Site icon Dinknesh Ethiopia

ከኮሮናቫይረስ ያገገሙት የ114 ዓመቱ የዕድሜ ባለፀጋ ማን ናቸው?

aba Tilahun

ምንጭ፡ https://www.bbc.com/amharic/

ሐሙስ እለት ከኤካ ኮተቤ ሆስፒታል ዳይሬክተር የፌስቡክ ሰሌዳ ላይ የተገኘው መረጃ አንድ የ114 ኣመት አዛውንት ከኮሮና ማገገማቸውን የሚያበስር ነበር።

ግለሰቡ ከኮሮናቫይረስ ቢያገግሙም ለተጨማሪ ሕክምና ወደ የካቲት 12 ሆስፒታል መላካቸው በዚሁ መልዕክት ላይ ሰፍሯል። የካቲት 12 ሆስፒታልም የጀመሯቸውን ሕክምናዎች ጨርሰው ያለመሳርያ እገዛ መተንፈስ በመጀመራቸው ወደ ቤታቸው መሄዳቸውን ትናንት ያነጋገርናቸው የሕክምና ተቋሙ ባለሙያዎች አረጋግጠውልናል።

እንዲሁም የልጅ ልጃቸው ቢንያም ለቢቢሲ እንዳረጋገጠው በሙሉ ጤንነት ላይ ሲሆኑ ሆነው በቤታቸው ይገኛሉ።

ለመሆኑ እኚህ የ114 መት አዛውንት ማን ናቸው?

ከኮሮና ያገገሙት የእድሜ ባለፀጋ አባ ጥላሁን ይባላሉ። ወደ እርሳቸውጋር ስንደውል ገና ከሆስፒታል መውጣታቸው ስለነበር ቃለምልልስ ለማድረግ በሚያስችል ሁኔታ አልጠነከሩም። ስለዚህ ከጎናቸው ሆኖ የሚንከባከባቸው የልጅ ልጃቸው ቢንያም ልኡልሰገድም ስለእርሳቸው አጫውቶናል።

አባ ጥላሁን የተወለዱት በቡልጋ ሲሆን ወደ አዲስ አበባ የመጡት በልጅነታቸው ነው። በአሁን ሰዓት የሚኖሩት በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 25 ።

አባ ጥላሁን ወደ አዲስ አበባ በመጡበትና ኑሯቸውን በመሰረቱበት ወቅት በተለያዩ ስራዎች በመሰማራት ሕይወታቸውን መግፋታቸውን ቢንያም ይናገራል። የተለያዩ የኤሌክትሮኒክስ ጥገናዎችን መስራት፣ ቀለም በመቀባት የእለት ገቢያቸውን ማግኘት ብቻ ሳይሆን ነየተካኑበት ሙያቸው ነበር።

በርግጥ ጊዜውን በውል ባያስታውሱትም ከባድ የሆነ የኤሌክትሪክ አደጋ አጋጥሟቸው ስራውን ማቆማቸውንም ቢንያም ለቢቢሲ ጨምሮ አስረድቷል።

ከዓመታት በኋላ ባለቤታቸው ሲሞቱና የልጅ ልጃቸው ሲወለድ አባ ጥላሁን መነኮሱ።

በአሁን ሰዓት አብሯቸው የሚኖረው የልጅ ልጃቸው በቅርብ እንክብካቤም የሚያደርግላቸው መሆኑን ይናገራል።

አባ ጥላሁን ሳል ይዟቸው መኖሪያ ሠፈራቸው በሚገኘው ጤና ጣብያ ሲታከሙ እነደነበር የሚገልፀው ቢንያም፣ የኮሮናቫይረስ ምርመራ ሲደረግላቸው በቫይረሱ በመያዛቸው በመታወቁ ወደ ኤካ ኮተቤ ሆስፒታል በመወሰድ ህክምና ክትትል ጀመሩ።

ኤካ ኮተቤ ሆስፒታል የተለያዩ ሕሙማን ማረፊያ ክፍሎች እንዳሉት ይናገራል። አባ ጥላሁን ይበልጥ ተጋላጭ የሆኑ ሕሙማን የሚታከሙበት ክፍል የነበሩ ሲሆን በሆስፒታሉ የሚገኙ የሕክምና ባለሙያዎች የቅርብ ክትትልና እገዛ እንዳደረጉላቸው ይመሰክራል።

