም አስተባባሪዎቹ ለሚዲያዎች በሰጧቸው መግለጫዎች እና ማብራሪያዎች ያከሸፉቸው መሆኑን ስለተገነዘበ በአዲስ አበባ ከተማ የተለያዩ ክፍሎች በመጪው ሰልፍ ይሳተፋሉ ተብለው የሚጠበቁትን የህብረተሰብ ክፍሎች በተለይም ወጣቶችን የማፈስ እና የማጎር ድርጊቱን አጠናክሮ ገፍቶበታል፡፡ትላንት በ27/03/2016ዓ.ም የሰልፉን አስተባባሪ የሆኑትን አራት አመራሮችንም አስሮብናል፡፡ በተመሳሳይ ቀን ማታ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ለማስፈጸም በተቋቋመው የፌዴራል የጸጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይል በኩል በሰልፉ ቀንና ማግስት በህዝባችን ላይ የሚወስደውን እኩይ ድርጊት የሚያሳይ አጥፊ እና ኃላፊነት የጎደለው መግለጫ በሚዲያዎቹ በኩል ይፋ አድርጓል፡፡
አስተባባሪ ኮሚቴው ያቀደው ህዝባዊ ሰላማዊ ሰልፍ አላማ በጣም ግልጽ ነው፡፡ በሀገራችን ያሉት ጦርነቶች እንዲቆሙ በማድረግ እልቂትና ውድመት ማስቆም ሃገር ከመፍረስ አደጋ ለመታደግ ነው፡፡ ሆኖም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ የአዲስ አበባ ፖሊስ፣ የፌዴራል ፖሊስ እና የፌዴራል መንግስት የጸጥታና ደህንነት ግብረ ሀይል በአጠቃላይ የፌዴራል መንግስት የህዳር 30/2016 ዓ.ም ሰላማዊ ሰልፉ ይዟቸው የተነሳ ሃገር አዳኝ አላማዎች ለማሳካት ከመተባበር ይልቅ ሰልፉን ከታለመለት አላማ ውጭ እንዲሄድ እየገፋው ይገኛል፡፡መንግስት በህዝባችን ላይ ተጨማሪ ጥፋት እና ውድመት እንዲፈጸም ሀላፊነት የጎደለው እና ሰላም ጠል በሆነ መልክ እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑን አስተባባሪው ኮሚቴ ድምዳሜ ላይ የደረሰበት በመሆኑ ሰልፉን በተሻለ እና ውጤታማ በሆነ ሁኔታ ለማድረግ የተወሰነ ጊዜ በማራዘም ለህዳር 30/2016 ዓ.ም ተጠርቶ የነበረው ሰልፍ ለሌላ ግዜ የተላለፈ መሆኑን ህዝባችን እንዲያውቀው በታላቅ አክብሮት እና ትህትና እንገልጻለን፡፡
የጦርነት መልካም የሰላም መጥፎ የለውም !!
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ
ህዳር 28 ቀን 2016 ዓ.ም.
አዲስ አበባ ኢትዮጵያ