Dinknesh Ethiopia

የኢትዮጵያ ማህበረሰብዓዊ ድርጅቶች ትብብር ስለ ታገቱት የደምቢዶሎ ዩኔቨርሲቲ ተማሪዎች መግለጫ

በሰላማዊ ዜጎች ላይ የሚደርሰውን ዒሰብዓዊ ጥቃት አጥብቀን እንቃወማለን!!!

 

አስራ ሰባት የደምቢዶሎ ዩኔቨርሲቲ ተማሪዎች በሕዝብ ማመላለሻ ወደ ቤተሰቦቻቸው እየተጓዙ ባልታወቁ ሕገወጥ ኃይሎች ታፍነው ወደ አልታወቀ ሥፍራ ተወስደው መታገታቸውን ከመካከላቸው አምልጣ በወጣች ወጣት አማካኝነት ከሰማን ሁለት ወር ሊሞላ ነው።  በዚህ ጊዜ ውስጥ ከተለያዩ የመንግሥት አካላት ተወካዮች የተሰጡት ቁንፅል ያልተናበቡና ያልተረጋገጡ መረጃዎች ወላጆችንና ሕዝብን ከማረጋጋት ይልቅ የበለጠ ሥጋትና ውዥምብር የሚፈጥሩ እየሆኑ መጥተዋል።

የዜጎች በነፃ የመዘዋወርና በሰላም የመኖር መብት መሠረታዊና በዓለም አቀፍ የስብዓዊ መብት ሕግጋት ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ በመሆኑ ይህ ክስተት እጅግ አሳሳቢና የሚመለከታቸውን አካላት ከፍተኛ ትኩረት የሚጠይቅ መሆኑ አያከራክርም።  ከዚህ አንፃር የችግሩ ውስብስብነትና መፍትሔ የማስገኘቱ ሂደት እንደተጠበቀ ሆኖ በመንግሥት በኩል ሕዝብን የሚያረጋጋና ታማኝነት ያለው መረጃ ማቅረብ አለመቻሉ ተቀባይነት የለውም። በመሆኑም የኢትዮጵያ ማህበረሰብዓዊ ድርጅቶች ትብብር በታገቱት ዜጎች ላይ በሚፈፀመው ኢሰብዓዊ ስቆቃ የተሰማውን ትልቅ ኃዘንና ቁጣ እየገለጠ የሚከተለውን ጥሪ ያቀርባል።

1ኛ- ይህንን አሰቃቂ ድርጊት የሚፈፅመው ኃይል ዓላማው ምንም ይሁን ምን በሰላማዊ ዜጎች ላይ አረመናዊ ጥቃት በማድረስ ከውግዘትና በሕዝብ ከመጠላት በቀር የሚያገኘው ውጤት እንደማይኖር ተረድቶ ወጣቶቹን በአስቸኳይ እንዲለቅ እንጠይቃለን፡ ይህን ሳያደርግ ቀርቶ በወጣቶቹ ላይ ለሚደርሰው ሰቆቃ ሁሉ ውሎ አድሮ ሁሉም ነገር መታወቀ ስለማይቀር በሕዝብ ጠላትነት የሚፈረጅና ተጠያቂ መሆኑ እንደማይቀር ማስገንዘብ እንወዳለን።

2ኛ- መንግሥት ይህንን አሳሳቢ ጉዳይ በሚመለከት ለወላጆችና ለሕዝብ ትክክለኛ ግንዛቤ በማስጨበጥ ረገድ ባሳየው ድክመትና በፊፀመው ስህተት ተፀፅቶ በአስቸኳይ ሕዝብ ሊያውቅ የሚገባውን ትክክለኛና አስተማማኝ መረጃ እንዲሰጥ ታጋቾችንም ለማስለቀቅ የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ እንዲቀጥል ለታጋች ቤተሰቦች ተገቢውን እንክብካቤና የማረጋጋት ድጋፍ እንዲሰጥ እንጠይቃለን።

3ኛ- የዘገየም ቢሆን ሕዝባዊ ድርጅቶችና የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪዎች ሁሉ በማኅበራዊ ሚዲያና በሰላማዊ ሰልፎች አማካኝነት ማሰማት የጀመርነዉ ህዝባዊ ድምጽ ተገቢና አስፈላጊ ስለሆነ ችግሩ እልባት እስኪያገኝ ተጠናክሮ እንዲቀጥል እናሳስባለን።

4ኛ- ይህ አሳዛኝና አሰቃቂ ክስተት በአጠቃላይ በአገራችን እየተባባሰ የሔደው ሥርዓተ አልበኝነትና የሰላም መታጣት የደረሰበትን አሳሳቢ ደረጃ የሚያመላክት በመሆኑ ባለ ድርሻ አካላት ሁሉ ሰላምና መረጋጋት ማስፈን በሚያስችሉ የመፍትሔ ሃሳቦች ዙሪያ ትኩረት ሰጥተው እንዲንቀሳቀሱ ወገናዊ ጥሪ እናቀርባለን። ይህ በአገር ላይ ያንዣበበ አደጋ ለመንግሥትና ለፖለቲካ ኃይሎች ብቻ የሚተው ጉዳይ ስላልሆነ ሕዝባዊ ድርጅቶች ከሁሉ በፊት ለዜጎች መብትና ለሃገር መረጋጋት ከምንጊዜም የበለጠ ጥረት ለማድረግ ቃል እንገባለን።

 

hijacked studentsለተጨማሪ በፎቶ የተደገፈ መረጃ

Exit mobile version