Site icon Dinknesh Ethiopia

ለዋዜማ ሬዲዮ – የህዳሴውን ግድብ ዜናችሁን ላስተካክልላችሁ

abiy

የውሃ ሃብት ባለሙያ ነኝ፤ የግድቡ ጉዳይ ቀጥታ ከሙያዬ ጋር ባይገናኝም እንደዜጋ ሁኔታውን በቅርብ እከታተላለሁ፤ ፖለቲካንም እንዲሁ። የዋዜማን ሰዎች ዋዜማ ሳትሆኑ ነው የማውቃችሁ፤ ካገር ከመውጣታችሁ በፊት ማለቴ ነው። የማውቃችሁም በግል ሳይሆን እንደማንኛውም የሚዲያ ተጠቃሚ ነው፤ ስለዚህ እናንተ አታውቁኝም። አሁንም ዋዜማን እከታተላለሁ። ከዳያስፖራ ከሚመነጩት የዜና ዘገባዎችና መረጃዎች የእናንተ በተሻለ መጠን ተዓማኒነትና ሥርዓት የያዘ ነው ብዬ ስለማምን አነባችኋለሁ።

ኢትዮጵያን ቋሚ ባለዕዳ የሚያደርገው የህዳሴ ግድብ ስምምነት ላይ መንግስት የመፈረም ፍላጎት እያሳየ ነው” በሚል ርዕስ ያወጣችሁትን ዘገባ አንብቤዋለሁ። ዘገባው እንደሚለው ለረጅም ጊዜ የተጠበቀውን ሰነድ ስምምነት እንድትፈርም ኢትዮጵያ ግፊት እየተደረገባት እንደሆነ፤ ይህም “ኢትዮጵያን ቋሚ የውሀ ባለ እዳ የሚያደርግ መሆኑን”፤ ረቂቅ ሰነዱ እጃችሁ እንደገባ፤ ፕሬዚዳንት ትራምፕ ጠ/ሚ/ር ዐቢይ ላይ ተጽዕኖ እያደረጉባቸው እንደሆነ፣ ኢትዮጵያ ካልፈረመች ከአሜሪካ የምታገኘው ድጋፍ መስተጓጎል እንደሚገጥመው ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ “በገደምዳሜ መጠቆማቸው” በእናንት በኩል ግምት እንዳለ፣ ወዘተ የሚያትት ነው።

ዜናው መረጃ የሚያስተላለፍ መሆን ሲገባው ግምት፣ መላምት፣ ጠማማነትና ምኞትን የሚገልጽ ሆኖ አግኝቼዋለሁ። ከዚህ ይልቅ ግን የዘነጋው አንድ ትልቅ እውነታ አለ – ጠ/ሚ/ር ዐቢይ ስምምነቱ እንዳይፈረም መመሪያ ስለመስጠታቸው ነው።

ሰኞ ዕለት ጠ/ሚ/ር ዐቢይ በተወካዮች ም/ቤት በኩል ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ባስተላለፉት መልዕክት ላይ “የህዳሴ ግድብ ስምምነት ፊርማ እንዲዘገይ አመራር ሰጥቻለሁ” ብለዋል። ዶ/ር ዐቢይ ረቂቁን ተመለከቱ፣ የትራምፕን፣ የዓለም ባንክ ፕሬዚዳንት እና የአሜሪካውን የገንዘብ ሚ/ር አነጋገሩ፤ ፍላጎታቸው ምን እንደሆነ በስልክ ንግግራቸው ተረዱ፤ ረቂቁ እንዳይፈረም ትዕዛዝ ሰጡ። እንዲያውም በውጭ አገር ከሚገኙ ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች የሚሰጣቸው የሙያ ምክር ጠቃሚ መሆኑን በመጥቀስ ምስጋና ሁሉ አቅርበው ነበር። ይህ ሊያስመሰግናቸውና እናንተም ባወጣችሁት ጽሁፍ መግለጽ የሚገባችሁ ነበር። የኢትዮጵያን ጥቅም አሳልፈን አንሰጥም ነው ያሉት!

