Site icon Dinknesh Ethiopia

ሐዋርያ- ዜግነታቸውን የቀየሩ ፖለቲከኞች ጣልቃ ገብነትና የመንግሥት ዝምታ – ከበየነ ከበደ

hawarya

ምንጭ። ሐዋርያ : HAWARYA facebook

ስደት ቅጣት ቢሆንም እንኳን ጠቃሚ ቁሳቁሶችንና ገንዘብን ወደ ደሃ አገሮች በማሻገር ረገድ ጥቅም አለው። አንዲት ሃገር እድለኛ ከሆነች በስደት የሚገኙ ልጆችዋ ቴክኖሎጂና ሳይንስ ይልኩላታል። ስደተኛ በሚኖርበት ሃገር ላይ ህግን ተመርኩዞ የትውድል ሃገሩን አምባገነን ሥርዓት በመታገል ረገድም ትልቅ አስተዋጾ ያደርጋል። በቦሌ በኩል ከወጡት ጥቂት ባለሃብቶች በቀር በርካቶች ለምዕራቡ ዓለም ነዋሪነት የበቁት ማንነታቸውን ሸጠው ብቻ አይደለም፣ እጅግ ከፍተኛ የሕይወት መስዋዕትነት ጭምር ከፍለው ነው። ለአስከፊው ስደት የተዳረጉ አንድ ሚኒስቴር ወይም ጄኔራል ቀድሞ ዋልጌ ከነበረ ስደተኛ ጋር ነው አብረው ነው በስደቱ አግዳሚ ወንበር ላይ የሚቀመጡት። የምዕራቡ ዓለም ዴሞክራሲ ሁለቱንም እኩል አድርጓቸዋል። ይህን የሞነጫጨርኩት ስለ ስደት ለመጻፍ ሳይሆን ዜግነታቸውን የቀየሩ ፖለቲከኞች ሃገር ሲያምሱ ስመለከት አዝኜ ነው።

በአምባገነን መሪዎች ቁም ስቅሏን የምታየው ኢትዮጵያ አሁን ደግሞ ልጆቿን በመሰሉ የውጭ ዜጋ ፖለቲከኞች እየታመሰች ትገኛለች። አማሺዎቹ አይደሉም ጥፋተኞች፣ እንዲያምሱ ፈቃድ የሠጣቸው መንግሥት እንጂ። ባለፈው ጊዜ በሻሸመኔ ተዘቅዝቆ ሲገደል ዝም ያለ መንግሥት፣ በአርሲና በባሌ ኦርቶዶክሶችንና አማሮችን በአሰቀቂ ሁኔታ እንዲገደሉ አደረገ። በዚህ አልበቃም – በቅርብ በአርሲ፣ ሻሸመኔ፣ ባሌና አንዳንድ ቦታዎች ላይ አሁንም ከተሞች እስኪነዱ ድረስ በኦርቶዶክሶችና አማሮች ላይ እጅግ የከፋ ዘግናኝ ግፍ እስኪፈጸም ድረስ መንግሥት ዝም አለ። እጅግ ያሳዝናል።

አንድ ዜግነቱን የቀየረ ስደተኛ ተከበብኩ፣ ተነካሁ ስላለ ብቻ ኢትዮጵያ ብዙ ግፍ ተፈጸመባት። ምናልባት በሃገራችን ላይ የደረሰው ይህ ዓይነቱ ግፍ በግራኛ መሃመድ ወረራ ዘመን ተፈጽሞ ይሆናል። ዶክተር አብይ አንድ የፖለቲካ እምነት አላቸው። “እስኪ ይሂድ የት ይደርሳል” ይላሉ። ዶክተር አብይ ሌላም መርህ አላቸው። “እስኪ ይግደል፣ ስንቱን ገድሎ ይጨርሳል” የሚል ነው። አንድ ስደተኛ – ቢሄድ ቢሄድ– ቢገድል ቢገድል – እሳቸውን እንደማይነካ ያውቃሉ። የዶክተር አብይ ሁለቱም መርሆ ግን አዋጪ አልነበሩም። ስደተኛው ሄዶ ሄዶ – ገድሎ ገድሎ – እሳቸው እሚሰበሰቡበት አዳራሽ ድረስ ተጠጋ። አሁን ፈሩ። እንደዋዛም ዘብጥያ ወረወሩት።

