Site icon Dinknesh Ethiopia

የኢትዮጽያ ምርጫና የፖለቲካ ፓርቲዎች ህግ

Aklilu Wondaferew

የፖለቲካ ፓርቲዎችን የመመዝገቢያ ቁጥር ከነበረውስድስት እጥፍ  ከፍ ማድረግ  እንደምታው ምን ይሆን? ወቅቱንስ የጠበቀ ነውን?

ከአክሊሉ ወንድአፈረው ( ethioandenet@bell.net )

ጁላይ 26፣ 2019

መግቢያ

ምርጫ ቦርድና መንግስት  ማክስኞ ሃምሌ 16፣ 2011 የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባን በተመለከተ አዲስ ህግ አርቅቀው በፓርላማው የህግ ቋሚ ኮሚቴ በኩል ለውይይት በሚል አቅርበዋል። ፓርላማው  ይህንኑ ረቂው  ብዙም ሳይለወጥ የሚያጸድቀው  ከሆነ እንደምታው  ምንድን ነው የሚለውን በዚህ አጭር ጽሁፍ ለውይይት መንደርደሪያነት አቀርባለሁ።ረቂቅ ህጉ ብዙ ጉዳዮችን የሸፈነና በበጎ ጎኖች ያሉት  ቢሆንም በዚህ ጽሁፍ የማተኩርበት  ግን ስለፓርቲዎች ምዝገበ በተመለከተ ለምዝገባ ማቅረብ አለባቸው ( አስር  ሽህ የደጋፊዎችን ፊርማ )  በሚለው ላይ ነው። የግለሰብ ተወዳዳሪወችንምበተመለከተ የሰፈረውን በዚሁ መልክ መገምገም ይቻላል።

የመደራጀት መብት የዴሞክራሲ መብት ነው ይህን መብት ማስፋት እንጂ ማጥበብ ጎጂ ነው

ከአምበባገነን ስርዓት ወደ ዴሞክራሲ በሚደረገው ጉዞ የፖለቲካ ፓርቲዎችን አደረጃጀትን ለመወሰን፣ ለእንቀስቃሴያቸውም ህጋዊ እውቅና ለመስጠትም ይሁን ለመገደብ የሚችሉ ይህን መሰል ህጎች ፣ በሀገሪቱ ቀጣይ ፖለቲካ ስርዓት ምስረታና ግንበባታ ውስጥ  ዜጎች ሊኖራቸው የሚችለውን ተሳትፎ ለማበረታታትም ይሁን ለማዳከም እጅግ ከፍተኛ ሚና ይጫወታሉ።

በስልጣን ላይ የሚገኙ መንግስታት የሚደነግጓቸውና ተግባራዊ የሚያደርጓቸው  ህግጋትና ደንቦች ዴሞክራሲያዊ ስርአትን እውን ለማድረግ ሊያግዙም  እንቅፋት ሊሆኑም ይችላሉ።

አንዳንድ ህግጋት መደራጀትንና ህዝብም በፖለቲካ ፓርቲወች ውስጥ የሚኖረውን ተሳትፎ የሚያበረታቱ ሲሆን ሌሎች ደግሞ የተለያየ መሰናክሎችን በመደርደር ህዝብ ከመደራጀትና በፖለቲካውም ንቁ ተሳታፊ ከመሆን ወደኻላ እንዲል አደርጋሉ።

ለምሳሌ የ ኢትዮጵያ ህገ መንግስት መደራጀት መሰታዊ ሰብአዊ መብት እንደሆነ ቢደነግግም የማህበራት ህግ  (Charities and associations) የተባለው ህግ ባሰቀመጠው እንቅፋት የተነሳ ማህበራዊ ድርጅቶች በነጻ እንዳይደራጁ ህዝቡም በነዚህ ድርጅቶች ውስጥ ከመሳተፍ ራሱን እንዲያርቅ  በማድረግ በሀገራችን ነጻ ህዝባዊ ድርጅቶች ድምጥማታቸው እንዲጠፋ ተደርጓል። በፖለቲካ ድርጅቶችም ላይ የተለያየ ተጽእኖ በማሳደር የተቃዋሚ ድርጅቶች አቅመ ቢስ የህዝብ ተሳታፊነትም እጅግ የጎደላቸው የቀጨጩ ድርጅቶች ሆነው እንዲቆዩ መደረጉ ይታወቃል።

