Site icon Dinknesh Ethiopia

የምግብ ቤት ባለቤቶቹ በማጭበርበር ወንጀል የ1 ሺህ 446 ዓመት እስር ተፈረደባቸው

የምግብ ቤት

ታይላንድ ውስጥ የሚገኝ አንድ ፍርድ ቤት ኅብረተሰቡን አጭበርብረዋል በሚል በሁለት የምግብ ቤት ባለቤቶች ላይ በእያንዳንዳቸው የ1ሺህ446 አመታት እስር በይኗል።

ለዚህም ምክንያቱ ባለፈው ዓመት ሌምጌት የተባለው የባሕር ምግብ አቅራቢ ምግብ ቤት በበይነ መረብ በኩል በቅድሚያ በሚደረግ ክፍያ የምግብ ማስተወወቅ ተግባር አከናውኖ እስከ 20ሺህ ከሚደርሱ ሰዎች 1.6 ሚሊዮን ዶላር የሚደርስ ገንዘብ ሰብስቦ አገልግሎቱን ባለማቅረቡ ነው።

ከዚያም በመቶዎች የሚቆጠሩ ገንዘባችንን ተበላን ያሉ ሰዎች ክስ በማቅረባቸው ምግብ ቤቱ ባለቤቶች የሆኑት አፒቻት ቦዎረንባናቻራክ እና ፕራፓሶርን ቦዎረንባናቻራክ የተባሉት ግለሰቦች ተይዘው ፍርድ ቤት ከቀረቡ በኋላ ነው የረጅም ዘመን እስር የተፈረደባቸው።

በታይላንድ ውስጥ በማጭበርበር ወንጀል ላይ ተሳትፈው የተያዙ ሰዎች ላይ በጣም ረጅም አመታት የእስር ቅጣት መጣል የተለመደ ሲሆን፤ በተለይ በርካታ ሰዎች ክስ ያቀረቡበት ጉዳይ ከሆነ ደግሞ ቅጣቱ ይከብዳል።

በዚህ የማስተዋወቂያ ሽያጭ ምግብ ቤቱ ከባሕር ውስጥ እንስሳት የሚሰራን ምግብ በርካሽ እንደሚያቀርብ ገልጾ የበርካታ ሰዎችን ቀልብ መሳብ በመቻሉ ከአንድ ሚሊዮን ዶላር በላይ ገንዘብ ለመሰብሰብ ችሎ ነበር።

በርካታ ሰዎች በኢንተርኔት አማካይነት ክፍያ ፈጽመው ስለነበረ ቀድመው ግዢውን የፈጸሙት ሰዎች የሚፈልጉትን ያገኙ ሲሆን፤ በኋላ ላይ የገዢው ቁጥር ከፍተኛ በመሆኑ ምግብ ቤቱ በሚፈለገው ፍጥነት ምግቡን ማቅረብ ባለመቻሉ ክፍያውን የፈጸሙ ሰዎች ተራቸው እስኪደርስ ለወራት መጠበቅ ነበረባቸው።

ነገር ግን ከሚችለው በላይ የምግብ ትዕዛዝ የተቀበለው ምግብ ቤቱ በመጋቢት ወር ላይ “አልቻልኩም” ብሎ ድርጅቱን መዝጋቱን አስታወቀ።

የአገሪቱ መገናኛ ብዙሃን እንደዘገቡት ምግብ ቤቱ ግዢውን ለፈጸሙ ሰዎች ገንዘባቸውን እንደሚመልስ አሳውቆ ከ818 ገዢዎች ውስጥ ለ375ቱ ገንዘባቸውን ተመላሽ አድርጓል።

ነገር ግን ቀሪዎቹ በመቶ የሚቆጠሩ ሰዎች በድርጅቱ መጭበርበር ተፈጽሞብናል በሚል በባለቤቶቹ ላይ ክስ መስርተዋል።

በዚህም ሁለቱ የምግብ ቤቱ ባለቤቶች በሐሰተኛ መልዕክት ሕዝብን ማጭበርበርን ጨምሮ በሌሎች ክሶች ተይዘው ታስረዋል።

ክሱን የተመለከተው የታይላንድ ፍርድ ቤት በ723 ሰዎች ላይ በተፈጸመ ማጭበርበር ተከሳሾቹን ጥፋተኛ ሆነው ስላገኛቸው ትናንት ረቡዕ እያንዳንዳቸው ላይ የ1 ሺህ 446 ዓመታት እስር ወስኗል።

ነገር ግን ተከሳሾቹ ጥፋተኝነታቸውን በማመናቸው ፍርድ ቤቱ የእስር ብይኑን በግማሽ ቀንሶላቸው እያንዳንዳቸው ላይ የ723 ዓመት እስር በይኗል። ነገር ግን በአገሪቱ ሕግ መሰረት ግለሰቦቹ የታሰሩት ቢበዛ ለ20 ዓመታት ነው።

ከዚህ በተጨማሪም ምግብ ቤቱ ላይ የገንዘብ ቅጣት የተጣለበት ሲሆን ለቀሪዎቹ ደንበኞችም ገንዘባቸውን መልሶ ካሳም እንዲከፍል ተወስኖበታል።

ከሦስት ዓመት በፊት ይኽው የታይላንድ ፍርድ ቤት አንድ በማጭበርበር ወንጀል የተከሰሰ ግለሰብ ላይ 13 ሺህ ዓመት እስር መፈረዱ ይታወሳል።

ምንም እንኳን ፍርድ ቤቱ ይህንን ውሳኔ ያሳልፍ እንጂ የአገሪቱ ሕግ ሕዝብን በማጭበርበር የተከሰሱ ሰዎች የሚታሰሩበት ጊዜ ከ20 ዓመት እንዳይበልጥ ይገድባል።

Source:  BBC/Amharic

Exit mobile version