አክሎግ ቢራራ (ዶር)
Opinion

ኢትዮጵያን ለመታደግ የተዋህዶን እምነት አንድነት መደገፍ ያስፈልጋል – አክሎግ ቢራራ (ዶር )

“We but mirror the world. All the tendencies present in the outer world are to be found in the world of our body. If we could change ourselves, the tendencies in the world would also change. As a man changes his own nature, so does the attitude of the world change towards him. This is the divine mystery supreme. A wonderful thing it is and the source of our happiness. We need not wait to see what others do.” Mahatma Gandhi

የታወቁት የሕንድ አባትና መሪ፤ መሃታማ ጋንዲ የተናገሩት የዛሬውን የሚያሰጋ የኢትዮጵያን ሁኔታ ይገልጸዋል። እኔ የዛሬ አንድ አመት ተኩል፤ በውድ አገራችን ለውጥ መጣ ሲባል የነበረኝ ተስፋ ከፍ ያለ ነበር። ለአገራችን ዘላቂነትና ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሰላም፤ እርጋታ፤ ደህንነት፤ ፍትህ-ርትህ፤ ሰብአዊ መብትና ክብር፤ የሕግ የበላይነት፤ የዜጎች እኩልነት፤ አብሮነትና ሕዝቡ የፖለቲካ ሥልጣኑ የበላይነት ስኬታማ የሚሆንበት ዘመን መጣ ብየ ነበር። ከብሄር ጥላቻ ራሳችንን ነጻ አውጥተን የኢትዮጵያን ሕዝብ ከድህነት አሮንቃ ነጻ የምናወጣበት ጊዜ አጭር ይሆናል የሚል ግምት ነበረኝ።

እውነትም፤ የአገሬን ምሁራንና ልሂቃን አላውቃቸውም ማለት ነው። በተለይ፤ የማይለወጡትን የብሄርና የኃይማኖት ጽንፈኞችን፤ የውጭ ባህልና ገንዘብ አምላኪዎችን። “ከድጡ ወደ ማጡ” እንዲሉ ኢትዮጵያ ወደ ባሰ የብሄርና የኃይማኖት ግጭት በመሸጋገር ላይ ትገኛለች። የባህርይ አለመለወጥ፤ እያወቁ ማበድ ችግሩ ይኼው ነው።

ለውጡ ሲከሰት የነበረኝን ህልምና ምኞት ስኬታማ ለማድረግ፤ ምሁራን፤ መንፈሣዊ አባቶችና እናቶች፤ ወጣቶች፤፤ ሽማግሌዎች፤ የፖለቲካ ልሂቃን በግል ሆነ በቡድን ራሳችንን ተመራምረን እንልወጣለን የሚል ግምት ነበረኝ። ምክንያቱም፤ የራሳችን ዝንባሌ፤ አስተሳሰብና አመለካከት ለመለወጥ ካልፈለግን ሕብረተሰባችንን ለመለወጥ አንችልም። ራሳችን ከለወጥን ግን የህብረተሰባችንን አሰቃቂ የኑሮ ሁኔታ ለውጠን መላው ዓለም እንዲያከብረን ለማድረግ እንችላለን። ጋንዲ እንዳሉት፤ “ሰው ተፈጥሮውን (አመለካከቱን) ሲቀይር፤ ሌላው የሚመለከተው አለም (በዙሪያው) ያለውም ተመልካችም ይለወጣል።” ህጻናት ጥላቻን አስወግደው፤ በሞራል ተገንብተው ያድጋሉ። ቁም ነገሩ፤ “ሌላው እንዲለወጥ ከመጠበቅ ይልቅ መጀመሪያ” ራሳችን ለውጠን አርዓያ ለመሆን እንችላለን” የሚለው ነው። ፈረንጅ አምላኩ እየሆንን ስለሄድን ነው እንጅ ጋንዲን የጠቀስኩት፤ እኛም ብዙ ተመክሮዎች አሉን። አበው ሲናገሩ፤ “የዝብራት በራፍ ሳይዘጋ ያድራል” እንደሚሉት፤ አንዱ ሌላውን በጎሪጥ እያየ፤ በሌላው እያመካኘ ከሄደ፤ አገር ተቆርቋሪ ታጣለች፤ ጥፋት ይከተላል።

ጠ/ሚንስትር ዶር ዐብይ አህመድ ሥልጣን ከያዙ በኋላ ሁኔታዎች ተባብሰዋል። ከቁጥጥር በላይ ሆነዋል። እርግጥ ኢትዮጵያ አልፈረሰችም፤ የሚያፈርሷት ሁኔታዎች ግን ስር እየሰደዱና እየተስፋፉ ሄደዋል። ልንክደው የማንችለው ሃቅ፤ ጥቂቶችም ቢሆኑ፤ የኦሮሞ ብሄር ጽንፈኞች ከአጋራቸው ከህወሓት ጋርና ከውጭ የገንዘብ ደጋፊዎች ጋር ሆነውና ባንኮችን እየዘረፉ፤ ኢትዮጵያን በማፈራርስ ላይ ናቸው። እኔን ያሳሰበኝ፤ ይህ የተቀነባበረ አገርን፤ ባህልን፤ ቋንቋን፤ ኃይማኖትን፤ ተቋማትን የማውደም ዘመቻ ወደ የእርስ በርስ ጦርነት እያመራ መሄዱ ነው።

ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ፤ የፖለቲካውን አመራርና “ሽግግሩን” የሚያሰላው አንዱ የብሄር ቡድን ለተወሰነ ጊዜ ከገዛና ከበላ በኋላ በሌላ የብሄር ቡድን መተከቱ አግባብ ያለው መሆኑን ማስተጋባቱ አደጋውን አባብሶታል። ለጽንፈኖች መጠናከር ግብዓት ሰጥቶታል። እንደ ተራ ነገር፤ አንዱን ብሄር ከሌላው ለይቶና አብልጦ ማሳደግና መንከባከብ ወይንም አንዱን ብሄር ከሌላው አብልጦ ጨቋኝና ግፍ ፈጻሚ አድርጎ ማቅረብ የተለመዱ የገዢው ፓርቲ መገለጫዎች ሆነዋል። ይህ ሕዝቡ የፈጠረው አይደለም። ስርዓቱ ሆነ ብሎ የመሰረተውና የሚጠቀምበት የፖለቲካ የበላይነት መሳሪያ ነው። በዚህም የተነሳ፤ የአማራው ሕዝብ በተለየ ሁኔታ ታሪኩ፤ ባህሉ፤ ልምዱ፤ አስተዋጾውና ሌላው አሻራው ሁሉ እንዲጠፋ እየተደረገ ነው።

ትኩረት የሰጠሁት የተዋህዶ ክርስትና እምነትና ተቋም ሁኔታ ከላይ ከጠቀስኩት ማንኛውንም የቆየ የኢትዮጵያ አሻራዎች ሙሉ በሙሉ ከማውደሙ ዘመቻ ጋር የተያያዙ ሆነው አያቸዋለሁ። የሽግግሩ መሪዎች፤ በተለይ ጠ/ሚንስትሩ ይህን የአፍራሾችን ጉዞ ለምን ሊቋቋሙትና ደፍረው አቋም ሊወስዱበት እንዳልችሉ ለማወቅ የሚያስችለን የወደፊት ታሪክ ነው። ለጊዜው ግን የኃይል ሚዛኑ የሚያሳየው ጠባብ ብሄርተኞችና ጽንፈኞች አንበሳውን ኃይል እንደያዙ ነው።

