Neamin Zeleke
Current Opinion

የህወሓትን ሀገር አፍራሽ፣ ሕዝብ አጫራሽ ሴራ በጋራ ቆመን፣ በአንድነት በመንቀሳቀስ ማምከን ይጠበቅብናል ― ነአምን ዘለቀ

ሰላም ወገኖቼ፥

የወቅቱ አብይ ጥያቄ ኢትዮጵያ ሀገራችንንና ኢትዮጵያዊነት ከህወሓት ሀገር አፍራሽ፣ ሕዝብ አጫራሽ ሴራ በጋራ ቆመን፣ ከዳር እሰክዳር በአንድነት በመንቀሳቀስ ማምከን ነው። መሆን ወይንም አለመሆን ነው ለእያንዳዱ ዜጋ የቀረበው ጥያቄ!

የክፋት፣ የነውር፣ የመሰሪነት ጥግ የሆኑት፣ ይህ ነው የማይባል ዘረፋ፣ ዘረኝነትና ግፍ በሚሊዮኖች ዜጎች ላይ የፈጸሙ፣ በእውነቱ ቃላትም የማይገልጻቸው የህወሓት መሪዎች ኢትዮጵያን በበላይነት ካልገዛን ትፈርሳለች የሚል ለዘመናት የቆየ ቅዠት እውን ለማድረግ እየተቅበዘበዙ መሆናቸውን የሰሞኑ ዋና መነጋገሪያ መሆኑ ይታወቃል። ከነበራዊ እውነታ ጋር የተጣሉ፣ የሞራልም የእእምሮም በሽተኞች በመሆናቸው የ27 ዓመት የክፋት፣ የዘረፋ፣ የከረፋ ዘረኝነታቸው ውስጥ ፍዳውን ሲያይ የነበሩ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ዜጎች የሚረዳው መሆኑ ግልጽ ነው።

ከለውጡ በኋላ ወደ ስልጣን የመጣው አመራር የነዚህን ጉዶች ባህርይና ለዘመናት የተተበተበ በሽታ በሚገባ ተገንዝቦ፣ ስትራቴጂም ነድፎ ህወሓትን የማዳከም ልዩ ልዩ እርምጃዎችን መወሰድ ይገባው ነበር። ያ ግን አልተደረገም። በተለይም ወንጀለኛውን ጌታቸው አሰፋ ሕግ ፊት እንዲቀርብ የፌደራል መንግሥቱ ሲጠይቅ አናስረክብም ባሉ ጊዜ፥ በሀገሪቱ ልዩ ልዩ ክፍሎችም ግጭት ለመፍጠር በርካታ የሳቦታጅ ሥራዎች ማደራጀታቸው፣ መቆስቆሳቸው በሚገባ የሚታወቁ ሆነው ሳለ፥ ፈዴራል መንግሥቱ ከጦርነት በመለስ ሁሉንም የመንግሥት ማድረግ አቅም መጠቀምና ህወሓትን አይቀጡ ቅጣት መቅጣት ነበረበት። በቅርብ ሳምንት በቤኒሻንጉል-ጉሙዝ ክልል በአማራ ማኅበረሰብ አባላት ላይ የተደረገውን አሰቃቂ ጭፍጨፋ በገንዘብና በመሣሪያ ያገዙ፣ በክልሉ ሰፊ መሬት ያላቸው የህወሓት አባል የሆኑ ባለሃብቶች መሆናቸው የክልሉ መንግሥት ባለስልጣን ለኢሳት ጋዜጠኛ መሳይ መኮንን የተናገረውን ልብ እንበል።