አሁን የቀረውን የህግ ረቂቅ ስንመረምርም መጠየቅ የሚገባው አንዱ  ጥያቄ ይህ ህግ ዜጎች በፖለቲካ ድርጅት እንዲሳተፉ ሁኔታወችን ይብልጥ የሚያመቻች ነው ወይንስ በቀጥታም ይሁን በተዛዋሪ እንቅፋት የሚፈጥር  ነው የሚለው ነው።

አንዳንድ ሰዎች  መቶ ሚሊዮን ህዝብ ባለበት ሀገር አስር ሽህ  የደጋፊ ፊርማ አቅርቡ  ማለት ምን ችግር አለው ? ፖለቲካ ድርጅቶች የህዝብ ድጋፍ ካላቸው ለምን ይጨነቃሉ ይላሉ።የምርጫ ቦርዱ አንድ ባለስልጣንም ይህንኑ በቪኦኤ ቃለመጠይቃቸው ሲያሰተጋቡ ተደምጧል።

በኔ አመለካከት ለፓርቲዎች ምዝገባ አስፈላጊ ነው የሚባለውን ቁጥር አሁን በስራ ላይ ካለው 1500 ወደ 10000 (አስር ሽህ)  ከፍ ማድረግ የቁጥሩ ጉዳይ ወይንም የድርጅት ድጋፍ  ማግኘትና ማጣት መመዘኛ ብቻ አይደለም። ሲጀመር ባንድ ወቅት ድጋፍ ያለው ድርጅት በሌላ ጊዜ ድጋፍ ላይኖረው ይችላል። ድርጅቶች በትንሽ ሰዎች ቁጥር ተጀምረው ወደ ታላቅ ሀይልነት እንደሚያድጉ የታወቀ ነው። በአንድ ወቅት ድጋፍ አላቸው የሚባሉ ገናና ድርጅቶች በሌላ ወቅት ባዷቸውን ሊቀሩ ይችላሉ። ይህ ብዙሀዊነት ባለው የፖለቲካ ስርአት  ውስጥ እውነታ ነው።

የመደራጀት መብት የዴሞክራሲ መብት ነው። በፖለቲካ ፓርቲ የመደራጀት መብት ደግሞ ከፍተኛው የፖለቲካ መብት መገለጫ ሲሆን  ምዝገባውን በተመለከተ የሚያስፈልገው ቁጥር ከፍ ወይም ዝቅ ማለቱ ከምህዳሩ መስፋትና መጥበብ ጋር በቀጥታ የሚያያዝ ነው። ለመመዝገብ ከሚፈልጉት ፓርቲዎች አመቺ ሁኔታ መኖር አለመኖር ጋር ብቻ ሳይሆን የህዝብንም አማራጭ ከማስፋትና ከማጥበብ ጋር በቀጥታ የሚያያዝ ጉዳይ ነው።

አሁን  የተረቀቀው “ማሻሻያ“ አዳዲስ ድርጅቶች በያዙት ሃሳብ ዙርያ ከትንሽ የአባላትና  ደጋፊወች  ቁጥር  ተነስተው እንዲያድጉ የሚያበረታታ ምህዳር  የሚፈጥር ሳይሆን ገና ከጅምሩ እጅግ ከፍተኛ የሆነ ተግዳሮት ከፊታቸው እንዲደቀን ያደርጋል። እንደ ረቂቅ ህጉ ከሆነ አንድ ድርጅት አስር ሽህ አባላት  ወይም ደጋፊወችን እስኪያፈራ ድረስ በህጋዊነት ስለማይታወቅ (ስለማይመዘገብ)  ህጋዊ የፖለቲካ ድርጅቶች የሚኖራቸው  የህግ ከለላና መብት አይኖረውም ።ለምሳሌ በማንኛውም ደረጃ በፖለቲካ ውድድር ውስጥ አይሳተፍም። በዚህ ወሳኝ የሽግግር ወቅትም በሀገሪቱ መሰረታዊ ጉዳዮች ላይ ይህ ነው የሚባል ተሳትፎ ሊያደርግ አይችልም። ተሳትፎው ሁሉ በ መንግስት ችሮታ እንጂ እንደመብት የሚጎጎናጸፈው አይሆንም።

