Site icon Dinknesh Ethiopia

ኢሕአፓ, መኢአድ, አብንና, አትፓ በሱዳን የተወረረውን መሬት ለማስመለስ ሁሉንም አማራጭ እንደሚጠቀሙ ተቃዋሚ ፓርቲዎች አስታወቁ

parties

በሀይማኖት ግርማይ                       መጋቢት 30 ፣ 2013

ኢትዮጵያ እና ሱዳን የሚወዛገቡበትን የድንበር ላይ የግዛት ይገባኛል ጥያቄ በተመለከተ በሕዝብ ይሁንታ ተመርጠው ሥልጣን ቢይዙ ለጉዳዩ እንዴት እልባት ሊሰጡት እንደሚችሉ በ6ተኛው ብሔራዊ ምርጫ ላይ ለሚወዳደሩ አራት የፖለቲካ ፓርቲዎች አዲስ ዘይቤ ጥያቄ አቅርቧል።

አዲስ ዘይቤ ጥያቄ ያቀረበላቸው የፖለቲካ ፖርቲዎች የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን)፣ የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ)፣ የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) እና አዲስ ትውልድ ፓርቲ (አትፓ) ናቸው።

“ስርነቀል የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ለውጥ እናደርጋለን” በማለት ንግግራቸውን የጀመሩት የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የውጭ ጉዳይ ኃላፊ አቶ ቴዎድሮስ ኃ/ማርያም (ዶ/ር) ፓርቲያቸው “የችግሩ አንደኛው መንስዔ ፓሊሲው የአገርን ሉዓላዊነት አሳልፎ የሚሰጥ፣ ሕዝብን ያላማከለ መሆኑ፣ የተለያዩ መዋቅራዊ ችግሮች ያሉበት እና በተለያዩ የዓለምአቀፍ መድረኮች ለሽንፈት ያበቃ እንዲሁም አገሪቱን ወደ ኋላ ያስቀረ ስርዓት እንደሆነ ያምናል” ብለውናል።

“ይህ ፖሊሲ ለአገር ተቆርቋሪ ካለመሆን አልፎ የሚደራደር እና መሬት ቆርሶ እስከመስጠት የሚደርስ ነው” የሚሉት የውጭ ጉዳይ ኃላፊው “ነገር ግን አሁን የገጠመን ጉዳይ አስቸኳይ መፍትሄ የሚሻ ስለሆነ በመጀመሪያ የጋራ ጥቅም፣ ታሪክ  እና የዓለምአቀፍ  ሕግን መሰረት በማድረግ በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ይሞከራል፤ ካልሆነ ግን የአገርን ሉዓላዊነትን ለማስከበር በወታደራዊ ኃይል መወጣት ያስፈልጋል” ሲሉ ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል። “አማራ እና ኢትዮጵያ የማይነጣጠሉ ናቸው” የሚሉት ቴዎድሮስ ኃ/ማርያም (ዶ/ር) “ጉዳዩ የክልል ሳይሆን አገራዊ ነው” ሲሉ ያነሳሉ።

የአዲስ ትውልድ ፓርቲ (አትፓ) የፖለቲካ ዘርፍ ባለሙያ አቶ ሞሐመድ ዑመር በኢትዮጵያ እና ሱዳን መካከል የተፈጠረውን የድንበር ላይ የግዛት ይገባኛል ጥያቄ በተመለከተ ፓርቲያቸው ጉዳዩን እስከ መጨረሻው ድረስ በውይይት ለመፍታት እንደሚሞክር ገልጸው ነገር ግን በውይይት የማይፈታ ከሆነ ወታደራዊ የአፀፋ ምላሽ እንደሚሰጡ ተናግረዋል። እንደ አቶ ሞሐመድ ዑመር ገለፃ ከሆነ የሱዳን ድንበር አልፎ ወደ ኢትዮጵያ መግባት ከግብጽ እና አባይ ጉዳይ ጋር እንደሚያያዝም ፓርቲያቸው ያምናል። ይህም ግብፅ ለተለያዩ አገራት ኢትዮጵያ ውሃ ልታሳጣን ነው ብላ መናገሯ አንዱ ማሳያ ነው ይላሉ። “አገሪቱ እስካሁን ተደፍራ መቆየቷ ሕዝቡንም እኛንም ያሳዘነ ነው” ሲሉ አቶ ሞሐመድ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢህአፓ) የውጭ ግንኙነት ኃላፊ አቶ መዝገቡ ፋንታሁን በበኩላቸው ጉዳዩን እንደሚያወግዙት ከተናገሩ በኋላ በቅደም ተከተል በኢጋድ፣ የአፍሪካ ኅብረት እና ዓለምአቀፍ ሕግ ችግሩን ለመፍታት ይሞከራል ብለዋል።

