የፋኖ ትግል እየጎመራ መቀጠልን ተከትሎ አንዳንድ ምሁራን በስጋት የሚያነሱት ጉዳይ አለ። እርሱም ፋኖ ወደ አዲስ አበባ ሲጠጋ ገዥው መንግስት ባለው መከላከያ ሰራዊት እና ፖሊስ አቅም መክቶ ስልጣኑን ማስቀጠል እንደማይችል ስለሚረዳ የጦርነቱን መልክ ይቀይረውና የእርስ በእርስ ጦርነት ይደረጋል የሚል ነው። በእርግጥም ተጨባጭ ስጋት ነው። ምክንያቱም ገዥዎቹ የስልጣናቸው ዘብ ካደረጉት መከላከያ በተጨማሪ ህዝብን ቀስቅሰው እርስ በእርሱ ከማጫረስ ወደ ኋላ እንደማይሉ ይታወቃል። ስልጣን ከመልቀቅም ይልቅ ህዝቡን አጫርሰው በስልጣን መቀጠል እንደሚፈልጉ በቆየንባቸው ውጊያዎች ሁሉ የነበራቸው ሞራል ይመሰክራል። በመሆኑም የአዲስ አበባን የባለቤትነት ጥያቄ የህዝብ ስስ ብልት ስላደረጓት የፋኖውን ስርአት የመገልበጥ ትግል በቀላሉ ከአዲስ አበባ አጀንዳ ጋር አቆራኝተው ቅስቀሳ ያደርጋሉ። ከመደበኛ እና ኢመደበኛ ታጣቂዎቻቸውም በተጨማሪ እንወግንልሀለን የሚሉትን ህዝብ ቀስቅሰው እልቂት እንደሚያስፈጽሙ ሳይታለም የተፈታ ነው። ፋኖ ይህ እንደሚደረግ ሳያውቅ ቀርቶ አይደለም እየታገለ ያለው ወይም የእርስ በእርስ ጦርነት (civil war) ይመጣል ብሎ በመፍራት ትግሉን ለአፍታ አይተውም። ምክንያቱም ከዘር እልቂት (ጄኖሳይድ) የእርስ በእርስ ጦርነት ይሻላል። ከሁለቱ መጥፎ አማራጮች የተሻለውን መምረጥ ብቸኛው የህልውና መንገድ ስለሆነ ነው ህዝቡ ‘ቁጭ ብለን አናልቅም’ ብሎ የተነሳው።
የእርስ በእርስ ጦርነት ሊነሳ ይችላል የሚሉት ምሁራን ታዲያ ድርድር እንዲደረግና ውጊያው በአስቸኳይ እንዲቆም በማሳሰብ ድምጸት ፍራቻቸውን ገልጸዋል። በድርድር እልቂቱን ማስቀረት የሚቻል የመሰላቸው ግን አዲስ አበባ ላይ ላለፉት ተከታታይ አምስት ዓመታት ሲደረግ የቆየውን የጄኖሳይድ ዝግት ባለማወቅ ይመስለኛል፡፡ እንጅ ምሁራኑ የፈጠሩት የትንተና ግድፈት አድርጌ አልወስደውም። ታሪካዊ ዳራውን ሳያጤኑ፡ የፋኖውን ትግል ወደ አዲስ አበባ መቃረብ ተከትሎ የሚከሰተውን የእርስ በእርስ ጦርነት ብቻ ነው የተገነዘቡት። በእውኑ ግን የፋኖ ትግል አዲስ አበባ ደረሰም አልደረሰም አዲስ አበባ ላይ የተደገሰ የዘር ጭፍጨፋ አለ። ፋኖ መገስገስ ያለበት እና ሌሎቹም የሀገራችን ማህበረሰቦች ሁኔታውን በሚገባ ተረድተው መተባበር የሚጠበቅባቸው የአዲስ አበባ ህዝብ ከመጨፍጨፉ በፊት እንዲደርሱለት ነው።