የውሃ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስትራችን ዶ/ር ኢንጂነር ስለሺም ረቡዕ ዕለት ለሚዲያ ሰዎች ሲናገሩ “በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ በሚደረገው ስምምነት የኢትዮጵያን በወንዙ የመጠቀም መብት በዘላቂነት በማያስጠብቅ ሁኔታ አንድም ቃል ከተካተተ ኢትዮጵያ” አትፈርምም ነው ያሉት። ይህንንም ጨምረዋል፤ “የግድቡ የውኃ ሙሌትና አለቃቀቅን በሚመለከት ውይይት የተደረገ ሲሆን፥ በተለይም ድርቅ በሚከሰትበት ወቅት የሦስቱን ሀገራት ጥቅም በሚያስጠብቅ መልኩ ተካሂዷል” ነው ያሉት። መቼም ዐቢይን ባታምኗቸው ዶ/ር ስለሺን የምትጠራጠሯቸው አይመስለኝም።

ይህ ሁሉ እውነታ እያለ ኢትዮጵያን ባለዕዳ የሚያደርግ ስምምነት ሊፈረም ነው ብሎ መናገሩ የሚዲያችሁን ተዓማኒነት ትልቅ ጥያቄ ላይ ጥሎታል፤ በተለይ ለእኔ። ሌሎቹንም ዘገባዎቻችሁን በጥንቃቄና በዓይነቁራኛ እንዳነብ ያስገደደኝ ሆኗል። በተለይ እናንተ ከለውጡ ጋር በተያያዘ በአገር በቀል መፍትሔ ፍለጋ ላይ ቀጥተኛ ተሳትፎ እያደረጋችሁ ያላችሁ በዚህ መልኩ ይህንን ዘገባ ማውጣታችሁ “ውይ እንደነ እንትና ዋዜማም …” አስብሎኛል። ልድገመውና – ረቂቁ አልተፈረምም፤ እንዳይፈረም ዶ/ር ዐቢይ ትዕዛዝ ሰጥተዋል። እንደ መሪ ይህ ትክክለኛና ተጠቃሽ ተግባር ነው።

እናንተ በዘገባችሁ ሌላው ያከላችሁት ነገር ኢትዮጵያ ተጽዕኖ እየተደረገባት ነው፤ እነ ዶ/ር ዐቢይም ሊፈርሙ እየተዘጋጁ ነው የሚል ነው። ለዚህም ያቀረባችሁት መላምት ኢትዮጵያ ካልፈረመች አሜሪካ የምትሰጠውን ዕርዳታ መያዣ አድርጋባታለች የሚል ነው። ሌላውና ውሃ የማይቋጥረው መላምታችሁ ትራምፕ ለፍልስጤምና እስራኤል ያቀረቡት የሰላም ሃሳብ “በመላው የዓረቡ አለም ተቀባይነት ባለማግኘቱ” ግብጽ የአረቡ ዓለም ተጽዕኖ ፈጣሪ በመሆኗ ይህንን ሰነድ አረቡ ዓለም እንዲቀበል ካግባባች “(ለ)ውለታዋ የህዳሴ ግድብ እንደ እጅ መንሻ” እንደቀረበላት ነው።

ይህንን በጣም የወረደ አመክንዮ ሆኖ አግኝቼዋለሁ። ሲጀመር የትራምፕን የሰላም ዕቅድ “መላው የዓረቡ አለም” አልተቃወመውም። ሳዑዲ አረቢያ፣ አረብ ኤሜሬትስ፣ ግብጽ፣ ኳታርና ሞሮኮ ከአዎንታዊ አስተያየት እስከ ጥንቃቄ የተሞላበት ድጋፍ ሰጥተዋል። በተለይ ሳዑዲ አረቢያ ከመቼውም በተለየ መልኩ እስራኤልን በመደገፍ መቆሟ አነጋጋሪ ጉዳይ ሆኗል።

ሌላውና ዋንኛው ነጥብ በዚህ የፍልስጤም ተወካይ ወይም መሃሙድ አባስ በሌሎበት ትራምፕና የእስራኤሉ ጠ/ሚ/ር ኔታንያሁ ብቻቸውን ይፋ ያደረጉት “ፕላን” ፍልስጤምን ታሳቢ ያላደረገ የፖለቲካ ቁማር ነው። ኔታኒያሁ ከሙስና እና ማጭበርበር ጋር በተያያዘ ትልቅ ክስ ተመሥርቶባቸው ግራ ገብቷቸዋል። ወር ባነሰ ጊዜ ውስጥ ደግሞ አገር አቀፍ ምርጫ ይጠብቃቸዋል። ለሕዝባቸው “የሚሸጡት” የምርጫ ሸቀጥ ያስፈልጋቸዋል። ለዚህም ደግሞ እስራኤልን በጭፍን ከሚደግፍ ፕላን የተሻለ አይኖርም።

