ኢትዮጵያ ውስጥ እስከ 80 የፖለቲካ ፓርቲወች አሉ ይባላል። የሚታዩ እና የሚዳሰሱት በተጨባጭ ምናልባት ሦስት ወይንም አራት ቢሆኑ ነው። ከሁሉም አስገራሚ የሚያደርገው እነዚህ እስከ 80 የሚደርሱት 99% የገዥው ፓርቲን አደረጃጀት (የዘር) እና የፖለቲካ አቋም የሚጋሩ ናቸው።
የፖለቲካ አቋሞች እና አታላይ የፖለቲካ አስተሳሰቦች ጎልተው ከሚታዩ ለገሐዱ አለም ውስጥ የ “ኢዜማ እና አብን” ተቃዋሚ ፓርቲ ነን ብለው መደራጀት አስገራሚ ናቸው። ልጥቀስ ብርሐኑ ነጋ እና የመሰረተው ፓርቲ ሙሉውን የዘር ፖለቲካ አመራርን በተለይ በኦሮሞ ብልጽግና የሚካሄደውን የፖለቲካ አቋም ሙሉ በሙሉ ይደግፋል ይስማማበታል እናም ጥያቄየ እንዲህ ይቀመጣል።
ኢዜማ በአብይ አህመድ የሚመራውን የዘር ፖለቲካ እና ፍጅቱን ሙሉ ለሙሉ ከደገፈ ለምን የኦሮሞ ብልጽግና ወይንም የሌላ “ብልጽግና” ሆኖ አይቀላቀልም?
ተመሳሳይ ጥያቄ በአዕምሮየ ይመላለሳል፦ በዶ/ር በለጠ ሞላ የሚመራው አብን ከበአዴን የተለየ አቋም አይታይበትም። ይህ ድርጅት ሰፊ በነበረበት ጊዜ ማለትም በዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ አመራር ስር በነበረበት ግዜ በእርግጥም ጸረ በአዴን አቋም በህወሓት/ኢሕአዴግ ህገመንግስት የማያምን እና የዚህን ሕገመንግስት ጸረ አማራ እና ጸረ ኢትዮጵያ መሆኑን በማመን ኢንዲወገድ ይታገል የነበረ ድርጅት ነበር። ዛሬ ግን ለኢትዮጵያ ችግር እና የመፍረስ አደጋ ላይ መንጠልጠል ያለማቋረጥ ላለፉት 7 አመታት በአማራ ሕዝብ ላይ እየተካሄደ ያለውን የዘር ፍጅት (Genocide) worst of all the ongoing genocidal war against the Amhara people በተግባር ደግፎ የገዥውን በአብይ አሕመድ የሚመራውን የኦሮሞ ብልጽግና ሙሉ ለሙሉ በመደገፍ የጸረ አማራ ፕሮፖጋንዳ አካል እና አፍ በመሆን የሚሰራ ድርጅት በመሆኑ – እንዴት ከበአዴን ተለይቶ “ተፎካካሪ” ነኝ ማለት አስቻለው?
በኢትዮጵያ ፖለቲካ ማደናቆር እና ማስመሰል 1960 ዎቹ የጀመረ የፖለቲካ ተውኔንት ነው። በዚያ ዘመን ቀይሽብርን በግንባር ቀደምትነት የመሩት ከደርጉ የተለየን ነን ያሉት እነ መኢሶን፤ ኢጭአት፤ ወዝ ሊግ፤ ማልሬድ — የተባሉ ድርጅቶች ናቸው እነዚያ ድርጅቶች በቅርጽ የተለያየ ስብስብ እና ግለሰቦችን አቅፈዋል በተግባር ግን ደርጎች ነበሩ በኋላ ሲከስሙም ከባሮ ቱምሳ በቀር ደርግ ውስጥ ነው የቀለጡት። እናም አስገራሚው የቀይ ሽብሩ ኮሚሽንን በሊቀመንበርነት ይመራው የነበር የማልሬዱ ዋና ጸሀፊ ነበር። ቀይ ሽብር ይፈፋም!! ብለው መፈክር ያወጡት የመኢሶን አመራሮች ነበሩ ደርጉ እና አባሎቹ ወታደሮች የማያውቁትን ቀይ ሽበር ያስተማሩ እነ ሰናይ ልኬ እና ሐይሌ ፊዳ ነበሩ ተመክሮውን የወሰዱት የሶቪዬቱ መሪ ጆሴፍ እስታሊን ያልተማረ በውርስ የቦልሸቢክን ፓርቲ ከሌኒን የተረከበ ስለነበር በእውቀት እና በተሞክሮ እና በትምህርት የሚበልጡትን እና Genrikh G. Yagoda, Lev Kamenev, Ivan Smirnov, Karl Radek እና Trotisky አይነት ታላላቅ ምሁራንን ቀይ ሽብር በተባለ ፍርድቤት እና ዳኝነት የማያየው አዲስህገወጥ ሽብር ያጠፋቸው!! በጎን ቀይ ሽብርን እያስተማሩ እነ ሰናይ ልኬ ነገደ ጎበዜ እና አንዳርጋቸው አስግድ አስታጥቁን አታስጨርሱን የሚል መፈክርም አንስተው እስከአፍጢማቸው በመታጠቅ!! ዲሞን በዲሞትፈር!! የሚሉ መፈክሮችን አውጥተው የደሐ ልጅን በየመንገዱ አርደውታል። ሰላም ይውረድ የፖለቲካ ልዩነት በሰላም እና እርቅ ይካሄድ ያሉትን የደርጉ መሪ ጄኔራል ተፈሪ በንቲን ጭምር መገደል በመደገፍ እስከዚህ ዘመን የዘለቀውን መገዳደል ባህል እና ቀጣይ እንዲሆን የደገፉ ያበረታቱ ከመንግስት ውጭ ነን ያሉ የፖለቲካ ኃይሎች ነበሩ።
ዛሬም እንደትናንቱ ወይንም በከፋ እና በገለማ መልክ የዘር ፍጅት እያካሄደ ያለውን መንግስት። አንድ ሀይማኖትን ነጥሎ ላለፉት ሰባት አመታት በኦርቶዶክስ ላይ እየተካሄደ ያለውን ጭፍጨፋ ደግፈው የቆሙ እንደትናንቱ ከመንግስት የተለየን ነን የሚሉ የፖለቲካ ድርጅቶች ናቸው። በዚህ ፍጅትን በመደገፍ እና ፍጅቱን መልክ የለሽ በማስመሰሉ የፕሮፖጋንዳ ስራ ሌት ተቀን ላለው መንግስት አፍ እና ጀሮ የሆኑትም አይነተኛ የፖለቲካ ተቀናቃኝ ነን ባዮች ኢዜማውያን እና አብኖች ናቸው። ስም እና ቁጥራቸው የምይታወቁት ግን የዚህ የፍጅት መንግስት አካላት ተቃዋሚ ነን ባዮች ዛሬም ሆነ ነገ በስም ለመጥቀስ የሚያታክቱ በእውን አለም የሌሉ ተከታዮች ናቸው።
እስኪ የነዚህ ልብ አውልቆችን ገመና እንዲህ ገላልጠን እንየው።
ብልጽግና ተብሎ ስም የተሰጠው የፍጅት መንግስት እና ድርጅት የተወለደው ከህወሓት ኢሕአዴ ነው!! ይህን ሊክዱ ሲዳክሩ ማየት ሌላው አስቂኝ ተውኔት መሆኑ እውነት ነው። ብልግና የህወሓት ልጅ ለመሆኑ የህወሓትን አወቃቀር (የዘር ክልል፤ የዘር የፖለቲካ አደረጃጀት የመንግስትን ስልጣን የተቆጣጠረው ጸረ አማራ ጸረ ሚኒሊክ ጸረ ሰንደቃላማ መሆኑ)
የኤርትራ መገንጠልን እንደ ነጻነት ቆጥረው የደገፉ። ኤርትራ ኢትዮጵያ ናት ያሉትን ተስፋፊወች እና አሀዳውያን እና ትምክህተኞች ያሉ የህወሓት ጸረ ኢትዮጵያ መርህ ሙሉ ለሙሉ የደገፉ በዚያም አብረው የታገሉ የገደሉ ያሰሩ። በስለላው መዋቅር ሁነኛ ቦታ የነበራቸው ከጠቅላይ ሚኒስቴሩ ጀምሮ ስልጣን የተጋሩ ህወሓት ሰራሹን ስርአት እና ህወሓት/ኦነግ የጻፉትን ህገመንግስት የተቃወሙትን ያሰሩ ያሳሰሩ የገደሉ እና ያስገደሉ ናቸው።
በገሐዱ አለም በስልጣን ላይ ያለው መንግስት ኢሕአዴግ (2ኛ) መሆኑን ከላይ ያሰፈርሁት ህገመንግስት እና ዋና የመርሐ መንግስቱ አላማውችን በማሳየት ኢሕአዴግ ስም ለውጦ እና የበለጠ ከፍቶ መወለዱን እንጅ የተሻለ ወይንም የተለየ ሆኖ አለመገኘቱ ብዙ መጓዝ ሳያስፈልግ ሕገመንግስቱን መፈተሽ በቂ ነው። የሁለቱ ቀጣይ ጦርነት እና አለመግባባት የእኔ ልግዛ እንጅ የመርህ ልዩነት አለመኖሩን የጌታቸው እረዳ እና ጻድቃን ገ/ተንሳይ ወደስልጣን መመለስ እና በሰላም የወልቃይት እና የራያን ይመለስልን ጥያቄ ማስቀጠል አይነታ መለያ ነው።
ለማጠቃለል ስልቻ ቀልቀሎ/ቀልቀሎ ስልቻ ቢባል የቃል ካልሆነ የትርጉም ልዩነት የለውም!! በዚህ አባባል ምሥል ኢዜማም፤ አብንም፤ ብልጽግናም የስም ካልሆነ የመርህ እና የይዘት ልዩነት የላቸው። ምናልባት የሚለዩት መሳርያ አስቅዞ ትእዛዝ እየሰጠ ከሚያስፈጀው መንግስት እነሱ የሚያዝዙት ወታደር እና ጋሻጃግሬ ስለሌላቸው ብቻ ነው!!