ገዥው መንግስት የፋኖን ወደ አዲስ አበባ መቃረብ እንደ ሰበብ ወይም (Immediate cause) ተጠቅሞ ጭፍጨፋውን ሊጀምር ይችላል። ለጭፍጨፋው ግን ቀድሞም ኃይሉን አደራጅቶ አስፍሮ ፊሽካዋን በመጠባበቅ ላይ የቆየው ከሶስት ዓመታት በፊት ጀምሮ ነው። ማይካድራ ላይ የተፈጸመውን አይነት ጭፍጨፋ ለማድረግ ሶስት አመት ሙሉ እየተዘጋጀ የኖረ ከ200’000 በላይ ወጣት ተመልምሎና ሰልጥኖ አዲስ አበባ ተቀምጧል።
የቲም ለማ እንቅስቃሴ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሶ በነበረበት ወቅት ከተፈጠሩት አበይት የሀገራችን ክስተቶች አንዱ የኢትዮ-ሶማሊ እና ኦሮሞ አጎራባች አካባቢ የእርስ በእርስ ግጭት ነበር። በግጭቱ የተፈናቀሉ ወደ 67000 የሚደርሱ ኦሮሞዎች አዲስ አበባ እና ለገጣፎ መጥተው እንዲሰፍሩ ተደርጓል። ለገጣፎ የተመደቡት ተፈናቃዮች አበበች ጎበና በሚባለው አካባቢ እንዲሰፍሩ ተደርጎ ከህዝቡ ገንዘብ ተሰብስቦ ቤት ተሰርቶላቸው በቋሚነት ሰፍረዋል። አዲስ አበባ ደግሞ ቦሌ አራብሳ አካባቢ እና ከጎሮ ወደ ኮዬ ፈጨ በሚወስደው መንገድ በስተግራ በኩል ሙሉ ወጩን በመንግስት ተከፍሎ የብቻቸው መንደር ተሰርቶላቸዋል። ምንም እንኳ ከመጡበት አካባቢ ግጭቱን የፈጠረው አብዲ ኢሌ ቢታሰርና አካባቢው ወደ ሰላም ቢመለስም ተፈናቃኞቹን ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ በማድረግ ፈንታ በቋሚነት አዲስ አበባ እንዲኖሩ ነው የተፈለገው። ምክንያቱም ቲም-ለማ ከቆመላቸው መሰረታዊ አጀንዳዎች አንዱና ዋናው የአዲስ አበባን የህዝብ ስብጥር መቀየር ነበር። ይህን በራሳቸው አንደበት በግልጽ ደጋግመው የተናገሩት እና የመንግስት የፖለቲካ ፕሮግራም አካል የተደረገ ዓላማ ነው።
Subjecting Gondar To A Cycle Of Assault Is Tantamount To Dismantling Ethiopia – Dr. Aklog Birara
የመጀመሪያው ማስፈር ሲሆን አፈጻጸሙም የተለያዩ ስልቶችን ሊጠቀም እንደሚችል ስምምነት ተደርሶበታል። በመሆኑም ከሐረርጌ እና ባሌ አካባቢ ተፈናቅለው የመጡት ዜጎች ቤት የተሰራላቸው በዚህ የማስፈር ስልት ሰፊ መርሀግብር ተይዞ ነው። ሁለተኛው ማስፈር ደግሞ ከተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች በተለይም ከአምቦ ዙርያ ወጣቶችን አምጥቶ አዲስ አበባ ቤት ሰጥቶ እንዲኖሩ ማድረግና ለሚሰጣቸው ቀጣይ ተልእኮ ብቁና ዝግጁ ሁነው በተደራጀ መልኩ እንዲኖሩ ማድረግ ነው። በነዚህ የማስፈር እቅዶች የህዝብ ምጥጥን ያሉትን አላማ ማሳካት ካልተቻለ ደግሞ ያዘጋጁት ሌላኛው መርሀግብር ‘ማፈናቀል’ ነው። ማለትም የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪውን ከቤቱ አስወጥቶ በማባረር የከተማውን የህዝብ ቁጥርና የብሔር ስብጥር እነርሱ ባስቀመጡት ቀመር ልክ ማድረግ። ይህንን የማፈናቀል መርሀግብር ለመፈጸም ስልጠና ወስደው የተዘጋጁትም ከኦሮሚያ አካባቢዎች ተመልምለው የገቡና ኮንደሚኒየም ቤት የተሰጣቸው ወጣቶች ናቸው።
