abiy
News

ትግራይ: መከላከያ ሠራዊት በሕወሃት ላይ የኃይል እርምጃ እንዲወስድ መታዘዙ ተሰማ

ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አህመድ የአገር መከላከያ ሠራዊት በሕወሃት ላይ የኃይል እርምጃ እንዲወስድ ትዕዛዝ መሰጠቱን ይፋ አደረጉ።

ጠቅላይ ሚንስትሩ በአገሪቱ ብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ ቀርበው “ይህንን ጡት ነካሽ ኃይል ለማሳፈር እና ለመደምሰስ አስፈላጊውን ሁሉ የምናደርግ መሆኑን እገልጻለሁ” በማለት ጦርነት መከፈቱን አስታውቀዋል።

ጠቅላይ ሚንስትሩ መከላከያ ሠራዊት አገር የማዳን ግዳጅ እንደተሰጠውም አስረድተዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ “ሕወሐት በትግራይ በሚገኘው የመከላከያ ካምፕ ላይ ጥቃት አድርሷል። ሰሜን ዕዝንም ለመዝረፍ ሙከራ አድርጓል” ብለዋል።

ጠቅላይ ሚንስትሩ ሠራዊቱ ከሃያ ዓመታት በላይ የትግራይን ሕዝብ ሲጠብቅ የቆየ መሆኑን ገልፀው በቦታው የሚገኘውም የትግራይን ሕዝብ ከጥቃት ለመከላከል ነው።

“ሕወሐት ግን እንደ ባዕድና እንደ ወራሪ ሀገር ሠራዊት ቆጥሮ፤ የመከላከያ ሠራዊቱን ለመምታትና ለመዝረፍ ተነሥቷል። በዳልሻሕ በኩልም ጦርነት ከፍቷል” ብለዋል።

አክለውም “የመከላከያ ሠራዊታችን በኮማንድ ፖስት እየተመራ ሀገሩን የማዳን ተልዕኮውን እንዲወጣ ትእዛዝ ተሰጥቶታል። ቀዩ መሥመር የመጨረሻው ነጥብ ታልፏል። ሀገርና ሕዝብ ለማዳን ሲባል ኃይል የመጨረሻው አማራጭ ሆኗል” በማለት ገልፀዋል።

ከፌደራሉ መንግስት ጋር ውጥረት ላይ የሚገኘው የትግራይ ክልል መንግሥት የኢትዮጵያ ፌደራላዊ መንግስት “በትግራይ ላይ የኃይል እርምጃ ወደ መውሰድ እየተሸጋገረ ነው” ሲል መግለጫ የሰጠው ሰኞ እለት ነበር

የትግራይ ክልል መሪ ደብረጽዮን ገብረሚካኤል (ዶክተር) ሰኞ ዕለት ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ መንግሥት በትግራይ ላይ የሃይል እርምጃ ሊወስድ እንደሚችል በመግለጽ ‘ሕብረተሰቡ ዝግጅቱን አጠናክሮ ይቀጥል’ ብለዋል።

“ብዙ ጫናዎች ብዙ የሚድያ ዘመቻዎች ብዜ የኢኮኖሚ ዱላዎች ያደረሰብን ሳይበቃው፤ አሁን ደግሞ በኃይል እጨፈልቃለሁ ብሎ እየተንቀሳቀሰ ነው። ብዙ ምልክቶችም አሉ” ሲሉ ተናግረው ነበር።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ በቅርቡ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው ሲናገሩ ከትግራይ ክልል ጋር የተከሰተው አለመግባባት “በሕግ እና ሕግ ብቻ የሚመለስ ይሆናል” በማለት መናገራቸው ይታወሳል።

ሰሞኑን፤ በኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አደረጃጀት ላይ ለውጥ መደረጉን ተከትሎ የትግራይ ክልል መንግሥት እርምጃውን ተቃውሞ መግለጫ ማውጣቱም የሚታወስ ነው።

“የፌደራሉ መንግስት ስልጣኑ መስከረም 25/ 2013 ዓ.ም ላይ ያበቃ በመሆኑና ሕጋዊ ተቀባይነት ስለሌለው በመከላከያ ሰራዊት አደረጃጀት ላይ ለውጥ ሊያደርግ አይችልም” ብሏል በመግለጫው

የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በበኩሉ ይህን የትግራይ ክልል መግለጫ “ኢ-ህገመንግስታዊ” በማለት ተቃውሞ መግለጫ አውጥቷል።

ዶ/ር ደብረጽዮን፤ የፌደራሉ መንግሥት ትግራይ ላይ የሓይል እርምጃ ለመውሰድ እየተዘጋጀ መሆኑን “የሚያሳዩ ምልክቶች አሉ” ሲሉ ነበር የተናገሩት።

በወቅቱ ለክልሉ ጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ወቅት “ምልክቶች፣ ዝግጅቶች አሉ። አንዱ ምልክት፤ ሰራዊቱ በተጠንቀቅ ላይ እንዲሆን ተነግሮታል” ያሉ ሲሆን ዝርዝር መረጃ ግን አልሰጡም።

አክለውም፤ የትግራይ ክልል መንግሥት የመጀመርያው ፍላጎት ሰላም መሆኑን በመግለጽ “ቢሆንም፤ እኛም ሰራዊት አዘጋጅተናል፤ ሚሊሻችንን አዘጋጅተናል፤ ልዩ ኃይላችንን አዘጋጅተናል። ጦርነት ለማስቀረት ነው የተዘጋጀነው። መዋጋት ካለብን ግን፤ ድል ለማድረግ ተዘጋጅተናል” ሲሉ ተናግረው ነበር።

የትግራይ ክልል የጸጥታ ቢሮም በፌስቡክ ገጹ ላይ “ጸረ ህልውናችን የተሰለፉ ኃይሎች ግልጽ መሰባሰብ እያደረጉ ነው” ሲል ጽፎ ነበር።

ዶክተር ደብረጽዮን በሰኞ መግለጫቸው ላይ “የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ መንግሥትና የኤርትራው መንግስት በትግራይ ላይ አብረው እያሴሩ ነው” ሲሉ ከስሰው ነበር።

source: bbc amharic

በአፋር ክልል የትምህርት ሚኒስቴር ሰራተኞችን ጨምሮ 10 ሰዎች የተገደሉት “በአሸባሪዎች” ነው ተባለ

 

የኢሕአፓ መግለጫ በምዕራብ ወለጋ ዞን፣ ጉሊሶ ወረዳ፣ ጋዋ ቃንቃ ቀበሌ በተፈጸመ የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋ ላይ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *