የትግል ግንባር በማስፋት የሚዛባ ኃይል፤ የሚቀር ድል የለም!
(ከአማራ ፋኖ ጎንደር ዕዝ የተሰጠ መግለጫ)
ግንቦት 27/2016 ዓ.ም ንጋት ላይ በአማራ ጠቅላይ ግዛት በሰሜን ጎንደር ዞን አድርቃይ ወረዳ፣ አሊጣራ ቀበሌ ‹አንካቶ› በተባለ አካባቢ፣ ሰርገው መንገድ በተከፈተላቸው የትሕነግ ታጣቂዎች በተፈጸመ የጅምላ ጥቃት በርካታ ሰብዓዊና ቁሳዊ ጉዳት ደርሷል፡፡
በቅድሚያ በዚህ አሳዛኝ የጅምላ ጥቃት ለሞቱ ወገኖቻችን ነፍስ ይማር እያልን ለሟች ቤተሰቦች መጽናናትን እንመኛለን፡፡
ይህ የጅምላ ጥቃት ከተፈጸመ 48 ሰዓታት በኋላ ግንቦት 30/2016 ዓ.ም አመሻሽ ላይ የትሕነግ ታጣቂ በከፍተኛ የጦር መሳሪያ ታጅቦ ተከዜን ተሻግሮ ታላቁን ገዳም ዋልድባን ጨምሮ የጠለምት በረሃማ ስትራቴጂያዊ ስፍራዎች እንዲወር ተደርጓል፡፡ ተጨማሪ ወራሪ ኃይል ተከዜን ለመሻገርና ህዝባችን ለመጨፍጨፍ ተጠግቷል።
ትሕነግ ይህን ወረራ የፈጸመው በፋሽስቱ ዐቢይ አሕመድ ፍቃድ፣ በብአዴን ታዛዥነት እንደሆነ የአማራ ፋኖ ጎንደር ዕዝ የደህንነት ክትትል መረጃዎች አረጋግጠዋል፡፡
ትሕነግ፣ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ከሚሰበሰበው ግብር፡- መደበኛና የካፒታል በጀት ተፈቅዶለት፣ ተጨማሪ ወታደራዊ ሎጀስቲክ ቀርቦለት፣ ውድና በቀላሉ የማይገኙ ወታደራዊ መረጃዎች እየቀረቡለት፣ ከሁሉም በላይ አማራ ራሱን ከወረራ እንዳይከላከል የሚያደርግ ወታደራዊና መዋቅራዊ የፖለቲካ ሽፋን እየተሰጠው በቀጥታ ድጋፍ ወረራዎችን እየፈጸመ ይገኛል፡፡
በዚህ መሰል ሁለንተናዊ ድጋፍ የአማራ ታሪካዊ ርስቶችን ለትሕነግ አሳልፎ እየሰጠ፣ ሕዝባችንንም ለዳግም ወረራ እየዳረገ ያለው ብልጽግና የሚባለው የአማራ ጠላት ነው፡፡
በመሆኑም የአማራ ፋኖ ጎንደር ዕዝ በዚህ ጉዳይ ያለውን የትግል ግምገማና ግልጽ አቋም ለአማራ ሕዝብ፣ ለአማራ ወዳጆችና የትግሉ ደጋፊዎች በሙሉ ማሳወቅ ይወዳል፡-
ኦሕዴድ ብልጽግና እየተዋጋ ያለው የኦሮሞ ኢምፓየር ለመመስረት ነው፡፡ በአንጻሩ ብአዴን ብልጽግና የገዛ ወገኖቹን እየወጋ ያለው የዕለት የደም እንጀራውን ለመብላት ነው፡፡ ኦሕዴድ ብልጽግና አማራን እየወጋ ያለው የራሱን አገረ-መንግሥት ለማቆም አማራን አገር አልባ ለማድረግ ነው፡፡ ብአዴን ብልጽግና ደግሞ ከዕለት ሆድ የዘለለ ተሻጋሪ ዓላማ የለውም፡፡ ለዚህም ነው ከአማራ ሕዝብ ቀጥተኛ ጠላቶች ጋር ወግኖ፣ ሕዝቡን እጁን የፊጢኝ አስሮ፣ ለጥቃት ማጋለጡ ሳያንስ ተባብሮ ማስወጋቱ፤ የዘር ማጥፋት ዓላማ ባለው ጦርነት ውስጥ፣ በአጥፊው መዋቅር ውስጥ ሆኖ ወገኑን ማጥፋት የቀጠለው፡፡ በአጠቃላይ የጠላት ዓላማ አስፈጻሚ በሆነው ብአዴን ብልጽግና የሚቀማ እንጂ የሚመለስ የአማራ ሕዝብ ጥያቄ የለም።
