Site icon Dinknesh Ethiopia

የባለሥልጣናትና የባለሀብቶች ግንኙነት ሥርዓት ይኑረው!

The Reporter Ethiopian

October 1, 2023

 

በሕዝብ ድምፅ ሥልጣን የያዘ ፓርቲ የሚመሠርተው መንግሥት ከምንም ነገር በፊት ለሕግና ለሥርዓት መከበር ኃላፊነት ሊኖረው ይገባል፡፡ ይህንን ኃላፊነት በሚገባ ሊወጣ የሚችለው ሥራውን በግልጽነትና በተጠያቂነት መርህ ሲያከናውን ነው፡፡ የመንግሥት አሠራር በግልጽነትና በተጠያቂነት መርህ ሲመራ በሥልጣን መባለግም ሆነ፣ ለሕገወጥነት የሚገፋፉ ድርጊቶች በሙሉ ይመክናሉ፡፡ በቅርቡ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባውን ያከናወነው ገዥው የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት፣ የአመራሩ ዲሲፕሊን መሻሻል ማሳየቱንና የመፈጸምና የማስፈጸም አቅሙም እየጎለበተ መሆኑን መግለጻቸው ይታወሳል፡፡ በተጨማሪም በተለይ የሕዝብ ቅሬታ የሚነሳባቸው የመንግሥት አገልግሎቶች ላይ ትርጉም ያለው ለውጥ ለማምጣት፣ አገልግሎት የማዘመንና የተቋማት ግንባታን ማጠናከር በትኩረት እንደሚከናወን፣ ሌብነትና ብልሹ አሠራርን ለመከላከልና ለመቆጣጠርም የተጠናከረ ሥራ እንደሚከናወን አቅጣጫ መቀመጡን ማስታወቃቸው አይዘነጋም፡፡ ይህ ቃል በሕዝብ ዘንድ አመኔታ የሚያገኘው የፓርቲም ሆነ የመንግሥት ሥራዎች በሥርዓት ሲከናወኑ ነው፡፡ በተለይ የመንግሥት ሥልጣን የተቆናጠጡ ግለሰቦች በእያንዳንዱ ድርጊታቸው ኃላፊነትና ተጠያቂነት እንዳለባቸው ሲገነዘቡ ነው፡፡ የተሰጣቸውን ኃላፊነት ለግል ጥቅም መሸጥ ሲያቆሙም ነው፡፡

በኢትዮጵያ በባለሥልጣናትና በባለሀብቶች መካከል የሚፈጠር የጥቅም ወዳጅነት አዲስ አይደለም፡፡ የሩቅ ዘመኑን ትተን በአንድ ወቅት ወዳጅነቱ ጣሪያ ከመንካቱ የተነሳ፣ ‹‹የኢሕአዴግ ደጋፊዎች ባለሀብቶች ማኅበር›› የሚል ስያሜ የነበረው ስብስብ ነበር፡፡ ይህ ስብስብ በምርጫ 2002 ጊዜ ለኢሕአዴግ የምርጫ ቅስቀሳ ድጋፍ ከማድረግ አልፎ 40 ሚሊዮን ብር ከአባላቱ አሰባስቦ ማበርከቱም ይታወሳል፡፡ በግለሰብ ደረጃም የባለሥልጣናትን ልጆች ውጭ አገር ድረስ ልከው የሚያስተምሩ፣ ለትዳር አጋሮቻቸው ውድ ስጦታዎችን ከመስጠት አልፈው የንግድ መደብር የሚከፍቱ፣ ዓመት በዓል በመጣ ቁጥር በግ፣ ፍየል፣ ውስኪና ሌሎች ውድ ነገሮችን የሚያበረክቱ፣ የመኖሪያ ቪላ በነፃ ገንብተው የሚያስረክቡ፣ እንዲሁም በማንኛውም ጉዳይ ሲፈለጉ ከተፍ ብለው የሚጠየቁትን የሚሰጡ ብዙ ነበሩ፡፡ እነዚህ ባለሀብቶች ይህንን ሁሉ ያደርጉ የነበረው መሬት፣ የባንክ ብድር፣ የውጭ ምንዛሪ፣ ከቀረጥ ነፃ መብት፣ ያለ ጨረታ ኮንትራቶችን ማግኘት፣ ዕቃዎችን ማቅረብና የመሳሰሉ ጥቅሞችን ለማጋበስ ነው፡፡ አሁንም በዚህ መንገድ የሚጠቀሙ በብዛት እንዳሉ የታወቀ ነው፡፡

ኢትዮጵያ ከ1984 ዓ.ም. ጀምሮ ገበያ መር የኢኮኖሚ ሥርዓት የምትከተል አገር እንደሆነች በይፋ ቢታወጅም፣ የኢኮኖሚ አመራሩም ሆነ የግብይት ሥርዓቱ በጤናማ ውድድር የማይመራ በመሆኑ ከፍተኛ በደሎች ተፈጽመዋል፡፡ በነፃ ገበያ ሥርዓት ስም ገበያው መረን ተለቆ ሸማቾች ያለ መንግሥታዊ ጥበቃ ሲበዘበዙ ተመልካች የለም፡፡ የሁሉም ምርቶች አቅርቦት በጥቂት የንግዱ ተዋናዮችና ከለላ ሰጪ ባለሥልጣናት ታንቆ፣ ከነፃ ገበያ ሥርዓት በተቃራኒ ግብይት ሲከናወንና ጥቂቶች ከመጠን በላይ ሀብት ሲያጋብሱ የሚቆጣጠር የለም፡፡ ግብር ከማጭበርበርና ከመሰወር ታልፎ በይፋ የኮንትሮባንድ ንግድ ተስፋፍቶ ከአቅም በላይ ሲሆን፣ ከዚህ በስተጀርባ ያሉ ሥውር እጆች ያለ ከልካይ ያሻቸውን እያደረጉ አገር እየደማች ነው፡፡ ኤክስፖርት ተደርገው ለአገር ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ማስገኘት ያለባቸው ምርቶች ታግተው፣ በኮንትሮባንድ ወደ ጎረቤት አገሮች እየወጡ እየደረሰ ያለው ኪሳራ ከሚታሰበው በላይ እየሆነ ነው፡፡ ለአገር የሚጠቅሙ ታላላቅ ፋይዳ ያላቸው ፕሮጀክቶች በውጭ ምንዛሪ እጥረት እየተጨናገፉ፣ ጥቂቶች በሕገወጥ መንገድ የተንደላቀቀ ሕይወት የሚመሩበት ምክንያት ከማስገረም አልፎ ያስቆጫል፡፡

ሌላው ቀርቶ በመሠረታዊ የምግብ ምርቶች ማለትም በጤፍ፣ በስንዴ፣ በጥራጥሬ፣ በዘይትና በመሳሰሉት አቅርቦቶች ላይ የሚስተዋለው ሕገወጥነት ከባድ ጉዳት እያደረሰ ነው፡፡ ከምርቶቹ እጥረት በተጨማሪ አጋጣሚውን በመጠቀም የግብይት ሥርዓቱን በመረበሽ የዋጋ ንረት እየተባባሰ ነው፡፡ በየዕለቱ በእያንዳንዱ የፍጆታ ዕቃና ሸቀጣ ሸቀጦች ላይ የሚታየው የዋጋ ጭማሪ የቁጥጥር መላላትን ያሳያል፡፡ የቁጥጥሩ መላላት ደግሞ ንግዱ ውስጥ ያሉት ተዋንያን ከባለሥልጣናት ጋር ያላቸውን ግንኙነት ያመላክታል፡፡ እዚህ ላይ ልብ ማለት የሚገባው መንግሥት በቀጥታ ግብይት ውስጥ ገብቶ ዋጋ ይወስን ማለት እንዳልሆነ ነው፡፡ ነገር ግን የግብይት ሥርዓቱን ጤና የሚነሱ ሕገወጥ እጆች ሲበረክቱና የአቅርቦት ሰንሰለቱ ሲረዝም፣ መንግሥት ሕግ ለማስከበር ታጥቆ መነሳት የሚጠበቅበት ኃላፊነት ነው፡፡ ነገር ግን የባለሥልጣናት ቤተሰቦች ጭምር የምግብ፣ የሲሚንቶና የሌሎች ሸቀጣ ሸቀጦች ንግድ ውስጥ ከባለሀብቶች ጋር አብረው ሲሠሩ ነው ችግሩ የሚደጋገመው፡፡ ባለሥልጣናትና ባለሀብቶች አንድ ላይ ሆነው አገር ሲያደሙ ዝምታው እስከ መቼ ነው መባል አለበት፡፡

