Site icon Dinknesh Ethiopia

የተፈቀደላቸው መብታቸው ተከብሮ በአስቸኳይ ሊፈቱ ይገባል-ኢሰመኮ

Lidetu Ayalew

የፍርድ ቤት የዋስትና መብት የተፈቀደላቸው በሙሉ በአስቸኳይ እና ያለምንም ቅድም ሁኔታ ከእስር እንዲፈቱ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ጠየቀ።

ኮሚሽኑ አቶ ልደቱን በመሚመለከት ባወጣው መግለጫ ላይ አላስፈላጊ እስር ማስቀረትና የዋስትና መብት ማከብር ያስፈልጋል ሲል ጠይቐወል።

አቶ ልደቱ አያሌው በአንድ መቶ ሺህ ብር ዋስ ከእስር እንዲወጡ መስከረም 12/2013 ዓ.ም ትዕዛዝ ቢሰጥም እስካሁን አለመፈታታቸው ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) የሰብዓዊ መብቶች መከበር ዋና ዋስትናው የፍርድ ቤት ውሳኔ መከበር መሆኑን በመግለጫው ላይ አመልክተዋል።

አክለውም አቶ ልደቱን ጨምሮ በፍርድ ቤት ዋስትና መብት ተፈቅዶላቸው ከእስር እንዲለቀቁ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ የሰጠላቸው ታሳሪዎች “በሙሉ በአስቸኳይ እና ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ከእስር ሊፈቱ ይገባል” ማለታቸው በመግለጫው ላይ ተጠቅሷል።

ጠበቃቸው ምን አሉ?

በአንድ መቶ ሺህ ብር ዋስ እንዲፈቱና ጉዳያቸውን ከውጭ ሆነው እንዲከታተሉ በፍርድ ቤት የተፈቀዳለቸው አቶ ልደቱ አያሌውን ፖሊስ አልፈታም በማለቱ አቤቱታ ለፍርድ ቤት ማስገባታቸውን ጠበቃቸው አቶ አብዱልጀባር ሑሴን ለቢቢሲ ተናገሩ።

የምሥራቅ ሸዋ ዞን ፍርድ ቤት መስከረም 12/2013 ዓ.ም አቶ ልደቱ በዋስ እንዲፈቱ ቢወስንም ፖሊስ “በአደራ ነው እዚህ የተቀመጡት” የሚል ምላሽ ሰጥቶ ሊፈታቸው ፈቃደኛ ባለመሆኑ “ፖሊስ የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ ባለማክበሩ ትዕዛዙን እንዲያስከብር” በዛሬው ዕለት ጠበቃቸው ባስገቡት የአቤቱታ ማመልከቻ ጠይቀዋል።

አቶ አብዱል ጀባር በትናንትናው ዕለት፣ መስከረም 14/ 2013 ዓ.ም የፍርድ ቤት ትዕዛዙን ይዘው ወደ ቢሾፍቱ ፓሊስ ጣቢያ ቢያመሩም ፖሊስ ሊለቃቸው ፈቃደኛ እንዳልሆነ አስረድተዋል።

በዛሬው [ሐሙስ] ዕለት አዳማ ለሚገኘው ከፍተኛ ፍርድ ቤት ባስገቡትም ማመልከቻ ፖሊስ የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ አለማክበር በወንጀል ህግ ቁጥር 4፣ 48ና ተከታታይ ድንጋጌዎች ስር መሰረት አቶ አብዱልጀባር “ወንጀል ነው” ይላሉ።

“ይህ የፍትህ ሥርዓቱን ማስተጓጎል ነው። እንደ ችሎት መድፈር ስለሚቆጠርም ማስረጃ ሳያስፈልግ ፍርድ ቤቱ ቅጣት ሊጥልበት የሚችል ወንጀል ነው” ብለዋል።