ከአምስት መቶ በላይ የሰው ሕይወት ዘግናኝ በሆነ ሁኔታ ሲጠፋ እንዲሁም ከተሞች እንደ አሌፖ ሲጋዩ ዝም ያሉት ዶክተር አብይ እራሳቸውን መጠበቅ ግን ይችሉበታል። ስደተኛው ሌላውን ይግደል እንጂ እሳቸውን እንደማይነካ በድንግዝግዝም ቢሆን አውቀዋል። በእርግጥ ዳክሮ ዳክሮ እመዳፋቸው ላይ ወደቀላቸው። የሚገርመው ሌላ ነው። ስደተኛው – ሄዶ ሄዶ – ገድሎ ገድሎ – ዶክተር አብይ ዘንድ መድረስ እንደማይችል ግን “ኢትዮጵያዊ ነው፣ መልኩ እኛን ይመስላል” ብለው የፓርቲያቸው አባል ያደረጉት እውቁ ፕሮፌሰር መራራ ጉዲና ግን አንዳች አልተጠራጠሩም። ስደተኛው መግደልና ከተማ ማቃጠል ብቻ አይደለም ክህሎቱ ስንቶች የሚያከብሯቸውን ዶክተር መራራንም ከጥቅም ውጭ አድርጓል።

ሉዓላዊት ኢትዮጵያ የብዙ ዓመታት ኅልውና ታሪክ እንዳላት የሚያውቁት ዶክተር መራራ የኢትዮጵያን ታሪክ ከአጼ ሚኒልክ እንዲጀምሩ ያሳሳታቸው ስደተኛው ፖለቲኛ ይሆን? ዶክተሩ እሺ ትርክቱን ከቀዳማዊ ሚኒልክ ወይም ከአጼ በካፋ አይጀምሩ – ቢያንስ ቢያንስ ግን ከአጼ ዳዊት አልያም ከአጼ ልብነ ድንግል መጀመሩ ለምን አስፈራቸው? ምንድነው ምክንያቱ ጽንፈኞችን ባጼ ሚኒልክ ስም ላይ ላይ የቸከላቸው? ሃገሪቱን ከቅኝ ገዝዎቹ ኃይላት ታድገው ማቆየታቸው ነው እንዴ አጼ ሚኒልክና ፊታውራሪ ጎበና ዳጬን ጥምድ ያስደረጋቸው? አጼ ሚኒልክ፣ እቴጌ ጣይቱ፣ ራስ መኮንን፣ ራስ ጎበና ዳጬ፣ ፊታውራሪ ኃብተጊዮርጊስ፣ ባልቻ አባ ነፍሶ፣ ወዘተ፣ ባይዋጉ እኮ እንድሌሎቹ አፍሪካ ሃገሮች ቅኝ ተገዢዎች ነበርን። የዘንድሮ ፖለቲከኞች አንድ ችግር ደርሶባቸው ይሆናል እንጂ ይህን እውነት ከኢትዮጵያዊ አብራክ የወጡ ሁሉ አያውቁትም ማለት አይቻልም

ጥቂት ፖለቲከኞች እየተሳሳቱ ነው። የትንተና ስህተት አይደለም የተጠናወታቸው። በሉዓላዊ ሃገርና አንድ ወቅት ገዢ ሆነ ባለፈ ሰው መካከል ያለውን ልዩነት ማወቅ አልቻሉም። ምን ነካቸው? ስደተኛው ፖለቲከኛ አፍዝ አደንዝዝ አድርጎባቸው ከሆነ መፍትሄው ፈውስ ብቻ ነው። ሕዝቡ በእነሱ ምክንያት ለምን መራር መከራ ይጨድ? መንግሥትና የብሔራው አስመራጭ ኮሚቴው ሊያስተውሉ ይገባል።

የውጭ ሃገር ዜግነት የያዙ ሰዎች በአንዲት ሉዓላዊት ሃገር ፖለቲካ ውስጥ ጣልቃ መግባት አይችሉም። እንኳንስ ወደ ትውልድ ሃገራቸው መጥጠው በወሳኝ ጉዳዮች ላይ መፈትፈት ይቅርና እተሰደዱበት ሃገር ሆነው የትውልድ አገራቸውን ጥቅም የሚፈታተን ነገር መፈጸም አይችሉም። ቢፈጽሙ እንኳን መንግሥት ከሚኖሩበት ሃገር መንግሥት ጋር ተነጋግሮ የጋራ ውሳኔ ላይ መድረስ ይችላል። አሁን በዛ – ስደተኛው ፖለቲከኛ ዘብጥያ ወረደ ብለው የመኖርያ ፈቃድ ለማግኘት የኤምባሲዎችን አጥር ዘለው ገብተው ባንዲራ የሚቀዱ ስደተኞችን አደብ ማስያዝ ይገባል። ማንም ህጉ በፈቀደ መጠን ተቃውሞ ማድረግ ይችላል፣ ደሆችን በግፍ ያስገደለን ሰው ግን “ይፈታ” ብሎ ባንዲራ እስከ መቅደድ መድረስ አግባብ አይደለም። ሌላው ቀርቶ የስደት ጥያቄ ያቀረቡለት ሃገርም ቢሆን እነዚህን ጋጠወጦች እንደዋዛ እንዳያያቸው አስተያየት መለገስ ይገባል።

ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር

 

Exit mobile version