Site icon Dinknesh Ethiopia

በአዲስ አበባ ዙሪያ የሚደረገው ዜጎችን የማፈናቀል ዘመቻ አስመልክቶ ከኢሕአፓ የተሰጠ መግለጫ

eprp

 

ከኢሕአፓ: የአንድ መንግሥት ዴሞከራሲያዊነት መሠረታዊ መግለጫው የዜጎች በተሟላ ክብር መኖር መቻል ነው። በክብር መኖር ማለት ቅንጦት አይደለም፣ መሠረታዊ ሰብዓዊ መብቶች የሚከበሩበት ሕይወትን መምራት መቻል ማለት ነው። ዝቅተኛዎቹ የሰብዓዊ መብት መገለጫዎች ደግሞ ረሀብን ለማሰታገስ የሚችል ምግብ፣ ርቃነ-ሥጋን የሚሸፍኑበት ልብስ እነዲሁም ጎንን ማሳረፍ ሚቻልበት መጠለያ ማግኘት ናቸው። እነዚህ ያልተሟሉለት ሰብዓዊ ፍጡር ስለክብር መናገር አይችልም፣ እንዲህ ዓይነት ሕይወት የሚኖሩ ዜጎች የተትረፈረፉበት መንግሥትና አገርም ስለዴሞክራሲያዊነት ሊናግር የሞራል ብቃት አይኖረውም።

ኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ዴሞክራሲን ዕውን ለማድረግ በለውጥ ሂደት ውስጥ መግባቷ ሲነገር ሰንብቷል፣ ይህንኑም የሚያመላክቱ የተስፋ ብልጭታዎች መታየት መጀመራቸውን አሌ ማለት አይቻልም። ሆኖም ይህን ለውጥ በሕዝቡ ዕለታዊ ሕይወት ውስጥ ሲተገበር ማየት ሳይሆን የከፉ ሁኔታዎች የሚከሰቱባቸው አጋጣሚዎች የተለመዱ ሆነዋል። ከመሠረታዊ መብቶች ጥሰቶች አንዱን ብቻ በመውሰድ በውስጣዊ መፈናቀል ከቤታቸው በሚሰደዱ ዜጎች ቁጥር ከዓለም በመጀመሪያ ተርታ የምትሰለፍ ሀገር ከሆነች ሰንብቷል። የዚህ መፈናቀል ዋናው ምክንያት የዘር ፖለቲካ ትርክት የወለደው ጨካኝ አመለካከት ሲሆን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በአዲስ አበባ አካባቢ ከቤት ማፈናቀሉን መንግሥትም ተያይዞታል። ለዚህ በትር ተጋላጭ የሆኑት ለገጣፎ እና ሱሉልታ የሚባሉት አካባቢዎች ተጠቃሽ ናቸው። የቤት ማፍረሱና ሕዝብን ጎዳና ላይ የላስቲክ ውስጥ ኑሮ የመግፋት እንቅስቃሴው ጥቂት አደብ ገዝቶ ከሰነበተ በኋላ ሰሞኑን ደግሞ እንደገና ተጋግሎ በሺዎች የሚቆጠሩ ቤቶች በመፍረስ ላይ ይገኛሉ፡፡

መንግሥት የዜጎቹን መጠለያ የማግኘት መብት ማረጋገጥ ሲገባው “ሕገወጥ ግንባታ” በማለት ከዘረኝነት ትርክት ባልወጣ አስተሳሰብ ኢ-ሰብአዊ በሆነ መልኩ ዜጎችን ከቤታቸው ማፈናቀሉ በምንም መመዘኛ ትክክል ሊሆን አይችልም። ከቀናት በፊት የወለደች እናትን ከጎጆዋ አውጥቶ፣ ቤቷን ከነዕቃዎቿ አጥፍቶና ቆርቆሮውን ለአፍራሽ ግብረሃይል

የሚያከፋፍል የመንግሥት አካል ዴሞክራሲያዊ ሊሆን ቀርቶ ከዴሞክራሲ ጋር የሚተዋወቅ ነው ሊባል አይችልም። ቤታቸው የሚፈርስባቸው ዜጎች ሃብታሞች አይደሉም፣ በዐረብ አገራት ተንከራተው፣ ኮብል ድንጋይ ቀጥቅጠው መዳፋቸውን እያደደሩ…ወዘተ ባጠራቀሟት ገንዘብ እንደሰው በክብር የሚያርፉበት ቤት ቀልሰው ለመኖር የሞከሩት ከዓመታት በፊት ከባለይዞታዎች በግዢ ባገኙት ቦታ ላይ ነው።

