Site icon Dinknesh Ethiopia

መንግሥት የሚመራበትን ሕገ መንግሥት ማክበር ግዴታው ነው

eprpHeader2020

የኢሕአፓ ሊቀመንበርና ሌሎችም የኅሊና እስረኞች ያለምንም ቅድመ-ሁኔታ ይፈቱ

ግንቦት ፰ ቀን ፪ ሺህ ፲፮ ዓ. ም

ኢትዮጵያ እንደ አገር እንድትቀጥል በአገራችን ውስጥ የሕግ የበላይነት ሊኖር ይገባል። የአገር ሕገ-መንግሥት ዜጎች ብቻ ሳይሆኑ መንግሥትም የሚገዛበት የአገሪቷ ሉዓላዊ ሕግ መሆኑ መታወቅ ይኖርበታል፡፡ የመንግሥት ፈርጣማ ጉልበት በሕገ መንግሥት የሚገታ ካልሆነ አንድ መንግሥት ሕዝብን ብቻ እንዳፈተተኝ አስተዳድርበታለሁ ካለ ሕገ መንግሥቱ ቅቡልነት አይኖረውም። የመንግሥት የፀጥታ አካላትም ጭምር በሕግ አግባብ መሠረት ልጓም ሊደረግበቸው ስለሚገባ ነው በሕግ መተዳደር ያስፈለገው። የመንግሥት አካላት ዜጎችን እንደፈለጉ ማሰር፣ መግደል፣ ማፈናቀል፣ መደብደብ፣ ማፈን፣ ማንገላታት፣ ማሳደድ፣ ቤት ንብረታቸውን መቀማት ከጀመሩ መንግሥትንና ሕዝቡን የሚያስተሳስረው ሕግዊ ሥርዓት ትርጉም-አልባ ሆኗል ማለት ነው።

መንግሥት በቅድሚያ ሕግ አክባሪ ሲሆን ነው ሕግን ማስከበር የሚችለው፡፡ ስለዚህ ነው ኢሕአፓ የሕግ የበላይነት ይስፈን የሚለው፡፡ ይህ ብቻም አይደለም ኢትዮጵያ የፈረመቻቸው የአፍሪካ የሰብዓዊ መብት ቻርተርና የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብት ቻርተር፣ መንግሥት የዜጎችን ስብዓዊ መብቶች ማክበር እንዳለበት ግድ ይላሉ፡፡ የሕዝብ መብት ባልተከበረበት ሁኔታ ተጨቁኖና ታፍኖ በጉልበት እየተገዛ ያለ ሕዝብ የአመፅ ትግል እንደሚመርጥ በተለያዩ አገራት ውስጥ የተከሰተ ለመሆኑ ታሪክ በተደጋጋሚ አሳይቶናል፡፡

ያለጥርጥር ጭቆና ነው አመፅን የሚወልደው። ስለዚህ በኢትዮጵያችን ውስጥ እስከዛሬ ድረስ የፈሰሰው የደም ጎርፍ ሊበቃ ይገባልና የብልጽግና መንግሥት በአገራችን ውስጥ ሠላምን ለማስፈን ተቀዳሚ እርምጃ በሕዝብ ላይ ጦር መስበቁን፣ ሠራዊት ማዝመቱን፣ በድሮንና በአየር ኃይል ሠላማዊ ሕዝብን መፍጀቱን በአስቸኳይ ማቆም ይኖርበታል፡፡ ሕዝብን ከዕልቂት ሀገርንም ከውድመት ማዳኛው ብቸኛው መንገድ ዛሬም ሠላማዊ የትግል መንገድ ነውና።

የብልጽግና መንግሥት እመራበታለሁ በሚለው ሕገ-መንግሥት ሊገረሰሱ የማይገባቸው ተብለው የተቀመጡ የሰብዓዊ መብት ጥበቃ አንቀጾችን እየጣሰ ይገኛል። ኢ-ሰብዓዊ በሆነ መንገድ ዜጎችን መያዝና ማንገላታት፣ ወይም በዜጎች ላይ ሰቆቃ መፈጸምን አንቀጽ 18 ይከለክላል። አንቀጽ 25 ደግሞ አድልዖአዊነት ይከለክላል። ዜጎችን በቋንቋና ብሔረሰብ ፍረጃ ወይም በዕምነትና በሃሳብ ልዩነት ላይ ተመርኩዞ ነጥሎ ማጥቃት፣ በኢትዮጵያችን ውስጥ በብልጽግና መንግሥት እየተፈጸመ ነው። አፈሳ፣ ያለአግባብ ዜጎችን ማሰር፣ ዘመድና ወዳጅ እንዳያገኛቸው በስውርና ርቀት ባላቸው ሥፍራዎች ማቆየት፣ አንዳንዴም መሰወር የወገኖቻችን የዘወትር ዕጣ ፈንታ ሆነዋል፡፡