ባንጻሩ አሁን ጎላ ብለው የሚታዩና  እስካሁን በነበረው ሁኔታ  የተመዘገቡ ድርጅቶች ብቻ  የፖለቲካ መድረኩ ዋና ተዋናይ ሆነው እንዲቀጥሉና መድረኩንም እንዲቆጣጠሩ ስለሚያግዝ ያለውን ሁኔታ (ስታተስኮ status quo)  የሚያስቀጥል እንጂ አዳዲስ ሀሳብ ያላቸው ሀይሎችን በፖለቲካ ሜዳው ውስጥ ገብተው አማራጫቸውን ለህዝብ እንዲያቀርቡ  የተሻለ ሁኔታን የሚፈጠርና የሚያበረታታ  አይደለም።

በዚህ ሂደት የሚፈጠረው የፖለቲካ ምህዳርም  የተወሰነ የፖለቲካ አስተሳስብ ዙሪያ እየተሽከረከረ  እንዲቀጥል ይህ አስተሳሰብም ጎልቶ እንዲወጣም ያግዛል። ይህ ደግሞ  በህጋዊ መድረኩ  ለህዝብ   የሚቀርቡ የፖለቲካ አማራጮች ውሱን እንዲሆኑ (እንዲጠቡ)  በማድረግ  ምህዳሩ ለ” አውራ ፓርቲና መሪ አመለካከት” ስር መስደድ የተመቻቸ እንዲሆን ያደርጋል።

ለህጋዊነት ለመመዝገብ የሚያሰፈልገውን ቁጥር ዝቅ ማድረግ ደግሞ አዳዲስ ሀሳቦች በየጊዜው  እንዲፈልቁ፣ ዜጎች ወደ ፖለቲካ መድረኩም እንዲገቡ ሁኔታወችን ያመቻቻል። የተወሰነ ሀሳብ የበላይነትን ይቀንሳል። ፖለቲካ ፓርቲወችም ሁል ጊዜ አዳዲስ ተወዳዳሪ ሀሳብ ስለሚሞግታቸው ለህዝብ ፍላጎት ተገዥነታቸውንና  የፈጠራ ችሎታቸውን  እጅግ ያጠናክራል።

ከዚህ በታች የሚገኘው መረጃ እንደሚያሳየው በዴሞክራሲ የገፉም ሆኑ በዴሞክራሲያዊ ሽግግር ውስጥ የሚገኙ አብዛኛወቹ ሀገሮች ፖለቲካ ድረጅቶች በህጋዊነት ለመመዝገበብና ለመንቀሳቀስ የሚያስቀምጡት የ አባላት ወይም  የደጋፊወች ቁጥር አሁን ሀገራችን ውስጥ የተረቀቀው ህግ ከሚጠየቀው ( 10 ሽህ ) እጅግ ያነሰ መሆኑን ነው።

ሀገር ዝቅተኛ ቅጥር  ሀገር ዝቅተኛ ቁጥር ሀገር ዝቅተኛ ቁጥር
ህንድ 100 ላትቪያ 1000 ታንዛንያ 500
ፊሊፒንስ 5 ፖላንድ 1000 ፈረንሳይና እንግሊዝ ዝቅተኛ ቁጥር የለም
ናፓል 0 ስዊድን 1500 ካናዳ 250
ካምቦዲያ 4000 ፊንላንድ 5000 ርዋንዳ ለፕሬዚደንትነት 600
በጋና 210 በናሚቢያ 3500 በዩጋንዳ 6500
ቼክ ሪፐብሊክ 1000 ስሎቫንያ 500 ደቡብ አፍሪካ 500
ቤልጅየም 3050 ናይጀሪያ 500 ሱዳን 500
ኤስቶንያ 1000 ላይበሪያ 500 ዛምቢያ 1000

