Site icon Dinknesh Ethiopia

ጉዳዩ፡ በዶ/ር ሙላቱ ተሾመ ንግግር ላይ ማብራሪያና ምላሽ ስለመጠየቅ

የወልቃይት ጠገዴና ጠለምት

በዶ/ር ሙላቱ ተሾመ ንግግር ላይ ማብራሪያና ምላሽ ስለመጠየቅ: የወልቃይት ጠገዴና ጠለምት ማህበረሰብ እራሱን የትግራይ ህዝብ ነፃ አውጭ ግንባር/ትህነግ/ እያለ በሚጠራው ድርጅት የተፈጸመበትን የመሬት ወረራና መስፋፋት ጥቃትና ከዚህም ጋር ተያይዞ የደረሰበትን የዘር ማፅዳት ወንጀል መታገል ከጀመረ እነሆ 40 ዓመታት ተቆጥረዋል።

በኢትዮጵያ አንድነትና ዳር ድንበር መከበር፣ በርስቱና፣ በማንነቱ ድርድር የማያውቀው ህዝባችን በተለይም የትህነግን አገር አፍራሽ እኩይ ሴራና ድርጊት ቀድሞ በመረዳት አቅሙና ሁኔታው በፈቀደለት መንገድና መጠን እራሱን አደራጅቶ በመታገሉ የትህነግን ቀጣይ መስፋፋት እቅድና የሃገር ግንጠላ ሴራ ያከሸፈ ሲሆን፤ ይልቁንም ህዝባችን አማራዊ ማንነቱን ለማስከበር ባደረገው የተቀናጀ መራር ትግል መላውን አማራና ፍትህ ወዳዱን የኢትዮጵያ ህዝብ ከጎኑ በማሰለፍ የትህነግን ፋሽስታዊና አምባገነናዊ ስርዓት ተወግዶ በለውጥ ሃይሉ እንዲተካ አስችሏል።

በዚህ መራራ ትግልና የላቀ መስዋዕትነት በተገኘው ሃገራዊ ለውጥና አንፃራዊ ሰላም ተጠቅሞ ድርጅታችን ልሳነ ግፉዓን ከለውጥ ሃይሉ ጋር በወልቃይት፣ ጠገዴና፣ ጠለምት ህዝብ መሰረታዊና ስር የሰደዱ ጥያቄዎች ላይ ታሪካዊ መነሻ፣ ምንነትና፣ ምላሽ በሚያገኙበት አግባብ ዙሪያ ተደጋጋሚ ውይይቶችና ድርድሮች በማድረግ ግልጽ ስምምነት ላይ ተደርሶ ወደ ስራ ተገብቷል። እነሱም፦

1ኛ. አብዛኛው የወልቃይት፣ ጠገዴና፣ ጠለምት ክፍል በትህነግ ቁጥጥር ስር የወደቁት የደርግ መንግስት ከመውደቁ እጅግ ቀደም ብሎ በትጥቅ ትግሉ ወቅት መሆኑ፣

2ኛ. ህዝባችን የትህነግን ህገ-ወጥ ወረራን መስፋፋት በመቃወም ከ1972 ዓ.ም መታገል እንደጀመረና በዚህም ምክንያት ከፍተኛ ቁጥር ያለው ህዝባችን አንደተገደለ፣ አካሉን እንዳጣ፣ በግፍ እንደታሰረ፣ ፍጹም ፋሽስታዊ የሆነ ስቃይ እንደተፈጸበትና፣ ብሎም ከፍተኛ ቁጥር ያለው ህዝባችን ለስደት እንደተዳረገ ግንዛቤ የተጨበጠ ሲሆን፤ ዛሬም ድረስ አካባቢው ለነፃ ጋዜጠኞችና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ዝግ በመሆኑ ምክንያት በአካባቢው የተፈጸመውን ግፍና ወንጀል በቅርበት መመርመርና ማጣራት እንዳልተቻለ፣