በመንፈሥም ሆነ በሌላ ገንቢ መስፈርት ስመለከተው፤ እኛ ተነክተናል። ምን ነክቶን ነው እርስ በእርሳችን የምንጋደለው፤ የምንናከሰው፤ የምንወነጃጀለው? ምን ነክቶን ነው አስተሳሰባችን፤ አመለካከታችን፤ ዝንባሌያችን፤ አአምሯችን 110 ሚሊየን ከደረሰው ከኢትዮጵያ ሕዝብ ምኞትና ፍላጎት ጋር ሊመዛዛንና ሊጣጣም ያልቻለው? ሕዝቡ የሚፈልገው ቂም በቀልነትን፤ ዘረኝነትን፤ የብሄር ሆነ ያኃይማኖት ጽንፈኝነትን፤ “ትላንት አንተ በልተሓል፤ ዛሬ የእኔ ተራ ነው” ባይነትን፤ በማንነት ስም አገር ማጥፋትን፤ ጦርነትን፤ የንብረት ውድመትን፤ ግድያንና አፈናን ወዘተ እንዳልሆነ አምናለሁ። እነዚህን የሚያመጣቸው ተራው ሰርቶ አደር ሕዝብ አይደለም። ተራው ሕዝብ የብሄር ወይንም የዘር የፖለቲካ ንግድ አገዛዝን የሚፈልግ አለመሆኑንም አምናለሁ። ምክንያቱም፤ ወጣት ልጆቹ በገፍና በጭካኔ በህወሓት አልሞ ተኳሾች መጨፍጨፉቸውን ያውቃል። ተራው ሕዝብ የሚመኘው ኑሮው እንዲሻሻልለት፤ በሃገሩ ተክብሮ በሰላም መኖርን ነው።

እናስብ፤ ብዙ ትምህርት ለመማር የሚፈልጉ ወጣቶች ደብተር፤ እርሳስ፤ መቀመጫ ወንበር፤ መጽሃፍ ወዘተ ለመግዛት በማይችሉባት ኢትዮጵያ መሳሪያ እየገዙ ለጦርነት የሚዘጋጁ ኃይሎች ሽር ጉድ የሚሉበት ሁኔታ የተበከለ የሕህብረተሰብ ክፍል እንዳለ ያሳያል። ከልማት ይልቅ፤ ጦርነነትና እልቂት የሚመርጥ ክፍል ይታያል። ዓለም ለእድገትና ለሥልጣኒ ይሯሯጣል፤ እኛ ለጦርነት!!

እኔ የማላውቀው መምህር መስፍን የተባለ ወጣት “ሃገሬ ምን ነካት?” በሚል አርእስት የአስተሳሰብ ድህነትና መጥፎነት የሚያስከትለውን አደጋ የህሊናን አጠቃቀም ግድፈቶች አስመልክቶ ያቀረበው ጥልቀትና ብስለት ያለው ዘገባ ለሚሰማው ተራራን ያናጋል። የሌለ ታሪክና ትርክት ፈጥሮ ሕዝብን ለግጭትና ለእልቂት መቀስቀስ አገርን ያጠፋል፤ የእርስ በእርስ ጦርነት ያስከትላል። ተቋማት እንዲወድሙ ያደርጋል። ጦርነት ሥልጣኔ አይደለም። ዛሬ ሶስት ወይንም አራት ሚሊየን ሕዝብ ተፈናቅሎ ከሆነ ነገ፤ የእርስ በእርስ ጦርነት ቢካሄድ፤ አስርቶች ሚሊየን ይፈናቀላል። መስፍን እንደጠቀሰው፤ ዛሬ ኢትዮጵያ የሶሪያን ስደተኞች እንዳስተናገደችው ሁሉ፤ ነገ ኢትዮጵያዊያን በገፍ ስደተኞች እንደሚሆኑ ከአሁኑ መገመት አያዳግትም። ያውም የሚቀበላቸው አገር ቢገኝ ነው። ስድተኞችም ባይሆኑ፤ በሳውዲ አረብያ ብቻ 750,000 ወገኖቻችን ይሰቃያሉ። አንድ ዘገባ እንዳሳየው፤ ፖሊሶች በበትር እየደበደቡ፤ “ውሻ” ብለው ሰድበዋቸዋል። “ውሽ” ተብለን ለመጠራት ያበቃን አገር ስለሌለን አይደለም። የፖለቲካ ልሂቃኑ ህሊና ቢስነት፤ ብሄር ተኮሩና የአፓርታይድን አይነት አስተዳደር የጫነው የኢህአዴግ ስርዓት፤ ዘውጋዊውና ኃይማኖታዊው ቂም በቀልነት፤ የብሄርና የኃይማኖት ጽንፈኛነት፤ አድር ባይነት፤ በመምህሩ አነጋገር “የአአምሮ ብልሹነት” ነው። ለሁሉም የምትበቃ የተቀደሰች አገር ተረክበን በመሬት ይገባኛልነት፤ “የእኔ ብቻ፤ የእኛ (ኬኛ) ብቻ” ባይነት እንዋጋለን። እኛ እርስ በእርሳችን እየተገዳደልን አገሪቱን አደጋ ጫፍ ላይ አድርሰናታል። ይህ እርግማን ነው።

እኛ ስደተኞችን እያስተናገድን ራስችን ስደተኛ እንፈጥራለን። እኛ ወደ ክልላችን “አትምጡብን” ወይንም ከክልላችን “ውጡልን” እያልን የደቡብ አፍሪካን መንግሥት እባካችሁ የኢትዮጵያን ስደተኞችን ሰብአዊ መብት አክብሩልን አንላለን። አገርን በመገንባት ፋንታ፤ ሁሉም ኢትዮጵያዊያን መስዋእት የሆኑላትንና ለመላው የጥቁር ህዝቦች ተምሳሌት የሆነችውን ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሽር ጉድ አንላለን። ህወሓቶች ኢትዮጵያን ሊገዟትና ሊመዘብሯት እስከቻሉ ድረስ እንደ አገራቸው ይፈልጓታል፤ ሃብት ያካብቱባታል፤ ይቀራመቷታል። ከሥልጣን ሲወገዱ ግን “እንገነጠላለን” እያሉ ይዝቱባታል። ኦነጎች “ለብዙ መቶዎውች አመታት ተጨቁነናል” እያሉ ያስፈራሯታል። ሁለቱም ስሟን አዘውትረው ለመጥራት ይጠየፋሉ። መለያዋን ሰንደቅ ዓላማ አይጠቀሙም።

ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነቱን ሙጥኝ ብሎ የያዘው መከረኛው የአማራው ሕዝብ “ጨቋኝና ትምክህተኛ ነህ” ተብሎ ተከሶና ተወንጅሎ፤ በተለይ ባለፉት 28 ኣመታት፤ መስዋእት በሆነላት ኢትዮጵያ ሆነ ተብሎ በማንኛውም የልማት መስፈርቶች የመጨረሻ ድሃና ኋላ ቀር እንዲሆን ተፈርዶበት ቆይቷል። መለስ ዜናዊና የሚመራው የኢህአዴግ መንግሥት በየዓመቱ የሚያወጡት ባጀት ድርሻ፤ በመጀመሪያ ደረጃ ለትግራይ ክልል፤ በሁለተኛ ደረጃ ለኦሮምያ ክልል ይመደብ እንደነበር ዓለም ባንክ ስሰራ አውቅ ነበር። ጥያቄ ሳቀርብ የሚሰጠኝ መልስ ”እኛ ድህነትን ለማጥፋት እንረዳለን እንጅ ውሳኔው የኢትዮጵያ መንግሥት ነው” ይሉኝ ነበር። በመጨረሻ ግን፤ ዓለም ባንክ ያወጣው ዘገባ ሁለቱ ክልሎች ተጠቃሚ መሆናቸውና የልማት ውጤት ማሳየታቸውን አምኗል። ይህ የተዛባ ባጀት የተዛባ የልማት ውጤት ማሳየቱ በግልጽ ይታያል;፡ በአብዛኛው፤ የአማራው ክልል ግፍና በደል ተፈጽሞበታል። ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የጎንደር ከተማ ነው። እንኳን ዘመናዊ መሰረተ ልማት፤ ዘመናዊ ህንጻዎች፤ ኢንዱስትሪዎች እና የኢንዱስትሪ ፓርኮች ሊሰሩበት ቀርቶ ጣሊያኖች የሰሯቸው ህንጻዎችም ፈርሰዋል። ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በሚያሳፍርና በሚተች ደረጃ ፈራርሰዋል።

በኢህአዴግ ኢትዮጵያ እንገነጠላለን የሚለው ማስፈራሪያ ማንን እንድሚጎዳ ለማሳየት እችል ነበር። ለጊዜው ልቆጠብና ስንት አገሮች ልንፈጥር ነው? የሚለውን ጥያቄ ላቅርብ። ዘጠኝ፤ አስራ ዘጠኝ፤ ሃያ? ለማሳየት የምፈልገው ሃሳብ አንድ ነው። እንገነጣጠል ብንል፤ ቀይ መስመር ወይንም ድንበር አይኖረውም። ለጽንፈኞችና ለብሄርተኞች ይመስላል እንጅ፤ እያንዳንዱ ክልል አንድ ወጥ አይደለም። እያንዳንዱ ክልል የራሱ የሆነ የተቀበረ ቦምብ አለው። ሩቅ ሳንሄድ፤ ሶማልያ ምሳሌ ናት። ደቡብ ሱዳንም ልትጠቀስ ትችላለች።

በአጭሩ፤ የተቀደሰች አገር ተረክበን በመንፈስ የተረገመ ትውልድ፤ በተለይ የተበከለ የፖለቲካ ልሂቃን መፈጠሩ ያስደነግጣል፤ ያሳፍራል። መተኪያ የሌላት አገር ተመጣጣኝ ማህበረሰባዊ አመራር ያስፈልጋታል። ሁሉን በፍትህ፤ በእኩልነት የሚያስተናግድ።

የብዙ ሽህዎች አመታት ተከታታይ የነጻነት ታሪክ፤ መንግሥታትና ዝና ያላት ኢትዮጵያ የምትታወቀው ከሁሉም ብሄር፤ ብሄረሰብና ሕዝቦች ተወጣጥተው ግዛታዊ አንድነቷን፤ ነጻነቷን፤ ክብሯን፤ ዘላቂ ጥቅሟንና ሉዐላዊነቷን ባስጠበቁት ጀግኖቿ መስዋእትነት ነው። ይህን ልንክደው የማንችለውን ሃቅ የሚያስታውሱኝ ብዙ ክስተቶች ቢኖሩም፤ በዛሬው ትንተናየ እምነቴን ያጠናከረልኝ፤ የግል ሃሳቤንና አቋሜን ለኢትዮጵያ ሕዝብ እንዳቀርብ ያስድገደደኝ የኢትዮጵያ ተዋህዶ እምነት ጉዳይ ነው።

እምነት የግል ነው የሚለውን መርህ ብቀበልም፤ የኢትዮጵያ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ታላቅ ተቋም ናት፤ የአገር መከታና መመኪያ ናት። ፊደል ያስቆጠረችኝ ይህችው ቤተክርስቲያን ናት። የዚህችን ታሪካዊ ተቋም መከፋፈልና ማፈራረስ የፖለቲካ ጉዞና ሴራ ከኢትዮጵያ መፈራረስ ጋር አጣምሬ አያቸዋለሁ።

ከ 1,600 ዓመታት በላይ የኢትዮጵያ መለያና መታወቂያ የሆነው የኢትዮጵያ ተዋህዶ የክርስትና ኃይማኖት ተቋም ተከታታይ ጥቃቶች እየደረሱባት መሆኑ ለሁሉም የእምነት ተከታዮችና አገር ወዳዶች እጂግ በጣም አሳሳቢ ነው። ምክንያቱም፤ ከኢትዮጵያ ህልውና ጋር የተያያዘ ነው።

ጥንታዊቷና የብዙ ቅርሶች ባለቤት የሆነችው፤ ለመላው የጥቁር ሕዝብ ሁሉ መመኪያና መለያ ሆና የምትጠቀሰው፤ አብዛኛዎቹ የጥቁር አፍሪካ አገሮች የኢትዮጵያን አረንጓዴ፤ ብጫና ቀይ ሰንደቅ ዓላማ እያሰባጠሩ የራሳቸው ሰንደቅ ዓላማ አድርገው መለያዋን የእኛም መለያችን ነው ብለው የተቀበሏት እናት አገራችን ከመሬት በላይ እና ከመሬት በታች ተቀብረው ያሉና ወደፊት የሚገኙ መለያ የሚሆኑ ብርቃማ ቅርሶች አሏት። እነዚህን ለብዙ ሚሊየኖች የስራ እድል የሚፈጥሩና ግዙፍ ገቢዎች የሚያስገኙ ኃብቶችን ግን የማይቀበሉና ለማውደም የተዘጋጁ ኃይሎች እንዳሉ ይታያል። አንድን አገር ለማጥፋት ከተፈለገ በሁሉም ደረጃ ጥሪቶችንና ቅርሶችን (National Assets and Heritges) ቢቻል ማውደም አለያ መቀየር ያስፈልጋል። ውድመት በሶርያና በአፍጋኒስታን ተፈጽሟል።