ትሕነግ አቅምና ዕድል ባገኘበት ጊዜ ሁሉ አማራ ላይ የጥፋት ሰይፉን መዝዞ አጥቅቶታል። ዛሬም ጊዜና ሁኔታዎችን አስልቶ፣ በአማራ ሕዝብ ላይ የጭካኔ ሰይፉን ማሳረፉን እንደቀጠለ በራያ እና በጠለምት አማራ በኩል ያደረጋቸው ሰሞነኛ ጥቃቶች ጉልህ ማሳያ ናቸው፡፡ ይህ ኃይል፣ ከቀደመ ስህተቱ የማይማር ፋሽዝምን ዕድሜ ልኩን መመሪያው ያደረገ የጥፋት ኃይል በመሆኑ ከእርሱ እየተቃጣ ያለን ጥቃት መመከት ምርጫ ሳይሆን ግዴታ ነው፡፡ ለዚህ ጠላት ትልቅ አቅም የሆነው ለወረራ ማስፈጸሚያው የበጀትና ወታደራዊ ሎጀስቲክ ምንጩ ብልጽግና ስለመሆኑ ለአፍታም ቢሆን መዘንጋት የለበትም፡፡
የጀመርነው የህልውና ትግል ውስብስብና ዘርፈ ብዙ ግንባሮች እንዳሉት እናምናለን፡፡ ሁሉም ግንባሮች ግን ምንጫቸው አንድ ነው፡፡ እርሱም አማራ-ጠልነት ነው፡፡ አማራ ለጥቅምና ለመብቶቹ መከበር የቆመለት፣ ጋሻ መከታ የሚሆነው ኃይል የሌለው በመሆኑ አማራ ጠል ኃይሎች ርስትና ታሪካዊ ግዛቶቹን በመቀራመት አማራን የማጥፋት የጋራ ግብ ይዘው ተነስተዋል፡፡ ለዚህም ነው ግንባሩን በተለያየ ሁኔታ ሲያሰፉት፤ ሲያወሳስቡት የሚታየው፡፡ የፋኖ ትግል፣ የአማራ ሕዝብን የጥቃት ተጋላጭነት የጨመረውንና መዋቅራዊ የሕልውና አደጋ እንዲጋረጥበት ያደረገውን ሥርዓታዊ አደጋ ከምንጩ በማድረቅ የሕዝባችንን ሕልውና ከማስከበር አልፎ ጥቅምና መብቶቹን በዘላቂነት ማስከበር ነው፡፡
ከዚህ በላይ በቀረቡ ማዕከላዊ የትግል ነጥቦች መሰረት፡- የአማራ ሕዝብ ሲዋደቅላቸው የኖረው፤ በመሰረታዊነትም ለፋኖ ትግል መነሻ ከሆኑት የትግሉ አስኳል አጀንዳዎች አንዱ የሆነው፡- ራያ፣ ወልቃይት-ጠገዴና ጠለምት ታሪካዊ ርስቶቻችን በሁኔታዎች የማይቀያየሩ፣ ቋሚና ዘላቂ የማንነት እና የክብር ጉዳይ ናቸው፡፡
እነዚህ ታሪካዊ የአማራ ርስቶች የግዛት ሁኔታና የሕዝባችንን ሥነ-ልቦናዊ ስሪት የሚወሰኑ የዕጣ ፈንታው ወሳኝ ጉዳዮች በመሆናቸው በሕልውና ትግሉ ሂደት ቀይ መስመር ሆነው የሚቀጥሉ መሆናቸውን የአማራ ፋኖ ጎንደር ዕዝ በድጋሚ ያረጋግጣል፡፡ እነዚህ የአማራ ታሪካዊ ርስቶች ዳግም ወረራ እየተፈጸመባቸው ያለው ባርነት በማይሰለቸው ብአዴን ታዛዥነት መሆኑ ለአፍታም ቢሆን መዘንጋት የለበትም፡፡
ስለሆነም፡-
አንደኛ፡- የወረራው ቀጥተኛ ተጋላጭ በሆኑት የራያ፣ የወልቃት-ጠገዴ እና ጠለምት ምድር የምትኖረው ባለርስቱ ሕዝባችን ከዳግም ወረራ ሊያድንህ የሚችለው ፋኖነትህ ብቻ በመሆኑ በአርበኝነት ስሜት የወትሮ ዝግጁነት አቅምህን እንድታሳድግ፤ በተጠንቀቅ እንድትቆም ብሎም ለክብርህና ለማንነትህ እንድትፋለም የትግል ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡
ሁለተኛ፡- የሚዋጋለትን ዓላማ የማያውቀው የብልጽግና ሰራዊት በአራቱም አቅጣጫ በገባበት ቦታ ሁሉ ዙሪያው እሳት ሆኖበት እየተለበለበ ይገኛል፡፡ በዚህም መሬት ላይ ያለውን የውጊያ እውነታዎች መቀየር ባለመቻሉ፣ ብልጽግና ቀደም ሲል አሳልፎ ለመስጠት የተስማማውን የአማራ ታሪካዊ ርስቶች በትሕነግ ታጣቂዎች በማስወረር የኃይል ሚዛን ለማዛባት የትግል አቅጣጫ ለማስቀየር የተለመደ ቁማሩን ቀጥሎበታል፡፡ ይህን ከንቱ ሴራ ‹ከእሳቱ ለመውጣት እሾኽ መጨበጥ ትርፉ መጋጋጥ!› ብለነዋል፡፡