እንደሚታወሰው 194’000 (አንድ መቶ ዘጠና አራት ሽህ) የ20/80 ኮንደሚኒየም ቤቶች ተሰርተው በመጠናቀቃቸው ለእጣ እንደሚቀርቡ እና ተገቢውን ቁጠባ ላደረጉ ተመዝጋቢዎች እንደሚተላለፉ የቤቶች ልማትና አስተዳደር ካሳወቀ በኋላ በአቶ ጃዋር ሙሀመድ የሚዘወር መንጋ ቱሉዲምቱ እና ኮየፈጨ አካባቢ ለተቃውሞ ወጣ። በዚህም ሰበብ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ የቤቶቹን እጣ መርሀ-ግብር አስቀረ። ድጋሜም የኮንደሚኒየም ቤት ግንባታ እንደሌለና መንግስትን እንዳከሰረ አሳወቁ። ተመዝግቦ ሲጠባበቅ ለኖረው ህዝብ እንደመፍትሔ ያቀረቡት ታዲያ በቡድን ተደራጅተው ቤት የሚሰራበት መሬት መስጠት ነበር። መሬት! የጃዋርን እንቅስቃሴ ተቃውሞ አስመስለው ያስነሱት እራሳቸው አብረው መክረውና ወስነው እንጅ የማያውቁትና ያልጠበቁት ክስተት አልነበረም። ዝርዝሩን በሚቀጥለው ንዑስ ርዕስ እናየዋለን። ለሀያ ዓመታት አንጀቱን አጥፎ የቤት ባለቤት ለመሆን ሲቆጥብ ለኖረው ህዝብ ማምታቻ አጀንዳ መፍጠር ስለነበረባቸው ግን ጃዋርን የመንግስት ተቃዋሚ አድርገው አስነሱ። ተቃዋሚ! ነገር ግን የቤተመንግስት ሪፐብሊካን ጋርድ እንዲጠብቀው የተመደበለት!
የሆነው ሁኖ ተገንብተው የተጨረሱት ቤቶች ላልተመዘገቡና ፈጽሞም የአዲስ አበባ ነዋሪ ላልሆኑ ወጣቶች ተላለፈ። 194ሽህ ቤቶች! እነዚህ ቤቶች ከ20/80 መርሀ-ግብር ላይ ብቻ የተወሰዱ ናቸው። ከ40/60 መርሀግብር የተወሰዱ ደግሞ ለከተማ መስተዳድሩ ካድሬዎችና ስውር ሚና ለሚኖራቸው፡ (ምናልባትም አዲስ ያሰፈሯቸውን ወጣቶች የሚመሩ እና የሚያስተባብሩ ሊሆኑ ይችላሉ)፡ በአዲስ አበባ ከተማ ም/ከንቲባ አቶ ታከለ ኡማ ተፈርሞ ከ5000 በላይ ቤቶች ተላልፈዋል። ይህንን አሀዝ የመንግስት ቤቶች አስተዳደር ኤጀንሲም በወቅቱ ይፋ አድርጎታል። ያልተነገሩና ያለምንም ሰነድ የተሰጡና በጉልበት የተወረሱ ደግሞ እስከ 50 ሽህ ቤቶች እንዳሉ የቤቶቹን ምዝገባ እና ቁጥጥር የሚያደርገው ኤጀንሲ የጥናት ግብረ-ኃይል አዋቅሮ ባስደረገው ቆጠራ ይፋ አድርጓል። ስለዚህ በአጠቃላይ ከሶስት መቶ ሽህ በላይ ቤቶችን በተለያዬ መንገድ በመንጠቅ ለሚፈልጓቸው ሰዎች አስተላለፈዋል፤ ከአዲስ አበባ ውጭ ያመጧቸውን ሰዎችም በቋሚነት አስፍረዋል። ሰፋሪዎቹም ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ወጣት ወንዶች ናቸው። ይህም ከመስፈር ባለፈ በቀጣይ የሚሰጡት ተልእኮ ምን እንደሆነ ለመረዳት ቀላል ያደርገዋል።
እነዚህ ወጣቶች በአስር እና አስራ-አምስት አባላት ቡድኖችን አዋቅረው የተለያዩ የስራ ፈቃድ ተሰጥተው እስከ አሁንም በመንቀሳቀስ ላይ ናቸው። ቤት ለቤት እየተንቀሳቀሱ የከተማውን ነዋሪ የሚጨፈጭፉበትን ትእዛዝ እስከሚሰጡ ድረስ በእቃ አውራጅና ጫኝ ስም ከከተማ አስተዳደሩ ደረሰኝ ተሰጥተው፡ ህዝቡን በህጋዊነት እየዘረፉት ከርመዋል። አስር ሽህ ብር የተገዛን ፍሪጅ ከመኪና ለማውረድ ሀያ ሽህ ብር ያስከፍላሉ። ባለቤቱ “እራሴ አወርደዋለሁ” ቢል እንኳ ማውረድ አይችልም። ‘የተደራጀንበት ስራ ስለሆነ እኛ ብቻ ነን መስራት የምንችለው’ ብለው ያስገድዱታል። በዚህ መልኩ በየሰፈሩ ተደራጅተው እስከ አሁን ድረስ እየዘረፉ ነው። ከአማራ ክልል ወደ አዲስ አበባ በመኪና ሲመጡ ከመንገድ ላይ አስወርደው በሚሊዮን ብር አምጡ ከሚሉት አጋቾች የተለየ አይደለም። አምጡ የሚባለው የገንዘብ መጠን ይለያይ እንደሆን እንጅ ድርጊቱን የሚያስፈጽመው መሪ አስተሳሰብ አንድ ነው።
በዚህ ሁኔታ ህዝቡ በየእለቱ በሚጋፈጠው የኑሮ ውድነትና እነዚህ ወጣቶች በጋረጡበት ስጋት ተሸብቦ በሰቀቀን እንዲዋጥ የተደረገው በገዥዎቹ እቅድና ውሳኔ ነው። በአዲስ አበባ ከተማ ላይ ለሚያደርጉት ማናቸውም ውሳኔ ተቃውሞ እንዳይኖርና ተቀናቃኝ ኃይሎችም የሚያነሱት የፖለቲካ ጥያቄ ህዝባዊ እንዳይሆን ለማፈን ህዝቡን ሰቀቀን አውጀውበታል። የመጨረሻውና ከሁሉም የሚከፋው እኩይ አላማ ደግሞ እነዚህ ሰፋሪዎች የተዘጋጁት ዘር መርጠው በመጨፍጨፍ እና በማፈናቀል የህዝብ ቁጥሩን ምጥጥን ለማስተካከል ነው። ምክንያቱም የራሳቸውን ሰው አስገብተው አስፍረው የሚፈልጉትን ያህል ለውጥ ማምጣት አልተቻለም፥ በተለያዬ ስልት ለማፈናቀልም ሞከሩ፡ ይህም ያን ያህል የጎላ ዲሞግራፊያዊ ለውጥ አላመጣም። ስለዚህ በስተመጨረሻ የዘር ጭፍጨፋ ማድረጋቸው የማይቀር ነው። በበቂ ደረጃ ያዘጋጁት ኃይልም ስላለ ወደ ኋላ የሚሉበት አንዳች ነገር የለም። የአዲስ አበባ ህዝብ በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ ታፍኗል። ተመችቶት አይደለም ዝም ያለው። ታፍኖ ነው።