ከሠላማዊ ድርድር (ዲፕሎማሲያዊ) አፈንግጦ የሚወጣ ኃይል ካለ ግን ፓርቲያቸው እንደማይታገስና ጦርነት ተወዶ የሚገባበት ጉዳይ ባይሆንም ሳንወድ በግድ እነርሱ በፈለጉት መንገድ ወደ ጦር እንገባለን በማለት የመጨረሻ አማራጭ ያሉትን ሃሳብ አስቀምጠዋል። ከሱዳን በስተጀርባ ሆና እንደ ሁለተኛ እጅ የምትጠቀምባት ግብፅ እንደሆነች የሚናገሩት ኃላፊው የአባይ ግድብ እንዲያስተጓጉል ግን በፍፁም አንፈቅድም ሲሉ ገልጸዋል።

“ሁኔታው ግራ የሚያጋባ ነው፤ የአባይ ግድብ ግንባታ ለወረራው መንስዔ ሊሆን አይችልም፤ ምክንያቱም በሱዳንም ሆነ በግብጽ ላይ የሚፈጥረው አሉታዊ ተፅዕኖ የለም” የሚሉት የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ሊቀ-መንበር አቶ ማሙሸት አማረ “ሱዳን በኢትዮጵያ ሲተዳደር የነበረን ግዛት መውረሯ የሱዳን መሬት ነው በሚል አልያም በግብጽ ግፊት ወይም ከአባይ ጋር በተያያዘ ምክንያት አይደለም” ይላሉ። እንደ ሊቀ-መንበሩ አስተያየት “በቀደመው መንግስት (ኢህአዴግ) መሬት ለሱዳን ሊሰጥ መዋዋሉን ሱዳን እንደምትናገር አንስተው የዚህ እውነተኝነት ተረጋግጦ መፍትሄ ሳይሰጥ መንግስት ዳር ድንበር አስደፍሯል” ሲሉ ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል።

“ኢትዮጵያ ለሱዳን መሬት ቆርሳ ለመስጠት ተፈራርማለች ለሚለው ጉዳይ ፓርቲያቸው ሥልጣን ከያዘ መፍትሄዎች አበጅቷል” የሚሉት ሊቀ-መንበሩ “በቅድሚያ የተባለው ስምምነት መኖሩን ያረጋግጣል፤ ስምምነቱ ካለ የተፈፀመው ሕዝቡ ሳያውቀው፣ ዲፕሎማቶች ሳይወያዩበትና ሳይሳተፉበት፣ የታሪክ አዋቂዎች ያላወቁት፣ መረጃ እና ማስረጃ ያለተሰባሰበበት እንዲሁም የፓለቲካ ድርጅቶች (ተፎካካሪዎች) ሳያውቁ የተደረገ በመሆኑ አገራዊ አይሆንም” ብለዋል።

“ለኢትዮጵያ ከሱዳን የቀረበ ለሱዳን ደግሞ ከኢትዮጵያ የቀረበ ጎረቤት የለም” የሚሉት የመኢአድ ሊቀ-መንበር “በድንበር አካባቢ ያለው ሕዝብ በማኅበራዊ ግንኙነት የተሳሰረ እና ተመሳሳይ ቋንቋ የሚናገር ማኅበረሰብ ነው፤ በፓለቲካው ምክንያት ኅብረተሰቡ መጎዳቱ ያሳስበናል” ሲሉ ተናግረዋል።

“ኢትዮጵያ በጦር ተዳክማለች ተብሎ ቦታን ወሮና በጠመንጃ ይዞ ድርድር ልክ አይሆንም” የሚሉት አቶ ማሙሸት “በአገር ጉዳይ ቀልድ የለም፤ በሕዝባዊ ተሳትፎ መሬቷን፣ ክብሯን እና ሉዓላዊነቷን እናስጠብቃለን” በማለት ገልጸዋል። “ኢትዮጵያም ሆነች ሱዳን በምርጫ ሳይሆን በጉልበት ወደ ስልጣን የሚወጣባቸው አገራት ስለሆኑ መንግስታት በተቀያየሩ ቁጥር የድንበር ጉዳይ ችግር እንዳይሆን ለቀጣዩ ትውልድ ጭምር በሠነድ የተቀመጠ መፍትሄ እናዘጋጃለንም” ብለዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት በትግራይ ክልል ሕግ የማስከበር ዘመቻ ብሎ የጠራውን ጦርነት መጀመር ተከትሎ የኢትዮጵያ ሠራዊት ከሱዳን አዋሳኝ ድንበር ሲለቅ ሱዳን ድንበር አልፋ ገብታለች ከተባለ 5 ወራት ተቆጥረዋል።

 

ምንጭ; አዲስ ዘይቤ

Exit mobile version