ከላይ ከተጠቀሱት ሌላ ፓርቲወችን ህጋዊነት ለመስጠት እጅግ የተጋነነ ያባላት ቁጥር  የሚጠይቁ አንድ ሁለት ሀገሮች አሉ ከነርሱም ውስት አንዷ ኬንያ ነች። ኬንያ ቁጥሩን የጨመረችው በብሄር በሪጅንና በሀይማኖት መደራጀትን ሙሉ በሙሉ አግዳ እንጂ የብሄር ፍጥጫ እና ግጭትን የሚጋብዝ ህገመንግስታዊ ድባብ ውስጥ ሆና አይደለም።

የፖለቲካ ድርጅቶች መብዛት ለዴሞክራሲ እንቅፋት አይደለም

የፖለቲካ ድርጅቶች ህጋዊነት ለማግኘት የ 10 ሽህ ሰው ድጋፍ መማቅረብ ይገባቸዋል የሚለው ሀሳብ አስፈላጊነት በሚገልጹ ክፍሎች በኩል የሚቀርበው አንዱ  ሀሳብ  በሀገራችን ውስጥ የፖለቲካ ድርጅቶች ቁጥር በዝቷል ። ይህም ለዴሞክራሲያዊ ሂደት እንቅፋት ነው ። ስለዚህም እንዲቀነሱ ማድረግ ያሰፈልጋል ከሚለው አስተሳሰብ ጋር የተያያዘ ነው።

ይህ ግን ከእውነታ ጋር የሚጋጭ ነው፡

ለምሳሌ ህንድ በአለም ትልቅ የህዝብ ቁጥር ያላት ሀገር  ስትሆን  በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚንቀሳቀሱ ከ ሁለት ሽህ በላይ ፖለቲካ ፓርቲወችም ይገኙባታል።ይህ የህንድን ዴሞክራሲ አጠናከረው እንጂ አላቀጨጨውም፡፡ በአፍሪካ የተሳካላት ዴሞክራሲያዊ ስርአት በመገንባት ተሳካላት የምትባለው ቤኒን እስከ አለፈው አመት (2018) ድረስ በህጋዊነት የሚንቀሳቀሱ ሁለት መቶ ያክል ፖለቲካ ፓርቲወች ነበሯት በዚህ ጊዜ ውስጥ በቤኒን ውስጥ ዴሞክራሲ ስር ሰደደ እንጂ አልተደናቀፈም፡

ባንጻሩ  በራሽያና መሰል ሀገራት የሚታየው ደግሞ እጅግ ዝቅተኛ ቁጥር ያላቸው የፖለቲካ ድርጅቶች ብቻ ህጋዊ ሆነው ሲንቀሳቀሱ ነው። በነዚህ ሀገሮች ውስጥ ደግሞ ዴሞክራሲ ተፍኖ ያንድ ድርጅት እና ግለሰብ የበላይነት እንደሰፈነ ነው።

ይህ እውነታ የድርጅቶች መብዛት ለዴሞክራሲ እንቅፋት አለመሆኑንና ችግሩ የሚመነጨው ከሌሎች የመንግስታት ፖሊሲና ተግባር እንደሆነ ነው።

በሀገራችን ሁኔታ ድርጅቶችን ቁጥር መቀነስ ያሰፈልጋል ቢባል እንኳ አዳዲስ ድርጅቶችን ለመመዝገብ 10 ሽህ ድጋፍ አምጣ ከሚለው አላስፈላጊ እርምጃ  ውጪ ቅነሳውን እውን ለማድረግ በሚያሰችሉ እርምጃወችን ሊወስድ ይቻላል። ለምሳሌ  በሀገራችን ካሉት “የተመዘገቡ ድርጅቶች” ውስጥ ብዙዎቹ ቀደም ሲል ኢህአዴግ አጅበውት እንዲጓዙ የፈለፈላቸው ስለሆኑ  እነርሱን ማስወገድ ከፈለገ ኢህአዴግ አሁንም በአንድ ቀን ሊያደርገው የሚችለው ቀላል ተግባር ነው።