ሰሞኑን ትኩረት እንድሰጠው ያስገደደኝ፤ “እናት ቤተክርስትያን” ተብላ የምትታወቀው የኢትዮጵያ ተዋህዶ ቤተክርስትያን የወደፊት እድል ጉዳይ ነው። ለእኔ፤ ይህች የኢትዮጵያ መለያ እናት የሆነችው ቅርሳችን፤ የመላው ክርስቲያኖች፤ ወዳጅና ወገን የሆኑት የሌሎች ኃይማኖቶች፤ ለምሳሌ የእስልምናና የአይሁዶች እምነት ተከታዮችም ኃብት ናት። የእስልምና ኃይማኖት ተከታዮች ግፍና በደል ሲደርስባቸው ተቀብላ ያስተናገደቻቸው ክርስቲያኗ ኢትዮጵያ ናት። በዚህም ምክንያት፤ የክርስትናና የእስልምና ኃይማኖት ተከታዮች በመከባበርና በመፈቃቀር አብረው ኑረዋል። እኔ ባደግሁበት አካባቢ የሁለቱ ኃይማኖቶች ተከታዮች በጉርብትና፤ በንግድ፤ በበአል አከባበር፤ በሃዘን፤ በሰርግ፤ በጋብቻ፤ አገርን ከጠላት በመታደግና በሌሎች አብረውና ተናበው እንደሚኖሩ አስታውሳለሁ።

“እናት ቤተክርስቲያን” ብዙ በመላው ዓለም የሚኖሩ ጥቁር ሕዝቦችም የሚኮሩባት መሆኗን የሚያሳዩ ምልክቶች አሉ። በርሙዳ በተባለች በካሪቢያን የምትገኝ ትንሽ ደሴት የሚኖሩ ጥቁሮች ይህችን ቤተክርስትያን የኣኛም ቅርስ ናት በሚል እምነት ቤተክርስትያን ሰርተው ሲያስመርቁ የተሰማኝ ኩራት መጠን የለውም። በጃማይካ የቆየው ተደናቂነት እየተስፋፋ ወደ ሌሎች የካሪቢያን ደሴቶች እንደተዛመተ አውቅ ነበር። በሃርለም፤ አሜርካ የቆየ እውቅና ያለውን ተመሳሳይ ምሳሌ ለመጥቀስ ይቻላል። በመላው ዓለም የሚኖሩ የዚህች እምነነት ተከታዮች ቤተክርስቲያን እየሰሩ ለኢትዮጵያ ኩራትና መለያ አብርክተዋል። ይህችን መለያችን የሆነች ታሪካዊ የተዋህዶ ክርስትና ተቋም ማፈረስ አይቻልም፤ ጣሊያኖችና ሌሎች የውጭ ኃይሎች ሞክረው ተሸንፈዋል።

እኔን ያሳሰበኝ፤ በኢትዮጵያ ኦሮምያ ክልል የሚገኙ የእናት ቤተክርስትያኗ ተከታዮችን “እንወክላለን” የሚሉ ግለሰቦች የኦሮሞ ተዋህዶ ክርስትና ምእመናን የራሳቸውን “ማንነት” ለማጠናከር የራሳችን የተለየ እውቅና፤ የተለየ አመራር፤ የተለየ ሲኖዶስ ያስፈልገናል የሚል ውሳኔ ማድረጋቸው ነው። ባለፉት ሃያ ስምንት ዓመታት፤ የራስን የፖለቲካ አጀንዳ ለማራመድ ማንኛውንም ማህበረሰባዊ ጥያቄ፤ ከማንነት ጥያቄ ጋር በማያያዝ፤ ብዙ የፈጠራ ታሪክ ተጽፏል፤ ተሰብኳል። እልቂት ተካሂዶበታል። መሬት ተነጥቆበታል።

ወልቃይት ጠገዴ “የእኛ፤ ወሎ የእኛ፤ አዲስ አበባ የእኛ” ወዘተ የሚለው አዲስ የበላይነት ስሌት እየተስፋፋ ሂዶ፤ ዛሬ ወደ ተዋህዶ እምነት “የእኛነት” ተዛምቷል። አደገኛነቱ ለምን? የሚለውን ጥያቄ በአጭሩ ልመልስ። ኃይማኖትና ፖለቲካ አይለያዩም፤ የአንድ ሳንቲም ግልባጭ ናቸው የሚለው ሰው ሰራሽ ፍልስፍና ወደ ጽንፈኝነት ያመራ ትርክት ነው። አቀራረቡ በተውሶ የፖለቲካ ባህል የፈጠራ አስተሳሰብን እየቀመሙ፤ ሕዝብ እንዲወናበድ፤ እርስ በእርሱ እንዲጋጭና የጥቂቶች ዓላማ ስኬትማ እንዲሆን የሚደረግ የፖለቲካ ትግል ስልት ነው።

ጥቂት ግለሰቦች፤ አንድ ግለሰብ “ወፍ ዘራሽ ምሁራን” ብሎ የሰየማቸው፤ በህወሓት ተመርጠው ወደ መቀሌ ሂደው ልክ እንደ ሃቀኛ ምሁራን ታጅበው “ወሎ የኦሮሞ ሕዝብ መሬት ነው” ያሉት ህወሓቶች ራያና አዘቦን፤ ወልቃይት-ጠገዴን በፈጠራ ታሪክ ተደግፈው መሬቱ “የታላቋ ትግራይ” አካል ነው ካሉት አይለይም። በሰሜን ታላቋን ትግራይ፤ በደቡብና በሌላው ታላቋን ኦሮምያ” እያልን ለልማት ማነቆዎችን እየፈጠርን ነው። ህወሓት ከስልጣኑ ከወረደ በኋላ፤ ይህ የመሬት ነጣቂዎች ትብብር ለምን በአዲስ መልኩ አሁን ተከሰተ? የሚለውን ጥያቄ እያንዳንዱ አገር ወዳድ ማሰብ ይኖርበታል። ድብቅ አጀንዳ እንዳለ ያሳያል። አጀንዳውን የሚያጠናክር አንድ ምሳሌ አቀርባለሁ። ለውጡ ሲካሄድ፤ በመቀሌ ከተሳተፉት ጠባብ ብሄርተኞች፤ ጽንፈኞችና አክራሪዎች መካከል አንዱ “ከ 5,000 በላይ የሚገመቱ የኦሮሞ ልጆች መስዋእት” ሆነዋል ብሎ በተደጋጋሚ ተናግሯል፤ ቀስቅሷል። እነዚህን ንጹሃን የረሸናቸው ማነው? ህወሓት መራሹ የኢህ አዴግ መንግሥት ነው። አልሞ ተኳሾቹ ህወሓቶች ናቸው። አማራውና የኢትዮጵያ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አይደሉም።

አበው ሲናረጉ “ታጥቦ ጭቃ” የሚሉት ለዚህ ነው። ትላንት ህወሓትን ማውገዝ፤ ዛሬ ህወሓትን ሙጥኝ ብሎ የአብይን መንግሥት መቃወም፤ የተዋህዶ ቤተክርስቲያኖችን ማቃጠል፤ የኦሮሞ ሲኖድ ይመስረት ብሎ አዲስ ትርክት መፍጠር ከየት መጣ፤ ለምን አላማ? በእኔ እምነት፤ ይህን ክስተት የተለየ የሚያደርገው ሁኔታ አለ። ይኼውም፤ ከህወሓት ጋር የሚያሴረው ቡድን፤ እንደ ልቡ ይናገራል፤ ያስፈራራል፤ እንደ ልቡ ታሪክ ይፈጥራል፤ እንደ ልቡ “እኔም መንግሥት ነኝ” ይላል፤ እንደ ልቡ ከውጭ አካላት ጋር ይተባበራል ወዘተ። አንዳንድ ተመልካቾች “ኢትዮጵያ ሁለት ወይንም ሶስት መንግሥታት አሏት” እያሉ የሚተቹት” ይገባኛል።