ትራምፕ በዩክሬይን ጉዳይ ከፍተኛ ቅሌት ገጥሟቸው የውጭ ጉዳይ አመራር ላይ ዜሮ ናቸው የሚለው ቁጥር የጨመረበት ወቅት ላይ ናቸው። እጅግ ውስብስብ የሆነውን የፍልስጤምና እስራኤል ጉዳይ ለመፍታት ከመድፈር አልፎ የሰላም ዕቅድ ይዘው ብቅ ማለታቸው የውጭ ጉዳይ ፖለቲካ ላይ በሳል ናቸው ከማስባል ባለፈ ለዚህ ዓመቱ (የፈረንጆች) የአሜሪካ ምርጫ ጥሩ ደጋፊ እንዲያስገኝላቸው ታልሞ የተሠራ ነው። እሳቸውም የራሳቸውን ዕቅድ “የክፍለዘመኑ ስምምነት” በማለት የጠሩት ያለምክንያት አይደለም።

ሌላው ቢቢሲ እንደዘገበው ይህ ዕቅድ ለትራምፕ የዚህ ዓመት ምርጫ ትልቅ ድጋፍ የሚያሰጣቸው ነው፤ በተለይ በ2016ቱ ምርጫ በጭፍን ለደገፏቸው የኢቫንጀሊካል (ወንጌላውያን) ክርስቲያኖች። እነዚህ ኢቫንጀሊካሎች ለእስራኤል ጭፍን ድጋፍ ያላቸው ከመሆን በተጨማሪ ለትራምፕ ምርጫ ትልቅ የገንዘብ ድጋፍ አድራጊዎችም ናቸው። ያለፈውን ዓይነት ድጋፍ በዚህኛው የምርጫ ዘመቻ ለማግኘት ይህንን መሰሉ የመካከለኛው ምስራቅ ዕቅድ ማውጣት ወሳኝ ነው። በዚህ ላይ የትራምፕ ምክትል ማይክ ፔንስና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ማይክ ፖምፔዎ ተጠቃሽ ኢቫንጀሊካል ናቸው።

ይህ የፖለቲካ ጥቅም ከማስገኘት ያላለፈ ምኞት ያለውንና ፍልስጤምን ያላሳተፈ ዕቅድ የተቃወሙትን አረብ አገራት ለማሳመን ከግብጽ ይልቅ ባልተለመደ ሁኔታ ለእስራኤል ልዩ ድጋፍ እያደረገች ያለችውና ዕቅዱን የደገፈችው ሳዑዲ አረቢያ የተሻለችና ዋንኛ ተመራጭ ነች።

ለማንኛውም እናንተ እጃችን ገብቷል ያላችሁትን ረቂቅ፥ የስምምነት ሰነድ ሆኖ እንዳይፈረም ጠ/ሚ/ር ዐቢይ መመሪያ ሰጥተውበታል። ይህ መጠቀስ የሚገባው ትልቅ ሥራ ነው። ዕቅዱን የተቃወሙትን የአረብ አገራት ለማሳመን ግብጽ የተሻለች ነች፤ ይህንንም ካደረገች የአባይን ግድብ ስምምነት እሷን እንዲጠቅም ተደርጎ እንዲወሰን ይደረጋል የሚለውም የዓለምን በተለይም የአሜሪካንና የመካከለኛው ምስራቅ ፖለቲካ ያላገናዘበ ስንኩል “ትንታኔ” ነው።

ዋዜማዎች እንደ አንዳንድ ስም አይጠሬ ጭፍን ሚዲያ እንዳትሆኑ ተጠንቀቁ። ውሃ ሲወስድ እያሳሳቀ ነው።

ባለሙያው ነኝ

Source: http://www.goolgule.com/

Exit mobile version