Site icon Dinknesh Ethiopia

“እየደበደቡ፤ በሳንጃ አንገታቸውን እየቀሉ ሲገሏቸው ተመልክቻለሁ” – የማይካድራው ጭፍጨፋ የዓይን እማኝ

ወጣት ዳንኤል ማሚን።

መላ ሰውነቱ ይንቀጠቀጣል፤ ከንፈሩ ደርቋል። ለሁለት ቀናት ምግብ አላገኘም። ድንጋጤ አለቀቀውም። ከማይካድራ ግድያ አምልጦ ሁመራ ከተማ መከላከያ ሠራዊት ካምፕ በር ላይ ያገኘነው ወጣት ዳንኤል ማሚን።

የደቡብ ክልል የቴፒ ተወላጅ ነው፤ አገር ሰላም ብሎ በማይካድራ ልብስ እየነገደ መኖር ከጀመረ 13 ዓመት ሆኖታል። በዚች ከተማ ይህን ያህል ሲኖር የከፋ አይደለም፤ ቀለል ያለ ችግርም አጋጥሞት አያውቅም። በሚኖርባትና ህይወቱን ለማሻሻል በሚደክምባት ከተማ ቤትና ንብረትም አፍርቷል።

ከሰባት ቀናት በፊት ከቀኑ 9 ሰዓት አካባቢ በማይካድራ ከተማ በአማራና በሌሎች ብሄሮች ተወላጆች ላይ ያልታሰበ፣ አስደንጋጭና ዘግናኝ ግድያ ሲፈጸም በዓይኑ ተመልክቷል፤ እሱም ከዚህ ዘግናኝ ጭፍጨፋ አምልጦ በመከላከያ ሠራዊት ቁጥጥር ስር ወደ ዋለችው ሁመራ ከተማ መምጣቱን ይናገራል።

የትግራይ ልዩ ኃይልና ሚሊሻዎች በአማራና በሌሎች ብሄሮች የፈጸሙት ግፍና ግድያ በጣም የሚያስደነግጥ ያልታሰበ ነበር የሚለው ወጣቱ፤ በትግራይ ክልል ማይካድራ ከተማ በምንኖር ንጹሐን ሰዎች ላይ በትግራይ ሚሊሻዎችና ልዩ ኃይሎች ዘግናኝ ጥቃት ይደርስብናል ብለን አስበንም አልመንም አናውቅም። ግን የጭካኔያቸው ጭካኔ በከተማዋ በሚኖሩ አማራን ጨምሮ በሌሎች ብሄሮች ዘግናኝ ድርጊት ፈጸሙ ይላል።

“መጀመሪያ ላይ ጥቃቱን የጀመሩት በወልቃይት አማራዎች ላይ መሆኑን የሚገልጸው ወጣት ዳንኤል ንጹሐን ሰዎችን በየመንገዱ እየደበደቡ፤ በሳንጃ አንገታቸውን እየቀሉ ሲገሏቸው ተመልክቻለሁ። ሰው ሮጦ እንዳያመልጥ እንኳን መንገዱ በሚሊሻ ተከቧል። ሩጠው ለማምለጥ የሚሞክሩትን በጭካኔ በጥይት እየመቱ ገድሏቸዋል” ብሏል።

በአይኔ ሰው ሲገደል አይቻለሁ። እኔም የዳንኤል ቤት የትኛው ነው እያሉ ሲጠይቁ ሰምቼ ሩጬ ማምለጥ ችያለሁ የሚለው ወጣቱ፤ በዚህ ቀውጢ ስዓት እሱም ሆነ ብዙ በርካታ ሰዎች እየሮጡ ጫካ ባይገቡና ባያመልጡ ኖሮ በማይካድራ ከተማ በግፍ እንደተገደሉት ንጹሐን ሰዎች ሁሉ የእሱም ዕጣ ፋንታ በህወሓት አሸባሪ ቡድን ይገደል እንደነበር ነግሮናል።

