ኃይሉ ከበደ
ይርጋ አበበ ታዬ በበረሃ ስሙ ሀው ጃኖ በቀድሞው ወሎ ክፍለ ሀገር የራያና ቆቦ አውራጃ መናገሻ በነበረችው በአላማጣ ከተማ ተወለደ። የኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄን /ኢህዴን/ ወይም በአሁኑ አጠራር ብአዴንን በ1975 ዓመተ ምህረት መጨረሻ ላይ ተቀላቀለ። ይርጋ ሕይወቱ እስካለፈበት እስከ 1983 ዓመተ ምህረት ድረስ በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች የሰራ ቢሆንም አብዛኛው ጊዜውን ያሳለፈው ሰራዊቱን በመምራት ነበር።በነበረው የወታደራዊ አመራር ብቃትና የትምህርት ዝግጅት ወሳኝ ከሚባሉት የኢህዴን ማዕከላዊ ኮሚቴዎች መካከል አንዱ የነበረና ኢህአዴግ ወደ መሃል አገር መገስገስ በጀመረበት ጊዜ በአገሪቱ ይካሄድ የነበረው ጦርነት ከህወሃትና ከኢህዴን በተውጣጡ የማዕከላዊ ኮሚቴዎች ወይም የደጀን አመራር ይመራ ስለነበር ይርጋም የዚህ የግንባር አመራር አባል ነበር።
ይርጋ በተለያዩ ዓውደ ውጊያዎች ሰራዊቱን በመምራት በብዙ ዓውደ ውጊያዎች የተሳተፈ ብቻ ሳይሆን እንደ አንድ ተራ ተዋጊ ታጋይ በነፍስ ወከፍ መሳሪያ ምሽግ ድረስ እየገባ ሀው ጃኖ እያለ በመፈከር በብቃት ያዋጋና ይዋጋ ስለነበር በኢህዴን ሰራዊት ውስጥ ይበልጥ የሚታወቀው ሀው ጃኖ በሚለው ቅጽል ስም ሲሆን ትርጉሙም በራይኛ የጃኖ ወንድም ማለት ነው። ጃኖ በጣም የሚወዳት ታላቅ እህቱ ነች። ከፍተኛ የጦር አዛዥ ሆኖ እያለ እንደ ተራ ተዋጊ በሚያደርገው የውጊያ ተሳትፎ ብዙ ጊዜ በኢህዴን ታጋዮች “ጀብደኛ ነህ ” እየተባለ ይገመገም ነበር።
ይርጋ ኢህዴን ነበሩኝ ከሚላቸው ወታደራዊ ስትራቴጅስቶች አንዱ እንደነበር ይታወቃል።ዓበይት የሚባሉ ዓውደ ውጊያዎች እንዲመራም ይደረግ ነበር :: ለአብነት ያህል “ሰላም በትግል” ኦፕሬሽን በመባል የሚታወቀውና ኢህአዴግ በ1981 ዓመተ ምህረት ክረምት ላይ ከማይጨው እስከ ወልዲያ ያካሄደው ኦፕሬሽን በዋነኛነት የተመራው በህወሃቱ ኃየሎም አርአያና በኢህዴኑ ይርጋ አበበ /ሀው ጃኖ/ ነበር።
ይርጋ ህወሃት በኢህዴን ውስጥ ያደርገው የነበረው የበላይነት በተለይም የነ በረከት ስምዖን፣ታደሰ ጥንቅሹ፣ህላዌ ዮሴፍ የመሳሰሉት የመለስ ዜናዊ ተላላኪዎችን አካሄድ አምርሮ ከሚቃወሙ የኢህዴን አመራሮች ውስጥ አንዱና ዋነኛው ነበር። ኢህዴን ሌላውን ህዝብ ነጻ ለማውጣት ቅድሚያ ራሱን ነጻ ሊያውጣ ይገባል ብሎም የሚሞግት ነበር።
በተለይም በኢህአዴግ ውስጥ የህወሀት የበላይነት በግልጽ እየተንጸባረቀ ነው፣ የኢህዴን አመራርም ይህን ሁኔታ እስከመቼ በዝምታ እያየ ያልፈዋል? የሚል ጠንከር ያለ አቋም በመያዝ በጽሁፍ ጭምር ከመለስ ዜናዊና ከታምራት ላይኔ ጋር በድፍረት ተሟግቷል::
ማንም ሊገምተው እንደሚችል ይህ ዓይነት አቋም ለዚያውም ወደ ትግራይ ሊያካልሉት ከሚቋምጡለት በለምለምነቱና በሜዳማነቱ ለግብርናም ሆነ ለከብት እርባታ አመች ከሆነው የተፈጥሮ ሐብት ባለቤት ከሆነው ከራያ ማህበረሰብ የወጣው ይርጋ አበበ ይህ ዓይነት አቋም መያዙ ህወሃትን እንቅልፍ የሚያስተኛ አልነበረም።
ኋላ ላይ እንደምገልጸው ይርጋ በ1983 ዓመተ ምህረት በህወሃት ከፍተኛ አመራሮች ትዕዛዝ እስከ ተገደለበት ድረስ አሁን ወደ ትግራይ የተካለሉት ዋጃ፣አላማጣና ኮረም በኢህዴን ክፍለ ህዝቦች ነበር የሚተዳደሩት። ለምሳሌ ያህል ይርጋ ማዕከሉን ወልዲያ አድርጎ የደጀን አመራር በነበረበት ጊዜ ኋላ ላይ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር የነበረው ዮሴፍ ረታ /ገይድ/ በ1982 ዓመተ ምህረት የአላማጣ ወረዳ ከፍለ ህዝብ ወይም አስተዳዳሪ ነበር።
በአንድ ወቅት የኢህዴን ክፍለ ህዝብ የነበረና በ1990 ዓመተ ምህረት በተከሰተው የኢትዮ_ኤርትራ ጦርነት ኤርትራዊ ነህ ተብሎ ከኢትዮጵያ የተባረረው ጋዜጠኛ ሰናይ ገብረ መድህንም አላማጣ በኢህዴን አስተዳደር እንደነበረችና እሱም የአላማጣ ወረዳ ክፍለ ህዝብ እንደነበር ከSBS አውስትራልያ ራዲዮ ጣቢያ ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ ገልጿል። ሌሎችም መጥቀስ ይቻላል። እዚህ ላይ የምንገነዘበው ይርጋ በሕይወት በነበረበት ወቅት ህወሃቶች ይህንን አካባቢ ወደ ትግራይ ለማካለል አልደፈሩም ነበር።
ለምን እንደዚህ እንደሆነና ለምንስ ሁኔታው ተለወጠ? እንደ ማዕከላዊ ኮሚቴነቱና የአካባቢው ተወላጅነቱ እንዲሁም በኢህአዴግ የህወሃትን የበላይነትና ህወሃት በኢህዴን ላይ ያደርገው የነበረው ጣልቃ ገብነት ከመቃወሙ አንጻር የይርጋ አቋም ምን ይመስል ነበር? ፍጻሜውስ እንዴት እንደዚህ ሊሆን ቻለ የሚሉትን ጉዳዮች በዝርዝር ሊያስረዱን የሚችሉት አቶ ታምራት ላይኔ ብቻ ናቸው _ በወቅቱ የድርጅቱ መሪ ስለነበሩና አሁን ባሉበት ሁኔታ እውነቱን የመናገር ነጻነት ስላላቸው።
አንድ ቀንም ያደርጉታል የሚል ተስፋ አለኝ።ከላይ ይርጋ ኢህዴንን በመወከል የሰላም በትግል ኦፕሬሽን ከኃየሎም አርአያ ጋር በጋራ እንደመሩት ጠቅሻለሁኝ:: በጄኔራል መርዳሳ ሌሊሳ ይመራ የነበረው የ605ኛ ኮር ጳጉሜን 3፣1981 ዓመተ ምህረት አላማጣ ላይ ተደምስሶ ወደ ቆቦ ሲያፈገፍግ ኃየሎም አርአያ የራሺያ ስሪት በሆነች ክፍት ዋዝ መኪና ይርጋ አበበ ደግሞ ሽሮ ቀለም ባላት ፒክ አፕ ሆኖ አላማጣ ሼል ማደያ ለተወሰነ ሰዓት ዕረፍት አድርገው ስለነበር ይርጋን የራያ ሰዎች በደስታና ፈገግታ እየተቀባበሉ ሲስሙት በዓይኔ አይቻለሁኝ።
ተስፋ ያደረጉበትም ይመስላል _ ህወሃትን በተመለከተ ራያዎች በሩቁ/በወሬ ይሰሙት የነበረው ራያዊ ማንነታቸውንና ባህላቸውን እንደሚያጠፋ /እንደሚጨፈለቅና ራያነት የሚለውን ወደ ትግራዋይነት እንደሚቀይረው ስጋቱ የነበራቸው ይመስላል። ይርጋን የመሳሰሉ ሰዎች በኢህዴን ውስጥ መኖር ደግሞ ራያዎች ይህ ሊሆን እንደማይችል ተስፋ ነበራቸው _ አልሆነም እንጂ!የሆነው ሆኖ ህወሃትና ኢህዴን የሰላም በትግል ኦፕሬሽን በጋራ ሲያካሂዱ በውጊያው አመራር ሂደት ላይ በኃየሎምና በይርጋ መካከል የተወሰኑ ያለመግባባቶች ተከስተው ነበር _ የተለመደው እኛ የበላይ ነን ዓይነት አካሄድና ይርጋ ደግሞ እሱን ተወው! በሚል። ይህም ነገር አቶ ታምራት ድረስ ደርሶ ጦርነቱ እስኪጠናቀቅ ተስማምተው እንዲሰሩ መመሪያ ቢሰጥም መስማማት ባለመቻሉ ይርጋም በዚህ መልኩ ከህወሃቶች ጋር አልሰራም በማለቱ ነገሮች ይበልጥ እየከረሩ መሄድ ጀመሩ።
ከዚህ በኋላ ነበር ይርጋ ወልዲያ ላይ ሆኖ የግንባሩ የትጥቅና ስንቅ ሃላፊ እንዲሆን የተደረገው። ሆኖም ከህወሃት ጋር የነበረው አለመግባባት ይበልጥ እንዲያገረሽ ያደረጉ ሁለት ነገሮች ወልዲያ ላይ ተከሰቱ። የመጀመሪያው ክስተት የኢህዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልና የደጀን አመራር የነበረው ይርጋ አበበ ሳያውቀው በወቅቱ ክፍለ ኢኮኖሚ ተብሎ ይጠራ በነበረው ክፍል ተመድባ ትሰራ የነበረች እሌኒ የተባለች ተራ የህወሃት ታጋይ በምርኮ የተገኙ የተለያዩ ንብረቶችን አስጭና ወደ ትግራይ ልትልክ ስትል በአካባቢው ያልነበረው ይርጋ ባጋጣሚ ቦታው ላይ ይደርስና የሆነውን ይመለከታል። ምንድን ነው እየተጫነ ያለው? ወዴት ነውስ የሚጫነው? ማንስ ፈቅዶ ነው? ሲል ይጠይቃል። እሌኒም ወደ ትግራይ እንዲጫን አለቆቼ አዘዋል የሚል መልስ ስትሰጥ፡ይርጋም የተጫነው እንዲራገፍ በማዘዝ ያለሱ ፈቃድ አንድም ንብረት እንዳይንቀሳቀስ በማዘዙ እሌኒም የሆነውን ነገር ለመለስ ዜናዊ በሬዲዮ ሪፖርት በማድረጓ መለስም ይርጋ እያደረገው ያለው ነገር የማያዛልቅ እንደሆነ ኢህዴን ይርጋ ላይ የማያወላዳ ዕርምጃ እንዲወስድ ማስጠንቀቁ ይነገራል።
