በባጤሮ በለጠ
ፊቨርዋሪ 5፣ 2026 የምርጫ ቦርድ ባለድርሻዎችን ሰብስቦ በሀገሪቱ ውስጥ ያለውን “የጸጥታ ሁኔታ ” አረንጓዴ ቢጫ ቀይ በሚል መድቦ ውይይት ማካሄዱን ይፋ አድርጓል፡፡
ይህ ጉዳይ ብዙ ጥያቄ የሚያስነሳ ሲሆን ከትንሹ ለመጀመር ምርጫ ቦርድ ያቀረበው ሪፖርት በማን የተሰበሰበና የተጠናቀረ መረጃን ያያዘ ነው የሚል ነው፡፡ ጥናቱ የተካሄደው ከገዥው ፓርቲ ከብልጽግና ነጻ በሆነ አካል ነውን?
ብልጽግና በአሁኑ ሰአት ሁሉንም የጸጥታ ተቋሞች ነጻነታቸውን ግፍፎ በሙሉ የርሱ አገልጋይ እንዳደረጋቸው የማይካድ ሀቅ ነው፡፡ ለምሳሌ የመከላከያ ሆነ የፖሊስ ሀይሉ ባለስልጣኖች በየቀኑ በ መገናኛ ብዙሀን እየቀረቡ ታቃዋሚውን መስደብ መንግስትን ማሞገስ ከመንግስት ፐሮፓጋንዳ ክንፍ በበለጠ ሁኔታ የፖለቲካ ቅስቀሳ አድራጊ ሆነው እንደሚገኙ ለማወቅ የተለያዩ ሚዲያዎችን መመልከቱ ብቻ በቂ ነው፡፡
ልክ እንደ ብልጽግና የህዝብ ግንኑኙት ሰራዊት ”ተቃዋሚ የሚባል የለም ሁሉም ተደምስሠው ዋሻ ውስጥ ተደብቀዋል፣ እየለቀምናቸው ነው፤ እንደ ጉም ተበትነዋል፤ በቅርቡ ሁሉም እጅ እንዲሰጡ እናደርጋለን “ ወዘተ ሲሉ ነው የሚደመጡት፡፡ ታዳ አሁንስ እነርሱ ያዘጋጁት የጸጥታ ግምገማ ሪፖርት እንዴት ገለልተኛና ተአማኒ ሊሆን ይችላል?
ይህን የመንግስት መስሪያ ቤቶች ሪፖርት እውነታውን እንደሚገልጥ አድርጎ ማቅረብ ራስን ማታለለ አይሆንምን? ህዝብንስ ማሳሳት እይሆንምን? የምታዩትን የምታውቁትን ትታችሁ ብልጽግና የሚለውን እንደ ትክክለኛ መረጃ ተቀበሉ ማለት አይደለምን?
በርግጥ ነጻ የሆነ ግምገማ ከተፈለገ ከአገዛዙ ተጸኖ ነጻ የሆኑ ድርጅቶች ለምሳሌ አለማቀፍ ድርጅት ሂውማን ራይትስ ዋች Human Rights Watch፣ ወይም የተባባሩት መንግስታት UN የሚወክለው አካል ወይም የክራይሥስ ግሩፐ Crisis Group ገምጋሚዎች የተቃዋሚ ፓርቲዎች ግባት ታክሎበት ገብተው የሚያደርጉት ጥናት እንዲካሄድ ማድረግ ያስፈልጋል እንጂ ብልጽግናማ ከጅምሩ ምንም ችግር የለም ሁሉንም ነገር ተቆጣጥሬ ነው ያለሁት እንደሚል የታወቀ ነው፡፡
እውነታው ግን ሀገራችን የተረጋጋችም ጸጥታ የሰፈነባትም እንዳልሆነች ነው፡፡ በምስራቅ አፍሪካ ከሱዳን ቀጥሎ ቀውስ ላይ የምትገኝ ሀገር ኢትዮጰያ ነች፡፡ ሰሞኑን የወጣ የውጭ ሀገር መንግስታት ( አውስትራሊያ፣ ካናዳ እንግሊዝ፣ አሜሪካ ) ግምገማ፡ ትግራይ፣ አማራ በሙሉ ኦሮሚያ በከፊል ጋምቤላ፣ ቤነሻንስጉል በሙሉ ፡ ሶማሌ ክልል እና አፋር በከፊል ዜጎቻቸው እነዚህን አካባቢዎች ጥለው እንዲወጡ ወይም በፍጹም ወደነዚህ ቦታዎች እንዳይሄዱ እያሳሰቡ ነው የሚገኙት፡፡