አዲስ አበባ ላይ ለመፈጸም የተዘጋጁበትን እልቂት ሊያከሽፍ የሚችል አልያም ታላቅ ዋጋ የሚያስከፍል ብቸኛ ኃይል ቢኖር የፋኖ መንሰራራት ነው። ሰብረነዋል ብለው የዘበቱበት ህዝብ ከአጽናፍ አጽናፍ በአንዴ ሲነሳ ደንግጠዋል። የክልሉን ዋና ዋና አመራሮች በተሳካ ሁኔታ ገድለው፤ ክልሉን ማድከም የሚችል ከፍተኛ ወረራ በተደጋጋሚ እንዲደረግበት ሆን ብለው የጦርነት ማዕከል በማድረግ፤ በቢሊየን ዶላር የሚገመት የህዝብና የግል ንብረት እንዲወድምና እንዲዘረፍ አስደርገው፥ በስተመጨረሻም የክልሉን ልዩ ኃይል በትነው . . . ስንቱን ሻጥር ሰርተውም በዚህ ደረጃ ትጥቅ አሟልቶ የሚዋጋ ህዝብ መሆኑ እጅግ አስገራሚ ነው። በሰው አዕምሮ ሊታሰብ የሚችለውን ሁሉ ክፋት በአማራ ህዝብ ላይ ዶልተውበታል። ብቸኛውን የህዝብ ተቆርቋሪ የጸጥታ አካልም በቀላሉ ነበር የበተኑት፤ እግዚአብሔር ይህን ህዝብ ሊታደገው ስለፈለገ ግን የተበተነውን ሰበሰበውና ፋኖ አድርጎ አስነሳው።
አሁን ፋኖ ጥይት የማይፈራ ከድል በስተቀር የሚያቆመው አንዳች ነገር የሌለ የእሳት አሎሎ ሁኖ ተነሳ። በዚህን ጊዜ ኦሮሙማ የማሳመን ወይም ማወናበድ (convince or confuse) ማኗሉን ማገላበጥ ጀመረ። በሽማግሌ ተማጽኖ እንደ እስከ ዛሬው ቄስና ሸክ በመላክ የሚቆም እንዳልሆነ ተረድተውታል። ለድርድር ያቀረቡት ጥያቄም እንዴት እንደተጨናገፈ አይተዋል። ስለዚህ በአይነቱ የተለዬ ብራንድ ስልት መቀየሳቸው የሚጠበቅ ነው።
አገዛዙ በህዝብ የተጠላ መሆኑን ስለተረዱት፡ አሁን የተነሳው የህዝብ ትግል ተወደደም ተጠላም አሽቀንጥሮ እንደሚጥላቸው አውቀዋል። ይህንን ትግል ለማምከን የራሳቸውን መፈንቅለ መንግስት ያደርጉ ይሆናል። ይህንንም ለማድረግ የሚያስችል በቂ የድራማ ልምድ አላቸው። ስለዚህ ትክክለኛው የህዝብ ትግል አራት ኪሎ እስከሚደርስ ሳይጠብቁ ባዘጋጇቸው የራስ ተቃዋሚዎች መፈንቅለ መንግስት ሊያደርጉ ይችላሉ። መፈንቅለ መንግስቱን ሲያደርጉ ህዝብ አሳማኝ እንዲሆንና ተቀባይነት እንዲኖረው ማንኛውንም ጥበብ ይጠቀማሉ። ለምሳሌ በሚታወቀው የኦሮሙማ አሰላለፍ ሸኔ አሸባሪ ታጣቂ ነው፤ እነ ለማ እና ታከለ ኡማ ደግሞ ያኮረፉ ፖለቲከኞች ተደርገው ነው የተመደቡት። ጃዋርም የሚነዳውን መንጋ ይዞ በሚፈለግ ሰአት መነሳት የሚችል የአገዛዝ ስርአቱ ጠላትና እንዴያውም እስረኛ ተደርጎ የተሰናዳ ነው። በአራቱም ዋና ዋና ዘርፎች ኦሮሙማ የራሱ ተቃዋሚ ጠላት ያሰለፈበት ምክንያት ስልጣን ላይ ያለው ኦሮሙማ ሲጠላ እና የያዛቸውን አጀንዳዎች ሁሉ በያዘው ስልት ሰርቶ ሲጨርስ አፈጻጸሙ በጋራ ተገምግሞ በጠላትነት ተደራጅቶ የተቀመጠው ኦሮሙማ መፈንቅለ መንግስት ያደርግና አዙሪቱ ይቀጥላል። የጋራ ቃልኪዳናቸው በማንኛውም ሁኔታ፡ ስልጣን ከኦሮሙማ እጅ እንዳይወጣ ማድረግ ነው። ስለሆነም ለህዝቡ በሚታይበት ጊዜ ከስልጣን የሚወርዱት በተቃዋሚ ወይም በጠላት ወንበር ላይ የተቀመጡ እንዲመስል ይደረጋል እንጅ ሁሉም እኩል የሚሰሩና አንድ ስብስብ ናቸው።