ሁለተኛው ክስተት ዉጊያ ወደ ሚካሄድበት ዓውደ ግንባር በወልዲያ በኩል ያልፉ የነበሩ የኢህዴን ታጋዮች እነ ይርጋ ወደነበሩበት ቢሮ በመምጣት ቀለብና ልብስ እንዲሰጣቸው ይጠይቃሉ። ይርጋ ታጋዮቹ የጠየቁትን እንድታሟላላቸው ለእሌኒ ትዕዛዝ ይሰጣል:: እሌኒ ተራ ታጋይ ሆና እያለች አንድ የማዕከላዊ ኮሚቴና የደጀን ኮሚቴ አመራር አካል የሰጣትን ትዕዛዝ እንደመፈጸም ለታጋዮቹ የተፈቀደላቸውን ቀለብና ስንቅ ትከለክላለች። ጉዳዩ ይርጋ ዘንድ ይደርስና ይርጋም በሁኔታው ተገርሞ መጋዘኑን ራሱ ከፍቶ ለታጋዮቹ የሚበቃቸውን ያህል እንዲወስዱ አድርጎ ይሸኛቸዋል። እሌኒም በሆነው ተበሳጭታ ከነመለስ ጋር በሬዲዮ ግንኙነት በማድረግ ከይርጋ ጋር መስራት እንደማትችልና ከቦታው እንዲያነሷት ትጠይቃለች::
በዋነኛነት የህወሃት የበላይነት በመቃወሙና ሌሎች ከላይ የጠቀስኳቸው ሁኔታዎች ተደማምረው መለስ ኢህዴን ይርጋን እንዲገመግምና ከማዕከላዊ ኮሚቴና ከያዘው ወታደራዊ ኃላፊነት እንዲነሳ ከዚያም እንዲታሰር ታምራትም ይህንን እንዲያስፈጽም ይታዘዛል። እዚህ ላይ ስለ እሌኒ ጥቂት ልበል:: እሌኒ የሰለሞን ተስፋይ /ጢሞ/ ሚስት ስትሆን ሰለሞን/ ጢሞ/ የህወሃት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልና የኦሮሚያ ክልል የበላይ ጠባቂ የነበረ በ1993ቱ የህወሃት ክፍፍል ከነ ገብሩ አስራት ጋር የተባረረ ነው። እሌኒ ኋላ ላይ በሌትናል ኮሎኔል ማዕረግ የመከላከያ ሚኒስቴር በጀት መምሪያ ኃላፊ እስከመሆን ደርሳ በ1993 ዓመተ ምህረት ከእነ ጄኔራል ጻድቃን ጋር በመለስ ዜናዊ ትዕዛዝ ከመከላከያ ሚኒስቴር ተባረረች።
የህወሃትን ትዕዛዝ ለማስፈጸም በ1983 ዓመተ ምህረት አጋማሽ ላይ ይርጋ ባልተገኘበት የኢህዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ ተሰብስቦ ይርጋ ከማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነቱና ከተሰጠው ሃላፊነት ሁሉ እንዲታገድና እንዲታሰር ይወስናል ። ይርጋ በወቅቱ በስራ ጉዳይ ጎንደር ውስጥ አዲስ ዘመን አካባቢ በነበረ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ይገኝ ስለነበር ውሳኔውን ለማስፈጸም የተወሰኑ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ወደዚያው ይላካሉ።
ይርጋ ህወሃትና ተላላኪው ኢህዴን እየሄዱበት የነበረ ሁኔታ የተገነዘበ ይመስላል። በግልጽም ባይሆን የይርጋ አቋም ትክክለኛነት የሚያምኑ አንዳንድ የአመራር አባላት በእሱ ላይ ሊወሰድ ስለታሰበው ዕርምጃ ሳይገልጹለትና ጥንቃቄ እንዲያደርግ ሳያሳስቡት እንዳልቀረም ይገመታል። ከዚህ በበለጠ ግን ይርጋ ራሱ ያያቸው ከነበሩ ሁኔታዎች በመነሳት ምን ጊዜም በተጠንቀቅ ላይ ሁኖ የሚመጣውን በመጠባበቅ ላይ ስለነበር ወደ አዲስ ዘመን የተላከው የማዕከላዊ ኮሚቴ ቡድን ይርጋን አግኝቶ ውሳኔውን አሳወቆ በቍጥጥር ስር እንደዋለም ይገልጽለታል። ይርጋም ውሳኔውን ካዳመጠ በኋላ ሁሌም ከእጁ የማይለይ በነበረው ሽጉጡ ንጉሴ ጺሞ የተባለውን የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ገድሎ በንጉሴና አብሮት በነበረው የትግል አጋሩ ተይዞ የነበረውን የድርጅት ሰነድ በክብሪት ለኩሶ በማቃጠል የተሻለ ተገን ይዞ ራሱን ለመከላከል ድርጊቱ ከተፈጸመበት ቦታ ወጥቶ ሲሄድ እዚያው አዲስ ዘመን አካባቢ በተደረገ የተኩስ ልውውጥ ተገደለ። እዚህ ላይ የህወሃት/መለስ ዜናዊ ተላላኪ ከሆኑት የኢህዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት መካከል ህላዌ ዮሴፍም እንደነበረበትና ለጥቂት ከይርጋ ቅጣት እንዳመለጠ ይነገራል:: ሁኔታዎች አልተመቻቹለትም እንጂ ታደሠ ካሳንም /ታደሠ ጥንቅሹ/ ይርጋ እስከ መጨረሻው ሊያሰናብታቸው ከሚፈልጋቸው ተላላኪዎች አንዱ ነበር።
ይርጋ ለተላላኪዎቹ የኢህዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ምን ያህል ስጋት እንደነበር አንድ ምሳሌ ልጥቀስ። በትጥቅ ትግሉ ወቅት ዋግ ውስጥ በረሃ ላይ ሁሉም የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት አንድ ቦታ ላይ በጋራ ማደር ነበረባቸው:: እንደ አጋጣሚ ይርጋ ቦታው ላይ ቀድሞ ደርሶ ስለነበር ኩሽፍ /ሽርጥ/ ለብሶ ሸለብ አድርጎታል። ሙሉ ለሙሉ ግን እንቅልፍ አልወሰደውም። በረከትና ታምራትም ቦታው ሲደርሱ ይርጋ ጋደም እንዳለ ስለነበር የተኛ ነበር የመሰላቸው ። በረከት ይርጋን በጣም ይፈራው ስለነበር ወደ ታምራት እየተመለከተ “ይሄ ልጅ እኮ አንድ ቀን ሳይጨርሰን አይቀርም፡ እንዴት እሱን አምነን አብረን እንተኛለን?” ሲል ይርጋ ከተኛበት ብድግ ብሎ ወደ ታምራት እየተመለከተ “ እሱ /በረከት/ ተረጋግቶ እንዲተኛ ይሄውና ሽጉጤንና መሳሪያዬን ተረከበኝ። እሱ /በረከት/ ትጥቁን ሳታስፈታው ይተኛ “ ሲል ታምራት “ግድ የለም ኣንተም ትጥቅህን መፍታት አይጠበቅብህም ለጋራ ዓላማ የተሰለፍን ጓዶች ነን ። መተማመን ይኖርብናል” ብሎ እንዳስተካከለው ይነገራል።