እውነታው ከአዲስ አበባ 50 ኪሎ ሜትር ርቀት እንደልብ ሄዶ መመለስ አይቻልም፡፡ ከአዲስ አበባ 100 ኪሎ ሜትር በማይሞላ ርቀት ገብረጉራቻ ላይ አውቶቡስ እያስቆሙ አፈና ማካሄድ የተለመደ ነው፡፡ ከአዲአበባ 45 ኪሎ ሜትር ርቀት ሸኖ ላይ ጦርነት ይካሄዳል፡፡ 120 ኪሎ ሜትር ደብረ ብርሀን ላይ መንግስት ከከተማው ውጭ መነቃነቅ እንደልቡ አይችልም፡፡ ጎጃም በሙሉ ጦርነት ነው ጎንደር ወሎ ሰሜን ሸዋም እንደዚሁ መንግስት 70% እስከ 80% የሚሆነው ቦታ ላይ ቁጥጥር የለውም፡፡ ትግራይ ሌላ ሀገር ነው የሚመስለው፡፡ ከአዲስ አበባ አዋሳ እንደልብ በመኪና መንቀሳቀስ አይቻልም። ከህወሀት ሰራዊት ውጭ አንድም የፊደራል ጸጥታ ሀይል ትግራይ ውስጥ የለም፡፡ ከአዲስ አበባ መቀሌ ድረስ ያለው መንግድ በፋኖ የተያዘ ነው አለበለዚያም በማንኛውም ጊዜ ውጊያ ሊከፈትበት የሚችል መረጋጋት የሌለበት ቦታ ነው፡፡ ወለጋ፤ ጉጂ እና ቦረና ተመሳሳይ ሁኔታ ሰፍኗል፡፡
ይህ እውነታ ምርጫ ቦርድ ያቀረበው ሪፖርት መርጫ ቦርድ አመነም አላመነም ህዝብ የሚያውቀው ነው፡፡
ይህ እየሆነ ባለበት ሀገር፡ ምርጫ ቦርድ ብዙውን የሀገሪቱን ክፍል ምርጫ ሊካሄድበት የሚችል አስመስሎ ተእማኒነት የሌለው ሪፖርት ማቅረቡ ምን ይባላል? ምንስ ይፈይዳል? ራሱ ምርጫ ቦርድን ተአማኒነቱን ጥያቄ ውስጥ አያስገባውምን?
ምርጫ ተአማኒ እንዲሆን ሁሉንም ዜጋ እኩል አሳታፊ እንዲሆን ያስፈልጋል፡፡ ለዚህ ደግሞ በሁሉም ቦታ የጸጥታ ሁኔታው ለምርጫ ምቹ ማለትም የተረጋጋ ሊሆን ይገባዋል፡፡
ይህ ባልሆነበት የሚካሄድ ምርጫ የተወሰኑ የሀገሪቱ ክፍሎችን ብቻ የሚወክል ነውና “ተመረጠ” የሚባለውም መንግስት የሁሉም መንግስት ሳይሆን የነዚያ ጥቂት ሰዎች መንግስት ይሆናል፡፡ ሁሉንም ለማስተዳደርም ቅቡልነት (legitimacy) አይኖረውም ማለት ነው፡፡ ህዝብ ደሞ ላልመረጥኩት መንግስት አልገብርም ፡ ያልመረጥኩት መንግስት አያስተዳድረኝም፣ ቢል አይፈረድበትም፡፡
የአሜሪካ ሪቮሊሽን አንዱ መፈክሩ “ላልመረጥኩት መንግስት አልገብርም” no taxation without representation የሚል እንደነበረ ፣ ህዝቡ በዚህ መፈክር ዙሪያ ተሰባስቦም በግድ ልግዛህ ያለውን ወራሪ መንግስት በተለያየ የተቃውሞ ስልት ሲፋለም ቆይቶ በመጨረሻም ገዝዎቹን አስወግዶ ነጻነቱን አዋልዷል፡፡
አሁንም ለነጻና ሁሉን አሳታፊ ምርጫ አስቻይ ሁኔታ እውን እንዲሆን አበክሮ መታገል ይቅደም፡፡
አስቻይ ሁኔታ ባልተሟላበት የሚካሄድ ምርጫ ውጤቱ የህዝብን ድምጽ አይወክልም፡፡ ህዝብ ደግሞ በነጻነት ድምጹን ላልሰጠው መንግስት ቅቡልነትን አይቸርም፡፡ ለዚያ መንግስት አልገብርም አልገዛም ቢል በቂ ምክንያት አለው፡፡
አደባብሰው ቢያርሡ ባረም ይመለሱ፡
