Dinknesh Ethiopia

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ይፈቱ! – ያሬድ ኃይለማርያም

አዎ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ይፈቱ!  መቼም ይህ ሁሉ ውርጅብኝ በአገር እና በሕዝብ ላይ እንደማያባራ ዝናብ ሲወርድ ዝም ማለትዎ አንድም አቅም ማጣት፣ አንድም በፓርቲ ሰንሰለት ተጠርንፈው፣ አንድም ከብሽቀት፣ አለያም ምን ይዤ ነው ሕዝብ ፊት የምቀርበው ከሚል በሰዋዊ ስሜት ተውጠው ይሆናል። ወይም lema-abiy-jawarእኛ ልንገምተው ያልቻልነው ሌላ ችግር ገጥሞዎት ይሆናል።
ለማንኛውም ግን ዝምታዎ እስከ አሁን ግርምታን ፈጥሯል። ከዚህ ካለፈም እና በዚሁ ከዘለቁም ውስጣችን ሌላ ጥርጣሬን ይጭራል።

በእኔ በኩል የፖለቲካ እስረኛ የሆኑ ስለመሰለኝ እነ ኤሊያስ ገብሩ እንደተፈቱት ጠቅላይ ሚኒስትሩም፤ በዋስም እንኳ ቢሆን ይፈቱልን ልል ትንሽ ነው የቀረኝ። አዎ በድርጅታዊ ትብታብ እና በመንጋዎቹ ማስፈራሪያ ተጠርንፈው የህሊና እስረኛ ሆነዋል ብዮ ባስብ ይቀለኛ እርሶን ከበዳዮች ጋር አብረዋል ወይም ከበዳዮች ተርታ ተሰልፈዋል ከማለት።

አዎ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይፈቱ!

ይፈቱ እና ለቅሶ ይድረሱ፤ ይፈቱና የድረሱን ጣር ድምጽ እያሰሙ ላሉት ወገኖች አጋርነትዎትን አሳዩ፣ ይፈቱና በዳዮችን በስም እየጠሩ ያውግዙ፣ ለፍርድ ያቅርቡ፤ ይፈቱና የደረሰውን ጉዳት ልክ ቡራዩና ጌዲዮ ሄደው እንዳደረጉት ይጎብኙ፤ ይፈቱና የጠቅላይ ሚኒስትርነት ስራዎትን በአግባቡ ይሥሩ፤
አዎ ጠቅላይ ሚንስትሩ ከተተበተቡበት ድርጅታዊ ማነቆ፣ ለሕግ የበላይነት ካላቸው የተዛባ ግንዛቤ፣ ከገጽታ ግንባታ እና ድራማ ከሚመስሉ ሥራዎች ይፈቱ! ይፈቱ! ይፈቱ!

እኛና ይፈቱ የምትለዋ ቃል ለአሥርት አመታት አብረን እንዳለን አለን፤ ትላንት እስክንድር ይፈታ፣ በቀለ ይፈታ፣ መራራ ይፈታ፣ ኤሊያስ ይፈታ፣ እገሌ ይፈታ ስልንል ቆይተናል። ዛሬ ዘቅጠን ይሁን ወግ ደርሶን ጠቅላይ ሚኒስትሩም ይፈቱ ለማለት በቅተናል። አዎ ከተተበተቡበት የኢህአዴግ ፖለቲካ ይፈቱ ወይም ይፋቱ እና ይችን አገር ይታደጓት። ካለዛ ከሕዝብ ጋር መፋታትም አለ። ያኔ ቅጣምባራችን ይጠፋል።

ይች አገር አሁን ያለችበት ሁኔታ ሌላ አቢዮት ወይም የመንግስት ስር ነቀል ለውጥ እንድታስተናግድ የሚፈቅድ አይደለም። እንኳንም ዘንቦብሽ ነው ነገሩ። እንኳን መንግስት ተፈንቅሎ ገና በመንገዳገዱ ብቻ ንጹሃን በጠራራ ጸሃይ እየታረዱ አስከሬናቸው በአደባባይ በገመድ ሲጎተት እያየን ነው። ኢትዮጵያ እንዲህ አስነዋሪ፣ አዋራጅ እና አንገት የሚያስደፋ ነገር ገጥሟት የሚያቅ አይመስለኝም።

ከለየለት አንባገነናዊ ሥርዓት ጋር መታገል ወግ ነው። ትግሉም መልክ ይኖረዋል። የገዛ ወገኑን፣ ሕጻናትን፣ አዛውንትን፣ ህሙማንን፣ ሴቶችን በእሳት እያቃጠለ፣ ሰውነት እየቆራረጠ በጅምላ የሚጨፈጭፍ መንጋ ገጥሟት አያውቅም ብል ማጋነን አይሆንም።

ለማንኛውም የኢትዮጵያ ሕዝብ ዛሬ ለእርሶ ደብዳቤ ጻፍ ቢባል ይህን የሚል ይመስለኛል፤

ይድረስ ለዶ/ር አብይ፤ እርሶ እንደምን አሉ? እኛ እንዳለን አለን፤ እንደተሸበርን፣ እንደተሳቀቅን፣ ፍርሃት እንደዋጠን፣ የገዛ ጥላችን ከመንጋዎቹ ውስጥ አንዱ እየመሰለን እየተገላመጥን፣ ወጥተን እስክንገባ ምን ይገጥመን ይሆን የሚል ስጋት ይዞን እግዚያ ማህረነ አስራ ሁለት ጊዜ እያል፣ እረ የመንግስት ያለህ አስራው ሁለት ጊዜ ደጋግመን እየቆጠርን እኛ እንዳለን አለን፤

+አገር በመንጋዎች ሲታመስ፣ የንጹሃን ዜጎች ደም በግፈኞች በትር ሲፈስ እርሶ እንደምን አሉ?
+ ክቡሩ የሰው ገለ በሜንጫ፣ በዱላ፣ በጥይት ሲወቃ፣ ሲደቃ፤ ሃዘን በየቤቱ ጉዋዙን ይዞ ገብቶ እንባ እያራጨ ሕዝብ ደረት ሲደቃ እርሶ እንደምን አሉ?
+ እልጆቻቸው ፊት ባሎቻቸውን መንጋ የነጠቃቸው ኢትዮጵያዊ እናቶች በየመጠለያው ታጉረው፣ ታርዘው የመንግስትዎ ያለህ እያሉ ሲጮሁ እርሶ እንደምን አሉ?
+ ስንት ጀግኖች ወድቀው ያቆያቱን አገር በመንጋዎቹ ሰልፍ በታበየ አንድ ቀልብ የራቀው ጎረምሳ ስትታመስ፣ እኛም አብረን እንደ ገብስ ቆሎ ስንታመስ፣ ስንወቀጥ፣ ስንታኘክ እርሶ እንደምን አሉ?
+ በዛ ውብ ቃልዎ ያጽናኑናል ብለን፣ በዛ እሩህሩ ልብዎ፣ አዛኝ ስበዕናዎ አደባባይ ወጥተው አይዟቹ ይሉናል ብለን ብንጠብቅ የውሃ ሽታ መሆንዎ ምነው? እርሶ እንደምን አሉ?
+ ፍቅር ያሸንፋል በሚል መርህዎ ጽናትን ሊያሰርጹ የጀመሩት ጎዞ እንዲህ ያለ የግፍ ናዳ ሲወርድበት እያዩ ምነው መጥፋትዎ? እርሶ እንደምን አሉ?
+ ማቅ ለብሰን ማቅ ወርሰን አንድም እንዲያጽናኑን፣ አንድም በዳዮቻንን ለፍርድ በማቅረብ ፍትሕ አንግሰው እኛን እንዲክሱን ደጅ ደጁን እያየን ስንጠብቅዎ አንዴ ወደ ሐረር፣ አንዴ ወደ አንቦ እየገሰገሱ ግራ እንደገባው ሰው ክው ከው ማለትዎ? ከግፉዋን ጩኸት ይልቅ የመጋው ቁጣ ያስደነበርዎ? እርሶ እንደምን አሉ?

ቅዱስ መጽሃፉ በሆነ ገጹ እና በሆነ ምእራፉ ላይ “የግፉዋን አፍ ጥልቅ ጉድጓድ ነው” ይላል። ይህ ጉርጓድ ብዙዎችን ውጧል። የዛሬዎቹን በመንጋ የተደራጁ ግፈኞችም እንደሚጥ አንጠራጠርም። አብሮ እንደ እርሶ ያሉ ደግ ሰዎችን እንዳይውጥብን ግን አጥብቀን እንሰጋለን።

በየአደባባዩ ምስልዎትን ለብሶ ድጋፉን ካሳየዎት እና የመንጋ ሰለባ ከሆነው ሕዝቦ የተጻፈ።

ያሬድ ኃይለማርያም

Source: ZeHabesha

Exit mobile version