Site icon Dinknesh Ethiopia

በኦሮሚያ ክልል ለሰሞኑ ህይወት መጥፋትና ንብረት መውደም ምክንያት የሆኑ አካላቶች ለሕግ እንዲቀርቡ

ሲነዶሱ

በኦሮሚያ ክልል ለሰሞኑ ህይወት መጥፋትና ንብረት መውደም ምክንያት የሆኑ አካላቶች ለሕግ እንዲቀርቡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ-ክርስቲያን ጠየቀች

 

በኦሮሚያ ክልል ለሰሞኑ ህይወት መጥፋትና ንብረት መውደም ምክንያት የሆኑ አካላቶች ለሕግ እንዲቀርቡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ-ክርስቲያን ቅዱስ ሲነዶስ ምልዓተ-ጉባኤ አሳሰበ። በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን የቅዱስ ሲነዶስ ምልዓተ-ጉባኤ ከጥቅምት 12 እስከ 24 ቀን 2012 ዓ.ም ያካሄደው ጉበኤ ዛሬ ተጠናቋል።

ይህንንም ተከትሎ አባ ማቲያስ ቀዳማዊ ፓትርያሪክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ዛሬ በሰጡት መግለጫ ”ሲኖዶሱ ከሰሞኑ የጠፋው ህይወትና ንብረት አሳስቦታል” ብለዋል።

በተለይም ደግሞ በአብያተ ክርስቲያናትና በእምነቱ ተከታዮች ላይ እየደረሰ ያለው ጉዳት፣ ስደትና መከራ ጎልቶ እየታየ መሆኑን ገልጸው፤ ”ጉዳዩ ትኩረት ሊደረግለት ይገባዋል” ነው ያሉት።

በዚህም መሰረት መንግሥት ሰላም እንዲያስከብር፣ የዜጎችን ደህንነት እንዲጠብቅና የተፈናቀሉ ወደ ቀዬአቸው እንዲመለሱ ማድረግ እንዳለበት አሳስበዋል።

ጎን ለጎንም ለጠፋው ንብረት መቋቋሚያ እንዲደረግላቸው ጠይቀው በተለይም አጥፊዎችን ለሕግ በማቅረብ መንግሥት የበኩሉን መወጣት እንዳለበት ገልጸዋል።

ቅዱስ ሲነዶሱ በኦሮሚያ ክልል በተከሰተው ችግር ከባድ አደጋ ላይ ለወደቁ ወገኖች በጊዜያዊነት የሚደርስ ምግብና አልባሳት ለማቅርብ ገንዘብ መመደቡን ጠቁመዋል።

በቀጣይም በክልሉ ይህንን ችግር እየተከታተሉ ዘለቄታዊ ርዳታ የሚሰበስብ ኮሚቴ እንዲቋቋም ሲኖዶሱ መወሰኑን ፓትሪያርኩ ተናግረዋል።

በተጓዳኝም ቤተ-ክርስቲያኗ ተከታዮቿን በተለያዩ ቋንቋዎች ለማገልገል እንዲቻል ለአብነት ትምህርት ቤቶች ቋሚ በጀት እንዲመደብ መወሰኑን ገልጸዋል።

በቀጣይ ደግሞ ሁሉንም የአፍ መፍቻ ቋንቋ በማዕከል ማሰልጠኛ እንዲቋቋም ቅዱስ ሲኖዶሱ ውሳኔ ማሳለፉንም ጠቁመዋል።

በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ በተለያዩ አከባቢዎች የሚታየውን ችግር እንዲያበቃ ሕዝበ -ክርስቲያኑ አምላኩን በጸሎትና በምህላ እንዲጠይቅ ጥሪ አስላልፈዋል።

ኢዜአ፤ ጥቅምት 24/2012

Exit mobile version