3ኛ. ትህነግ በትጥቅ ትግሉ ወቅት የያዛቸውን ሌሎች አካባቢዎች ለቆ ሲወጣና ወደ ቀደመው አስተዳደራቸው ሲመለሱ በጎንደር ክ/ሃገር ውስጥ ይካለሉ የነበሩትን የወልቃይት፣ ጠገዴና፣ ጠለምት መሬቶች ለቆ አለመውጣቱን ና አካባቢዎቹም ወደ ጎንደር አለመመለሳቸው፣

4ኛ. በአዋጅ 7/1984 መሰረት በ1985 ዓ.ም በሽግግሩ መንግስት ወቅት ክልሎች በሚካለሉበት ወቅት የጎንደር ክ/ሃገር ወደ ቀድሞው ክልል ሶስት/አማራ ክልል/ ሲካለል የክ/ሃገሩ ቀደምትና ታሪካዊ አካል የሆኑት ወልቃይት፣ ጠገዴና፣ ጠለምት በትጥቅ ትግሉ እንደተያዙ ባሉበት ሁኔታ በቀድሞው ክልል አንድ /ትግራይ ክልል/ ስር እንዲካለሉ መደረጋቸው፣

5ኛ. በዚህም የክልሎች አከላለል መሰረት የወልቃይት፣ ጠገዴና፣ ጠለምት ህዝብ በጦርነት እንደተያዘ ባለበት ሁኔታ ከክልል አንድ ጋር እንዲቀጥል መካለሉን በይፋ በመቃወም ቅሬታውን ለሽግግር መንግስቱና በወቅቱ የሽግግር መንግስቱ ፕሬዘደንት ለነበሩት አቶ መለስ ዜናዊ አማራዊ ማንነቱ እንዲከበርለትና ወደ ክልል አንድ እንዲካለ ጥያቄውን በይፋ እንዳቀረበ፣

6ኛ. ይልቁንም አሁን በስራ ላይ ያለው ህገ-መንግስት የጸደቀው በ1987 ዓ.ም ሲሆን እንደ ማንኛውም ህግ ህገ-መንግስቱ ወደ ኋላ ሄዶ የተፈጸሙ ችግሮችን እንደ ማይፈታ የታወቀ በመሆኑ የወልቃይት፣ ጠገዴና፣ ጠለምት ህዝብ ጥያቄ በህገ-መንግስቱም ሆነ ህገ-መንግስቱን መሰረት አድርጎ በሚሰራው የፌደሬሽን ምክር ቤት ሊፈታ እንደማይችል የጋራ መተማመንና ስምምነት ላይ የተደረሰበት መሆኑ፣

7ኛ. ትህነግ መራሹ መንግስትና የትግራይ ክልላዊ መንግስት በተቀናጀ ሁኔታ በወልቃይት፣ ጠገዴና፣ ጠለምት አካባቢን ቀደምት ነዋሪ የሆነው የአማራ ህዝብ ላይ ቀጥተኛና ስውር የዘር ማጽዳት ወንጀሎችን በመፈጸም አካባቢው ከአማራነት ያፀዱ ሲሆን በአንፃሩ ደግሞ አካባቢውን ትግሪያዊ ለማደረግ በተወሰደው ህገ-ወጥና ኢሰብዓዊ እርምጃ ከቀደምት ነዋሪው ህዝብ በላይ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የትግሬ ሰፋሪ በአካባቢው በማስፈር የህዝብ ስብጥሩ/Demography/ እንዲዛባና ትግሪያዊ እንዲሆን የተደረገ መሆኑ፣

8ኛ. በአጠቃላይ ከላይ የተዘረዘሩትን መሰረታዊ ጭብጦች በመመርመር የወልቃይት፣ ጠገዴና፣ ጠለምት ህዝብ ጥያቄ የሚፈታው መሬታችን በትህነግ ወረራ ከመያዙ በፊት በነበሩት ታሪኮችና የህዝብ ማንነትና ስብጥር መሰረት ባደረገ፣ ነፃና ገለልተኛ የፍትህ አካላት ሲሆን ለዚህም ከህዝብ የተወጣጣ ገለልተኛ አካል እንዲቋቋም ስምምነት ላይ ተደርሷል። በዚህም መሰረት ዛሬ ስራ ላይ የሚገኘው የአስተዳደር ወሰንና የማንነት ኮሚሽን መቋቋሙን ማስታወስ እንወዳለን።