በመንግሥት አካባቢ ብቻ ሳይሆን በሌሎችም ተንሠራፍቶ የነበረ ‘የት ይደርሳሉ?’ መሰል የተዛባና አደጋውን የመረዳት የማይመጥን አመለካከት ሳቢያም፣ ህወሓትን የልብ ልብ ሰጥቶ ኢትዮጵያን ወደ ጦርነት ለመክተት፣ በዚህም የትግራይንም ሆነ የሌላውን ኢትዮጵያዊ በጦርነት እሳት ለመማገድ ዛሬ ላይ የደረሰበት የለየለት እብደት እንዲደርስ ዕድል ባልተሰጠው ነበር፤ አጥፍቶ ከመጥፋትም አይመለሱም። ያ በሀገርና በሕዝብ ላይ የነበራቸውንም ዓይን ያወጣ የጥቂት ዘረኞች የበላይነት፣ ፈልጭ ቆራጭነት እንዳይመለስ አጥተውታልና አዲሱን እውነታ ፈጽሞ ተቀበለው በእኩልነት፣ በአቻነት ሊኖሩ በዘረኝነት፣ በትምክህትና በትእቢት የታጨቀው አእምሮአቸው አይፈቅድላቸውም።

ለሁለት ዓመት ተኩል የተዘጋጁበት፣ ከጅምሩም ህወሓትና አጋሮቹ እንደ ጊዜ ቦንብ እንዲፈነዳ ቀብሩውት የነበሩት ሰፋፊ የማንነት ስንጥቆች፣ የብሔር ቅራኔዎችን ተጠቅመው ሀገሪቱን በቀውስ ውስጥ ለመክተት፣ ብሎም ለመበታተን ላሰፈሰፉ በየክልሉ ያደፈጡ ጽንፈኞችም ምቹ ሁኔታዎችንም ፈጥሯል። የህወሓት መሪዎች ለበርካታ ዓመታት የነደፉትን መሰሪ ‘ፕላን B’ የሆነውን አባይ ትግራይ-ትግራይ ትግሪኝ፣ ወዘተ… ለመመሥረት የሚችል መስሏቸው እየተንፈራገጡ ይገኛሉ። ለሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ግልጽ መሆን ያለበት የጦርነት እሳት ኢንዲቀጣጠል፣ ብሎም በመላው ኢትዮጵያ እንዲዛመት ያላቸውን ሁሉ በማድረግ ላይ የሚገኙት መሰሪዎቹ ጸረ-ኢትዮጵያ የህወሓት መሪዎች በጠላትነት የፈረጁት ጠ/ሚ ዐቢይ አህመድን ብቻ እንዳልሆነ ግልጽ መሆን ይገባዋል፤ ወይንም ፈደራል መንግሥቱ፣ የብልጽግና ፓርቲ አይደሉም።

ይልቅስ ዓይን ቀቅሎ የበላው የሀሰትና የነውር ቋት የሆነው የስዩም መስፍንና ሌሎቹ የህወሓት መሪዎች መሠረታዊ ግብ ኢትዮጵያን የማፈራረስ ነው። በፍርስራሹም ላይ በዘረኝነት የታጨቀው የትግራይ ትግርኝ ሀገር መንግሥት የመመሥረት ቀቢጸ-ተስፋ እውን የማድረግ ግብ ነው። ይህ ነው አብይ ግባቸው። ለምን ቢባል የህወሓት መሪዎች ኢኮኖሚውን፣ መከላከያውን፣ ደህንነቱን፣ የውጭ ጉዳዩንና ባጠቃላይም በኢትዮጵያ ሀገረ መንግሥት ላይ በበላይነት የማያሸከረክሩባት፣ ፈላጭ ቆራጭና ሁሉን አድራጊ ፈጣሪ፣ ሌላው የእነርሱ አጎብዳጅ፣ ፈርቶና ተጎናብሶ የማይኖርባት የ27 ዓመቷ ኢትዮጵያ ማስቀጠል የማይችሉበት ነባራዊ ሁኔታን እንዴት ተቀብለው ሊኖሩ ይችላሉ?

