ዕጩነት ራስን ስለማግለል የተሰጠ ይፋዊ መግለጫ
ሀገራችን ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በታሪኳ አይታው በማታውቀው እጅግ አስከፊ የፀጥታ ቀውስ እና ደም አፋሳሽ ግጭት ውስጥ ትገኛለች። የዜጎች ህይወት እንደ ቅጠል በሚረግፍበት፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ከቀያቸው ተፈናቅለው በረሃብና በበሽታ በሚማቅቁበት፣ እንዲሁም ሀገራዊ ሉአላዊነታችንና አንድነታችን አደጋ ላይ በወደቀበት በዚህ አስቸጋሪ ወቅት በምርጫ ስም የሚደረገው ሂደት የህዝቡን ስቃይ የሚያረዝም እንጂ መፍትሄ የሚሰጥ አይደለም።
በመሆኑም፣ የሚከተሉትን መሰረታዊ ምክንያቶች በመጥቀስ «በትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት» ስም በአራዳ ክፍለ ከተማ ምርጫ ክልል 1/9 ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያቀረብኩትን ዕጩነት በማንሳት፣ ከዚህ የምርጫ ሂደት ራሴን በይፋ ማግለሌን አሳውቃለሁ።
1. የሰው ልጅ ህይወት ክብር እና የሞራል ጥያቄ
በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የሚካሄደው ደም አፋሳሽ ጦርነት ሳይቆም ምርጫ ማካሄድ ከፍተኛ የሞራል ዝቅጠት ነው። ላለፉት ስምንት አመታት በአማራ፣ በትግራይ፣ በኦሮሚያ፣ በቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ በጋምቤላ እና በሌሎችም አካባቢዎች ንጹሃን ዜጎች በማንነታቸውና በፖለቲካ አመለካከታቸው ምክንያት እየተገደሉና እየታሰሩ፣ በገዛ ሀገራቸው ዋስትና ባጡበት ሁኔታ «ምረጡኝ» ማለት የህዝብን ህመም መሳለቂያ ማድረግ ነው። በእንዲህ ያለ የለቅሶ ድንኳን ውስጥ የሚደረግ ምርጫ የህዝብን ድምፅ ሳይሆን የጥይት ድምፅን የሚያስተጋባ በመሆኑ ራሴን አግልያለሁ።
2. ለአምባገነንነት ህጋዊ ሽፋን የመስጠት አደጋ
የአሁኑ የምርጫ ሂደት ዲሞክራሲን ለመገንባት ሳይሆን፣ አምባገነንነትን በህዝብ ስም ለማስረጽና ህጋዊ ሽፋን ለመስጠት የሚደረግ ስህተት ነው። በጦርነትና በከፍተኛ ማህበራዊ ትርምስ ውስጥ የሚደረግ ምርጫ ነፃ፣ ፍትሃዊና ተዓማኒ ሊሆን አይችልም። በዚህ ሂደት ውስጥ መሳተፍ ማለት ገዳዮች ለቀጣይ ጥፋታቸው ህጋዊ እውቅና እንዲያገኙ መተባበር በመሆኑ፣ የታሪክ ተጠያቂነትን በመፍራት ይህንን ውሳኔ አስተላልፌያለሁ።
3. በአማራ ህዝብ ላይ የተደገሰው የጥፋት ድግስ
በአማራ ክልል በተለያዩ ዞኖች—በተለይም በጎጃም፣ በጎንደር እና በወሎ—በመንግስት የጥቃት ኃይሎች አማካኝነት ቁጥራቸው ከፍተኛ የሆኑ ንጹሃን ዜጎች ህይወታቸውን አጥተዋል። በመኖሪያ መንደሮች፣ በገበያ ቦታዎች እና በሃይማኖት ተቋማት ላይ የሚፈጸሙ የከባድ መሳሪያ ድብደባዎችና የድሮን ጥቃቶች የብዙዎችን ህይወት ቀጥፈዋል፣ እየቀጠፉም ይገኛሉ። አማራ እንደ ህዝብ የተደገሰለትን የሞት ድግስ ባልቀረበት እና በየቀኑ እያነባች ያለችው ንፁህ የአማራ እናት ባለችበት፣የዜጎችን ደህንነት ባላስከበረ አገዛዝ ስር በሚደረግ ምርጫ መሳተፍ፣ በቀጣይ በህዝቡ ላይ የታቀዱና የሚፈጸሙ ጥፋቶች እውቅና መስጠት በመሆኑ ሂደቱን እቃወማለሁ። በመቃወም ብቻ አላበቃም በህዝቡ/ህዝቤ ላይ እየደረሰ ያለ ታሪካዊ በደል በዳዮችን ህጋዊ ለማድረግ በሚደረገው ምርጫ ላይ ተመራጭ ሆኜ ራሴን ላለማቅረብ ከምርጫ ዕጩነቴን በይፋ ራሴን አግልያለሁ።
4. የትግራይ ክልል መገለልና ሀገራዊ አካታችነት ማጣት
የትግራይ ክልልን ከአስከፊው እልቂት በኋላም ቢሆን ለሁለት ተከታታይ የምርጫ ዘመናት (terms) ያገለለ ምርጫ፣ ሀገራዊ ተቀባይነት ሊኖረው አይችልም። የሀገሪቱ አንዱ ወሳኝ አካልና ህዝብ ሳይሳተፍበት የሚደረግ ምርጫ ኢትዮጵያን ሙሉ አያደርጋትም። ይህ አካሄድ ሀገራዊ መግባባትን ከመፍጠር ይልቅ ልዩነትን የሚያሰፋና የሀገሪቱን የወደፊት ህልውና አደጋ ላይ የሚጥል በመሆኑ፣ እንዲሁም አዲስ የጦርነት አዝማሚያዎችና እንዲሁም ያለፈውን አስከፊ ጦርነቱ የወለዳቸው ከአእምሮ በላይ የሆኑ ጠባሳዎች ሳይሽሩና ህዝቡን ከተፈናቃይ ካምፕ ሳይወጣ እንዲሁም ከጦርነት ስጋት ነፃ ሳይሆን ክልሉና የክልሉ ህዝብ በማራቅ የሚደረግ ምርጫ ለመኮነንና ለህዝቡን ክብርና ሞራል ስል ራሴን ከምርጫው ገለል በማድረግ ቀጣይ የሚኖረው የአገዛዙ የጥፋት መንገድ አካል ላለመሆን ወስኛለሁ።
5, ሰባት አመታት የተሻገረው የኦሮምያ ክልል ጦርነት
በኦሮሚያ ክልል ከ2011ዓ/ም ጀምሮ የተቀሰቀሰው እና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የመጣው የጦርነት፣ የፀጥታ እና የደህንነት ችግር እስካሁን ድረስ ዘላቂ የፖለቲካ መፍትሄ አላገኘም። የኦሮሞ ህዝብ በ8ቱ አመት የብልፅግና አገዛዝ የደረሠበት ሞት ፣መፈናቀል በታሪኩ አይቶት የማይውቅ ነው ብል ማጋነን አይሆንም። በዚህም አያሌ ንፁሃን የድሮን ሰላባ ሆነዋል እየሆኑም ይገኛሉ። ዜጎች ወጥተው መግባት በናፈቁበት እና መሰረታዊ የደህንነት ዋስትና ባጡበት በዚህ አስከፊ ሁኔታ ውስጥ፣ በምርጫ ስም ቀውሱን ማራዘም ፍጹም ተቀባይነት የለውም። በመሆኑም በዚህ ሂደት ውስጥ መሳተፍም ሆነ መቀጠል ከፍተኛ የሞራል ተጠያቂነት የሚያስከትል ታሪካዊ ስህተት በመሆኑ ራሴን አግልያለሁ።
6. የፖለቲካ ልሂቃን መታሰር እና መሰደድ
በአሁኑ ሰዓት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ የተሻለ አማራጭ ሀሳብ የሚያመነጩ ግለሰቦች፣ የምክርቤት አባላት፣ጋዜጠኞች በፖለቲካዊ አመለካከታቸውና በማንነታቸው ምክንያት “ህግ በማስከበር” ስም በእስር ቤቶች እንዲታጎሩ ተደርገዋል። አንዳንዶቹ አገር ጥለው እንዲሰደዱ፣ ለህክምና ወደ ውጭ የወጡትን ደግሞ ያለአግባብ ወደ አገራቸው እንዳይመለሱ ተከልክለው በስደት ህይወት እንዲማቅቁ ተገደዋል። እንዲህ ባለው ጨቋኝ ድባብ ውስጥ የሚደረግ ምርጫ፣ እነዚህ የዲሞክራሲ፣ የፍትህ እና የእኩልነት ታጋዮች የከፈሉትን ታላቅ መስዋዕትነትና ያደረጉትን ትግል ማዋረድ እና ማሳነስ በመሆኑ በሂደቱ መሳተፍን በጽኑ እቃወማለሁ።
7) ለገዳዮች እውቅና አለመስጠት
ንጹሃን እየተቀጠፉ ባሉበት ሁኔታ ውስጥ በምርጫ መሳተፍ ማለት፣ ነገ ለሚፈሰው ደም ተባባሪ መሆን ነው። በህዝብ ስቃይና እልቂት ላይ ስልጣን ለመያዝ መሞከር የፖለቲካ ነውር ነው። በመሆኑም የገዳዮችን ዕድሜ ለማራዘም የሚደረገውን ማንኛውንም የፖለቲካ ድራማ አልቀበልም።
¤ የመጨረሻ ጥሪ
ሀገራችን ኢትዮጵያ አሁን የሚያስፈልጋት ምርጫ ሳይሆን ሰላም ነው! የሚያስፈልጋት የፖለቲካ ሽኩቻ ሳይሆን እውነተኛ ሀገራዊ ውይይትና እርቅ ነው። የሰው ልጅ ህይወት ባልተከበረበት ሁኔታ የሚካሄድ ምርጫ የዲሞክራሲ ማሳያ ሊሆን አይችልም።
ስለሆነም፣ ከዚህ በኋላ በሚኖሩ የምርጫ ሂደቶች ውስጥ እንደ ዕጩም ሆነ እንደ ተሳታፊ የማልገኝ መሆኑን እያሳወቅኩ፤ እውነተኛ ለውጥ ፈላጊው የሀገራችን ምሁርና መላው የኢትዮጵያ ህዝብ የምርጫ ካርዱን ባለመጠቀም ለዚህ የይስሙላ ሂደት ያለውን ተቃውሞ እንዲያሳይ ጥሪዬን አቀርባለሁ።
አለም አቀፉ ማህበረሰብም የሀገሪቱን ተጨባጭ ሁኔታ በመገንዘብ፣ ይህ የደም ምርጫ እንጂ ዲሞክራሲን የማያራምድ መሆኑን ተረድቶ፣ በየቀኑ በጦርነት፣ በኑሮ ውድነትና በስደት እየማቀቁ ካሉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ንጹሃን ኢትዮጵያውያን ጎን እንዲቆም እጠይቃለሁ።
ፍትህ ለተገደሉና በየቀኑ እየተገደሉ ላሉ ንጹሃን! ሰላም ለሀገራችን!
ይስሃቅ ወልደይ ሓጎስ
የኢሕአፓ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ እና የትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት (ለኢትዮጵያ) የምክር ቤት አባል