የአስተዳደር ወሰንና የማንነት ኮሚሽን ከተሸከመው ሃገራዊ አጃንዳ አንገብጋቢነት አንፃር በፍጥነት ወደ ስራ መግባትና ጥያቄ ካቀረበው ህዝብ ጋር ከመገናኘት ቢዘገይም እንኳ በቅርቡ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር መወያየት ጀምሪያለሁ በማለት ከአማራ ክልል ከፍተኛ ባለስልጣናትና ከክልሉ ማህበረሰብ ተወካዮች ጋር ያደረገውን ውይይት ድርጅታችን ልሳነ ግፉዓን በከፍተኛ አትኩሮት ተከታትሎታል።

በውይይቱ ላይ የተሳተፉት የአማራ ክልል ከፍተኛ አመራሮችና ባለስልጣናት ለኮሚሽኑ አመራሮች የህዝባችንን መሰረታዊ ጥያቄዎች በዝርዝር በማንሳትና የመፍትሄ አቅጣጫዎችን በተገቢው ሁኔታ በማመላከታቸው ይበል ያሰኘንን ያህል ከኮሚሽኑ አባላት መካከል አንዱ የሆኑት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ “ከህገ-መንግስቱ በፊት ያሉትን ነገሮች ካዬን ትንሽ ያስቸግራል፣ ባህልና ታሪክን መሰረት ላደረጉ ጥያቄዎች እድል አንሰጥም” በማለት በሰጡት ምላሽና ማብራሪያ መደንገጣችንና ማዘናችን አልቀረም።

ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ በዚያ ስብሰባ ላይ የተገኙት ኮሚሽኑን ወክለው እንደ መሆኑ መጠን ኮሚሽኑ የአገር ህልውና ላይ ከፍተኛ ስጋትና አደጋ የዳረጉትን የማንነት መከበርና የአስተዳደር ወሰን ጥያቄዎች ላይ ዘላቂና ሚዛናዊ የመፍትሄ ሃሳብ ያቀርባል በሚል ትልቅ ተስፋ የተጣለበት ሲሆን፤ ይልቁንም ከቀደመው የትህነግ እብሪታዊና ህዝብን ወደ ከፋ ቁጣና አመፅ ከሚያስገቡ ምላሾች ትምህርትና እርምት በመውሰድ የተሻለና ህዝባዊ ወገንተኝነት የተላበሰ ኮሚሽን ይሆናል የሚል እሳቤ ነበረን።

ነገር ግን በዶ/ር ሙላቱ ተሾመ የተሰጠው ምላሽ ኮሚሽኑ ከህገ-መንገስቱ በፊት የተፈጠሩትን ችግሮች እንደማያይና ለታሪካዊና ባህላዊ እሴቶቻችንና መረጃዎች እድል አንሰጥም ማለታቸው ቀደም ባሉት ጊዜያት ህዝባችን አጥብቆ ከሚጸየፋቸውና በእጅጉ ያስቆጣው ከነበሩት የትህነግ የእብሪት ምላሾች ጋር ምንም አይነት ልዩነት የሌለውና፤ ይልቁንም ህዝባችን ለለውጥ ሃይሉ በቂ የስራ ጊዜ ለመስጠት በማሰብ ያዳፈነውን ቁጣ የሚቀሰቅስና ሃገራችንን ዳግም ወደ ብጥብጥና አለመረጋጋት የሚያስገባ ጠብ-ጫሪ ንግግር ሆኖ አግኝተነዋል።

በዚህም ምክንያት ድርጅታችን በኮሚሽኑ ገለልተኛነት ላይ ያሳደረውን ተስፋና የህዝባችን የዘመናት ጥያቄ በሰላማዊና በህጋዊ መንገድ ዘላቂ እልባት የሚያገኝበትን የመፍትሄ ሃሳብ ያቀርባል በሚል እምነት የጣልንበትን ኮሚሽን ተቋማዊ ብቃትና ተዓማኒነት ጥያቄ ውስጥ ያስገባ ሆኖ አግኝተነዋል። ስለሆነም ድርጅታችን ልሳነ ግፉዓን ለአስተዳደር ወሰንና የማንነት ኮሚሽን የሚከተሉትን ጥያቄዎች በአክብሮት እያቀረበ፤ ኮሚሽኑ ለጥያቄዎቻችን ግልፅና አስቸኳይ ማብራሪያ እንዲሰጥ በትህትና እንጠይቃለን።