ሁለተኛው በሀገራችን የፓርቲወች ቁጥር እጅግ የበዛው ህገመንግስቱ ከደነገገው የብሄር አደረጃጃት ጋር ተያይዞ እንደሆነ የሚታወቅ ነው። ለዚህ ደግሞ መፍትሄው በህብረ ብሄራዊ ድርጅቶች ላይ ተጽእኖ ማድረግ ሳይሆን ለየት ያለ  ቆራጥና ሁሉንም የሚያግባባ ዘመን ተሻጋሪ ባለራእይ እርምጃ በመውሰድ ነው። ይህም ቢሆን ሰፊ ውይይትና መግባባትን ይጠይቃል፡

ነጻ  የህዝብ ድምጽ የድርጅቶችን ቁጥር  እንዲበዛም እንዲቀንስም ያደርጋል።

ህዝብ የፈለገውን የመደገፍ የማይደግፈውን ደግሞ ያለመደገፍ መብቱን ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ እንዲያደርግ የሚያመቻች ሁኔታ ተግባራዊ ከተደረገ  ቀስ በቀስ የህዝብ  ድጋፍ ያላቸው  ፓርቲወች እንዲያድጉ የሌላቸው ደግሞ እንዲከስሙ ወይም  ከሌሎች ጋር እንዲዋሀዱ ሁኔታው ያሰገድዳቸዋል።። በዚህ መሰረትም የህዝብ ድምጽ የድርጅቶችን ቁጥር  እንዲበዛም እንዲቀንስም ያደርጋል።

ይህ አይነቱ አሰራር የድርጅቶችን ቁጥር ለመወሰን ከሚኖረው ታላቅ ሀይል በተጨማሪ ፖለቲካ ፓርቲወች  ለህዝብ ድምጽ ትልቅ ግምት እንዲሰጡና   ህዝብም  በፖለቲካው ውስጥ በንቃት ሲሳተፍ ከፍተኛ ተጽእኖ ፈጣሪነቱን  የሚያረጋግጥበት ሁኔታን (EMPOWERING ) ይፈጥራል ። ጠያቂና ንቁ ተሳትፎ የሚያሳይ ዜጋ ደግሞ ለዴሞክራሲያዊ ስርአት እውን መሆን  ጠንካራው መሰረት ነው። የዴሞክራሲያዊ ሽግግርን እውን ለማድረግ የዚህ አይነት የህዝብ ተሳትፎን ማእከል ያደረገ አካሄድ  አይነተኛ መሳሪያ ነው።

በተጽእኖ አማራጭን ማጥበብ የፖለቲካ ተሳትፎን ይቀንሳል የህዝብንም ብሶት ይጨምራል

የህዝብን የፖለቲካ አማራጭ  በፖለቲካ ውሳኔና አርቲፊሻል በሆነ መልክ አጥብቦ መጓዝ  የህዝብን  የፖለቲካ ተሳትፎ ያዳክማል እንጂ አያጠነክረውም። ህዝብንም እያደር ቅር ያሰኛል እንጂ አያስደስተውም። ይህ ደግሞ ጤነኛ የፖለቲካ ስርአትን ለመገንባት አይረዳም።

ለዚህ በምሳሌነት ሊጠቀሱ ከሚችሉት የተለያዩ ሀገሮች ውስጥ ደረም ብየ ያጠቀስኳት ምእራብ  አፍሪካዊቷ ሀገር ቤኒን አንዷ ነች። ቤኒን በአውሮፓውያን አቆጣጠር በ1989 በተካሄደ ብሄራዊ የመግባባት ጉባኤ ከ 1972 ጀምሮ በሀገሪቱ ያንሰራፋውን አምባገነን አገዛዝ አስወግዳ  ወደ ዴሞክራሲያዊ ስርአት ተሸጋግራ በተከታታይ ሰፊ የዴሞክራሲ ግንባታን በማካሄድ ታላቅ አድናቆትን አትርፋ ህዝብም በዚሁ ረክቶ ቆይታለች።