ሰዎች ሲገደሉ በዓይኑ ማየቱን የሚገልጸው ወጣት ዳንኤል ሁለቱ ከድብደባው ለማምለጥ ሲሮጡ በጥይት ሁለቱ ደግሞ በሳንጃ አንገታቸውን ተወገተው አስፓልት ላይ ሲወድቁ እግሬ አውጪኝ ብሎ ከአካባቢው ተሰውሮ ጫካ መግባቱን ንግሮናል። ሰው በጭካኔ እየተገደለ ባየሁበት ከተማ ለመኖር አልጓጓም ያለው ወጣቱ ከሁመራ ወደ ጎንደር ከዚያም ወደ ትውልድ አገሩ ቴፒ ለመሄድ መወሰኑን ገልጾልናል።

ወጣት ዳንኤል፤ በትግራይ ክልል ማይካድራ ከተማ የህወሓት ጸንፈኛ ቡድንን ያልደገፈ የሚደርስበት ጫና እንግልት ከፍተኛ መሆኑን ይናገራል። ለትግራይ ልማት የሚሆን ገንዘብ አዋጣ ሲሉኝ 100.00 ብር አዋጣሁ። ሁለተኛ ዙርም ለውጊያ አዋጣ አሉኝ። እኔም ውጊያውን ስለማላምንበት ብር የለኝም አልኳቸው። ለካስ ያላዋጣነው ሰዎች የቀበሌው የህወሓት ተላላኪዎች የስም ዝርዝራችንን ይዘው ኑሯል፤ ጊዜ ጠብቀው የበቀል ጭካኔያቸውን አወረዱብን።

“በየመኖሪያ ቤታችን እየዞሩ እስከ ወዲያኛው ሊያስናብቱን እየገሰገሱ መጡ። እግዚአብሔር አትርፎኝ ይኸው ሁመራ ከተማ አግኝተኸኛል” ሲል የጭካኔያቸው ጥግና የበቀል ዕርምጃቸው ከባድ መሆኑን ገልጾታል።

ማይካድራ ከተማ ውስጥ የሚኖር ማንኛውም የከተማው ነዋሪ ከትግራይ ቴሌቪዥንና ከወያኔ ድምፅ ቴሌቪዥን በስተቀር ሌሎች የቴሌዥን ጣቢያዎችን ማየት ወንጀል ነው የሚለው ወጣቱ፤ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን፣ ዋልታ፣ ፋና ቴሌቪዥንና ሌሎች ህወሓት የሚጠላቸውን የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ማየት ፈጽሞ የተከለከለና የሚያስቀጣ ነው። ሲያይ የተገኘም ካለ በህይወቱ የፈረደ ሰው ብቻ ነው ይላል።

ማይካድራ በመከላከያ ሠራዊት ቁጥጥር ስር ውሏል ማይካድራ ለምን አትምለስም የሚል ጥያቄ አቅርበንለት የወጣቱ ምላሽ ሌላ አካባቢ ሊስትሮም ቢሆን ሠርቼ መኖርን እመርጣለሁ እንጂ ሁለተኛ ትግራይ ክልል አልኖርም። ምክንያቱም ያየሁት የጭካኔ አገዳዳል ሌሊት በህልሜ ይመጣብኛል። ዘግናኝ ነው። ይህን እያስብኩ እዚያ ከተማ መኖር አልፈልግም። ህይወቴ ተመሰቃቅሏል ሲልም ያየው የጭካኔ ተግባር የቱን ያህል እንደጎዳው፣ ከቃላቶቹ በላይ ሁኔታውን ሲያስታውስ የሚሰማው ስሜት ይናገራል። (በጌትነት ምህረቴ፤ አዲስ ዘመን ህዳር 8 ቀን 2013 ዓ.ም)

ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ

 

በበረሃ ዘመኑ ህወሃት ካወደማቸው በጥቂቱ

Exit mobile version