በሙሉዓለም ገ.መድኀን
***
ባለፉት አራት በጋዎች፣ የወያኔና የአሳዳሪዎቹ የቀን ቅዥት የሆነው የኢትዮጵያ፣ ኤርትራና ሶማሊያን፣ የሦስትዮሽ ጥምረት ለመምታት ብዙ ተደክሟል፡፡ ለቀጣናው የሞግዚት አስተዳደር ካልሰየምን የሚሉት ምዕራባውያን (አሜሪካ-እንግሊዝ) የሦስቱን አገራት አዲስ ጥምረት ‹ቀጣናው ከእጃችን ሊወጣ ነው› በሚል ሊቀበሉት አልፈለጉም ነበር፡፡ በተለይም የባይደን አስተዳደር ወደሥልጣን በመጣ ማግስት የኢትዮጵያን የውስጥ ጉዳይ ለቀጣናው ጣልቃ ገብነት እንደዕድል ሊጠቀምበት ረዥም ርቀት ተጉዟል፡፡
በሕዳር ወር መግቢያ 2011 ዓ.ም ጎንደር ላይ የተገናኙት የሦስቱ ሀገራት መሪዎች ለቀጣናዊ ሠላምና መረጋጋት እንዲሁም ለኢኮኖሚ ውህደት ቅድሚያ ሰጥተው እንደሚሰሩ በጋራ ቃላቸውን መስጠታቸው ይታወሳል፡፡
የኢኮኖሚ ትስስር፣ የጋራ ደህንነት ቃል-ኪዳን (Collective Security) ጦር ማደራጀት፣ የሠላምና ደህንነት፣ የባህር ላይ ፀጥታ፣ የንግድና አካባቢያዊ ትስስር አጀንዳዎችን በጋራ መቅረጽ፣ ባለብዙ መድረኮችን የመፍጠር ሰፊ ራዕይ ይዞ የተነሳውን የሦስቱ ሀገራት መሪዎች ጥምረት በቀጣናው ሰላም ናፋቂዎች The New Horn ተብሎለት ነበር፡፡
በአንጻሩ ጥምረቱ ጎንደር ላይ በይፋ ከታየበት ጊዜ ጀምሮ ወያኔ እና የግራ ጥፍሩ የሆኑ አጋር ሚዲያዎቹ ‹የጎንደሩ ስምምነት› የሚል ስያሜ በመስጠት፣ እንቅስቃሴቸውን ለማደናቀፍ ከነጩ ቤተ-መንግሥት እስከ ቤኪንግሃም ፖለቲከኞች ድረስ ደጅ ጠንቷል፡፡ የአፍሪቃ ቀንድ ፍልሰተኞች ተጋላጭ የሆነው የአውሮፓ ህብረት፣ ጥምረቱን መደገፍ ሲገባው በጥርጣሬ እንዲያየው ወያኔ በወትዋቾቹ በኩል ተማጽኗል፡፡ ኦማር ጌሌን ‹ሊውጡህ መጡብህ› በማለት አስፈራርቷል፡፡ ኡህሩ ኬንያታን ‹ይህን ህብረት ከአሜሪካ-እንግሊዝ ጋር ቁመህ መስበር ከቻልክ ጊዜው ያንተ ነው ሲል በወኪሎቹ በኩል በስትራቴጂያዊ ጥናት ስም ተለማምኗል፡፡፡
መቀመጫውን በኬንያ ናይሮቢ ያደረገው ‹Sahan Research› የተባለ የስለላ ቡድን ራሱን የቀጣናው Makers and Breakers አድርጎ ይቆጥራል፡፡ ይህ የስለላ ቡድን ሞቃዲሾ ሰላም ውላ እንዳታድር፤ አስመራ ከዓለም ተነጥላ በማዕቀብ እንድትንበረከክ፣ አዲስ አበባ ወያኔን እንድትናፍቅ ውስጣዊ ቀውሶችን ለመፍጠር መነሻ የሚሆኑ የሐሰት መረጃዎችን በማሰራጨት አራቱን በጋዎች ላይ ታች ሲል ከርሟል፡፡
የድርጅቱ መስራች የእንግሊዝ ተወላጁ ማቲዮስ ብራይደን (ካናዳዊም ነው) የሶማሊ ላንድ ፓስፖርት ባለቤት ነው፡፡በተመድ የኤርትራ ጉዳይ ተቆጣጣሪ ሆኖ ተመድቦ ለዓመታት ሰርቷል፤ በዚህ ተልዕኮው ኤርትራን ከነመለስ ዜናዊ ጋር በመናበብ በማዕቀብ አዳክሟል።
ከተመድ ከተሰናበተ በኋላ Sahan Research የተባለ የግል የስለላ ተቋም ሲመሰርት የእነ ጌታቸው አሰፋ ሙሉ ድጋፍ አልተለየውም ነበር፡፡ መቀመጫውን ኬንያ ያደረገውም በምክንያት ነው። በርካታ የወያኔ ደህንነቶች አብረውት ሰርተዋል። አሁን ላይ አብረውት ከሚሰሩ ደህንነቶች ውስጥ እስከ 2011 መጨረሻ ድረስ በኢትዮጵያ የብሔራዊ ደህንነትና መረጃ መስሪያ ቤት ውስጥ የውጭ ጉዳይ ደህንነት ምክትል መመሪያ ኃላፊ የነበረው የወያኔ ሰው ይገኝበታል፡፡
ወያኔ ከአዲስ አበባ ከተነቀለ በኋላ በኢትዮጵያ ላይ የሐሰት መረጃ በማሰራጨት፣ በዓለማቀፉ ማኀበረሰብ ዘንድ ጫና እንዲደረግ ሲወትውት ቆይቷል። ወያኔ ሰሜን ዕዝን ከጀርባ ከወጋ በኋላ በተጀመረው የሕግ ማስከበር ዘመቻ፣ ‹‹አብዱላሂ ፎርማጆ ሦስት ሺህ ወታደሮችን ወደትግራይ አዘመተ›› የሚል ነጭ ውሸት በመፈብረክ ለነጩ ቤተ-መንግሥትና ለምዕራቡ ዓለም ሚዲያዎች እስከማድረስ የደረሰ አደገኛ ቡድን ነው፡፡
የSAHAN እና የወያኔን ገመናና ሴራ በመተንተን እና በማጋለጥ የሚታወቀው ሶማሊያዊው የምስራቅ አፍሪካ የፖለቲካ ተንታኝና ምሁር አብዲወሃብ ሼክ አብዱሰመድ ከወራት በፊት ናይሮቢ ውስጥ ባልታወቁ ሰዎች መታፈኑን በኬንያ ሚዲያዎች መዘገቡ ይታወሳል፡፡ ቡድኑ በፎርማጆ አስተዳደር የሞቃዲሾን ሰላምና መረጋጋት ለሚደግፉ ለየትኞቹም የሶማሊያ ምሁራን አደገኛ መሆኑን በተደጋጋሚ አሳይቷል፡፡
ይህ የስለላ ቡድን ከቀጣሪና አጋሮቹ ጋር ባደረገው ርብርብ ዛሬ ተሳክቶለት ሞቃዲሾ ላይ የወያኔን የቀድሞ ወዳጅ ወደሥልጣን እንዲመጣ ማድረግ ችሏል፡፡ የሶማሊያ ምርጫ የተለመደ ነው፤ የጎሳ መሪዎችን ቀድሞ በረብጣ ዶላር መያዝ የቻለ ቀሪው ነገር ድራማ ነው፡፡ በሁለቱ ምክር ቤቶች በኩል እንዲሁ ያልቃል፡፡
ከአንድ ዓመት በላይ ተራዝሞ በቆየው በሶማሊያው ምርጫ አህመድ ሺዴን ከአቅሙ በላይ ተልዕኮ የሰጠው ዐቢይ አህመድ በቀጣዩ የአፍሪቃ ቀንድ ዕጣ ፈንታ ላይ በወያኔ ገጽ አልቆመም ማለት አይቻልም፡፡ የሆነው ሆኖ የጅግጅጋ ወዳጆቻችን ሁነቱን በሰበር ዜና ሲገልጡት፦
‹‹#BREAKING: TPLF stooge and former President Hassan Sheikh Mohamud “selected’’ as new president of Somalia.›› በማለት ተሳልቀዋል፡፡
ሐሰን ሸክ መሀሙድ ከ2012-2017 ድረስ የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሆነው አገልግለዋል፡፡ ሰውየው በአመራር ዘመናቸው የወያኔ ጥብቅ ወዳጅ የነበሩ ሲሆን፤ የወያኔ ጀኔራሎች በሰላም አስከባሪነት ስም ሶማሊያ ላይ ከኢራን እስከ ኪስማዩ ወደብ በተዘረጋ የጦር መሳሪያ ንግድ ውስጥ ሲዘፈቁ ሰውየው አሻንጉሊት ነበሩ። አሁን ወደሥልጣን የተመለሱት እኒህ ሰው ናቸው!!
