አዲስ አበባ፡- በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የተፈጠሩ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ስብራቶችን ለመጠገን መደመር ትክክለኛ አማራጭ እንደሚሆን ተገለጸ።
የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት አማካሪ አቶ ሌንጮ ባቲ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ በኢትዮጵያ የተበላሸውን የፖለቲካ የኢኮኖሚ ስርአት ለማስተካከል ብቸኛው አማራጭ ፌዴራሊዝም ሲሆን መደመር ደግሞ እውነተኛ ፌዴራሊዝም እንዲመጣ የሚያደርግ አተያይ ነው።
ቀደም ሲል በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ በርካታ የማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ስብራቶች ተፈጥረዋል የሚሉት አቶ ሌንጮ እነዚህን ስብራቶች ለመጠገን ደግሞ መደመር ትክክለኛ አማራጭ እንደሚሆን አመልክተዋል። መደመር “አህዳዊነትን የሚያመጣ ነው” በሚል በአንዳንድ አካላት የሚነሳው ሃሳብም መሰረተ ቢስ መሆኑን ተናግረዋል።
የኢህአዴግ ውህደት ከፌዴራሊዝም ስርዓቱ ጋር ግንኙነት እንደሌለው የሚገልፁት አቶ ሌንጮ ፌዴራል የሚሆነው አስተዳደሩና አወቃቀሩ እንጂ የፖለቲካ ፓርቲው አይደለም ይላሉ።
ግርታ የፈጠረው ቀደም ሲል መንግስትና ፓርቲ አንድ ስለሆኑ ነው እንጂ መንግስትና ፓርቲ ሲለያይ ፌዴራሊዝም የመንግስት ስራ፤ ርዕዮተ ዓለም ደግሞ የፓርቲ ጉዳይ እንደሚሆንም ተናግረዋል።
አሜሪካንና ጀርመን ፌዴራል የሆኑ ግዛቶች ቢኖሯቸውም ፓርቲዎቹ ግን ፌዴራል አይደሉም ሲሉ የሚጠቅሱት አቶ ሌንጮ አስተዳደሩ ፌዴራል የሆነው ህዝቡ የራሱን ባህልና ቋንቋ ጥቅም ላይ እንዲያውል መሆኑን አመልክተው የኢህአዴግ መዋሃድ አህዳዊ ስርዓት ለማምጣት ነው በሚል ብዥታ ለመፍጠር የሚደረገው ጥረት በውል አለመገንዘብ፣ ወይም የአስተሳሰብና የእውቀት ጉድለት መሆኑን አመልክተዋል።
የኢህአዴግ አገዛዝ አጋር ድርጅቶችን ያገለለና እኩል ተሳታፊ ያላደረገ እንደነበር ያነሱት አቶ ሌንጮ ውህደቱ ሁሉንም ኢትዮጵያዊያን እኩል የሚያሳትፍና ውሳኔ ሰጪ የሚያደርግ መሆኑን ተናግረዋል።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 24/2012
ጌትነት ምህረቴ