ልብ እንበል፤ ቆም ብለን በቅጡ እናስብ፤ ያቺ ኢትዮጵያ ዛሬ ላይ የለችም። ይህን እጅግ መራር እውነታ ሊቀበሉ ሊውጡት ደግሞ ፈጽሞ አልቻሉም። የእነ ስዩም መስፍን “ዓይናችሁን ጨፍኑና እናሞኛችሁ” የለየለት ውሸቶች፣ ማስመሰሎች፣ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ቆመው፣ ሠርተው እንደነበር፣ ለሕዝብ ጥቅም የታገሉና ሲሠሩ እንደነበሩ ለቀባሪው ማርዳት ሙከራዎች ሁሉ ከዚህ ሃቅ የሚመነጭም ጭምር ነው። ይህን ሃቅ አስምረን ግልጽና ፍንትው አድርገን ማየት ቀዳሚው ተግባር ነው። ህወሓት ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ እውነተኛ ፍትህ፣ እኩልነት፣ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሞች የቆመበትና የሠራበት ሁኔታና ጊዜስ መቼ ነበሩ? ብለን ብንጠይቅ፣ እነ ስዩም መስፍን ነጋ ጠባ ሊያጭበረብሩን ከሚሞክሩት ውጭ ማንም አፉን ሞልቶ ሊመሰክር የሚችል ኢትዮጵያዊ የሚገኝ አይመስለኝም። ሀገሪቱን እንደ ቅኝ ተገዢ ሲመዘብሩ፣ በከረፋ ዘረኝነታቸውም ትግርኛ ተናጋሪ ያልሆነውን ኢትዮጵያዊ ሁሉ እንደ የበታችና 3ኛ ዜጋ ሲያንገላቱ፣ ሲገፉ፣ በንቀት ሲመለከቱ፣ ሲዘርፉና ሲገድሉ የነበረው መራራ ታሪክ ሁሉም ያለፈበት የቅርብ ጊዜ አስነዋሪውና አሳፋሪው ትሪካቸውና የእኛም የኢትዮጵያውያን ቁስል ነውና።

ለምን? ምክንያቱም ከጅምሩም የተነሱበት መሠረት በመሆኑ ለአያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ግልጽ መሆን ይገባዋል፤ መወናበድ ማክተም አለበት። ለአወናባጆችና ውዥንብር ነዥዎችም ሰለባ መሆን የለብንም፤ ብዙዎች ከዳር ቆሞው ጉዳዩ የዐቢይ አህመድ እና የህወሓት ጠብ አድርጎ መመልክት በሀገርና በሕዝብ ላይ ትልቅና ከባድ አደጋ፣ እንደ ሀገርና ሕዝብ ለውድቀትም ሊዳርግ የሚችል፣ ይህ ነው ተብሎ ሊገመት የማችል ዋጋ የሚያስከፍል ስህተት ይሆናል። አለፍ ሲልም ቅጥረኞችና ከራሳቸው ጥቅም በላይ ለጋራ ሀገር፥ ለኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ ማሰብ የማይችሉ፣ ዐቢይን ሰለጠሉ ኢትዮጵያም ሆነች ሀገረ መንግሥቱ ቢፈርስ፣ በፍርስራሹ ላይ ስልጣን የሚያገኙ የሚመስላቸው እኩዮች “ፓለቲካ ሊያስተምሩን” እንደሚዳዱት የህወሓትና የፌደራል መንግሥቱ/የብልጽግና ጠብና ግጭት ተደርጎ መወሰድ የለበትም። የህወሓት መሪዎች እንቅስቃሴ በሀገራችን ኢትዮጵያና በሕዝብ ሰላም፣ ደህነትና መረጋጋት ላይ የመጣ የህልወና አደጋ ተደርጎ መወሰድ ያለበት ነው።

የዛሬው አብይ ጥያቄ ኢትዮጵያ ሀገራችንንና ኢትዮጵያዊነት ከህወሓት ሀገር አፍራሽ፣ ሕዝብ አጫራሽ ሴራ ማምከን ነው። መሆን ወይንም አለመሆን ነው ለእያንዳዱ ዜጋ የቀረበው ጥያቄ።

ነአምን ዘለቀ

 

Source: semonegna.com

One Reply to “የህወሓትን ሀገር አፍራሽ፣ ሕዝብ አጫራሽ ሴራ በጋራ ቆመን፣ በአንድነት በመንቀሳቀስ ማምከን ይጠበቅብናል ― ነአምን ዘለቀ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *