Site icon Dinknesh Ethiopia

የእግር ኳስ ጨዋታው መንግስትና ጠቅላዩን ከገቡበት የገጽታ ቀውስ ሊታደጋቸው ይችል ይሆን?

Soccer Ball

Batero Belete

ሰኔ 26, 2015 (July 3, 2023)

ጠቅላይ ሚኒስቴር አብይ አና መንግስታቸው የገቡበትን እጅግ የተወሳሰቡ ውጥንቅጦች እና የተከሰተውን ቀውስ ለሚያስተውል ሁሉ ይች ሀገር ምን እየሆነች ነው ወዴትስ እየተጓዘች ነው ብሎ ማስቡ እና መጠየቁ አግባብ አለው፡፡ሀገር እና ሀዝብ በታላቅ ቀውስ ውስጥ ናቸው፡፡

በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ የሀገር ውስጥ ቀውሱ ሳያንስ ሰሞኑን ደግሞ ጠቅላዩ በአለም አቀፍ ግንኙነትም በተለይም በፓሪስ ጉዟቸው ከቀደመው ክብራቸውና ተደማጭነታቸው በተቃራኒ ከሌሎች አፍሪካ መሪዎች ተገልለው ብቸኝነት ገጥሟቸው እንደከረሙ በሰፊው ሲዘገብ ቆይቷል፡፡

ይህ ሁሉ ኢትዮጰያን ያክል የዲፐሎማቲክ ክብር የተጎናጸፈች ሀገርን ለሚመራ ሰው በቅርቡም የኖቤል ሽልማት አሽናፊ ለሆነ ሰው ሰነልቦና እጅግ የሚጎዳ ጉዳይ ነው፡፡

በሰፊው ሲታይ ከፕሪቶሪያው የብልጽግናና የህወሀት ስምምነት ውጭ ላለፉት ተከታታይ ወራት ጠቅላዩ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭው አለም በግልም በመንግስት ደረጃም ከስኬታማነት ይልቅ ወድቀት፣ ከተቀባይነት ይልቅ መገለል፣ ከሰላም ይልቅ ጦርነት፣ ከድጋፍ ይልቅ ውግዘት በዝቶባቸው በችግር ላይ ችግር ከአንድ ቀውስ ሳይወጡ በሌላው እየተዋከቡ ይገኛሉ፣ እጅግ ብዙዎችም የዚህ ሁሉ ችግር እምብርት ጠቅላዩንና ስርአታቸውን አድርገው ይሞግታሉ በሀላፊነትም ያስቀምጣሉ፡፡ ይህ ሁሉ ተደማምሮ ታላቅ የገጽታ ቀውስና የስነ ልቦና ተጽእኖም እንደዳሳደረባቸው መገመት ይቻላል፡፡

በዚህ ሁሉ መሀል ጠቅላይ ሚኒስቴሩ ትላንት ድንገት ብቅ ብለው አይን በሚስብ የስፖርት ልብስ ደምቀው የእግር ኳስ ሲጫወቱ የሚያሳይ ምስል በሰፊው እንዲሰራጭ አድርገዋል፡፡

ይህ በፈገግታ የተሞላው የእርግ ኳስ ጨዋታ ምስል ለምን አሁን ተለቀቀ ? ከገጠማቸውስ የገጽታ ቀውስ ሊያስቆምና የገጽታ ግንባታውንስ እውን ለማድረግ የሚኖረው አስተዋጽኦ ምን ሊሆን ይችላል በሚለው ላይ አንድ ሁለት የግል አመለካከቴን ላካፍላችሁ፡፡

የህዝብ ግንኙነት አዋቂዎች እንደሚያሳዩት አንድ ድርጅት ወይም መንግስት ቀውስ ሲደርስበት ከዚህ ለመውጣት የሚያደርገው ጥረት ውስጥ ጎልተው የሚታዩ ገጽታዎች ወይም ተደጋግመው የሚጠቀሱ ክፍሎች የጥረቱ ትኩረት በምን ላይ ያተኮረ እንደሆነ የሚጠቁም ነው፡፡

በሰሞኑ የስፖርት ተኮር የገጽታ ግንባታ ኮሚኒኬሽን በዋናነት የምስሉ ማእከል ተደርገው የቀረቡት ጠቅላይ ሚኒስቴሩ መሆነቸው የእስካሁኑ ቀውስ የርሳቸውን ገጽታ በግል እንደጎዳና ከዚህ ቀውስ ለመውጣትም መልሶ መገንባት የተፈለገው ገጽታ በጠቅላይ ሚኒስቴሩ ላይ ያተኮር እንደሆነ ያመላክታል፡፡