አንድ የጉርምስና ዘመኔ የፖለቲካ መምህር የነበረ ሰው ስለሶማሊያ ፖለቲከኞች ባህሪ ሲገልፅኝ ፦ “One thing I can say for sure is that Somali politicians don’t sympathize with any country or group based on principles or Allah; they sympathize with MONEY only.” ሲል ተሳልቆባቸዋል።
የነገር ክሩን ጥቂት ዓመታት ወደኋላ ተስበን እናቀጣጥለው፦ በወያኔ የአገዛዝ ዘመን፣ የአምባሳደርነት ሹመት በዋናነት ከፀጥታና ደህንነት ጋር በተያያዘ ልዩ ትኩረት የሚያሻቸው የምስራቅ አፍሪቃ አገራት በራሱ በወያኔ ሰዎች የተያዙ ነበሩ። ሱዳን ላይ አባዲ ዘሙ፤ ደቡብ ሱዳን ላይ ፍስሃ ሻውል በአምባሳደርነት ስም አገራዊ ሳይሆን የወያኔ ተልዕኳቸውን እንዳስፈጸሙት ሁሉ ሶማሊያ ሞቃዲሾ፤ ሰሜን ሶማሊያ ሶማሊላንድ እንዲሁም ፑንትላንድን የወያኔ ታጋዮች በአምባሳደርነት ተሹመውባቸው ነበር፡፡
ብ/ጄነራል በርሄ ተስፋዬ በሶማሊያ ሃርጌሳ ሲሾም፤ አቶ አስመላሽ ወ/ምህረት በፑንትላንድ በካውንስል ጄነራልነት የመቀሌ ሚሽኑን ሲመራ ቆይቷል፡፡ሌላው የወያኔ ቁልፍ ሰው ወንድሙ አሳምነው ሶማሊያ ሞቃዲሾ በአምባሳደርነት ተሹሞ የወያኔን ጉዳይ ሲያስፈጽም ቆይቷል፡፡
መቼም ዘንድሮ ስም የብሔር መለያ ማንነት እስከመሆን ደርሷልና ‹ወንድሙ አሳምነው› ሲባል ‹አማራ› የሚመስለው አንግዳ ፖለቲከኛ አይጠፋምና ሰውየው (ወንድሙ አሳምነው) እጅግ አደገኛ ከሚባሉት የወያኔ ዲፕሎማቶች አንዱ ስለመሆኑ እነዚህን ቃለ-መጠይቆች በማየት እንዲገነዘብ ጋብዣለሁ —
እና https://www.youtube.com/watch?v=dAf-hFss6aY
ይህ ሁሉ የሆነው፣ በዛሬው ዕለት በድጋሚ ወደፕሬዝዳንታዊ ሥልጣን የመጡት ሐሰን ሸክ ሙሀሙድ የሶማሊያ መሪ በነበሩበት ዘመን ነው፡፡ አሁን ወያኔ ከሥልጣን የተነቀለ ቢሆንም በቀንዱ ሀገራት ዙሪያ ‹የአጋር ያለህ…› እያለ በሚዋልልበት ጊዜ የቀድሞ ወዳጁ ሞቃዲሾ ላይ ወደሥልጣን መመለሳቸው ቀጣዩን ጊዜ ከአራቱ በጋዎች የተለየ ሊያደርገው እንደሚችል ይገመታል፡፡ ለዚህ ቀብድ ማስያዝ የፈለገው ወያኔ፣ ለሐሰን ሸክ ሙሀሙድ የእንኳን ደሳለዎት ደብዳቤ ለመፃፍ የቀደመው አልነበረም።
***
ጽንስ አስወራጅ… የባከኑ ወራት …?