የክልል ሆነ የፌደራል መንግሥት ባለሥልጥናት ለጠባብ ብሄርተኞች፤ ለጽንፈኞች፤ ለ“ወፍ ዘራሽ” ምሁራን ገደብ የሌለው፤ ሃላፊነት የጎደለው ነጻነት ሰጥተዋቸዋል። አገርንና ተቋማትን ከማፍረስ፤ ሕዝብን ከሕዝብ ጋር ደም ወደ ማፋሰስ ጫፍ ለማድረስ ካለ ጉዞ ውጭ ሌላ ምን አደጋ እንዲከሰተ እንደሚጠበቅ አይገባኝም። የኢህአዴግ መንግሥት ሃላፊነቱን በአስቸኳይ መወጣት አለበት።

“የእኛ ወይንም ኬኛ” ስለሚለው ቅስቀሳ አደጋ ከዚህ በፊት በሰፊው ስለጻፍኩበት አልመለሥበትም። “የእኔና የእኛ” መለያ ብቻ በሕግ ይታወቅልን የሚል መርህ ከክልልና ከአዲስ አበባ ይገባኛልነት አልፎ ቀስ በቀስ ወደ ሌሎች የኢትዮጵያ መለያ ወደሆኑት ተቋማትም እየተስፋፍ፤ ይህን ስኬታማ ለማድረግም ሰፊ፤ የተቀነባበረ ቅስቀሳና ግፊት መካሄዳቸውን የሚያሳዩ መረጃዎች ይታያሉ። ከእነዚህ መካከል የኢትዮጵያን ተዋህዶ ቤተክርስትያን እንደገና ለመከፋፈል የሚደረገው ጫና ዋናው ምሳሌ ነው። ይህን የመከፋፈል ጉዞ በፌደራልና በክልል የሚገኙ ባልሥልጣናት ለምን ዝም ብለው እንደሚያዩት አልገባኝም። ምክንያቱም፤ እቅዱ ኢትዮጵያን ለማጥፋት ከሚደረገው ሴራ የተለየ አይደለም። በኢትዮጵያ ረዢም የነጻነት ታሪክ፤ እንደ ተዋህዶ እምነት ወሳኝ የሆነ ሚና የተጫወተ የለም። በተጨማሪ፤ እውቀትን፤ ባህልን፤ ትምህርትን፤ የሞራል ብቃትን፤ አብሮነትን፤ ርህራሄን በማስፋፋት በኩል እንደዚህ ተቋም አስተዋጾ ያደረገ ማን ሊጠቀስ ይችላል? አይችልም።

ኢትዮጵያን ለማጥፋት ከተፈለገ ተዋህዶን ማጥፋት ያስፈልጋል የሚሉ ኃይሎች የቆየ ታሪክ አላቸው። ለምሳሌ፤ ህወሓት ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን ለማዳከም፤ ቢቻል ለማፈራረስ ክተጠቀመባቸው መሳሪያዎች መካከል አንዱ ሲኖዶሱን መከፋፈል ነበር። ይህን አገር አፍራሽ ክስተት ጠ/ሚንስትር ዶር ዐብይ አህመድ በጥበብና በብልሃት ለመፍታት ችለዋል። ለዚህ የኢትዮጵያን ሕዝብ አድናቆትና ምርቃት አግኝተዋል። ይህ የተቀደሰ ሁኔታ ስኬታማ ሆኖ ከአንድ ዓመት በኋላ የፖለቲካና የኃይማኖት ጽንፈኞች ባደረጉት ቅስቀሳና አዲስ ትርክት፤ የአገሪቱን ሕዝብ በኃይማኖት ዙሪያ ለመከፋፈል የሚደረገው ጥረት አደገኛ ብቻ ሳይሆን፤ አገር አፍራሽ ሆኖ አየዋለሁ። ምንም የማይካደው በኦሮሞያና በሌሎች አካባቢዎችም ማንኛውም ዘውግ ኃይማኖቱን በራሱ ቋንቋ የማስተናገድ መብቱ መከበር አለበት። ይህ ጠቃሚና አስፍላጊ ነው። የፈረንሳይ ሕዝብ ቋንቋው ከጣሊያኖችና ከሌሎች ይለያል። ኃይማኖቱ ካቶሊክ ነው። ካቶሊኮች የሚጋሩት የካቶሊኩ ፓፓስ የሚኖሩት በቫቲካን ነው። የቋንቋ ልዩነት መኖሩ አመራሩ እንዲለወጥ አላስገደደውም። በተመሳሳይ፤ የእስልምና ኃይማኖት ተከታዮችም የራሳቸው መለያዎች አሏቸው። ለምሳሌ፤ ቁራን በአረብኛ ቋንቋ መጻፉ። የካቶሊክ ኃይማኖት ተከታዮች የሚመሩበት የኃይማኖት ሕግና ደንብ፤ ቀኖና፤ አመራር፤ ስነስርዓት፤ መአከላዊነት ወዘተ አለ። የእስልምናም እንዲሁ። ኃይማኖትን በዘውግና በቋንቋ መለየት የፖለቲካ ውሳኔ እንጅ የመንፈሳዊ ውሳኔ ሆኖ አላየውም። ኃይማኖትን ከማንነት ጋር አያይዞ፤ አባቶችን፣ ምእመናንን መግደል፤ የተዋህዶ ቤተክርስቲያኖችን እየለዩ ማቃጠል ፖለቲካዊ ወንጀል እንጅ መንፈሳዊ ተግባር አይደለም።

በኢትዮጵያ የሚኖሩ የተዋህዶ እምነት ተከታዮች ስርጭት ወርቃማ ነው። ምክንያቱም ዘር አይለይም። ጉራጌዎችም፤ ወላይታዎችም፤ ኦሮሞዎችም፤ አማራዎችም፤ ትግሬዎችም ወዘተ በጋራ የሚመሩበት ሲኖድ አለ። ይህን የቆየ ኃይማኖትና አመራሩን ፖለቲካዊና ዘውጋዊ ማድረግ ለማን ይጠቅማል? ከጀርባ ሆኖ እንከፋፈል የሚለው ማነው? የመጨረሻ ዓላማው ምንድን ነው? የተለያዩ አገሮች ተፈጥረዋል ብሎ ለማረጋገጥ ነው? ህወሓት የጀመረው የመከፋፈል ሴራ ከአሁኑ በምን ይለያል?

ኢህአዴግ በደነገገው የዘውግ ሕገ መንግሥት መሰረት ብዙ አደገኛ ክስተቶች እየታዩ ነው። ዘጠኝ ወይንም ከዚህ በላይ “በቋንቋ “ መለያዎች በተሰየሙት ክልሎችና ዞኖች፤ “የእኔ ወይንም የእኛ ” መሬትና መንግሥት ብቻ ይከበር የሚሉ የፖለቲካ ልሂቃን፤ ምሁራን፤ አክቲቪስት ነን ባዮች፤ ትንንሽ አገሮችና መንግሥታት በመመስረት ላይ እንዳሉ የሚያሳዩ ሁኔታዎች መኖራቸው አይካድም። የሲዳማ የክልል ይገባኛልነት ጥያቄ የሚያቆም አይመስለኝም። ብዙ ሲዳማዎች ቢመሰረቱ ሕዝቡ እስከፈለገና ተጠቃሚ እስከሆነ ድረስ የዲሞክራሲ ጥያቄ ስለሆነ ትልልቅ ክልሎች ተከፋፍለው ትንንሽ ቢሆኑ የአስተዳደር ቅልጥፍና፤ የኢኮኖሚ ግንባታ ወዘተ ጥቅማቸው ሊያመዝን ይችል ይሆናል። ግን፤ የእያንዳንዱ ዜጋ መብት ካልተከበረ ችግሩ አይፈታም። የክልል ይገባኛልነት ጥያቄም ሆነ የሌላ በጥናት፤ በምርምር፤ በሕዝብ ተሳትፎ የሚሰራ ቢሆን የተሻለ ውጤት ይኖርዋል። ችግሩ ሕግ አልባነት ተደጋጋሚ መሆኑ ነው። የፖለቲካው ልዩነትና መከፋፈል ወደ መንፈሳዊው ሲዛመት የሚያስክተልው ውጤት የከፋ እንደሚሆን አንጠራጠር።

በመቀሌ ያለው የህወሓት ቡድን አልደራደርም፤ ከማንም ምንም የምማረው ነገር የለም በሚል እብሪተኛነት የራሱን “ሁሉን አቀፍ” ጉባኤ እያካሄደ፤ ሕዝብ ያመጣውንና የሚደግፈውን ለውጥ ተፈታትኖታል። የዱሮ ተጠቃሚዎች፤ “የቀን ጅቦች” ተብለው የተሰየሙትም ለውጡን ይቃወሙታል። በተመሳሳይ፤ በአዲስ አበባና በኦሮሞያ፤ የኦሮሞ ምሁራንና ልሂቃን፤ ቀስ በቀስ ኃይማኖትን ከማንነት ጥያቄ ጋር አጣምረው አገሪቱን ወደ ባሰ ፈተና እያሸጋገሯት ነው። ለውጡ ከመካሄዱ በፊት በሎንዶንና በአንድ የአሜሪካ ከተማ የተሰበሰቡ የኦሮሞ ምሁራን “ኢትዮጵያ እንድትፈራርስ አናደርጋለን” ብለው መፎከራቸው ትዝ ይለኛል። በተመሳሳይ፤ አቦይ ስብሃት ሲፎክር “የኢትዮጵያን ተዋህዶ እምነትንና አማራውን በማያሻማ ደረጃ አፍርሰናቸዋል” ብሎ ነበር። የትግራይና ሌሎች ኢትዮጵያዊያንም የእምንቱ ተከታዮች መሆናቸውን ረስቶታል ወይንም ሆነ ብሎ ለይቶታል።

የብሄር ምሁራንና ልሂቃን ሆነ ብለው ተቋማትንና ሕዝብን ለማፍረስ ወይንም ለመደምሰስ ሲፎካከሩ ኢትዮጵያ የመጀመሪያዋ በራሷ ፍጥረቶች የምትፈርስ አገር ትሆን? የሚል ጥያቄ በአእምሮየ አስባለሁ። ችግሩ እምነት አይደለም። ድንቁርና፤ ማን አለብኝ ባይነት፤ “ወፍ ዘራሽ” እና አገር አፍራሽ እውቀት ነው። ኢትዮጵያን ዋጋ እንድትከፍል እያስገደድናት ነው።

ዮሃንስ አድማሱ የጻፈውን ለመጥቀስ፤

“በሰንበሌጥ ቁጣ፤ ወደቀ አሉ ዋርካ! ተከካ አልተከካ! ተቦካ አልተቦካ! የምን ቸገረኝ ቤት ሁልጊዜ ፋሲካ”

አገርን ማፍረስ እንደ ፋሲካ የሚታይባት አገር ኢትዮጵያ ናት። በመቀሌ ሆነ በአዋሳ፤ በባህር ሆነ በአዲስ አበባ ራሳቸውን ሊቅ እያደረጉ፤ ራሳቸውን ተወካይ ነን እያሉ፤ ራሳቸውን መንግሥት ነን እያሉ፤ ታላቋን ኢትዮጵያን ያሴሩባታል፤ ዝቅ አድረገዋታል። የሚመጣውን እልቂት ዋርካው ሊቋቋመው አይችልም። ግን፤ ሕዝቡን መናቅ አደገኛ ነው።

የእኔ ዋና መከራከሪያ ሃሳቤ፤ በኢትዮጵያ እናት ቤተከርስትያን ዙሪያ የተከሰተው አደጋ ፈር የለቀቀ መሆኑን በምሳሌ ለመጥቅስ ነው። የዛሬ ሶስት ዓመት ገደማ በአክሱም፤ ትግራይ፤ ኢትዮጵያ የተገኘው መጽሃፍ ቅዱስ የእመነቷን ጥንታዊነትና የተቋሟን ወሳኝነት ያመለክታል። በፍየል ብራና በግእዝ ቋንቋ የተጻፈው፤ በስእል ያሸበረቀው፤ “የገሪማ ወንጌል” ተብሎ የሚጠራው መጽሃፍ ቅዱስ፤ “በዓለም የመጀመሪያ ነው” የሚለውን ሳነብ የተሰማኝ አድናቆት ከፍተኛ ነው። በጥንቃቄና በእንክብካቤ የተያዘው መጽሃፍ ቅዱስ በራሱ አስደናቂ ነው። የኢትዮጵያና የመላው ኢትዮጵያዊያን መለያ ቅርስ ነው። ጸሃፊው ይህን ታሪካዊ ቅርስ ጽፈው ለኢትዮጵያ ሕዝብ ያበረከቱት በአምስተኛው መቶ ዓመተ ምህረት ሲሆን፤ አባ ገሪማ ከኮንስታንትቲኖፕል ከተማ ወደ ኢትዮጵያ የመጡት በ 494 AD ነው።

ከላይ እንደገለጽኩት፤ ይህ ቅርስ፤ አድዋ በሚገኘው በታወቀው የአባ ገርሚ ገዳም በጥበቃ የተያዘ የሁሉም ኢትዮጵያዊያን ኃብት፤ ጥሪትና መለያ ነው። ለእኔ ያስገረመኝና ያስደነቀኝ፤ ልክ የላሊበላን አብያተ ክርስቲያናት በአድናቆት እንደማያቸው ሁሉ፤ ከመጽሃፍ ቅዱሱ በስተጀርባ ያለው ጥበብ ጭምር ነው። ብራናን አለስልሶ፤ ቀለምን አዘጋጅቶ፤ ፊደልን ተጠቅሞ፤ ምሁራንን አሰልጥኖ መጻፍ የስልጣኔ መረጃ ነው። የቀን መቁጠሪያ መፍጠርና መጠቀም ስልጣኔ ነው። መጻህፍትን በብራና ጽፈውና ጥበብ በተሞላበት ሁኔታ አያይዘው ለእኛ በረከት እንዲሆኑ ያደረጉልን መንፈሳዊ አባቶች ያሳዩን ረቂቅ ጥበብ ያላቸው መሆኑን ነው። ዛሬ ስልጣኔ ብለን የምንጠራው ትላንት የእኛ መለያ የነበረው ይኼው የጋራ ሃብታችንና መለያችን ነው። እንደመር ሲባልም ይኼው ነው።

ለእኔ አስደናቂ ሆኖ ያማገኘው ሌላ ምክንያት አለ። ኢትዮጵያ በአገር ውስጥና በውጭ ጦርነት የባከነች አገር ናት። ያ ባይሆን ኖሮ፤ ልክ እንደ ጃፓን በአጭር ጊዜ ዘመናዊ የመሆን እምቅ ብቃት ያላት አገር ናት። ታሪኳ የጦርነት ታሪክ ስለሆነ፤ የውጭ ወራሪዎች፤ የእስልምና ጽንፈኞች፤ የእንግሊዞችና የግብጾች፤ የቱርኮችና የጣሊያኖች ወዘተ ሴራዎች በተከታታይ ሲካሄዱ፤ ቅርሶችን በዱር በገደሉ፤ በዋሻውና በኃይቁ፤ ከተራራ ላይ በሚገኘው ገዳሙ ተንከባክባ የያዘች እመነት ተዋህዶ ናት። ፈረንጆች ሰርቀው ሆነ ቀምተው ያልወሰዷቸው ቅርሶች እስካሁን ሳይጠፉ መገኘታቸው ኢትዮጵያ በማንም ኃይል የማትጠፋ አገር መሆኗን ያረጋግጡልኛል።

የኢትዮጵያን ቅርሶች መናቅና ማጥላላት ከግልና ከቡድን አጀንዳ ፉክክር ጋር ቀጥታ የሆነ ግንኙነት አለው። እኔን የሚያሳስበኝ፤ አብሮነትና ኢትዮጵያዊንት የሚያስጨንቃቸው የፖለቲካ ልሂቃን፤ “ወፍ ዘራሽ ምሁራን” እና የኃይማኖት ጽንፈኞች የሚያስተጋቡት ደዌ ወደ ህብረተሰቡ እንዳይዛመት ነው። “የገሪማን ወንጌል” ከተደበቀበት አውጥተው ለዓለም ሕዝብ ያስታወቁት ግለሰቦችና “የኢትዮጵያ ቅርስ” ተቋም (The Ethiopian Heritage Fund) እንዲህ የሚል ድምዳሜ አቅርበዋል። “This is the most astoundng of all of our projects… ከማንኛውም ስራችን መካከል አስደናቂው የስራ ውጤት ይኼው ነው።” (ancient-origins.net or com 6/28/2016). ወንጌሉ በማያሻም ደረጃ የሚያሳየው፤ ባህላችን፤ ታሪካችንና ልምዳችን እንዳይጠፉ በመንከባከብ መለያችን ያደረገችው ይህቸው የተዋህዶ ቤተክርስትያን ናት።

ለማጠናከር፤ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ቤተመዘክር ናት፤ ቅርሶችን ተንከባክባ ከትውልድ ወደ ትውልድ ያስተላለፈች፤ የኢትዮጵያን የመንግሥት ስነ ስርዓት የጻፈችና ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ነጻነትና ክብር ድርሻዋን የተወጣች ቅርስ ናት።

ትምህርት—የነጻነት መሰረት ነው

ከላቲኑ የመጣው የትምህርት ዋናው ትርጉም መምራት ማልት ነው። ለመምራት የሞራል ብቃት ያስፈልጋል። ትምህርት የሚለው ቃል፤የመማር ወይንም የእውቀት ማመቻቸትን፤ መቅሰምን፤ ልዩ ልዩ ሞያዎችን ማግኘትን፤ እምነትን፤ እሴትን፤ ልምድንና ተመክሮ ማዳበርን፤ ከድንቁርና ዓለም ነጻ ወጥቶ ድህነትን ማሸነፍን፤ ለሌላው ሰው ወይንም ለአገር ማሰብን ወዘተ የሚያስችል የዘመናዊነት ዋና መለያና መሳሪያ ነው። ተምረናል ስንል፤ ሌላውን ለመምራት ወይንም ለማስተማር ችለናል ማለት ጭምር ነው።

የኢትዮጵያ ተዋህዶ እምነትና ቤተክርስትያን በኢትዮጵያ ረዥምና አስደናቂ ታሪክ ዋናውን የማስተማር ሚና ተጫወተዋል። የአክሱም ሥልጣኔ ካበረከታቸው ከፍተኛ አስተዋጾዎች መካከል፤ የግእዝን ፊደል አዳብሮ የመጻፍና ትምህርትን የማስፋፋት ልምድ በኢትዮጵያ እንዲስፋፋና እንዲሻሻልማድረጉ ታሪክ የሚጠቅሰውና መላው የጥቁር ዓለም ሕዝብ የሚኮራበት መሆኑ ዋናው ነው የሚል እምነት አለኝ። ምክንያቱም፤ የራስን ታሪክ ለማወቅ፤ አገርን ከሌሎች ለመለየት፤ ስልጣኔን ለመቀዳጀት፤ ማህበረሰባዊ፤ ኢኮኖሚያዊ፤ ባህላዊ፤ መንፈሳዊ፤ ፖለቲካዊ ወዘተ ግንኙነቶችን ለማጠናከር ፊደል፤ ቋንቋ፤ የቀን መቁጠሪያ፤ ጽህፈት፤ ትምሀርት ወሳኝ ናቸው።

የክርስትና ኃይማኖት ወደ ኢትዮጵያ ከገባና ከተስፋፋበት ከ 400 ዓ.ም. ጀምሮ ይህች ተቋም የግእዝን ቋንቋ የራሷ አድርጋና አዳብራ፤ የቤተክርስትያኗ፤ የኢትዮጵያ ነገሥታትና ሌሎች ከፍተኛ ባለሥልጣናት እንዲጠቀሙበት አድርጋለች። የኢትዮጵያ የጦርነት ታርኮች፤ የመንግሥት አስተዳደር፤ ድንበሮች፤ ሕዝቦች፤ ሕግና ደንቦች የተጻፉት በዚች ተቋም ነው። ኢትዮጵያ ወርቅ፤ ብር፤ ነሃስ፤ ጊጣጌጥ፤ ቅመማ ቅመም፤ የዝሆን ጥርስ፤ ከየትኞቹ አገሮች ጋር ትነግድ እንደ ነበር ለማወቅ የቻልነው በዚህች ተቋም ሰንዶች አማካይነት ነው።