የብልጽግና መንግሥት እጅግ አሳሳቢ በሆነ ድረጃ ሥራዬ ብሎ የተያያዘው ስለ ጦርነት መቆምና ሠላም መስፈን ጥያቄ የሚያነሱትን ወገኖች በማሳደድ ላይ ነው። ህዳር 30 ቀን 2016 ዓ .ም ሊጠራ ታስቦ የነበረው ሠልፍ ዋናው ጥያቄ “ጦርነት ይቁም፣ ሰላም ይስፈን” የሚል ነበር። በከፍተኛ የሀገርና የወገን ፍቅር ተነሳስተው ሠላማዊ ሠልፉን ለመጥራት የሞከሩትን የፖለቲካ ድርጅቶች መሪዎችና አባሎች መንግሥት ከህዳር 27 ቀን 2016 ዓ. ም ጀምሮ በማሰርና በማንገላታት ላይ እንደተጠመደ ነው ዛሬም እየተስተዋለ ያለው።

ጥቂቶች ከሦስት ወር ተኩል የአዋሽ አርባ እስርና እንግልት በኋላ የፓርቲያችን ተቀዳሚ ም/ሊቀመንበር መጋቤ ብሉይ አብርሃም ኃይማኖትና ጊደና መድሕን ቢፈቱም፣ በወቅቱ ከታሠሩት ውስጥ አቶ ናትናኤል መኮንን እስከዛሬ አለመፈታቱ እንዳለ ሆኖ፣ ሌሎችንም ሰልፉን ለመጥራት የሞከሩትንም እየተለቀሙ ታስረዋል። የኢሕአፓ ሊቀመንበር፣ ረ/ፕሮፌሰር ዝናቡ አበራ መጋቢት 17 ቀን 2016 ዓ. ም. ታስረዋል፡፡ ሌሎችም የእስረኞች አያያዝና ቆይታ ሰቅጣጭ በሆነበት አዋሽ አርባ ታስረዋል።

ብልጽግና ፖለቲከኞችን፣ ጋዜጠኞችን፣ ማኅበራዊ አንቂዎችን፣ ሌሎችንም ዜጎች እያፈሰ በማሠር፣ በማሰቃየት የፖለቲካ ሥልጣኑን ለማቆየት የሚችል ከመሰለው እጅጉን ተሳስቷል፡፡ ዕመቃ ግፋ ቢል መንበርን ለአጭር ጊዜ ያፀና ይሆን እንደሆን እንጂ ዘለቄታ ስለማይኖረው ገዢው ፓርቲ አገራችን እንደ አገር እንድትቀጠል እንዲሁም የወገኖቻችን ደህንነት እንዲጠበቅ፣ ሰላም እንዲሰፍን እስራቱ፣ አፈናው፣ ግድያው፣ ወከባው፣ ማስፈራራቱ፣ ሕግን መጣሱ ማብቃት አለበት፡፡ የተለየ ሃሳብ ያላቸውን ማፈን አምባገነናዊ ሥርዓትን ማንበርና በፍርሃት እየተናጡ፣ ሌሎችንም እፎይታ ነስቶ መቆየትን እንጂ ለአገር ሠላምና መረጋጋትን አያመጣም፣ ወደ ማኅበራዊና ኤኮኖሚያዊ እድገትም በፍጹም አይወስድም።

የኢሕአፓ ሊቀመንበር፣ ረ/ፕ ዝናቡ አበራ በአስቸኳይ ይፈቱ!

በህዳር 30 ሠልፍ ለመጥራት የሞከሩትን፣ ሁሉ የሰላማዊ ፖለቲካ አራማጆች ስለሆኑ ይፈቱ!

በዘርና በሌሎችም ፍረጃዎች የታሰሩትንና የኅሊና እስረኞችን በሙሉ የፈቱ!

ኢትዮጵያ ታፍራና ተከብራ በነፃነት ለዘለዓለም ትኑር!

 

 

ስልክ / Phone: +251 911 400 982                ኢሜይል / email: eprp@eprp-ihapa.com

Exit mobile version