በዚህም መሰረት ፍርድ ቤቱ ትዕዛዙ ባለመከበሩ እርምጃ እንዲወስድ፣ በፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ መሰረትም ደንበኛቸው በዋስ ከእስር እንዲወጡ የሚሉ ጥያቄዎችን በማመልከቻቸው ማካተታቸውን ገልጸዋል።

ማመልከቻቸውም ወደ ችሎት መዝገቡ ገብቶም እየተጠባበቁ እንደሆነ ለቢቢሲ አስረድተዋል።

በትናንትናው [ረቡዕ] ዕለት ወደ ቢሾፍቱ ከተማ ፖሊስ ባመሩበት ወቅት ከፍርድ ቤት የመጣውን ትዕዛዝ የዞኑ ግብረ ኃይል ምልክት እንዲያደርግበት ወይም ከግብረ ኃይሉ ሌላ ደብዳቤ ይዛችሁ ኑ እንደተባሉ የሚናገሩት ጠበቃው ወደ ወደ አዳማ ዞን ዐቃቤ ሕግ ሄደው ነበር።

ዐቃቤ ሕግ በበኩሉ የፍርድ ቤት ትዕዛዝ መከበር እንዳለበትና እነሱን እንደማይመለከት ጠቅሶ እንደሸኟቸውም ተናግረዋል።

ወደ ቢሾፍቱ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ተመልሰው በሚጠይቁበትም ወቅትም “እኛ በአደራ ነው ያስቀመጥናቸው ልንለቃቸው አንችልም” የሚል ምላሽ እንደሰጧቸው የሚናገሩት አቶ አብዱልጀባር በመጨረሻ ያሉትንም መፍትሄ ለመጠቀም ወደ ፍርድ ቤቱ የአቤቱታ ማመልከቻ ማስገባታቸውን ይናገራሉ።

በቢሾፍቱ ፖሊስ ጣቢያ በእስር ላይ የሚገኙት አቶ ልደቱ ካላቸው ተደራራቢ ህመም ጋር ተያይዞ ለኮሮናቫይረስ ስለሚጋለጡ በሚል ወደ አዳማ ማረሚያ ቤት እንዳይዛወሩና ባሉቡት እንዲቆዩ ፍርድ ቤት ባዘዘው መሰረትም የክስ ጉዳያቸውን ለመከታተልም ከቢሾፍቱ አዳማ ሲመላለሱ እንደነበረ ጠበቃው ተናግረዋል።

“የምን አደራ ነው? በፍርድ ቤት ትዕዛዝ ነው የተቀመጡት፤ ይሄ የፍርድ ቤት ትዕዛዝን አለመቀበል ነው እንጂ አደራ የሚባል ነገር ምክንያት ሊሆን አይችልም፤ ህጋዊ መሰረት የለውም” ሲሉ የተሰጣቸውን መልስ መቃወማቸውን አቶ አብዱልጀባር ተናግረዋል።

የሙዚቀኛ ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያን ተከትሎ በቢሾፍቱ ከተማ የተፈጠረውን ሁከት በማነሳሳት፣ መምራትና በገንዘብ መደገፍ ተጠርጥረው በእስር ላይ የሚገኙት አቶ ልደቱ አያሌው ጉዳያቸውን ሲያይ የነበረው ፍርድ ቤት ክሳቸውን ቢዘጋም እንገደና ያልተፈቀደ የጦር መሳሪያ በመያዝ ወንጀል ክስ ቀርቦባቸዋል።

ክሱ ከዚህ በፊት ሲታይ ከነበረበት የቢሾፍቱ ከተማ በመውጣት በአዳማ ከተማ በሚገኝ ፍርድ ቤት እየታየ የነበረ መሆኑ የሚታወስ ሲሆን፤ ፍርድ ቤቱም አቶ ልደቱ በ100 ሺህ ብር ዋስ ከእስር ወጥተው ጉዳያቸውን እንዲከታተሉ ወስኖ ለመስከረም 20/2012 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቶ ነበር።

Source: bbc.com

Exit mobile version