ጃዋር መሐመድ፣ ብርሃነመስቀል አበበ፣ በቀለ ገርባ
News

ጃዋር መሐመድ ፡ ዐቃቤ ሕግ አቶ በቀለ ገርባን ጨምሮ ሌሎች በውጭ በሚኖሩ ሰዎች ላይ ክስ መሰረተ

በአስር ላይ የሚገኙትን አቶ ጃዋር መሐመድ፣ አቶ በቀለ ገርባ እና አቶ ሀምዛ አድነን ጨምሮ ሌሎች ከአገር ውጪ በሚገኙ 24 ሰዎች ላይ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ክስ መመስረቱን ዛሬ [ቅዳሜ] አስታወቀ።

በእነአቶ ጃዋር ላይ ትናንት የክስ መዝገብ ይከፈትባቸዋል ተብሎ ሲጠበቅ የነበረ ቢሆንም ክስ አለመመስረቱን ጠበቃቸው አቶ ቱሊ ባይሳ ለቢቢሲ ተናግረው ነበር። ነገር ግን ዛሬ ከፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የወጣው መግለጫ እንዳመለከተው ሌሎችንም ሰዎች ጨምሮ ክስ መመስረቱን ገልጿል።

በዚህም መሠረት ከአቶ ጃዋር መሐመድ፣ ከአቶ በቀለ ገርባና ከአቶ ሀምዛ አድናን በተጨማሪ በሌሉበት የኦሮሚያ ሜዲያ ኔትወርክ (ኦኤምኤን) ኃላፊ አቶ ደጀኔ ጉተማ፣ ከወራት በፊት በአሜሪካ በሚገኝ የኢትዮጵያ ቆንስላ ዲፕሎማት የነበሩት ብርሃነመስቀል አበበ (ዶ/ር)፣ ነዋሪነታቸው አውስትራሊያ የሆነው አቶ ፀጋዬ ረጋሳን ጨምሮ በአጠቃላይ 24 ሰዎች ላይ ክስ መመስረቱ ታውቋል።

ከግለሰቦቹ በተጨማሪም ከወራት በፊት አዲስ አበባ ውስጥ የነበረው ቢሮው የተዘጋው የኦሮሚያ ሜዲያ ኔትወርክ (ኦኤምኤን) በተባለው የቴሌቪዥን ጣቢያ ላይም ክስ ተመስርቷል።

ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ እንዳከለው ክሱ የተመሠረተባቸው ተቋምና ግለሰቦች “እንደየተሳትፏቸው በ1996 የወጣውን የወንጀል ሕግ አንቀፅ 240 በመተላለፍ ብሔርንና ሐይማኖትን መሰረት ያደረገ የእርስ በርስ ግጭት በመቀስቀስ፣ አንዱ ወገን በሌላው ወገን ላይ እንዲነሳሳ በማድግ” የሚሉ ክሶች የቀረቡባቸው መሆኑን አመልክቷል።

በተጨማሪም ተከሳሾቹ የሽብር ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ ቁጥር 1176/2012፣ የቴሌኮም ማጭበርበር ወንጀል አዋጅ ቁጥር 761/2004 እና የጦር መሳሪያ አስተዳደርና ቁጥጥር አዋጅ ቁጥር 1177/2012 በመተላለፍ በፈፀሙት ወንጀልም ክስ መስርቷል።

የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ እንዳለው መስከረም 6/2013 ዓ.ም በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ የወንጀል ችሎት በመዝገብ ቁጥር 260215፤ በአጠቃላይ አስር ተደራራቢ ክሶች ማስከፈቱን ጠቅሶ ተከሳሾቹም ሰኞ መስከረም 11/2013 ዓ.ም ፍርድ ቤት ሲቀርቡ የተመሠረተባቸው ክስ ዝርዝር እንደሚደርሳቸው አመልክቷል።

ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በእነ አቶ ጃዋር መሐመድ ላይ ትናንት ክስ የሚመሰርትበት ቀን የመጨረሻ ቀን እንደነበረና በዚሁ መሠረትም በተጠርጣሪዎቹ ላይ ክስ ይመሰረታል ተብሎ ተጠብቆ ነበር።

ነገር ግን ክሱ ሳይመሰረት በመቅረቱ የእነ አቶ ጃዋር መሐመድ ጠበቃ አቶ ቱሊ ባይሳ በደንበኞቻቸው ላይ ክስ ስላልተመሰረተ “አካልን ነጻ የማውጣት አቤቱታ [ሃቢየስኮርፐስ] የፊታችን ሰኞ ለፍርድ ቤት እናቀርባለን” ብለው ለቢቢሲ ገልጸው ነበር።

ነገር ግን የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዛሬ እንዳስታወቀው በእስር ላይ ያሉትን ተጠርጣሪዎች ጨምሮ በውጪ አገራት በሚገኙ 24 ሰዎች ላይ አስር ተደራራቢ ክሶችን መስርቷል። ክሱም ሰኞ ዕለት ለተከሳሾቹ እንደሚቀርብ አሳውቋል።

ዐቃቤ ሕግ ክስ እንደመሰረተባቸው ሰዎች መካከል አቶ ጃዋር መሐመድ፣ አቶ በቀለ ገርባና አቶ ሀምዛ አድናን በአስር ላይ ሆነው ጉዳያቸውን ሲከታተሉ የቆዩ ሲሆን በውጪ አገር የሚኖሩት ተከሳሾች ዝርዝር ይፋ የተደረገው ዛሬ ነው።

ታዋቂው አርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ሠኔ 22/2012 ዓ.ም መገደልን ተከትሎ በአዲስ አበባና በአንዳንድ የኦሮሚያ አካባቢዎች ከተከሰተው አለመረጋጋት ጋር ተያይዞ በርካታ ፖለቲከኞችና ጋዜጠኞች በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ መሆኑ ይታወቃል።

Source: bbc.com

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *