ዶክትር ቶላ በሪሶ
Health News

ከጃፓናዊው ጋር ተገናኝተው የነበሩት የኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ እራሳቸውን ለይተው ተቀመጡ

የኦሮሚያ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ የሆኑት ዶክትር ቶላ በሪሶ በኮሮናቫይረስ ስጋት ምክንያት እራሳቸውን ለይተው በአንድ ክፍል ለብቻቸው መቀመጣቸውን ለቢቢሲ ተናገሩ።

ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ላይ በኢትዮጵያ የመጀመሪያው በኮሮናቫይረስ የተያዘ ሰው ተብሎ ይፋ ከተደረገውና ጃይካ የሚባለው በትምህርት ላይ ከሚሰራው የተራድኦ ድርጀት ባልደረባ ከሆነው ጃፓናዊ ጋር በሥራ ምክንያት መገናኘታቸው እራሳቸውን ለተወሰኑ ቀናት ለይተው እንዲያቆዩ ያደረጋቸው ምክንያት እንደሆነ ኃላፊው ገልጸዋል

ጃፓናዊው ከዶክትር ቶላ ጋር በተገናኘበት በዚያን ጊዜ “ገና ከውጪ አገር መምጣቱ ስለነበር ምንም አይነት የበሽታው ምልክት አይታይበትም ነበር” በማለት ከእርሱ ጋርም አንድ ኢትዮጵያዊ አብሮት እንደነበረ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ዶክተሩ አክለውም ከግለሰቡ ጋር በተገናኙበት ጊዜም በትምህርት ጉዳይ መነጋገራቸውን አመልክተዋል።

ይህ ጃፓናዊ ወደ ኢትዮጵያ ከመጣ በኋላ በአርሲ ዞን ሁለት ትምርት ቤቶችን ጎብኝቶ እንደነበረ የሚናገሩት ኃላፊው እሱ በሄደባቸው ቦታዎች አብረተውት የነበሩ ሰዎች ለብቻም እራሳቸውን ለይተው ክትትል እተደረገላቸው መሆኑን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ይህ ጃፓናዊ የኮሮናቫይረስ ምልክት የታየበት ሰኞ ዕለት ሲሆን በሽታው እንደበት ተረጋግጦ የመጀመሪያው ኢትዮጵያ ውስጥ የተገኘ የኮሮናቫይረስ ታማሚ መሆኑ የተገለጸው ግን አርብ ዕለት ነበር።

በዚህም መሰረት ዶክትር ቶላ ከዚህ ግለሰብ ጋር ከተገናኙ አስር ቀናት እንዳለፉ ቢሆንም አሁን ለብቻቸው ተለይተው እንዲቆዩና ክትትል እንዲደረግላቸው የተነገራቸው አርብ ዕለት ነበር።

ዶክትሩ ከጃፓናዊው ጋር በመገናኘታቸው ከተፈጠረው ጥርጣሬ ውጪ እስካሁን የተለየ ምልክት እንዳልታየባቸው ተናግረዋል።

የኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ ኃላፊው ለአስራ አራት ቀናት ከቤተሰባቸውም ሆነ ከሌሎች ሰዎች ጋር ሳይገናኙ ለብቻቸው እንዲቆዩም ተነግሯቸው ለቢቢሲ ተናገረው ይህንም እያደረጉ መሆኑን አረጋግተዋል።

በኢትዮጵያ እስካሁን በኮሮናቫይረስ መያዙ የተረጋገጠ አንድ ሰው ብቻ ሲሆን ሌሎች ሰዎች ደግሞ የበሽታውን ምልክት በማሳየታቸው ተለይተው እንዲቆዩና ምርመራ ተደርጎላቸው ነጻ መሆናቸው ተረጋግጦ ወደ ቤታቸው የተመለሱ ሲኖሩ፤ ሌሎች ደግሞ በለይቶ ማቆያ ውስጥ ይገኛሉ።

በኮሮናቫይረስ በወረርሽኝ ዓለም ዙሪያ ባለፉት ጥቂት ወራት ወደ ስድስት ሺህ የሚደርሱ ሰዎች ሲሞቱ፤ ቫይረሱ የተገኘባቸው ደግሞ 155 ሺህ በላይ ደርሷል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *