Site icon Dinknesh Ethiopia

ማልቀስስ ለእርሱ ነው

August 28, 2012  የተፃፈ ግን የተላንቱን ብቻ ሳይሆን የዛሬን የህዝብን ስሜት የሚገልጽ የተዋጣለት ግጥም

ምንድን ነው ማልቀሱ ኑሮ ለሚሞተው፤
ባልጋው በዙፋኑ ለተቀማጠለው፤
እግዜር በፍቃዱ መሬት ላወረደው፤
ከአፈር ተፈጥሮ አፈር ለሚሆነው፤
የአዳምን ፅዋ ጨልጥ ለተባለው፤
ሞቶ ተገንዞ ይነሳል ለሚለው፤
ማልቀስ ለቋሚው ነው በቁሙ ለሞተው።
ማልቀስ ላልቃሹ ነው፤
ባስለቃሾቹ ፊት ለሚንሰቀሰቀው፤
ቀባሪውን ቀብሮ ብቸኛ ለሆነው፤
አልቅሶ ሳይበቃው፤
አልቅስ ለተባለው፤
በእድሩ ዳኛ ቅጣት ለሚደርሰው፤
ማልቀስስ ለሕዝቡ ውሻ ለተባለው፤
አለቃ ምንዝሩን ለሚለማመጠው።
ማልቀስ ለቋሚው ነው፤
አይደለም ለሞተው፤
እንደ ሰው ሰው ሆኖ ሀዘን ላልተሰማው፤
እንኩዋን አፈር ለብሶ ገብቶ ከተማሰው፤
አይደለም ለሙቱ እግዜር ለወሰደው፤
መለስ መለስ አርጎ አፈር ለሚያለብሰው።
ማልቀስስ ለቀሪው፤
ከዘመን ዘመናት ለቅሶ ላልተለየው፤
ዐይኑ ፍጥጥ ብሎ ደም እንባ ላዘለው።
አንጀቱ ተጣብቆ ለሚንከላወሰው፤
ሳይበላ ሳይጠጣ ኑሮን ለሚፆመው፤
ጌቶቹ ባገሱ ተመስጌን ለሚለው።
አንደበት እያለው ድምፁ ለተዋጠው፤
አለም በቃኝ ገብቶ ብርሀን ለናፈቀው፤
አይቶ እንዳላየ ነፍሴ አውጭኝ ለሚለው፤
በሽንቁሩ መርከብ ሲንሳፈፍ ለኖረው፤
እንደ ኖህ አለቃ፤ ጠባቂ ለሌለው፤
ተናክሶ ተናክሶ ተባልቶ ለሚያልቀው፤
ማልቀስስ ለእርሱ ነው፤
አይደለም ለሞተው እግዜር ለነጠቀው።

Gebabdu Western Canada
August 28,2012

 

ለፋይል ማህደራችን ያገኘነው

Exit mobile version