ይህ ከንቱ ሴራ በተደራጀ፣ በነቃና ሕዝባዊነት በተላበሰው የፋኖ ትግል የሚቀለበስ፣ በምንም ሁኔታ የትግሉን ድል የማይቀይረው እንደሆነ እናረጋግጣለን፡፡
ሦስተኛ፡- የተከፈተብን ጦርነት የአካል ብቻ ሳይሆን የኢኮኖሚም በመሆኑ፣ የአማራ አርሶ አደር በአንድ እጅህ የነጻነትህ ዋስትና የሆነውን የጦር መሳሪያህን፤ በሌላኛው እጅህ የኢኮኖሚ ዋስትናህ የሆነውን እርሻህን እንዳታሳልፍ ሞፈርህን ጨብጠህ ከህልውና ትግሉ ሳትለይ ክረምቱን እንድትቀበል ጥሪያችንን ስናቀርብ ‹አንድ ሰኔ የጣለውን ሰባት ሰኔ አያነሳውም!› በሚለው አማራዊ ብሂል ነው፡፡
አራተኛ፡- ፋኖ ነጻ ባወጣቸውና በቀጣዩቹ ጊዜያት ነጻ በሚያወጣቸው አካባቢዎች የብአዴን ቅልብ ጦር ሆነው በመንገድ መሪነት፣ በጥይት አብራጅነት ለጠላት የሚያገለግሉ ሚሊሻዎች እርሻ ማረስ አይችሉም! ይልቁንም ነጻ በወጡ አካባቢዎች በፋኖ ውሳኔ ሰጭነት መሬት ጦም እንዳያድር ይደረጋል፡፡ የመሬት ድልድል ሥራው በጥናት የሚሰራ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ በወገናቸው ላይ ጦር ያነሱ ባንዳዎች የእርሻ መሬት ላይ ፋኖ እርምጃዎችን ይወሰዳል፡፡ በተጨማሪም የፋኖዎች፣ የታጋይ ሰማዕታት ቤተሰቦች የእርሻ መሬት በአግባቡ እንዲታረስ በባለቤትነት ስሜት የደቦ ስራዎች ስምሪት በመስጠት ትግሉን ሁሉን አቀፍ የማድረግ ስራዎች እንዲሰራ ከዕዙ ጠቅላይ መምሪያ ለሁሉም ክፍለ ጦሮችና በስራቸው ላሉ ሕዝባዊ አስተዳደሮች ትዕዛዝ ወርዷል፡፡
በአጠቃላይ የአማራ ፋኖ ጎንደር ዕዝ ትግሉን ስትራቴጂካዊ በሆነ መልኩ እየመራው ይገኛል፡፡በዚህ የህልውና ትግል ላይ በግልጽ መታወቅ ያለበት ጉዳይ፡- ኦሕዴድ ብልጽግና የሚዋጋው ለኦሮሞ ኢምፓየር፤ ትሕነግ ለዳግም ወረራ የተነሳው ለታላቋ ትግራይ ምስረታ በሆነበት ሁኔታ፣ ብአዴናውያን ከዕለት የደም እንጀራ ያልዘለለ ለሆድ አደር ዓላማቸው የአማራ ታሪካዊ ርስቶችን ዳግም አሳልፈው በመስጠት አማራን አገር አልባ ለማደርግ እየሰሩ የመሆኑን እውነታ ነው፡፡ የብአዴን መወገድ የአማራ የአገር ባለቤትነት ማረጋገጫ ወሳኝ እርካብ ነው፡፡ስለሆነም ሕዝባችን ከመቼውም ጊዜ በላይ ሕልውናውን በክንዱ ለማስከበር ከፋኖ ትግል ጎን በመቆም መፋለሙን እንዲቀጥል ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡
ፋሽስቱ ብልጽግና፤ ከእሳቱ ለመውጣት እሾኽ መጨበጥ ትርፉ መጋጋጥ!
የትግል ግንባር በማስፋት የሚዛባ ኃይል፤ የሚቀር ድል የለም!!
የአማራ ፋኖ ጎንደር ዕዝ
ዋና አዛዥ አርበኛ ሀብቴ ወልዴ
ጎንደር-አማራ-ኢትዮጵያ
ሰኔ 2/2016 ዓ.ም