Site icon Dinknesh Ethiopia

ስዊድን- ቁርዓንን የማቃጠል ዘመቻ መካሄዱ በስዊድን ቁጣን ቀሰቀሰ

ስዊድን

በስዊድን ካለፈው አርብ ጀምሮ ተቃውሞ ተነስቷል፡፡ መነሻው ደግሞ ነጭ አክራሪዎች ቁርዓንን የማቃጠል ዘመቻ ማድረጋቸውን ተከትሎ ነው፡፡

ድርጊቱን የተቃወሙ አደባባይ ወጥተው ከፖሊስ ጋር ተጋጭተዋል፡፡

ተቃውሞው በዋናነት የተቀሰቀሰባት ከተማ የደቡባዊ ስዊድኗ ማልመ ከተማ ናት፡፡

ሱቆችና መኪናዎች በሰልፈኞች ነደዋል፡፡ ሰብአዊ ጉዳቶችም ደርሰዋል፡፡ አሁን ተቃውሞውን ፖሊስ በቁጥጥር እንዳዋለው ተዘግቧል፡፡

10 ሰዎች ከተቃውሞ ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ሥር ውለዋል፡፡

ቁርአን የማቃጠሉ ተግባር የተፈጸመው ባለፈው አርብ በማልመ ከተማ ሮዘንጋርድ አካባቢ ሲሆን ሙስሊምና ጥቁር ጠል የሆኑ አክራሪ ነጭ ብሔርተኞች የተሳተፉበት ነበር፡፡

የቀኝ አክራሪው ዴንማርካዊ ፖለቲከኛ ራስመስ ፓሉዳን የሚመራው ክንፍና ደጋፊዎች በማቃጠሉ ተግባር ተሳትፎ ያደረጉት ራስመስ በዕለቱ ንግግር እንዲያደርግ ሲጠበቅ ነበር፡፡

ሆኖም ሚስተር ራስመስ ከዴንማርክ ወደ ስዊድን ለመግባትና በመርሐግብሩ ለመታደም ሲሞክር ፖሊስ ከድንበር መልሶታል፡፡

የስዊድን ፖሊስ ቀኝ አክራሪውንና ዝነኛውን የሙስሊምና የጥቁር ስደተኛ ጠል ሚስተር ራስመስን ከድንበር የመለሰው ስዊድን እንዳይገባ የ2 ዓመት ገደብ ስለተጣለበት ነው፡፡

ቀኝ አክራሪው ሚስተር ራስመስ በፌስቡክ ገጹ ላይ ወዲያውኑ ባሰራጨው መልእክት ‹‹እኔ አውሮጳዊው እንዳልገባ ተደረኩ፤ ሴት ደፋሪዎችና ወንጀለኞች (ስደተኞች) ግን ሁልጊዜም እንክብካቤ ይደረግላቸዋል›› ሲል ጽፏል፡፡

በዴንማርክ የጥቁርና ሙስሊም ጠል አክራሪ ፓርቲ (ስትራም ኩርስ) ሊቀ መንበር የሆነውን ሚስተር ራስመስ በዚህ ዓመት ጥላቻን በመስበክ ክስ አንድ ወር እስር ተፈርዶበት ነበር፡፡

Souce: bbc.com/amharic

Exit mobile version