ሌላው ማስታወስና ለወጣቱ ትውልድ ማስተማር የሚኖርብን ተግባር፤ የተዋህዶ፤ የእስልምናና የአይሁዳዊ እምነት (The Three Abrhamic Religions) ተብለው የሚጠሩት እምነቶች ተከታዮች በሰላም፤ በአብሮነትና በመከባበር ጎነ ለጎን አብረው ለብዙ ሽህ ዓመታት መቆየታቸውን ነው። እያንዳንዱ እምነት የራሱ ትምህርት ቤቶች፤ የራሱ ስብከቶች ወዘተ ነበሩት። የባህል ወይንም የጥንት ትምህርት ቤቶች በብዛት የተካሄዱት በተዋህዶ ቤተክርስትያን አማካይነት ነው። የመጀመሪያው የትምህርት እድል እንዲሰጥ ያደረጉት መሪ ንጉሥ ኢዛና ናቸው። ይህ የትምህርት ስርጭት ሶስት መቶ ዓመት (1200—1500) የቆየ የመስፋፋት ዘመን “ወርቃማው ዘመን (Golden Age)” በሚል መለያ ይታወቃል። በዚህ ረዥም ጊዜ ተዋህዶ ብዙ ግለሰቦችን አሰልጥና አገር አቀፍ በሆነ ደረጃ እምነቷን አስፋፍታለች። ምሁራኖችን፤ ሊቆችን፤ ደብተራዎችን፤ አስተማሪዎችን፤ መነኩሴዎችን፤ መሪዎችን፤ ጥበበኞችን አበርክታለች። አስተማሪዎች በተለየ መንገድ እንዲሰለጥኑና እንዲያስተምሩ ታዘጋጅ ነበር። መንግስትን የሚያገለግሉ ገዢዎች፤ አስተዳዳሪዎች፤ ዳኞች፤ ገንዘብ ያዢዎች፤ ጸሃፊዎች ወዘተ ልዩ ልዩ ትምህርት ይሰጣቸው ነበር። ይህ የሆነው አብዛኛዎቹ ያውሮፓ አገሮች ከመመስረታቸው በፊት ነው።

እነዚህ ትምህርት ቤቶች በዘመኑ አጠራር ኮሌጅና ዩንቨርስቲ የምንላቸው ናቸው። ዛሬ ስኮላር እንላለን እንጅ፤ ያኔ እኮ እውነተኛ ስኮላሮች ነበሩ። እድሚያቸውን ለትምህርትና ለምርምር ያዋሉ ኢትዮጵያዊያን ማለቴ ነው።

የኢትዮጵያ ሕዝብ የዚህች ታሪካዊ የተዋህዶ እምነትና ተቋም ባለ ውለታ ነው። ዛሬ በተዋህዶ ቢተክርስትያን ላይ የሚደረገውን አሰቃቂ ሁኔታ ስመለከት፤ ገዢውን ፓርቲና መንግሥትን የሚያገለግልው መገናኛ ብዙሃን ሃቁን ለማቅረብ አልቻለም። አሁንም ፍርሃቱ ከፍተኛና አደገኛ ነው።

በተጨማሪ፤ በትዮጵያ አሉ የሚባሉ ብልህና ጥበበኛ አስታራቂዎች አለመኖራቸው አሳሳቢ ነው። ይህን ክፍተት ችላ ልለው አልችልም።

ስለሆነም፤

  1. የተዋህዶ እምነትና ሲኖድ እንዳይከፋፈሉ እያንዳዳችን ድምጻችን እንድናሰማ ጥሪ አደርጋለሁ፤
  2. የኢትዮጵያ የፌደራል መንግሥት በተዋህዶ እምነት ምእመናን፤ ቀሳውስት፤ መንፈሳዊ አባቶችና በሌሎች ላይ ግድያ የፈጸሙትንና ቤተክርስትያኖችን ያቃጠሉትን ግለሰቦችና ቡድኖች በአስቸኳይ ለፍርድ እንዲያቀርብ ምክሬን እለግሳለሁ፤
  3. የፌደራልና የክልል ባልሥልጣናት በጋራ የተቃጠሉት ቤተክርስትያኖች እንዲሰሩና ወደፊት አደጋ እንዳይደርስባቸው ጥበቃ እንዲደረግላቸው አሳስባለሁ፤
  4. የፌደራሉ መንግሥትና ውድመት የተካሄደበት ክልል መንግሥት በጋራ ሆነው፤ ለተጎዱት ግለሰቦች መታሰቢያ እንዲቋቋም፤ ለማቋቋም የሚፈልጉትን እንዳይከለክሉ፤ ለቤተሰቦቻቸው ካሳ እንዲከፈል ምክሬን አቀርባለሁ፤
  5. ገለልተኛና የሕዝብ ተአመኔታ ያላቸው የኦሮሞ፤ የአማራና የሌሎች ዘውግና የእምነት አባቶች፤ ሽማግሌዎች፤ አባገዳዎች፤ እናቶች፤ አርቲስቶች፤ ወጣቶች፤ የሞያና ማህበረሰባዊ ድርጅቶች በአስቸኳይ ተሰብሰብውና ተመካክረው የክፍፍሉ እቅድ እንዲቆምና ለጋራ አገርና ለጋራ እመነት የጋራ መፍትሄ የሚሆን ምክራቸውን እንዲለግሱ ጥሪ አደርጋለሁ፤ እና፤
  6. ይህች እናት የተዋህዶ እምነት የኢትዮጵያ መለያ እንደመሆኗ መጠን፤ የኢህአዴግ ፌደራል መንግሥት ባለሥልጣናትና ምክር ቤቱ ያገባናል የሚል ግልጽና የማያሻማ አቋም ወስደው ማንኛውንም ትብብር እንዲያደርጉላትና አገሪቱን ከከፋ አደጋ እንዲያወጧት አሳስባለሁ።ደጋግሜ በመጻህፍቶቸ፤ በትንተናዎቸና በሌሎች አማካይነት እንዳሳሰብኩት፤ ህወሓትና አጋሮቹ ለራሱ ቡድንና ለራሱ ብሄር ሲል ሳይጠና፤ ምክክር ሳይደረግበትና ሕዝብ ሳይሳተፍበት በጫካ የጸነሰውና የመከረበት የዘውግ ሕገ መንግሥትና ከፋፍለህ ግዛው የሆነው የክልል አስተዳደር እስካተለወጠ ድረስ የኢትዮጵያ፤ የብሄራዊ ተቋማትና የሕዝቧ ሰቆቃ በምንም አይቀረፍም። ምርጫ ቢካሄድም ባይካሄድም ፖሊሲው፤ መዋቅሩና ሕገ መንግሥቱ እስካልተቀየሩ ድረስ ጠባብ ብሄርተኝነት፤ ጽንፈኛነት፤ አክራሪነት፤ ዘራፊነት ወዘተ ሊለወጡ አይችሉም።

ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር! ተዋህዶ ቤተክርስትያንን መከፈፈል በአስቸኳይ ይቁም! የሕግ የበላይነት ሚዛናዊ ይሁን!

September 10, 2019

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *