Site icon Dinknesh Ethiopia

ትግራይ ፡ የኢትዮጵያ ሠራዊት መቀለን መቆጣጠሩን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አስታወቁ

Mekele

 

 

የኢትዮጵያ ሠራዊት ትግራይ ክልል ዋና ከተማ የሆነችውን የመቀለ ከተማን መቆጣጠሩን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ዛሬ [ቅዳሜ] አመሻሽ ላይ አስታወቁ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ እንዳሉት መቀለን ለመቆጣጠር በተደረገው ዘመቻ “ንጹሐን ዜጎች ዒላማ ሳይሆኑ፣ ከተሞቻችንና ቅርሶቻችን ሳይጎዱ” ሠራዊቱ ከተማዋን መያዙን አመልክተዋል።

የአገሪቱ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጄነራል ብርሀኑ ጁላም ሠራዊቱ የመቀለ ከተማን ሙሉ ለሙሉ መቆጣጠሩን ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተጨማሪም በዘመቻው ወቅት “በሸሸበት ላይ የነበረው ኃይል ያፈረሳቸውን መሠረተ ልማቶች በፍጥነት በመገንባት የትግራይ ሕዝብ ወደ ሰላማዊ ኑሮው እንዲመለስ ማድረግ የቻልነውን ሁሉ እንደምናደርግ ቃል እገባለሁ” ሲሉ መነግሥታቸው ለክልሉ መልሶ መቋቋም ያለውን ቁርጠንነት ገልጸዋል።

ብሔራዊው ቴሌቪዥን ኢቲቪም የመቀለ ከተማ በሠራዊቱ መያዟን ጠቅላይ ሚኒስትሩንና የሠራዊቱን ኤታማዦር ሹሙን ጠቅሶ ዘግቧል።

ቅዳሜ ረፋድ

የኢትዮጵያ ሠራዊት የትግራይ ክልል ዋና ከተማ የሆነችውን መቀለ ከተማን ለመቆጣጠር ወታደራዊ ዘመቻ መጀመሩን የእርዳታ ሠራተኞችና የክልሉ አመራሮች ገለጹ።

የክልሉ ገዢ ፓርቲ ህወሓት እንዳለው የመቀለ ማዕከላዊ ክፍል “በከባድ መሳሪያና በመድፍ” ጥቃት እንደተፈጸመበት አመልክቷል።

ዛሬ ቅዳሜ ከረፋድ አራት ሰዓት ጀምሮ በከተማዋ ዙሪያ የከባድ መሳሪያ ድምጽና ፍንዳታዎች መሰማት እንደጀመሩ ቢቢሲ ያገኘው መረጃ አመልክቷል።

የእርዳታ ሠራተኞችና ዲፕሎማቶች በከተማዋ ውስጥ ከባድ ፍንዳታዎች መሰማታቸውን ከነዋሪዎች እንደሰሙ ተናግረዋል።

የአገሪቱ መከላከያ ሠራዊት ባለፉት ሦስት ሳምንታት በትግራይ ክልል ውስጥ የሚገኙ በርካታ ከተሞችን ተቆጣጥሮ ወደ መቀለ ከተማ መቃረቡን ተከትሎ፤ መንግሥት ሦስተኛና የመጨረሻው ምዕራፍ “ሕግ የማስከበር” ያለውን ዘመቻ መቀለ ውስጥ ይገኛሉ ባላቸው የህወሓት መሪዎችና ኃይሎች ላይ እንደሚያካሂድ አሳውቆ ነበር።

ትናንት በአገሪቱ መከላከያ ሠራዊት በተሰጠው መግለጫ ጦሩ ወደ መቀለ ከተማ ለሚያደርገው ዘመቻ ቁልፍ የሆኑ ከተሞችንና ቦታዎችን መያዙን አመልክቶ በከተማዋ ዙሪያ አስፈላጊውን ዝግጅት እያደረገ መሆኑ ተገልጾ ነበር።

ሮይተርስ የዜና ወኪል የህወሓት መሪን ጠቅሶ የኢትዮጵያ መንግሥት ኃይሎች የክልሉን ዋና ከተማ መቀለን ለመያዝ ቅዳሜ ጥቃት ማካሄድ መጀመራቸውን ዘግቧል።

ሮይተርስ ጨምሮም የህወሓት ሊቀመንበር የሆኑት ደብረጽዮን ገብረሚካኤል (ዶ/ር) በአጭር የጽሁፍ መልዕክት መቀለ ላይ “የከባድ መሳሪያ ድብደባ” እየተካሄደ መሆኑን ነገሩኝ በማለት ዘግቧል።