ይህም በብልጽግና ውስጥ ጭምር ጠቅላዩን ከጥቂት አመታት በፊት ተወዳጅና ሀገራችንንም ከገባችበት ችግር ሊያሻግር የሚችል ብቃት ያለው መሪ ናቸው እንደተባለው ሳይሆን ዛሬ ላይ እንደ ችግርና እዳ (liability) ማየት ጎልቶ እየመጣ መሆኑን ይጠቁማል::

ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ የገጽታ ግንባታ ጨዋታው እግር ኳስ መሆኑ በነሲብ የተወሰደ ሳይሆን ትርጉም ባለሁ ሁኔታ የተመረጠ ይመስለኛል፡፡

ሲጀመር የእግር ኳስ ጨዋታ በሀገራችን በገጠሩም በከተማውም እጅግ ተወዳጅ የሆነ እስፖርት በመሆኑ ጠቅላዩም ራሳቸውን ሊያቆራኙ የሞከሩት ከተወዳጅ እና ሁሉም ሰው ከሚያፈቅረው ተግባር ጋር የተሰለፉ እንደሆነ ነው፡፤የዚህ ቁርኝት መለክት እኔም ከህዝብ ተነጥየ የተንሳፈፍኩ በራሴ አለም ውስጥ የምኖር ጠቅላይ ሚኒስቴር ሳልሆን አሁንም ከሁላችሁም ውስጥ አንዱ ነኝ፡ የሚል ነው፡፡

በተጨማሪም የእግር ኳስ ጨዋት በሰፊው ተወዳጅ ሰለሆነ የርሳቸውንም የጨዋት ምስል፣ ብዛት ባለው ሀዝብ ውስጥ ውይይት እንደሚያጭር ታስቦ የተመረጠ ይመስላል፡፡

የእግር ኳስ ጨዋታ የግል ጥበብ የሚታይበት ቢሆንም በቡድን አባላት መሀል መተባበርን መተጋጋዝን መናበበን ወዘተ የሚሻ ጨዋታ ነው፡፡ በዚህ ጨዋታ ግለኛ ተዋናይ ቦታ የለውም፡፡ይህን እስፖርት ለገጽታ ግንባታ መሳሪያነት ሲመርጡ የጠቅላዩ ሰዎች ሊያሳዩት የሞከሩት እንደሚነገረው “እርሳቸው ብቻ የፈለጉትን የሚያደርጉ ፣ የማያዳምጡ ሳይሆኑ የቡድን ተጫዋች መሆናቸውን፣ ከሌሎች ጋር ተግባበተው ተናበው ተስማማተው የሚሰሩ መሆናቸውን ለማሳየት የተደረገ ጥረት ይመስላል፡፡ ለምሳሌ ጠቅላዩ ድሮ ሳይሆን ዘንድሮ የግራውንድ ቴኒስ ጨዋታ እንደለመዱና እንደሚወዱ ቢታወቅም ይህ እስፖርት በዋናነት የቡድን ሳይሆን የግል እስፖርት በመሆኑ ለዚህ የገጽታ ግንባታ አልተጠቀሙበትም፡፡

ከቀውስ ጋር የተገናኘ የገጽታ ግንባታ ውጤታማ እንዲሆን አንድ ድርጅት መንግስት ወይም ግለሰብ ከገባበት ቀውስ ለመውጣት በዚህ የገጽታ ግንባታ ውስጥ ሊያጠቃልላቸው የሚገቡ መሰረታዊ ጉዳዮች ውስጥ ፣ የቀውሱን መፈጠር መቀበልና የተፈጠረውን ቀውስ ማድበስበስ ሳይሆን ግልጥ አድርጎ ማስቀመጥ፣ ለተፈጠረው ቀውስ ሀላፊነት መውስድ እና ለዚህም ተጠያቂነት እንዲኖር ማድረግ ቁልፍ ጉዳዮች ናቸው፡፡

ከዚህ ሁሉ ጋር ደግሞ በቀውስ ውስጥ የተዘፈቀው መንግስት፣ ግለሰብ ወይም ድርጅት ቀደም ሲል ቀውስን በተመለከተ ያሳያቸው አቋሟች፣ ተአማኒነት ወዘተ አሁን ለሚያደርገው የገጽታ ግንባታ አሉታዊ ውይም አወንታዊ ተጸእኖ ይኖረዋል፡፡ ባለፉት ጊዜያት ቃሉን በተደጋጋሚ የሚጥስ፣ ተአማኒነቱ እጅግ የጎደለው አካል፣ የገጽታ ግንባታ እንዲህ በቀላሉ የሚጠገን እንዳልሆነ የሰዎችንም ልብ በትንሽ እርምጃ ማማለል እንደሚከብደው የተለያዩ ጥናቶች ያሳያሉ፡፡