አቶ ታምራት የኢህዴን የትግል ታሪክ ጉዞ ከጻፈ ስለ ይርጋ አበበም ይነግረን ይሆናል ብለን ተስፋ እናድርግ። ኢህዴንን በተመለከተ እስካሁን ሁለት መጻህፍት በኮሎኔል አከለ አሳዬና በገነት ታደሰ ተጽፈዋል። ሆኖም ግን ከላይ የተጠቀሰውን ታሪክ ለማንሳት ወኔያቸው ከድቷቸዋል። ምናልባት ለማንሳት ፈልገው የአለቆቻቸውን ተግሳጽ በመፍራት ትተውት ሊሆን ይችላል። ምክንያቱም ኢህዴን/ብአዴን ይህንን ታሪክ ማንሳት በጣም የሚፈራው ርዕስ ሰለሆነ። ለምን ? ቢባል ኢህዴን ከህወሃት ሞግዚትነት ወይም አሻንጉሊትነት ነጻ ይውጣ የሚል ስለነበር ይህንን በወቅቱ ማስተናገድ ከህወሃት መዐት ያወርድብናል ብለው ይፈሩ ስለነበር :: ይርጋ ከዛሬ ሶስት አሰርት ዓመታት በፊት ያነሳው የድርጅት ነጻነት ጥያቄ አሁን የዘመናችን ወጣቶች ጥያቄ ሆኖ ህወሃት/ኢህአዴግ ሊፈታው የማይችል አረንቋ ውስጥ ገብቶ አሳሩን እያበላው ይገኛል።
መቼም ህወሃቶች የጸጸት ልብ የላቸውም እንጂ ምነው ያኔ ይርጋን ሰምተነው በነበር የሚሉ ይመስለኛል። ለነገሩ ባለፈው ላጠፉት ጥፋት ይቅርታ መጠየቅ ለህወሃቶች ነውር ነው:: በቅርቡ በገዢው ፓርቲ ከሚተዳደረው የENN ቴሌቪዥን ጋር ቃለ ምልልስ ያደረገው የቀድሞው አየር ኃይል አዛዥ ጄኔራል አበበ ተ/ሃይማኖት ስለ የህወሃት የበላይነት በተመለከተ እንዲህ ይላል“ / የህወሃት የበላይነት አለ ስለሚባለው ነገር / ከሃያ ሰባት ዓመት በኋላ ኢህዴን ቢያነሳው እኔ አፍራለሁ:: ከሃያ ሰባት ዓመት በኋላ እነ አባዱላ ቢያነሱት አፍራለሁ። Where were they? ያሳፍራል በጣም ። እየፈሩ ነበር ማለት እኮ ነው ። ” ይለናል። አበበ ምን እያለን ነው? ኢህዴንም ሆነ አባ ዱላ እኮ የህወሃት የበላይነትና ጣልቃ ገብነት የተቃወሙ እንደነ ይርጋ አበበ ዓይነት ሰዎች ምን እንደ ደረሰበቸው እኮ አሳምረው ያውቃሉ። አበበ ራሱ እኮ ይህንን ጥያቄ ያነሱ ሰዎች በእሱ ድርጅት ትዕዛዝ እርምጃ ሲወሰድባቸው ሲያጨበጭብ የነበረ ሰው ነው።
ስለዚህ ርዕስ ሊያወራ ምን አንደበትና ሞራል አለው ? ህወሃት ሰለሞን ተስፋዬን /ጢሞ/ የኦሮሚያ ክልል ቢተው በላይን የደቡብ ህዝቦች ክልል የበላይ ጠባቂ አድርጋ ስትመድብ ከህወሃት የበላይነትና ጣልቃ ገብነት ውጪ ምን ሊያመለክት ይችላል? እነዚህ ሁለት ሰዎች በምን ስሌትና አካሄድ ከክልሎቹ ፕሬዝዳንቶችና ፓርቲዎች በላይ ስልጣን ተሰጥቷቸው ፈላጭና ቆራጭ ሆነው ክልሎቹን ሲቆጣጠሩና ሲያስተዳድሩ ለአበበ ይህ የህወሃት የበላይነትና ጣልቃ ገብነት አይደለም እንዴ?