በዚህ ጊዜ ውስጥ የፖለቲካ ፓርቲዎች ቁጥር ከ70 ወደ 200 አድጓል።  ይህን  እንደ ጤናማ ጉዞ ያልተመለከተቱትከሁለት አመት በፊት (እንደ አውሮፓ አቆጣጠር በ2016)  ወደስልጣን የመጡት አዲሱ የቤኒን ፕሬዚደንት ፓትሪስ ታሎን (Patrice Talon) በሚመሩት ሀገር የሚንቀሳቀሰው የምርጫ ኮሚሽን ፓርቲዎችን ለመቀነስ አዲስ እቅድ አወጣ።

ፖለቲካ ፓርቲዎችን በዛ ያለ የደጋፊ ፊርማ አምጥታችሁ እንደገና ተመዝገቡ ማለት እንደመያዋጣ የተረዳው ኮሚሽን አዲስ ዘዴ ቀየሰ። ለምርጫ ውድድር ሁሉም ድርጅቶች እያንዳንዳቸው  428000( አራት መቶ ሀያ ስምንት ሽህ  ዶላር) ማስያዝ ይኖርባቸዋል የሚል ህግ አርቅቆ  ፕሬዚደንት ፓትሪስ ታሎን ፓርቲ ብዙሀኑን መቀመጫ የተቆጣጠረው ፓርላም እንዲጸድቅ  ተደረገ።

ኮሚሽኑና መንግስት ይህን ሁኔታ እንዲያሰቆም ብዙዎች ቢማጸኑም “ የህዝብ ድጋፍ ካላችሁ ይህን ገንዘብ ማሰባሰብ እንዴት ይከብዳል “ በማለት ፕሬዚደንቱ በእቅዳቸው ቀጠሉበት።የገንዘብ ክፍያ ሊያሟሉ ያልቻሉ ተቃዋሚዎች በምርጫ ኮሚሽኑ ትእዛዝ ከጨዋታ ውጭ ሆኑ። ከፖለቲካ ውድድር ታገዱ።

ይህ ሆኖ በአውሮፓ አቆጣጠር በማርች 2019 (ዘንድሮ) በተካሄደው ምርጫ የፕሬዚደንቱ ፓርቲና አንድ ሁለት የርሳቸው ወዳጅ የሆኑ ፓርቲዎች የፓርላማውን ወንበር ሁሉ ጠቅልለው “ አሸነፉ” ተባለ።

እጅግ የሚገርመው ግን በዚህ ምርጫ ድምጽ የሰጠው ህዝብ  23% ብቻ መሆኑ ነው። ቀደም ባሉት ምርጫዎች  ድምጹን ለመስጠት የሚወጣው ህዝብ ቁጥር ከ75% ያላነሰ ነበር። ከቀረቡት ምርጫወች መጥበብ ጋር ተያይዞ ህዝብ ከፖለቲካ ሂደቱ ራሱን አገለለ። የቤኒን ዴሞክራሲ ወደኋላ መጓዝ ጀመረ። ከ1989 ወዲህ ያልታየ የጋዜጠኞች መታሰር፣ ፣ የተቃዋሚዎች መታሰር፣ የኢንተርኔት መዘጋት ወዘተ ተጀመረ። ከዚህ ጋርም ተያይዞ ህዝብ ለመጀመሪያ ጊዜ የመረረ የተቃውሞ ሰልፍ በማድረግ  መንግስቱንም  በአደባባበይ  ማውገዝ ጀመረ። በመንግስትና በህዝብ መሃል ቅራኔ መስፋት ፣ጀመረ።

በመላ አለም ስትሞገስ የነበረችው ቤኒን በአምንስቲ ኢንተርናሽናል፣ በአፍሪካ አንድንት ታዛቢዎች፣ በአሜሪካ አምባሳደር  ወዘተ  የቤኒን ጉዞ ዴሞክራሲን ቀልባሽ እንደሆነ ተገለጠ። እነ ዋሽንግተን ፖስት ሳይቀሩ “ ቤኒን ምን ነካት” እያሉ አዲሱን መንግስት ማብጠልጠል ጀመሩ። ባጠቃላይ ፓርቲወችም ዴሞክራሲም  ተቀነሱ።

የህጋዊ የድርጅቶች መብዛት መንግስትን ወጪ ያስወጣልን?