ታዲያ የሰሞኑ የጠቅላዩ የእግር ኳስ ጨዋታና ፈገግታ በአጠቃላይም የገጽታ ቀውሱን ለማስቆም የተደረገ የመልሶ ግገንባታ ጥረት እንደሆነ ግልጽ ቢሆንም ከላይ ከጠቀስኩት አስፈላጊ የገጽታ ስብራትን ማሻሻያ ሊያግዙ ከሚችሉ ጉዳዮች አኳያ ሲታይ ምን ተጨባጭ ተጽእኖ ሊያስገኝ ይችላል የሚለውን ለእርስዎ ግምገማ እተወዋለሁ፡፡

በኔ እይታ ጠቅላዩ ዘና ያሉ መስለው መታየታቸው በሀገሬ ውስጥ ብዙም ችግር የለም የሚል፣ ችግር ያልበዛበት ወይም ችግሩን የተቆጣጠረ መንግስት ገጽታን ለማስተላለፍ የታቀደ ይመስላል፡፡ ሌላው መልእክት እኔ ማንንም የማልሰማ ከህዝብ የተገነጠልኩ አምባገነን አይደለሁም የሚል ነው፡፡ የመልእክቱ ቁልፍ ሀሳቦች እነዚህ ናቸው፡፡

ጥያቄው የገጽታ ግንባታ በዋናነት የኮሚኒኬሽን ስራ ሲሆን ኮሚኒኬሽን ደግሞ መልክትን ላኪ (sender) ብቻ ሳይሆን ተቀባይም (receiver ) ይጠይቃል እና ከላይ የተጠቀሰውን መልእክት ተቀባዩ እንዴት ይተረጉመዋል የሚለው ነው፡፡

በኔ እይታ ጠቅላዩ በየጊዜው በብቸኛነት የሚወስዷቸውን እርምጃዎች ( በወልቂጤ ስብሰባ ከፈለግኩ በሰአታት ውሳኔ ክልል መመስረት እችላለሁ ማለታቸው ይታወሳል)

በሀላፊነት አልጠየቅም ባይነት ( የቤተ መንግስቱን ግንባታ ገንዘብ ልብ ይሏል) በሀገር ውስጥ የሚታየውን ቀውስ እየሰፋ መሄድ፣ የሰው መታገት ፣ የጦርነት መስፋፋት፣ (በኦሮሚያም በአማራ ክልልም) የረሀብ መስፋፋት፣ የሙሰኛነት መጠናከር፣ የሀግ የበላይነት ማስጠበቅ አለመቻል የእገታው መባባስ ፣ ከአዲስ አባባ ውጭ እንደልብ መንቀሳቀስ አስፈሪ መሆን የሰዎች መፈናቀል የገበሬው ብሶት የኦኮኖሚው ቀውስ፣ የኑሮ ውድነት እጅግ ማሻቀብ፣ የግብር ጫናውን ወዘተ እውቅና ያልሰጠ ለቀውሱም ሀላፊነትን መንግስት እንደሚወስድ ተጠያቂነትንም እውን እንደሚያደርግ በተጨባጭም ሆነ በተዘዋዋሪ ያላሳየ ሰለሆነ የፓርቲያቸው የብልጽግናን፣ የመንግስታቸውንም ሆነ የጠቅላዩን የግል ገጽታ ስብራት መልሶ ለመገንባት ከሚኖረው ጥቅም ይልቅ “ ሰውየውና መንግስታቸው ህዝብ እየተሠቃየ ሀገር እየተበጠበጠ እነርሱ አሁንም ግድ የላቸውም አታያቸውም ሲዝናኑ” ፡ ወደሚል እይታና መደምደሚያ ላይ ሊያደርስ ይችላል ወደሚለው አዘነብላለሁ፡፡

የጠቅላዩ የህዝብ ግንኙነት መሳሪያ ዝገት ገጥሞታል፡፡ የእግር ኳስ ጨዋታው ድርጅታቸውንም ሆነ እርሳቸው ከገቡበት የገጽታ ቀውስም ሊታደጋቸው የሚችል አካሄድ አይመስልም፡፡

ሰብራቱ ዘርፈ ብዙና ጥልቅ ነው፡ የተጎዳውም ህዝብ እጅግ ሰፊ ሰለሆነ ሁኔታውን ለማሻሻል ከእግር ኳስ ጨዋታና ከፈገግታ በላይ ገዝፎ የሚሄድ ተጨባጭ ተግባራዊ ሰራ ይጠይቃል፡፡ ያውም ባስቸኳይ፡:

 

 

Source:

Batero Belete facebook page

 

Exit mobile version