ነገር ግን የጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ፕሬስ ሴክሬታሪ ቢለኔ ስዩም ለሮይተርስ እንደተናገሩት የኢትዮጵያ ሠራዊት ሠላማዊ ሰዎች የሚገኙባቸውን አካባቢዎች ላይ የከባድ መሳሪያ ጥቃት አይፈጽምም ብለዋል።

ጨምረውም “በመቀለ ከተማም ሆነ በትግራይ ክልል ውስጥ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ደኅንነት የፌደራል መንግሥቱ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ሆኖ ይቀጥላል” በማለት ሠራዊቱ ለሰላማዊ ሰዎች ጥንቃቄ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።

ፌደራሉ ሠራዊት በመቀለ ላይ ወታደራዊ እርምጃ መውሰድ መጀመሩን ተከትሎ ከትግራይ አመራሮች በኩል በክልሉ ቴሌቪዥን ላይ የቀረበው መግለጫ ጥቃቱ ከትናት መጀመሩን ገልጾ የክልሉ ኃይል “የአጸፋ እርምጃ” እንደሚወስድ አስጠንቅቋል።

ቅዳሜ ረፋድ ላይ በመቀሌ ከተማ ውስጥ መሰማት የጀመረውን የከባድ መሳሪያ ድምጽ ተከትሎ በነዋሪዎች ዘንድ ድንጋጤ የተፈጠረ መሆኑ ምንጮች ተናግረዋል።

ከተቀሰቀሰ ከሦሰት ሳምንታት በላይ የሆነው ቀውስን ተከትሎ በትግራይ ክልል ያለው የስልክና የኢንትርኔት ግንኙነት በመቋረጡ ዝርዝርና አስተማማኝ መረጃ ለማግኘት አስቸጋሪ ሆኗል።

መቀለ

ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ነዋሪዎች አሏት የምትባለው መቀለ የትግራይ ክልል አስተዳደር መቀመጫ ስትሆን የክልሉ ትልቋ ከተማ ናት። የህወሓት ከፍተኛ አመራሮችና ቀደም ሲል በፌደራል መንግሥቱ ከፍተኛ ኃላፊነት ላይ ይገኙ የነበሩ ባለስልጣናት መቀመጫቸው መቀለ እንደሆነ ሲነገር ቆይቷል።

በፌደራል መንግሥቱ እና የትግራይ ክልልን በሚያስተዳድረው ህወሓት መካከል ለረጅም ጊዜ የቆየው አለመግባባት ባለፈው ዓመት ሊካሄድ የነበረው አገራዊ ምርጫ በኮሮናቫይረስ ወረርሽን ምክንያት ወደ ሌላ ጊዜ መሸጋገሩን ተከትሎ በከፍተኛ ሁኔታ መካረሩ ይታወሳል።

ተከትሎም የፌደራል መንግሥቱን ውሳኔ ባለመቀበል ባለፈው ዓመት ማብቂያ ላይ በትግራይ ክልል የተካሄደው የተናጠል ምርጫ የፌደራል መንግሥቱን ተቀባይነት ካለማግኘቱ በተጨማሪ በአገሪቱ ምክር ቤቶች ሕገ ወጥ ተብሎ ውድቅ ተደርጓል።

የፌዴሬሽን ምክር ቤትም የክልሉን አስተዳዳሪዎች ሕገ መንግሥቱን በመጣስና ከሕግ ውጪ ተንቀሳቅሰዋል በማለት የፌደራል መንግሥቱ ከትግራይ ክልል ክልል አስተዳደር ጋር የነበረውን የቀጥታ ግንኙነት አቋርጦ የበጀት ዕቀባ ጥሎ ነበር።

አለመግባባቱና መካሰሱ ያለማቋረጥ በቀጠለበት ሁኔታ ጥቅም 23/2013 ዓ.ም ምሽት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ በትግራይ ክልል በነበረው የፌደራሉ ሠራዊት የሠሜን ዕዝ ላይ በህወሓት ኃይሎች ጥቃት መፈጸሙን ይፋ ካደረጉ በኋላ የፌደራሉ ሠራዊት በትግራይ ክልል ኃይሎች ላይ እርምጃ መውሰድ ጀመሩ ይታወሳል።

 

Source: BBC amharic

Exit mobile version