ሌላው የፖለቲካ ድርጅቶች እውቅና ለማግኘት 10 ሽህ ሰው  ድጋፍ ማቅረብ አለባቸው ከሚለው ጉዳይ  ጋር ተያይዞ የሚጠቀሰው የፖለቲካ ድርጅቶች መብዛት መንግስትን ብዙ ገንዘብ  ያሰወጣዋል የሚለው ትርክት ነው።

ይህ ሲጀመር በመረጃ  የተደገፈ አይደለም። በሀገራችን ውስጥ መንግስት የገንዘብ ድጋፍ የሚሰጠው  ለሁሉም የተመዘገቡ ድርጅቶች አይደለም። የተመዘገበ ድርጅት ሁሉ በሀገራችን ውስጥ የመንግስት በጀት ድጋፍ አይሰጠውም።

ይህንን መቆጣጠር ከተፈለገም  ደግሞ የፖለቲካ ድርጅቶችን የገንዘብ ድጋፍ  የሚመለከት  ግልጽነትና ተጠያቂነት እንዲኖር  ማድረግ   ይህንንም ምላሽ የሚሰጥ ለየት ያለ ደንብ ማውጣትና  ተግባራዊ ማድረግ   እንጂ   የፖለቲካ ምህዳሩን ማጣበብ ፣ አማራጭንም መቀነስና የዜጎችን ምርጫ መገደብ አግባብ አይሆንም።

በነገራችን ላይ  ዶክተር አብይ ደጋግመው ግልጽ እንዳደረጉት ባለፉት 27 አመታት በሀገራችን የተመዘገበው አሳፋሪ ንቅዘትና የሀገር ሀብት መባከን የተከሰተው ኢህአዴግ ለብቻለው በተቆጣጠረው የፖለቲካ መድረክ እንደነበር ማስታወስም ተገቢ ነው።

ይህ የህግ ረቂቅ ጊዜውን የጠበቀ ነውን?

ከዚህ ሁሉ በተጨማሪ  ሌየሚነሳው ሌላው ጥያቄ ለመሆኑ ይህ የህግ ረቂቅ ጊዜውን የጠበቀ ነውን የሚለው ነው። አሁን ባለው  ያልተረጋጋ የሀገራችን ሁኔታ እጅግ ብዙ ተግዳሮቶች ይታያሉ ።

አለመታደል ሆኖ በሀገራችን  ድር ላይ ከሰፈነው የፖለቲካ ውጥረትና መካረር የተነሳ በተለይም ሀገር አቀፍ ድየፖለቲካ ርጅቶች በሁሉም የሀገሪቱ  ክፍሎች እንደልብ ተንቀሳቅሰው በነጻ ለማደራጀትና አባላትንም ለመመልመል አመች ሁኔታ የለም። ይህ ደግሞ ሀገራዊ ፓርቲወች የት ቦታ ተንቀሳቅሰው በነጻ ህዝብን ማነጋገር ጽህፈት ቤት ከፍተው መስራት ወዘተ ችለዋል የሚለውን በመመለስ በቀላሉ የምንገነዘበው ነው። አንዳንዶቹ ክልሎች እናኳንስ ህብረብሄራዊ ተቃዋሚ ፓርቲ ክልላዊ ተቃዋሚንም የማያስተናግዱ አይደሉም።  እንኳንስ የተለየ የፖለቲካ አስተሳሰብን በነጻ ለማሳወቅ አሁን ያለው ሁኔታ በተለያየ መመዘኛ “ከ እንርሱ”  ለየት ያሉ ሁሉ የሚፈናቀሉበት በፍርሀት ድባብ  ውስጥ የሚገኙት ነው፡