***
የወያኔ ከማዕከላዊ ፖለቲካ መነቀል ከፈጠራቸው የውጭ ዕድሎች አንዱና ወሳኙ ከጎረቤት አገራት ጋር ያሉ ግንኙነቶች መለወጥ ነበር፡፡ በዚህ ረገድ፣ ከኤርትራ ጋር የተፈጠረው ዕርቀ-ሠላም ትርጉሙ የላቀ ነው፡፡ ከአማራጭ ወደብ አቅርቦት በዘለለ፤ የባህር ላይ ደህንነት ጉዳዮችን በጋራ ለመከታተል የሚያስችሉ ዕድሎች ተከፍተዋል፡፡
ከዕርቀ-ሠላሙ በኋላ በኢትዮጵያ፣ ኤርትራና ሶማሊያ መካከል የኢኮኖሚና የፀጥታ ትብብር ለማጠናከር ስምምነቶች ተደርገውም ነበር፡፡ በርግጥ ኢትዮጵያን ሁነኛ አጋር አድርጋ የምትመለከተውና ‹በርበራ› ላይ 19 ከመቶ ድርሻ ወደብ ልማት እየገነባችባት ያለችው ሶማሌ ላንድ፣ የሦስቱን አገራት ስምምነት በበጎ ያየችው አይመስልም ነበር፡፡ ይህን በተመለከተ ዶ/ር አስናቀ ከፋለ ‹‹የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ በአፍሪቃ ቀንድ እና መካከለኛው ምስራቅ›› FSS Vol. 3. (2012 E.C) በተሰኘ ጥናታቸው፡- ‹‹የኢትዮጵያ የውጭ ፖሊሲ አርቃቂዎች በሶማሊያና በሶማሌ ላንድ መካከል ያሉትን ተጻራሪ ፍላጎቶች የሚያስተናግድና የኢትዮጵያን ዘላቂ ጥቅም የሚያስከብር ፖሊሲ መንደፍ›› እንዳለባቸው የሰጡት ምክረ-ሃሳብ ዛሬም በቸልታ የማይታይ ነው፡፡
በርግጥ የአዲሱ ፕሬዝዳንት የውጭ ጉዳይ ፖሊስ ወያኔ-ዘመም መሆኑ አይቀሬ ከሆነ ኢትዮጵያና ኤርትራ ሞቃዲሾ ላይ የሚይዙት አቋም ሶማሌ ላንድን ‘ማብቃት’ ላይ ሊያተኩር ይችላል፡፡ ይህም ወያኔ ሞቃዲሾ ላይ ፖለቲካዊ ግሉኮስ እንዲያገኝ የበለጠ ይረዳዋል፡፡
በሌላ ጫፍ፣ በፋርስ ባህረ-ሰላጤ፤ እንዲሁም በመካከለኛው ምስራቅ ለመሪነትና ለተጽዕኖ የሚካሄደው ፉክክር ማረፊያውን ቀይ ባህርና የአፍሪቃ ቀንድ ላይ የማድረጉ ሁነት እየሰፋ መጥቷል፡፡ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ለውጥ ከመጣ ወዲህ እንኳ የዐረቦቹ እጅ በቀጣናው ላይ በሰፊው ተዘርግቷል፡፡ ይህ ብዙ ኃይሎችን ያቀፈው ጂኦ-ፖለቲካዊ ፉክክር ለአካባቢው አገራት ሠላምና ፀጥታ መደፍረስ፣ ፖለቲካዊ አለመረጋጋት ተጨማሪ ምክንያት በመሆኑ፤ ሶማሊያና ኤርትራ፣ ከኢትዮጵያ ጋር በጋራ ለመሥራት ተነሳሽነት ማሳየታቸው የኢትዮጵያን የድጋፍ መሠረት አስፍቶት የነበረ ቢሆንም የሐሰን ሸክ ሙሀሙድ የውጭ ጉዳይ ፖሊስ ይህን ዕድል የሚያስቀጥለው አይመስልም፡፡
ሞቃዲሾ ላይ ግብጽ አዲሷ ባለሜዳ አትሆንም ማለት አይቻልም፡፡ በሞቃዲሾ አንካራን መግፋት የማይቻል ቢመስልም ወያኔ ቀድሞ በገባበት ቦታ ሁሉ ፈርዖኖቹ አይዘገዩም፡፡ ‹ውሻ በቀደደው ጅብ ይገባል› የሚለው ተረት በአፍሪቃ ቀንድ ያለው ትርጉም እንዲህ ነው የሚገለጠው፡፡
ባለብዙ ዋልታ (multi-polar) ወይም ብዙ ኃያላን የሚገኙበት ይህ ሥርዐት፣ አለቃ አልባ (anarchic) የዓለም ሥርዓት በመሆኑ፣ በአፍሪቃ ቀንድ የጥላቻ ተፎካሪዎችን ቁጥር እየጨመረ በሄደ ቁጥር The New Horn የሚለውን ተስፋ ገና በጽንሱ እያሟሟው በሰላም አስከባሪዎች ብዛት የዓለምን ሪከርድ ይዞ የሚቀጥል የግጭት ማዕከል ያደርገዋል፡፡