ለመሆኑ መንግሥት የነዚህን ቤቶች ግንባታ ተመልክቶ ለማፍረስ በወኔ የሚሰለፍ ግብረሃይል አቋቁሞ በኢ-ሰብዓዊነት ዘመቻ ማካሄድን እንደመፍትሄ መውሰዱ ትክክል ነው የሚል መከራከሪያ ይኖረዋል? የቤቶቹ ግንባታስ በማን እንደሚመቻች የማያውቅ ሆኖ ይሆን? ይህን የአደባባይ ሚስጥር የሆነ ሂደት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መፍትሄ ለመስጠትና የሕዝቡን መጠለያ የማግኘት መብት ለማረጋገጥ ለምን አልተፈለገም?

ይህ ምርምር የሚያስፈልገው ጉዳይ አይደለም ምክንያቱም ይህ ሁሉ በሕዝብ ላይ የሚደርሰው ስቃይ መንስዔው የራሱ የመንግሥት አካላት በመሆናቸው ነው። በመንግሥት መዋቅር በተለያየ ደረጃ ላይ የሚሰየሙ ሰዎች ተጨማሪ ገቢ የሚመነጨው ከዚሁ የቤት ግንባታ ሂደት መሆኑን ቤቶቻቸው የሚፈርስባቸው ዜጎችም ሆኑ የሚመለከታቸው ባለሥልጣናት በሚገባ ያውቁታል። መሬቱ ከገበሬም ሆነ ከሌላ ሲገዛ ጉቦ፣ በተገዛው መሬት ላይ ቤት መሥራት ሲጀመር ጉቦ፣ ቤቶቹ ተሰርተው አልቀው ገና እፎይ ብለው ሳይጀምሩ “ሕገውጥ ግንባታ” የሚል ዘፈን መቀንቀን ሲጀምር የሚጠቁሙትም እነዚያው ጉቦ ተቀባዮች፣ ፈረሳው ሲጀመር ቤቱ እንዳይፈርስ ለማድረግ እንደገና ጉቦ የሚወስዱትም እነዚያው ሹመኞች…ወዘተ ናቸው።

ለነዚህ ምስኪን ዜጎች ጉዳዩ “የቸገረው እርጉዝ ያገባል…” እንዲሉ ሆኖባቸው ያላቸውን እያሟጠጡ እስከመጨረሻው ጉቦ መክፈል ዕጣ ፈንታቸው ሆኗል። መዋቅሩ እንዲህ በሙስና የተጨማለቀ መሆኑን መንግሥት ካላወቀ ደግሞ ለእነዚህ የሰብዓዊ መብት ጥሰት የየዕለቱ ኑሮአቸው ለሆነባቸው ዜጎች ጆሮ ሰጥቶ ማዳመጥ ብቻ በቂው ነው። ዳሩ ግን “ተጨፈኑ ላሞኛችሁ” ካልሆነ በስተቀር በመሬት ሽያጭ የበለፀጉ ባለሥልጣናቱን መንግሥት አሳምሮ ያውቃቸዋል፣ ለችግሩ ዘላቂ መፍትሄ መስጠትም መዋቅራዊ ለውጥ የሚያሻው ጉዳይ መሆኑንም እንደዚያው። ለውጡ ግን የሕዝብን ሕይወት አወንታዊ በሆነ መልኩ ለመዳሰስ ብቁ ያልሆነ፣ ጭራሹንም በለውጥ ስም የሕዝብ መብቶች የሚጣሱበትን ሁኔታ እየወለደ መምጣቱ ይስተዋላል።

ኢሕአፓ በየክረምቱ እየተነሱ ቤት የማፍረስን አሠራር አጥብቆ ይቃወማል፣ በመሆኑም በአሁኑ ሰዓት በለገጣፎና በሱሉልታ እየተካሄደ ያለው የቤት ፈረሳ እንዲቆም አጥብቆ

ይጠይቃል። መንግሥት ይህንን ተግባር አቁሞ ለችግሩ ሕጋዊና ዘላቂ መፍትሄ በመስጠት የዜጎችን መሠረታዊ መብት እንዲያከብርም ያሳስባል።

መሠረታዊ የዴሞክራሲያዊ መብቶች ይከበሩ!

ነሃሴ ፳፪ ቀን ፪ ሺህ ፲፩ ዓ. ም August 28, 2019
አዲስ አበባ

Exit mobile version