አሁን በአብይ አህመድ የሚመራው ካቢኔ ባለበት መቀጠል ካልቻለ ጃዋር ወይም ታከለ አልያም ለማ የሚመራው ቡድን ስልጣን እንዲረከብ ወስነው ከተማውን ካተረማመሱ በኋላ ጸጥ እረጭ ለማድረግ ሊሞክሩ ይችላሉ።
ከዚህ በፊት አሰላለፋቸውን ‘በረጅሙ የታሰረ ተቃዋሚ’ – controlled opposition አስመስለው ብዙ ዘርፎችን እንዳደራጁ የአፍሪካ ህብረት የጸጥታ ጉዳይ ተሿሚው ጀነራል ኃይሉ ጎንፋ ተናግሮታል። ጎንፋው በአንድ ስብሰባቸው ላይ አብራርቶ እንደተናገረው ለአሰላለፍ እንዲመች ፖለቲከኛውን ከሁለት፥ የጸጥታ ኃይሉን ከሁለት፥ የመንግስት አገልግሎቱንም ከሁለት በመክፈል እርስ በእርሱ የሚቃረን አስመስለው እንዳዘጁት መስክሯል። ለአብነት ያህል ጀነራሉ ያነሳው ኦነግ ሸኔን ነበር። “ሸኔን ለትግል እንዲመቸን ነው አፈንጋጭ አድርገን የፈጠርነው፡ እንጅ ሁላችንም ሸኔ ነን፤ ለማ ሸኔ ነው፥ አብይ ሸኔ ነው፤ እኔ ሸኔ ነኝ፤ እናንተም ሸኔ ናችሁ” ነበር ያለው። ስለዚህ ጃዋርም ሸኔ ነው፤ ቲም ለማም ነው።
በመሰረቱ ቲም ለማ ከመጀመሪያው ጀምሮ በሁለት ስለት ሲቆርጥ የነበረ አደገኛ ክንፍ ነበር። በአንድ በኩል ከእነ አቶ ገዱ ጋር እየተነጋገረ ፍጹም ሀገር ወዳድና “ኢትዮጵያ ሱሴ ናት” እያለ የአማራዎቹን ፖለቲከኞች በቃላት እየደለለ ለሚፈልገው አጀንዳ ድምጽ እንዲሰጡት ያደርጋል። በሌላ አዳራሽ ደግሞ ቋንቋውን ቀይሮ ሸኔን ስለማደራጀትና የጃዋርን እንቅስቃሴ በማጋነን ትልልቅ የመንግስት ውሳኔዎችን በተቃውሞ ተገድደው ያደረጉ ለማስመሰል ያደራጅ ነበር። የአማራውን ኃይል ከገፉ በኋላ ቲምለማን ተቃዋሚ ወይም አኩራፊ ገጸባህሪ ሰጡትና ዙሩን እንዲጠብቅ አደረጉት። ለማ በወቅቱ የሚጠበቅበትን ሁሉ አድርጎ ለአብይ አስረክቧል። አብይ ደግሞ ህዝቡን ባሰመጠበት ንግግር መሄድ የሚችለውን ያህል እርቀት መጥቷል። አሁን ደግሞ በሆነ ኦሮሙማ-በቀል ስልት የህዝብ ጀግና ሁኖ የሚመጣ ታከለ ወይም ጃዋር ይኖራል። ይህንንም ድራማ ሰርተው ህዝባዊ አመጹና ትግሉ የማይቆም ሲሆን ነው በጫካም በከተማም ያሰማሩትን ሰራዊት ሰብስበው በአንድነት የሚያሰልፉት። ለህዝብ ጥሪ የሚያደርጉትና ውሱን ቀጠናዎችን ዘግተው ህዝብ ላይ እርምጃ የሚወስዱትም የማጭበርበር ድራማቸው በሙሉ ከከሸፈ በኋላ ነው። የዚያን ጊዜ ከረፈደም ቢሆን ህዝቡ የሚገለጥለት ነገር ይኖራል።