አገራቸውን በታማኝነትና በቅንነት እያገለገሉ ሀብት ለማፍራት የሚተጉ በርካታ ቅን ዜጎች አሉ፡፡ እነዚህ ወገኖች ጉቦ ስለማይሰጡ፣ ግብር ስለማያጭበረብሩ፣ ኮንትሮባንድ ስለማይነግዱ፣ በአጠቃላይ እላፊ ነገር ስለማይፈልጉ ብቻ ወደ ጎን እየተገፉም ቢሆን በንፅህና እየሠሩ መሆናቸው ይታወቃል፡፡ በንፅህና ሠርተው ለአገራቸው ጠቃሚ ሥራዎች ማበርከታቸው ቢታወቅም፣ በሌላ በኩል በሙስና በተካኑ ሹማምንትና በተባባሪዎቻቸው ሲዋከቡ ከለላ የሚሆናቸው የለም፡፡ በየምክንያቱ እየተዋከቡ የሌብነቱ ድር ውስጥ እንዲገቡ ይገፋሉ፡፡ ለሌብነቱ ተባባሪ መሆን አንፈልግም ብለው ካመፁ ምክንያት እየተፈለገላቸው ከጨዋታው ውጪ ይደረጋሉ፡፡ ከበፊቱም በዚህ አሳፋሪ ድርጊት የተካኑት ግን ከመሠረታዊ የፍጆታ ዕቃዎች ዕገታ እስከ ትልልቅ ኢንቨስትመንቶች ድረስ አገርን ለመዝረፍ ዓይናቸውን አያሹም፡፡ ለአገር ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ሊያስገኙ የሚችሉ ምርቶች ምንጮችን በተባባሪ ባለሥልጣናት በመታገዝ በመቆጣጠር፣ በዛሬው ብቻ ሳይሆን በመጪው ትውልድ ህልውና ላይ ከመቆመር ወደኋላ እንደማይሉ በርካታ ማጣቀሻዎችን ማቅረብ ይቻላል፡፡ በሁሉም የኢኮኖሚ ዘርፎች ደም ሥር ውስጥ እየገቡ አገር የሚያራቁቱ በዝተዋል፡፡

የባለሥልጣናትና የባለሀብቶች ግንኙነት ሥርዓት ሳይበጅለት ሲቀር፣ ለአገርና ለሕዝብ የማይጠቅሙ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ይወጣሉ፡፡ ለምሳሌ የኑሮ ውድነትንና የዋጋ ግሽበትን ፈር ማስያዝ የሚገባቸው ፖሊሲዎች ወይም ስትራቴጂዎች ተጠልፈው፣ የጥቂት ባለሀብቶችን ጥቅም ብቻ የሚያስጠብቁ ይሆናሉ፡፡ ከውጭ የሚመጡ ምርቶችን በአገር ውስጥ መተካት የሚችሉ አምራቾች ተገፍተው፣ ከፍተኛ ጥቅም የሚያጋብሱ አስመጪዎች በስንት ልፋት የሚገኝ ውስን የውጭ ምንዛሪ በከንቱ እንዲያባክኑ ይደረጋል፡፡ በአገር ልማትና ዕድገት ስም የሚወጡ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች የጥቂቶች ፍላጎት ማርኪያ እየሆኑ፣ ብዙኃኑ ሕዝብ የሚበላው እስኪያጣ ድረስ የችጋርና የጠኔ መጫወቻ ይሆናል፡፡ የባለሥልጣናትና የባለሀብቶች ግንኙነት መረን ሲለቀቅ ለግብርና ከሚውል መሬት ጀምሮ፣ እስከ ማዕድን ማውጫ ቦታዎች ድረስ የጥቂቶች መፈንጫ ይደረጋሉ፡፡ በ‹‹እከከኝ ልከክልህ›› መርህ አልባ ጉድኝት የሚፈጠር የሌብነትና የዘረፋ ግንኙነት፣ የመንግሥት መዋቅሮችን ጭምር በመቆጣጠር የጥቂት ‹‹መሣፍንቶች›› (Oligarchies) ሥርዓት ይፈጥራል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ማፍያዎች የሚሰባሰቡበት ሥርዓት ሲያብብ፣ ስለአገር ደኅንነትና ስለሕዝብ ህልውና በጭራሽ መነጋገር አይቻልም፡፡ ስለዚህ የባለሥልጣናትና የባለሀብቶች ግንኙነት ሥርዓት ይኑረው!

 

 

Source: The Reporter

Exit mobile version