እነዚህ እውነታወች  በሚታይበት ሁኔታ አዲስ የሚመዘገቡ ሀገራዊ  ድርጅቶችን  ከየክልሉ ትልቅ ቁጥር ያለው ድጋፍ ካላመጣችሁ እውቅና አንሰጥም ብሎ መደንገግ ዛሬ  በምድር ላይ ከሚታየው  እውነታ ጋር አይጣጣምም።

ለማጠቃለል

ለማጠቃለል በኔ ግምገማ አሁን የሚደረገው “ማሻሻያ”ብዙ በጎ ጎኖች ቢኖሩትም  እንዳለ ወደ ህግነት ከተቀየረ  የሚያስከትለው ዴሞክራሲን ማጠናከር፣ ሀገርንም ማረጋጋት ሳይሆን የምርጫውም ሆነ የዴሞክራታይዜሽኑን ሂደት ማጥበብ ማለትም መብትን መገደብና የህዝብን  ብሶት ማብዛት ነው።  የተወሰኑ ድርጅቶችንም  ከፖለቲካ ውድድሩ  ቢያንስ ለተወሰነ ጊዜ እንዲገለሉ ያደርጋል። አዳዲስ ድርጅቶችንም ለመፍጠር አያበረታታም።

ይህ ሁሉ  ለተረጋጋ መንግስትንም ሆነ ለዴሞክራሲያዊ ስርአት መሰረት መጣል ያግዛሉ ተብለው ተስፋ የተጣለባቸው ግለሰቦችና ተቋማትንም አላሰፋጊ አፍረሽ ጥላ ያጠላባቸዋል። ይህም እጅግ ጎጂ እንጂ ጠቃሚ አይሆንም ።

በኔ አመለካከት ባሁኑ ሰአት ምርጫውንም በተመለከተ አሁን ባለው ሁኔታ በታቀደው ጊዜ ውስጥ ማካሄድ መቻል አለመቻሉ በጥያቄ ውጥ ያለ ጉዳይ ነው። ስለዚህም ሁሉም የፖለቲካ ድረጅቶች ጊዚያዊ የምዝገባ ሰርቲፊኬት ተሰጥቷቸው  ለሚቀጥሉት ሁለት አመታት በነጻ  እንዲንቀሳቀሱና  ለሀገር መረጋጋትና መግባባት እገዛ እንዲያደርጉ፣ ራሳቸውንም ከህዝብ ጋር እንዲያሰተዋውቁ  ማበረታታት ያሻል። ሀገር ከተረጋጋ፣ መብት ማስከበሩ ስር ከሰደደና የዴሞክራታይዜሽኑ ሂደት ፈር ከያዘ በኋላ ያሉትን ጥንካሬና ድክመቶችን በመገምገም ከሁኔታው ጋር የሚመጥን ማሻሻያ ተግባራዊ ማድረግ ተገቢ ይሆናል።  ይህን ረጋ ባለ መንፈስ በተረጋጋ የፖለቲካ ሁኔታ ሰፊ የፖለቲካ ፍኖተ ካርታ ውስጥ ተካቶ መታየት የሚገባው እንጂ በተናጠል በሩጫ የሚደረግ መሆን የለበትም።

ሀገራችን የምትሻው  በብሶት ላይ ብሶት በቀውስ ላይ ቀውስ መጨመር ሳይሆን መተማመንን የሚያጎለብት ስርአቱንም ሆነ ህጉን ሁሉም የራሴ ነው ብሎ ለመንከባከብ የሚጋብዝ እርምጃን  መውሰድን ነው። የዴሞክራሲ ምህዳሩን ማስፋት እንጂ ማጥበብ አይደለም። ለመደራጀትና ለህዝብ ተሳትፎ እንቅፋትን ማስወገድ እንጂ አዳዲስ መሰናክልን አይደለም። በዴሞክራሲ መስፋት ተጠቃሚወች ሁሉም ኢትዮያውያን ናቸው።

ስለዚህም ነው የተረቀቀው ህግ እንደገና ለባለሙያወች ሰፊ ጥናት ይተላለፍ ወይም  ይስተካከል የምለው።

Exit mobile version