በሆስፒታሉ ገብተው ቤተሰቦቻቸውን ማስታመም የማይፈቀድላቸው ግለሰቦች የቤተሰቦቻቸውን ዜና የሚያቀብል፣ የሚያመጡላቸውን ምግብና የሚጠጣ ነገር ተቀብሎ የሚያደርስ ሰው መመደቡንም ያስረዳል።

የህክምና ክትትል ያደረጉላቸው ባለሙያዎች ምን ይላሉ?

አባ ጥላሁንን በቅርበት ካከሟቸው የሕክምና ባለሙያዎች መካከል አንዱ ዶ/ር ሕሉፍ አባተ ነው።

ዶ/ር ሕሉፍ ፣ አባ ጥላሁን እድሜያቸው 114 መሆኑን የሚያሳይ መረጃ ማግኘት ይከብዳል ሲል ለቢቢሲ ገልጿል። በእርሳቸው እድሜና ትውልድ ውስጥ የሚገኝ ግለሰብ የልደት ሰርተፍኬት እንዲሁም ሌሎች የእድሜ ማረጋገጫዎችን ማቅረብ ስለማይችል በሰነድ ማረጋገጥ ከባድ ነው ሲልም ሃሳቡን ያጠናክራል።

ነገር ግን ይላል ዶ/ር ሕሉፍ በእርሳቸው እድሜ የሚገኝ ሰው የእጅና እግር መገጣጠሚያዎች እና ጡንቻዎች በማየት እድሜያቸው ከ100 በላይ መሆኑን እርግጠኛ እንደሚሆን ይመሰክራል።

አባ ጥላሁን በቲቢ ተጠቅተው ስለነበር ተደጋጋሚ ምርመራ ተደርጎላቸው ከኮሮናቫይረስ ነጻ ከሆኑ በኋላ ወደ ካቲት 12 በመሄድ የቲቢ ህክምና ክትትል ተደርጎላቸዋል።

ከኮሮናቫይረስ አገግመው ወደ የካቲት 12 ሆስፒታል ለተጨማሪ ሕክምና ተልከው የነበሩት የ114 ዓመት አዛውንት ሕክምናቸውን ጨርሰው መውጣታቸውን ለቢቢሲ ያረጋገጡት በየካቲት ሆስፒታል የውስጥ ደዌ ህክምና ስፔሻሊስት የሆኑት ዶ/ር ሊያ ፋንታሁን ናቸው።

ዶ/ር ሊያ በየካቲት ሆስፒታል ለግለሰቡ ሕክምና ሲያደርጉ እንደነበር ገልፀው፣ ግለሰቡ ያለ መሳሪያ ድጋፍ መተንፈስ በመቻላቸውና የነበሩባቸውን ኢንፌክሽኖች በመታከማቸው ከሆስፒታል መውጣታቸውን ገልፀዋል።

ግለሰቡ እድሜያቸው 114 ይሆናል ተብለው የተጠየቁት ዶክተሯ ” የ114 ዓመት አዛውንት ናቸው። ልጆቻቸውም የልጅ ልጆቻቸውም አብረዋቸው አሉ” ሲሉ መልሰዋል።

በኢትዮጵያ እስካሁን የተደረገው የኮቪድ-19 የላብራቶሪ ምርመራ 232,050 ሲሆን 5,175 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል።

81 ሰዎች ከቫይረሱ ጋር በተገናኘ ህይወታቸው ሲያልፍ 1,544 ሰዎች ደግሞ ማገገማቸውን የጤና ሚኒስቴር መረጃ ይገልፃል።

በአሁን ሰዓት ቫይረሱ ያለባቸው 3 ሺህ 548 ሰዎች ሲሆኑ 30 ሰዎች በፀና ታመው የህክምና ክትትል እየተደረገላቸው እንደሚገኝ የጤና ሚኒስቴር ሪፖርት ጨምሮ ያሳያል።

Exit mobile version