Site icon Dinknesh Ethiopia

ኢትዮጵያ ውስጥ በግዙፍነቱ ቀዳሚ የሆነው ሸገር ዳቦ ፋብሪካ ተመረቀ

ሸገር ዳቦ ፋብሪካ

 

አዲስ አበባ (ፋና) – በአዲስ አበባ ከተማ የተገነባውና በሰዓት 80 ሺህ ዳቦ የሚያመርተው ሸገር ዳቦ ፋብሪካ ተመረቀ። በፋብሪካው ምርቃ ላይም ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ኢ/ር ታከለ ኡማን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በምረቃው ላይ ባደረጉት ንግግር፥ ፋብሪካው የዳቦ ፋብሪካ ብቻ ሳይሆን በምግብ ራሳችንን የመቻል ፍላጎታችንን፣ ከድህነት የመውጣት ጥማትን እና የብልፅግና ጎዳናን አመላካች ነው ብለዋል።

በኢትዮጵያ በ10 ወራት ፋብሪካ ገንብቶ ማጠናቀቅ የሚታሰብ አልነበረም፤ በተለይም ለሚድሮክ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ፥ ሚድሮክ ከነበረበት ድክመት ተላቆ ፋብሪካውን በዚህ ፍጥነት ማጠናቀቅ መቻሉ ለሌሎችም ትምህርት የሚሆን ነው ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አክለውም መንግሥት በቀጣይ ሁለት ዓመታት ስንዴን ከውጭ ማስገባት የማቆም ፍላጎት እንዳለው በመግለጽ፤ ለዚህም የሙከራ ምርቶች መጀመራቸውን አስታውቅዋል። ስንዴ ማምረት ብቻ ሳይሆን ምርቶቹን ወደ አግሮ ኢንዱስትሪ መቀየር አስፈላጊ መሆኑንም የገለፁ ሲሆን፥ ለዚህም ለግሉ ዘርፍ ጥሪ መቅረቡን አስታውቅዋል።

መንግሥት ላቀረበው ጥሪ ሼክ መሃመድ ሁሴን አሊ አላሙዲ ፈጣን ምላሽ መስጠታቸውን በመግለፅ፥ ሸገር ዳቦ ፋብሪካ እውን እንዲሆን በማድረጋቸውም ምስጋናቸውን ያቀረቡላቸው ሲሆን፥ የኢትዮጵያ መንግሥት ሁሌም ከጎናቸው እንደሆነ አረጋግጠዋል።

መሰል የዳቦ ማምረቻዎችን ከአዲስ አበባ ውጪ በክልል ከተሞችም ለማቋቋም እየተሠራ መሆኑን እና ለዚህም የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በሌሎች ከተሞች መሰል መለስተኛ የዳቦ ፋብሪካዎችን ለመገንባት እንቅስቃሴ መጀመሯን አስታውቀዋል። በተጨማሪም የዱባይ አልጋ ወራሽ መሐመድ ቢን ዛይድ አልናህያንም ከፍ ያለ ፋብሪካ ቃል መግባታቸውን እና ይህም በቅርቡ ወደ ሥራ የሚገባ መሆኑንም ነው ያስታወቁት።

እነዚህ አሁን የተገነቡ እና ወደ ፊት የሚገነቡ ፋብሪካዎች በቀን ዳቦ ለማግኘት ለሚያዳግታቸው ሕፃናት ዳቦ እንዲያገኙ የሚያስችሉ መሆናቸውን ነው የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ።

“አዲስ አበባን፣ ክልሎችን፣ ኢትዮጵያን ብሎም አፍሪካን እንለውጣለን” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ፥ “ኢትዮጵያ የጀመረችውን በሙሉ ታጠናቅቃለች፤ ይህም በየአደባባዩ እየጮኸች ሳይሆን ሪቫን እየቆረጠች ነው” ብለዋል።

ምክትል ከንቲባ ኢ/ር ታከለ ኡማም፥ ሸገር ዳቦ ፋብሪካ ተገንብቶ እውን እንዲሆን ለተሳተፉ አካላት መስጋና አቅርበዋል። የሸገር ዳቦ ፋብሪካ መገንባት የከተማውን ነዋሪዎች የኑሮ ጫና ይቀንሳል ያሉት ኢ/ር ታከለ፥ በቀጣይም የከተማዋ ነዋሪዎችን ጥያቄ የሚመልሱ ሥራዎችን በማቀድ ወደ ሥራ መገባቱብንም አስታውቅዋል።

የሚድሮክ ኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ አብነት ገብረ መስቀል በበኩላቸው፥ ሜድሮክ ኢትዮጵያ ለአዲስ አበባ እና አካባቢዋ ነዋሪ ሕዝብ በከፍተኛ ጥራት እና በተመጣጣኝ ዋጋ ዳቦ አምርቶ ማቅረብ እንዲቻል ሸገር ዳቦ ፋብሪካን ገንብቶ ለፍሬ አብቅቷል ብለዋል።

በ41 ሺህ ካሬ ሜትር ላይ ያረፈ ፋብሪካው፥ የዳቦ እና የዱቄት ፋብሪካ፣ የሻይ ቅጠል ማቀነባበሪያ እና 120 ሺህ ኩንታል ስንዴ ማከማቸት የሚያስችል 4 ጎተራ እንዳለው አስታውቀዋል። በ6 ሺህ ካሬ ሜትር ላይ ያረፈው የዳቦ መጋገሪያ ፋብሪካው በሰዓት 80 ሺህ ዳቦ የሚያመርት መሆኑን እና በቀን በሶስት ፈረቃ እስከ 2 ሚሊየን ዳቦ የሚያመርት መሆኑ ገልፀዋል።

ሸገር ዳቦ ፋብሪካ ግንባታው በአጠቃላይ በ900 ሚሊዮን ብር ወጪ መከናወኑን ያስታወቁት አቶ አብነት፥ አጠቃላይ ወጪውም በሚድሮክ እህት ኩባንያዎች የተሸፈነ መሆኑንም አስታውቅዋል። ፋብሪካው ከምርት እስከ ማከፋፈል ሂደት ቁጥራቸው 3 ሺህ 400 ለሚደርሱ ዜጎች የሥራ እድል የሚፈጥር መሆኑንም ገልፀዋል።

ምንጭ፦ ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት

Exit mobile version