M.Mohamed Abshir እ.ኤ.አ በሚያዚያ 20/2021 “Ethiopia, Eritrea, Somalia, Djibouti: The constant instability in the Horn of Africa” በሚል ርዕስ ባስነበበው ቀጠናዊ ዳሰሳ፣ ያለፉት 30 ዐመት ለአፍሪካ ቀንድ አስከፊ ስለመሆናቸው አውስቷል።
መረጋጋት የራቀው እና ተለዋዋጭ ማኀበረ-ፖለቲካ የተከሰተበት እንደነበረም ጠቅሷል። በአፍሪቃ ቀንድ የታየውን ያህል የሰላም አስከባሪ ሠራዊት ስምሪት፣ በየትኛውም የዓለም ክፍል አልታየም። የቀጣናው ተፈናቃዮችም ቁጥር፣ ከየትኛውም የዐለማችን አካባቢ የላቀ ሆኖ ተመዝግቧል። በዚህ የቀጣናው ሂደት ውስጥ ዓለም በልኩ ያልተመለከተው ዋንኛው ነጥብ፣ የአብዛኛዎቹ ቀውሶች ጠማቂ ወያኔ መሆኑን ነው፡፡
ከሁለት አሥርታት በፊት፣ በወያኔ መሪነት ለሁለት ዓመት ከኤርትራ ጋር የተደረገው እጅግ ደም አፋሳሽ ጦርነትን ጨምሮ፤ በሶማሊያ የእስላማዊ ፍርድ ቤቶች ህብረትን ለመዋጋት ሠራዊት ባዘመተበት ወቅት፣ ስምሪቱን ለቡድናዊ ጥቅመኝነት (በተለይ ለጦር መሳሪያ ዝውውር) በማዋሉ፣ ከቀጠናው ሰላም ይልቅ፤ ለቀውሱና አለመረጋጋቱ የአንበሳውን ድርሻ እንዲይዝ ያደርገዋል፡፡
M.Mohamed Abshir (2021) ‹‹የአፍሪካ ቀንድ ትልቁ ፈተና ከውስጥ የሚመነጭ ነው›› ይላል። ቀጣናውን በአጭር ሲገልጸው ‹‹ከራሱ ጋር ጦርነት የከፈተ››በሚል ነው፡፡ ከብሔርና ጎሳ ብጥብጦች እስከ ታሪካዊ ቅራኔ አጀንዳዎች ቀጠናውን እያመሱት ይገኛሉ። በዚህ ውስጥ ተፈልጎ የማይጠፋው ደግሞ፣ አሸባሪው ወያኔ ነው፡፡
ለዚህም ነው፣ ፀሐፊው ‹‹የውስጣዊውን ሁኔታ ከእነ ዐውዱ የሚረዱት ራሳቸው ናቸውና፤ መፍትሔው ከውስጥ ሊመነጭ ይገባል›› ሲል ምክረ-ሀሳቡን የለገሰው፡፡
የአፍሪቃ ቀንድ ሰላም ፈላጊ ወገኖች ከአዲስ አበባ እስከ አስመራ፣ ከጁባ እስከ ሞቃዲሾ የዚህ ኃይል መወገድ ‹የሰላማችን መንገድ ነው› ሲሉ ቢከርሙም በምዕራባውያን ጫና፣ በዐቢይ አህመድ መንታ ልብ ያዘለ የጦር መሪነት (ወያኔ የአፍሪቃ ቀንድ ዕዳ እንዳልሆነ ሁሉ የአማራና የአፋር መያዥያ አድርጎ የማሰብ ቅዥት በወለደው ጎደሎ አስተሳሰብ)፣ ወያኔ እጁን ዳግም የሚሰድበት ተጋላቢ ትክሻ ሞቃዲሾ ላይ ያገኘ ይመስላል፡፡
የማይረጋ፣ ሞገደኛና ተለዋዋጭነት አይነተኛ ባህሪው በሆነው የአፍሪቃ ቀንድ ፖለቲካ ውስጥ መሽቶ በነጋ ቁጥር የወያኔን ዕድሜ የሚቀጥሉ ሁነቶች መሰማታቸው ሊደንቀን አይገባም፡፡ ይልቁንስ ‹ጦርነቶች ሁሉ ሠላም ያመጣሉ› ማለት ባይቻልም፤ የወያኔ ጨርሶ መቃብር መውረድ ግን፣ ከኢትዮጵያም በዘለለ፤ የቀጠናውን በጎ ዕድል ያለጥርጥር ያሰፋዋል፡፡
Source: Mulualem G. Medhin facebook post