Dinknesh Ethiopia

“ከ 40,000 በላይ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ከትግራይ ወደ ሱዳን ገብተዋል” የተመድ ስደተኞች ኮሚሽን

*** በጦርነቱ ሳቢያ የረድኤት ሠራተኞች ከትግራይ ለቅቀው እየወጡ ነው።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከፍተኛ የስደተኞች ኮሚሽን በፌዴራልና በትግራይ ክልል መንግሥታት መካከል ተቀስቅሶ ለሁለት ሳምንታት ያህል እየተካሄደ ባለው ወጊያ ሳቢያ በቀን በአማካይ ከ4000 በላይ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ከኖቬምበር 10 ወዲህ የሱዳንን ድንበር እየተሻገሩ መሆኑ የሰብዓዊ ዕርዳታ ቀውስ ያሳሰበው መሆኑን ገልጧል።

የተመድ ከፍተኛ የስደተኞች ኮሚሽን ቃል አቀባይ የሆኑት ባባር ባሎች ሁነቱ የሰብዓዊ ቀውሱን ወደ ላቀ ደረጃ እያመራው መሆኑን ጠቁመው በኮሚሽኑ በኩል “የእርዳታው አስፈላጊነት በጨመረ ቁጥር ሰብዓዊ ዕገዛውን ከፍ እያደረገ” ያለ መሆኑን አስታውቀዋል።

tigray
Ethiopian refugees gather in Qadarif region, eastern Sudan –
AP

በጦርነቱም ሳቢያ የረድኤት ሠራተኞች ክልሉን ለቅቀው እየወጡ ይገኛሉ።

አንድ ዲፕሎማት አክለውም ከጦርነቱ በፊት በርካታ የትግራይ ክልል ነዋሪዎች የእርዳታ ምግብ እየተደጎሙ ያሉ እንደነበር፣ በዚህ ሳምንት ውስጥ 600 ያህል አብዛኛውን የውጭ አገር ዜጎች በሁለት ኮንቮይ አዲስ አበባ የገቡ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለም፤ የፌዴራል መንግሥቱ ትናንት ኅዳር 8 ይፋ ባደረገው መግለጫው “በምሥራቅ ግንባር ራያ ሙሉ በሙሉ ነፃ ወጥቷል። ጨርጨር፣ ጉጉፍቶ መሖኒን ሠራዊቱ ነፃ አውጥቷል። በአሁኑ ጊዜ ወደ መቀሌ በመገስገስ ላይ ነው” እንደሆነና በምዕራብ ግንባር “በአዲ ነብሪድና በአዲ ዳዕሮ የሚገኙ ከባድ ምሽጎችን በማፍረስ ሽሬን ተቆጣጥሮ ወደ አክሱም በመገስገስ ላይ ይገኛል” ብሏል። ለጊዜው በሕወሓት በኩል የፌዴራል መንግሥቱ ተቆጣጥሬያቸዋለሁ ያላቸውን ሥፍራዎች አስመልክቶ የተሰጠ ምላሽ አልተደመጠም።

Souce: https://www.sbs.com.au/

Exit mobile version