1ኛ. ኮሚሽኑ ከህገ-መንግስቱ በፊት የነበሩትን ጉዳዮች አልመለከትም ሲል ምን ማለቱ ነው? ኮሚሽኑ በተቋቋመበት የማቋቋሚያ አዋጅ በተቀመጠለት የስራ መመሪያና ስልጣን ውስጥ “ከህገ መንግስቱ በፊትና በኋላ” የሚል የጊዜ ማእቀፍ ተቀምጦለታልን?

2ኛ. አሁን ስራ ላይ ካለው ህገ-መንግስት መፅደቅ በኋላ በኢትዮጵያ ውስጥ የተደረገ የአስተዳደር ወሰን ማካለልና የማንነት ምደባ ተደርጓል ወይ? ከህገ-መንግስቱ መጽደቅ በፊት ወደ ትግራይ የተካለሉትንና ለኮሚሽኑ መቋቋም ዋነኛ ምክንያት የሆኑትን የወልቃይት፣ ጠገዴ፣ ጠለምት፣ ራያ፣ …ወዘተ ማህበረሰቦች ጥያቄ የማያካትት ከሆነ ኮሚሽኑ የትኞችን የአስተዳደር ወሰንና የማንነት ጥያቄዎችን ለማየትና የመፍትሄ ሃሳብ ለማቅረብ ነው የተቋቋመው?

3ኛ. ዶ/ር ሙላቱ በማብራሪያቸው “በታሪክ እንዲህ ነበር እንዲያ ነበር ለሚለው ነገር ባህልና ታሪክን መሰረት ላደረጉ ጥታቄዎችም እድል አንሰጥም” ሲሉ ምን ማለታቸው ነው? በመግቢያችን እንዳነሳነው በህዝባችን ላይ ትህነግ መራሹ የትግራይ ክልላዊ መንግስት በተቀነባበረ ሁኔታ ወልቃይት ጠገዴና ጠለምትን ትግሪያዊ ለማድረግ በማቀድ የህዝብ ስብጥሩን እስከ ማዛባት ለደረሰው መንግስታዊ የዘር ማጽዳት ወንጀልና ግፍ የህዝብን ባህልና ታሪክን ካላካተተ ኮሚሽኑ ምንን መሰረት አድርጎ ነው ለ40 ዓመታት የዘለቀውን የህዝባችንን የማንነት ጥያቄ መፍትሄ ሊሰጡ ያሰበው?

በመጨረሻም በዶ/ር ሙላቱ ተሾመ ግልጽነት በጎደለውና የህዝብን ጥያቄ ባላገናዘበ ንግግር ምክንያት ህዝባችን ወደ አላስፈላጊ ውዥንብር፣ ስጋትና፣ ቁጣ ከመግባቱ በፊት ኮሚሽኑ በአስቸኳይ ላነሳናቸው ጥያቄዎች ማብራሪያ እንዲሰጥ በድጋሚ እየጠየቅን ነገር ግን ይህ ሳይሆን ቀርቶ በሚፈጠረው ህዝባዊ ቅሬታና ቁጣ ተጠያቂው የአስተዳደር ወሰንና ማንነት ኮሚሽን መሆኑን ከወዲሁ አጥብቀን ማሳወቅ እንወዳለን።

ድል ለህዝባችን!

ኢትዮጵያ በክብር ለዘለዓለም ትኑር!

ልሳነ ግፉዓን ድርጅት

ታህሳስ 6, 2012 ዓ.ም

ኦሃዮ/ኮሎምበስ

ግልባጭ፡-

– ለኢ.ፌ.ድ.ሪ. ም/ጠ/ሚንስትር ቢሮ

አዲስ አበባ

– ለአማራ ክልላዊ መንግስት ፕሬዘደንት ጽ/ቤት

– ለአዴፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ ፅ/ቤት

ባህር ዳር

Exit mobile version