እንደ ማሳረጊያ ከይርጋ ጋር በተያያዘ አሳር አበሳውን እያየ ያለ አንድ የኢህዴን ነባር ታጋይ የነበረ ሰው የደረሰበት መከራ ልግለጽና ጽሁፌን ልቋጭ:: ካህሳይ ደርበው በበረሃ ስሙ /ጠርጣራው/ ይባላል:: እሱም ቅልሻ – አላማጣ ተወልዶ ትምህርቱን የተከታተለው እዚያው አላማጣ ሲሆን ኢህዴንን የተቀላቀለው በ1975 ዓመተ ምህረት መገባደጃ ነበር። ካህሳይ በሰራዊቱ ውስጥ በተለያየ የአመራር ኃላፊነቶች የሰራ በጣም ደፋር ተዋጊና መሪ ነበር። በደርግ ዘመን መጨረሻ ላይ በ1983 ዓመተ ምህረት አካባቢ የኢህዴኑ አዋሽ ከፍለ ጦር አመራር አባል ነበር። የተቃራኒ ጦር እንቅስቃሴ ፈጥኖ የመገንዘብና የመወሰን ከፍተኛ ችሎታ ስለነበረው በታጋዩ ዘንድ ጠርጣራው ተብሎ ነበር የሚጠራው። ከይርጋ /ሀው ጃኖ/ የህወሃት የበላይነት ተቃውሞ እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ ተገምግሞ ለተወሰነ ጊዜ ከታሰረ በኋላ ከሰራዊቱ ተሰናብቶ ወደ ፖሊስ ሰራዊት ተዛወረ። በመጀመሪያዎቹ የሽግግር ዓመታት በምስራቅ ጎጃምና በጎንደር በፖሊስ አዛዥነት ከሰራ በኋላ ክትትል ይደረግበት ስለነበር እንደገና ባህር ዳር ላይ በእስር ቆዬ። ከዚያም በአገሩ ሰርቶ መኖር ስላልቻለና ነጻነት ለማምጣት ታግሎ ነጻነቱን ስላጣ ወደ ኤርትራ ተሰደደ። እዚያ ከሚገኙ ተቃዋሚ ሃይሎች ጋር በመሆን በኢትዮጵያ ያለውን ኢዴሞክራሲያዊ አገዛዝ ለመገርሰስ ካህሳይ /ጠርጣራው/ ለሌላ የነጻነት ትግል እንደገና ተሰልፎ እንደነበር ኤርትራዊው ጋዜጠኛ ሰናይ ገብረ መድህን ከSBS አውስትራልያ ሬዲዮ ጋር ካደረገው ቃለ ምልልስ መረዳት ይቻላል:: አሁን ባለው መረጃ ግን በ2002 ዓመተ ምህረት ቋራ አላጥሽ ፓርክ አካባቢ በመንግስት ጦርና በአርበኞች ግንባር ተደርጎ በነበረው ውጊያ ተይዞ ላለፉት ስምንት ዓመታት አዲስ አበባና ዝዋይ በሚገኙ እስር ቤቶች እየማቀቀ ይገኛል።
መንግስት ጥቂት የህሊናና የፖለቲካ እስረኞች የፈታ ቢሆንም ህዝብ መታሰራቸውን አያውቅም ብሎ የሚገምታቸውን በርካታ የህሊናና የፖለቲካ እስረኞች አሁንም ለሰው ልጅ ህሊና የሚዘገንኑ ስቃይና መከራ በሚፈጸምባቸው የወያኔ ወህኒ ቤቶች የመከራ ጊዜ እያሳለፉ ይገኛሉ:: ስለዚህ መንግስት እንደነ ካህሳይ ደርበው /ጠርጣራው/ የመሰሳሰሉ በርካታ የፖለቲካ እስረኞችን መፍታት ሃገሪቱ ካጋጠማት ተግዳሮት ለመታደግ አንድ ዕርምጃ መሆኑን አምኖ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በአስቸኳይ ወደ ሰላማዊ ኑሮአቸው ሊመልሳቸው ይገባል።