Site icon Dinknesh Ethiopia

በህወሓት የተቀሰቀሰው ጦርነት በአስቸኳይ ይቁም!

eprp support

ከኢሕአፓ የድጋፍ አስተባባሪ ኮሚቴ የተሰጠ መግለጫ

የብልጽግና አገዛዝና ህወሓት በትግራይ፤ በአማራና በአፋር ክልሎች በሚሊዮን የሚገመተውን

የወገኖቻችንን ነፍስ የቀጠፈውንና ሚሊዮኖችን ከቀያቸው ያፈናቀለውን ጦርነት ለሁለት

ዓመታት ካካሄዱ በኋላ ዳግም ሌላ ጦርነትን ያደርጋሉ ተብሎ አይታሰብም ነበር፡፡ ሕዝባችን

በታሪኩ አይቶት የማያውቀው ረሃብና ድህነት እያሰቃየው ባለበት በአሁኑ ወቅት ለሌላ ጦርነት

መነሳታቸው እጅግ አሳዛኝ ክስተት ነው።

የትግራይና የአማራ ሕዝብ ጦርነት ባስከተለው አስከፊ ሁኔታ ውስጥ ባሉበት በዚህ ሰዓት

የብልጽግናው አብይ አህመድና የህወሓት መሪዎች ለሌላ ጦርነት በመሰናዳት ዛሬ በአላማጣ

ላይ በከባድ መሣሪያና በሜካናይዝድ ጦር ተደግፎ የተከፈተውን ጦርነት የኢሕአፓ የድጋፍ

አካል በጥብቅ ያወግዛል። በሕዝብ መካከል የሚደረግ ጦርነት በተጨባጭ እንዳየነው የጋራ

ውድቀትን እንጂ የአንዱን ልማት የሌላውን ውድቀት የሚያስከትል አይደለም። በግፈኛና ጦረኛ

ገዥዎች የታቀደውና አሁን የተጀመረው ጦርነት ውጤቱ በትግራይ፣ በአማራና በአፋር

ወገኖቻችን ላይ ባለፈው እንዳየነውና ዓለም እንደታዘበው የጋራ ውድቀት፤ ረሃብና ስደት

የሚያስከትል እንደሚሆን የታወቀ ነው፡፡

ህወሓትና ኦነግ የፈጠሩት “የእኛ እና የእናንተ” ፖለቲካ ጠባብ ብሄርተኞቹ እንደሚያስቡትና

እንደሚያምኑበትንም አንዱን አጥፍቶ በጠፋው ኅብረተሰብ ላይ የለማች ትግራይን የመፍጠር

ወይንም አማራን አጥፍቶ የሰፋችና የጠነከረች ኦሮሚያን የመገንባት አስተሳሰብ ፍጹም

ድንቁርና መሆኑን ለመረዳት የሌሎች አገሮችን ታሪክ በምሳሌነት መጥቀስ አያስፈልገንም፡፡

በሰሜኑ የአገራችን ክፍል ለሁለት ዓመታት የተከሄደው ጦርነት በቂ ማስረጃ ነውና፡፡ ጦርነቱ

በትግራይ፣ በአማራ፣ በአፋርና በኦሮሞ ወገኖቻችን ላይ ያስከተለውን ድህነት፣ ረሃብ፣ ስደት፣

እስራትና ግድያ መጥቀሱ ብቻ ከበቂ በላይ ነው፡፡ ስለዚህ ሕዝባችን እነዚህን ጦረኛ የፖለቲካ

ድርጅቶችን እኩይ ተግባራችሁን በአስቸኳይ አቁሙ ሊላቸው ይገባል።

በአብይ አህመድ የስብሰባ መሪነትና በህወሓት መሪዎች ተመሳጣሪነት የታቀደው ይህ በአላማጣ

በከባድ መሣሪያና በሜካናይዝድ ጦር ተደግፎ እየተካሄደ ያለው ጦርነት ሁለቱ ድርጅቶች፣

ሌሎች ድርጅቶችን ሳያካትቱ ተስማሙ የተባለው የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት የጣሰ መሆኑ

ሊታወቅ ይገባል። በሁለቱ ጦረኛ ድርጅቶች በአንዱ ታዛቢነትና በሌላው የውጊያው

ፊታውራሪነት ዳግም የተጀመረውን ከትግራይ ወደ አላማጣ እየሰፋ ያለን ጦርነት የኢሕአፓ

የድጋፍ አካል ሲያወግዝ የዓለማቀፍ ስምምነትን የጣሰ፡ ማንኛውም ወገን ጦርነት እንዳያነሳ

በአንቀስ 3 ንዑስ አንቀጽ 2 የሰፈረውን የጣሰ መሆኑንም ያሰምርበታል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም

አንቀጽ 6 ላይ እንደተጠቀሰው የትግራይ ኃይሎች ኅብረት (TDF) እስካሁን ትጥቁን

አለመፍታቱ በሁለቱ ውሉን ፈራሚ አካላት ጥሰት የተፈጸመ መሆኑን የአፍሪካ ኅብረትና

አደራዳሪዎች ወገኖች አውቀውት ጦርነቱ እንዲቆም ግፊት እንዲያደርጉና የጦርነቱ ዳግም ሰለባ

ከሆነው ሕዝባችንም ጎን እንዲቆሙ የኢሕአፓ የድጋፍ አካል ጥሪውን ያቀርባል።

ጦርነቱ በትግራይ፤ በአማራና በቀሪው የኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ በግድ የተጫነበትና የጦርነቱም

ውጤት የሀገር ጥፋትና የሕዝብ እልቂት የሚያስከትል በመሆኑ የኢትዮጵያ ሕዝብ በአንድነት

ተነስቶ “ጦርነት ይቁም፣ ሰላም ይስፈን” በሚለው መርኅ መሠረት ድምፁን ከፍ አድርጎ ትግሉን

አጠናክሮ እንዲቀጥል አናሳስባለን፡፡

አንድነት ኃይል ነው!

ሚያዝያ ፰ ቀን ፪ ሺህ ፲፮ ዓ. ም

April 16, 2024

Exit mobile version